Monday, March 4, 2024

‹‹የግብፅና የኢትዮጵያ ግንኙነት ከተሳሳተ ግንዛቤ ወጥቶ መልካም ወደሆነ ደረጃ ተሸጋግሯል ማለት ይቻላል››

- Advertisement -spot_img

በብዛት የተነበቡ

አምባሳደር መሐመድ እድሪስ፣ በኢትዮጵያ የግብፅ ተሰናባች አምባሳደር

አምባሳደር መሐመድ እድሪስ ተሰናባች በኢትዮጵያ የግብፅ አምባሳደር ሲሆኑ በአፍሪካ ኅብረትና በተመድ የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን ደግሞ ቋሚ የግብፅ ተጠሪ ናቸው፡፡ ከካይሮ ዩኒቨርሲቲ እ.ኤ.አ. በ1984 በሕክምና ተመርቀው የአንገት በላይ ሐኪም በመሆን ያገለገሉት ለሦስት ዓመታት ብቻ ነበር፡፡ እ.ኤ.አ. ከ1987 ጀምሮ የግብፅ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴርን ተቀላቅለው ከሕክምናው ወደ ዲፕሎማሲ ፊታቸውን አዙረዋል፡፡ በመቀጠልም ሁለተኛ ዲግሪያቸውን እንግሊዝ አገር ከሚገኘው የለንደን ዩኒቨርሲቲ በፖለቲካል ሳይንስ የትምህርት መስክ አግኝተዋል፡፡ ወደ ኢትዮጵያ እ.ኤ.አ. በ2011 ከመምጣታቸው በፊት በአሜሪካ፣ በቱርክና በሶሪያ በምክትል አምባሳደርነት እንዲሁም የልዑኩ አባል በመሆን ያገለገሉ ሲሆን በተመድ የግብፅ ቋሚ ተጠሪ በመሆን አገልግለዋል፡፡ አምባሳደሩ በአዲስ አበባ የነበራቸውን የሥራ ጊዜ አጠናቀው ወደ አገራቸው ሊመለሱ በዝግጅት ላይ ባሉበት ወቅት ስለሁለቱ አገሮች ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት፣ ስለዓባይ ወንዝ፣ በአዲስ አበባ ስለነበራቸው ቆይታ፣ በቅርቡ ተመርቆ አገልግሎት መስጠት ስለጀመረው የስዊዝ ካናል ማስፋፊያ ፕሮጀክትና ተያያዥ ጉዳዮችን በተመለከተ በግብፅ ኤምባሲ በመገኘት ነአምን አሸናፊ ከአምባሳደር መሐመድ ጋር ቆይታ አድርጓል፡፡

ሪፖርተር፡- እርስዎ አምባሳደር በመሆን ያገለገሉባቸው ያለፉት አራት ዓመታት በሁለቱ አገሮች ግንኙነት ላይ በተለየ አዳዲስ ክስተቶችን አስተናግደዋል፡፡ ከዚህ አንፃር ባለፉት አራት ዓመታት የታዩትን የሁለቱን አገሮች ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነቶች እንዴት ይገልጹዋቸዋል?

አምባሳደር መሐመድ፡-  በግሌ በጣም መልካም የሚባል ጊዜ ነበር፡፡ ፈታኝ ቢሆንም ውጤታማ የነበረ ጊዜ ነው፡፡ እርግጥ ነው ባለፉት አራት ዓመታት በሁለቱ አገሮች ግንኙነቶች ላይ በርካታ ለውጦችና ዕድገቶች እንደተመዘገቡት ሁሉ በርካታ ፈታኝ ሁኔታዎችም ነበሩ፡፡ ሆኖም በሁለቱ አገሮች የጋራ የሆነ አርቆ አሳቢ አመራር አማካይነት የተፈጠሩትን ፈታኝ ሁኔታዎች ለማለፍ ተችሏል፡፡ በዚህም የተነሳ የግብፅና የኢትዮጵያ ግንኙነት ቀደም ሲል ከነበረበት የተሳሳተ ግንዛቤ ወጥቶ ቀናና መልካም ወደሆነ ደረጃ ተሸጋግሯል ማለት ይቻላል፡፡ ስለዚህ አሁን ግንኙነቱን የተሻለ መንገድ ላይ ያደረስነው ከመሆኑም በተጨማሪ፣ ወደተሻለና ብሩህ ወደሆነ ደረጃ እየተሸጋገረ እንደሆነ ለመረዳት ይቻላል፡፡

ሪፖርተር፡- የሁለቱም አገሮች መሪዎችና ከፍተኛ ባለሥልጣናት የሁለቱ አገሮች ግንኙነት ቀደም ሲል ከነበረበት ፍጥቻ ወጥቶ ወደ መተባበር ደረጃ ተሸጋግሯል በማለት በተደጋጋሚ አስተያየት ይሰጣሉ፡፡ እንዲህ ያለውን አስተያየት እርስዎ እንዴት ይመለከቱታል?

አምባሳደር መሐመድ፡- እውነት ነው፡፡ ሁለቱ አገሮች በዘርፈ ብዙ ጉዳዮች ላይ ወደ ትብብር እየተሸገጋርን ነው፡፡ ቀደም ባሉት ዓመታት ጉዳዮችን የያዝንበትና ያስተናገድንበት መንገድ የሁለቱን አገሮች ግንኙነት ጎድቶታል፡፡ ባለፉት አራት ዓመታት እኔና በኤምባሲው የሚገኙ የሥራ ባልደረቦቼ ይህን ለማስተካከልና ዘርፈ ብዙ የሆነውን ግንኙነት ለማበልፀግ የተለየ ትኩረት ሰጥተን ስንሠራ ነበር፡፡ ሁለቱ አገሮች ታሪካዊ፣ ባህላዊ፣ ሃይማኖታዊና ኢኮኖሚያዊ ትስስሮች አሉዋቸው፡፡ በዚህም የተነሳ የሁለቱን አገሮች ግንኙነት በፐብሊክ ዲፕሎማሲው መስክ፣ እንዲሁም በሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነቱ መስክ ከፍ ወዳለ ደረጃ እንዲሸጋገር ሠርተናል፡፡ እርግጥ ነው በሁለቱም አገሮች ከፍተኛ ጠቀሜታ ያለው የዓባይ ወንዝ ጉዳይ አለ፡፡ ስለሆነም የግንኙነታችንን ገጽታና ባህሪ እንደ አዲስ እያጠናከርን ነው፡፡ ከዚህ በተጨማሪም በእርግጠኝነት መናገር የሚቻለው የተጠናከረ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ሲኖረን፣ የተሻለና የተጠናከረ የንግድና የኢንቨስትመንት ግንኙነት እንደሚኖረን ነው፡፡ በዚህም የተነሳ ወደፊት ነገሮች አሁን ካሉበት በተሻለ ደረጃ ሲፈጠሩ ማናቸውንም ዓይነት ልዩነቶችን በቀላሉ መፍታት ይቻላል፡፡

ሪፖርተር፡- ስለዚህ የሁለቱ አገሮች ግንኙነት ቀደም ሲል ከነበረበት መፋጠጥ ወጥቶ ወደ ተሻለና ትብብር ደረጃ ተሸጋግሯል እያሉ ነው?

አምባሳደር መሐመድ፡- በትክክል፡፡ አሁን ግንኙነቱ የሚያመጣቸውን ማናቸውንም ዕምቅ ሀብትና ዕድሎች እየተጠቀምን ነው፡፡ እነዚህ ነገሮች ደግሞ ዝም ብለው የሚታዩ ምናባውያን አልያም ደግሞ ልብ ወለድ አይደሉም፡፡ በእውነት ላይ የተመሠረቱ ናቸው፡፡ ስለዚህ ማድረግ የሚገባን ምንድነው? እነዚህን ዕድሎችና ዕምቅ ሀብቶች አሁን ካሉበት ደረጃ አሸጋግረን፣ በጋራ በእጃችን ላይ ያሉትን ዕድሎች ወደፊት እንዴት መጠቀም እንደምንችል በጋራ መሥራት ነው፡፡

ሪፖርተር፡- የሁለቱ አገሮች ግንኙነት ወደ ተሻለና አዲስ ደረጃ እየተሸጋገረ ነው የሚለው እንደተጠበቀ ሆኖ፣ የግብፅ ባለሀብቶች በኢትዮጵያ የንግድና የኢንቨስትመንት ዘርፍ ውስጥ ያላቸው ድርሻ እንዴት ይገለጻል?

አምባሳደር መሐመድ፡- ምንም እንኳን ህልማችንና ተስፋችን ገደብ የለሽ ቢሆንም መልካም በሆነ ጎዳና ላይ እየተጓዘ ይገኛል ማለት ይቻላል፡፡ ስለዚህ በርካታ ሥራዎችን መሥራት አለብን፡፡ የሁለቱን አገሮች ግንኙነት ከፍ ወዳለ ደረጃ ለማሸጋገርና አሁን የተፈጠረውን መልካም ግንኙነት ወደ ንግድና ኢንቨስትመንት ግንባር በመቀየር በርካታ ሥራዎችን መሥራት ይጠበቅብናል፡፡ ከሁለቱ አገሮች ግንኙነት የምንጠብቀው የንግድና የኢንቨስትመንት ዕድገት ከፍ ያለ ነው፡፡ ለዚህ ነው በርካታ ሥራዎችን መሥራት የሚኖርብን፡፡ በርካታ የግብፅ ኢንቨስተሮች ኢትዮጵያ ውስጥ መዋዕለ ንዋያቸውን እያፈሰሱ ይገኛሉ፡፡ ሌሎች በርካቶች ደግሞ በተለያዩ ዘርፎች ለመሠማራት በዝግጅትና ሒደት ላይ ይገኛሉ፡፡ በቅርቡ በኢትዮጵያ ውስጥ የግብፅ ኢንዱስትሪ ዞን ለማቋቋምና ለማስጀመር እየተንቀሳቀስን ነው፡፡ ይኼ ደግሞ በሁለቱ አገሮች መካከል የሚኖረውን የንግድና የኢንቨስትመንት ትብብርን ከፍ ወዳለ ደረጃ ያሸጋግረዋል፡፡

ሁለቱ አገሮች እያንዳንዳቸው ከ90 ሚሊዮን በላይ የሆነ የሕዝብ ብዛት ያላቸው  ናቸው፡፡ ይህ ደግሞ ግንኙነቱን በንግድና በኢንቨስትመንት ለማጠናከር የሚያገለግል ትልቅ ኃይል ነው፡፡ በመሆኑም እዚህ ላይ አበክረን እየሠራን ነው፡፡ ከኢትዮጵያ በርካታ ምርቶችን ወደ ግብፅ ለማስገባት እየሞከርን ነው፡፡ በአንፃሩ ደግሞ ከኢትዮጵያ ልማት ዕቅድ አንፃር ለአገሪቱ ገበያ የሚያስፈልጉ ምርቶችን ለማቅረብ እየሞከርን ነው፡፡ ይህም ለሁለቱም አገሮች የጋራ ተጠቃሚነት ይፈጥራል፡፡ በአንፃሩ ደግሞ እንዲህ ዓይነቱ ግንኙነት በሁለቱ አገሮች ሁለንተናዊ ግንኙነት ላይ መልካም ተፅዕኖውን ያሳርፋል፡፡   

ሪፖርተር፡- ከዚህ አንፃር የግብፅ ኢንቨስተሮች ቁጥርና የገበያ ድርሻ ባለፉት አራት ዓመታት ምን ያህል እንደሆነ ቢገልጹልን?

አምባሳደር መሐመድ፡- የኢቨስትመንት መጠኑ ወደ 1.7 ቢሊዮን ዶላር ገደማ ነው፡፡ ሆኖም ግን መዋዕለ ንዋያቸውን በኢትዮጵያ ለማፍሰስ በዝግጅት ላይ ያሉ በርካታ ኢንቨስተሮች አሉ፡፡ በእርግጠኛነት መናገር የምችለው የኢንዱስትሪ ዞኑ ሥራ ሲጀምር ይህ ቁጥር በከፍተኛ ሁኔታ እንደሚጨምር ነው፡፡ ከአሁኑ በርካታ ግብፃዊያን ኢንቨስተሮች ያላቸውን ዕቅድ ከኢንዱስትሪ ዞኑ ጋር ለማጣጣም በርካታ ሥራዎችን እየሠሩና የኢንዱስትሪ ዞኑን መከፈት እየተጠባበቁ ነው፡፡ ባለፈው መጋቢት የግብፅ ፕሬዚዳንት ኢትዮጵያን በጎበኙበትና ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝን በአነጋገሩበት ወቅት ከዚህ አንፃር እጅግ ወሳኝ ስብሰባ ተደርጎ ነበር፡፡ በወቅቱ መሪዎቹ ለሁለቱም አገሮች ኢንቨስተሮችና የንግድ ማኅበረሰብ ግልጽ የሆነ መልዕክት አስተላልፈው ነበር፡፡ ያስተላለፉት መልክዕት ደግሞ አሁን የተፈጠረውን መልካም የፖለቲካ ሁኔታ ተጠቅመው ንግዳቸውንና ኢንቨስትመንታቸውን እንዲያሳድጉ የሚል ነበር፡፡ እርግጥ ነው በፖለቲካ፣ በኢንቨስትመንትና በንግድ ሥራዎች መካከል ግልጽ የሆነ ግንኙነት አለ፡፡ በመሆኑም መልካም የፖለቲካ ሁኔታ ሲኖር ኢንቨስትመንትና ንግድ እንዲያድግ ይረዳል፡፡ ይህን እንዲሠራ የምንወተውተው ደግሞ በሁለቱም አገሮች የሚገኙ ኢንቨስተሮችና የንግዱን ማኅበረሰብ ተጠቃሚ ለማድረግ ነው፡፡ ስለዚህ የሁለቱ አገሮች የንግድ ማኅበረሰብ አባላት ይህን ዕድል በመጠቀም፣ ከሁለቱ አገሮች መልካም የፖለቲካ ሁኔታ የየራሳቸውን ተጠቃሚነት ማረጋገጥ ይኖርባቸዋል፡፡

ሪፖርተር፡- የኢትዮጵያ፣ የሱዳንና የግብፅ ተወካዮችን ያካተተው የሦስትዮሽ የቴክኒክ ኮሚቴ ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የሚያስከትለውን ተፅዕኖ የሚያጠኑ ሁለት ዓለም አቀፍ አማካሪ ድርጅቶች መርጧል፡፡ ከዚህ አንፃር በሁለቱ አገሮች መካከል ያለው ነገሮችን የመረዳትና የመተማመን ደረጃ እንዴት ይገለጻል?

አምባሳደር መሐመድ፡- ይህ ጉዳይ ሁለት ገጽታ አለው፡፡ የመጀመሪያው ፖለቲካዊ ገጽታ ሲሆን፣ ሁለተኛው ደግሞ ቴክኒካዊ ገጽታ ነው፡፡ በፖለቲካዊ ገጽታው በኩል ያለው መረዳት የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ በአንድ ወቅት እንደገለጹት ታላቁ የዓባይ ወንዝ ሁለቱን አገሮችና የሁለቱን አገሮች ሕዝቦች የሚያገናኝና የሚያስተሳስር እትብት ማለት ነው፡፡ ይህ በፖለቲካዊ መልኩ ያለው መረዳት በሁለቱም ወገኖች መካከል በከፍተኛ ደረጃ የሚታይ ዕመርታ ነው፡፡ ከዚህ በተጨማሪ ደግሞ ቴክኒካዊ ገጽታ አለው፡፡ መሬት ላይ ያለውን የፖለቲካ መግባባት እንዴት ወደ ቴክኒክ መረዳት ማሸጋገርና መለወጥ ይቻላል የሚል ነው፡፡ ይህ ገጽታ ግን እንደ ፖለቲካዊ ገጽታው ቀላል አይደለም፡፡ በውስጡ ያካተታቸው በርካታ ዝርዝር ሁኔታዎች አሉ፤ በርካታ የቴክኒክ ጉዳዮችና በርካታ ሳይንሳዊ ዝርዝር ሁኔታዎችም እንዲሁ ተካተዋል፡፡ ስለዚህ ከሦስቱም አገሮች የተውጣጣ የቴክኒክ ኮሚቴ እዚህ ላይ እየሠራ ይገኛል፡፡ አባላቱ በበርካታ ጉዳዮች ላይ ከስምምነቱ ላይ የደረሱ ሲሆን፣ ከፍተኛ የሚባል ውጤትም አስመዝግበዋል፡፡ ከተመዘገቡት ውጤቶች መካከልም የግድቡን ሁኔታ የሚያጠኑ ሁለት ዓለም አቀፍ አማካሪ ድርጅቶችን መምረጣቸው ተጠቃሽ ነው፡፡ የዚህ አማካሪ ቡድን ጥናት በፖለቲካዊው መስክ የተደረሰባቸው ስምምነቶችን በቴክኒክ መልኩም ቢሆን ተፈጻሚ መሆን የሚችሉ መሆኑን ማጥናት ነው፡፡ ከሦስቱ አገሮች የተውጣጡ የቴክኒክ ባለሙያዎች ስምምነት በተደረሰባቸው በርካታ ጉዳዮች ከተመረጠው የአማካሪ ቡድን ጋር እየሠሩ ሲሆን፣ ወደፊት ለሚሰጣቸው የቤት ሥራ የሚሆን ዝግጅትን በማጠናቀቅ ላይም ናቸው፡፡

ቀደም ባሉት ጊዜያት በእነዚህ የቴክኒክ ኮሚቴዎች አማካይነት በኢትዮጵያ፣ በሱዳንና በግብፅ የተካሄዱ በርካታ ስብሰባዎች ነበሩ፡፡ ባለፈው ሳምንት ሐሙስና ዓርብ ላይም እንዲሁ የተከናወነ ስብሰባም ነበር፡፡ የስብሰባው ዋና ዓላማ ደግሞ የቀሩትንና የተንጠለጠሉትን የቴክኒክ ጉዳዮች መቋጨት ነው፡፡ ስለሆነም ግልጽ የሆነ የመረዳት ደረጃ ላይ እንደምንደርስና ወደፊት መጓዝ እንደምንችል በእርግጠኝነት መናገር እችላለሁ፡፡ እዚህ ላይ ጠቃሚው ነገር የመነሻ ሥፍራችን የት ነበር? መድረሻችንስ የት ነው? የሚለው ይመስለኛል፡፡ ከዚህ አንፃር ስንመለከተው መነሻ ሥፍራችን ሦስቱንም አገሮች በታሪክ ለዘመናት ያስተሳሰረና ሁልጊዜም የሚያስተሳስር የጥቅምና የብልፅግናችን ምንጭ የሆነው ታላቁ የዓባይ ወንዝ ነው፡፡ መድረሻችን ደግሞ በዚህ ወንዝ ላይ በጋራ መዋኘትና መበልፀግ ነው፡፡ ስለዚህ ከዚህ አንፃር በጋራ ለመጠቀምና ለመተባበር ያለንን ጊዜ እንሰዋለታለን፡፡ ከዚህ አንፃር ምርጫ አለን፡፡ ምርጫችን ደግሞ መተባበር የሚለው ነው፡፡ እንደሚመስለኝ ከየት ተነስተን የት እንደደረስን በግልጽ መረዳት ይቻላል፡፡ በመነሻውና በመድረሻው መካከል የታለፈባቸው በርካታ ሒደቶችና ውጣ ውረዶች አሉ፡፡ ከእነዚህ ሒደቶች አንዱና ቀላል ያልሆነው ውስብስብ ቴክኒካዊ፣ ሳይንሳዊ እንዲሁም የአጠናን ዘዴን የሚከተለው የቴክኒክ ሒደት ነው፡፡ ነገር ግን ባለው የፖለቲካ ቀናነት፣ መልካም ፈቃደኝነትና የጋራ መግባባት በቀሩት የቴክኒክ ጉዳዮች ላይ መግባባት ላዳ ተደርሶ በእንጥልጥል ያሉት ጉዳዮች በቅርቡ መቋጫ ያገኛሉ ብዬ አስባለሁ፡፡ ይህ እንደሚሆን ደግሞ አልጠራጠርም፡፡ እርግጠኛ ነኝ፡፡

ሪፖርተር፡- ባለፈው ሳምንት መጨረሻ የተከናወነው የሦስቱ አገሮች የቴክኒክ ኮሚቴ ስብሰባ የቀሩትንና በእንጥልጥል ላይ የሚገኙት የቴክኒክ ጉዳዮች ላይ መፍትሔ የሚያስቀምጥ ይመስልዎታል?

አምባሳደር መሐመድ፡- በእርግጥ አንድ ስብሰባ ሲከናወን በተደራዳሪ ወገኖች መካከል ያለውን ልዩነት ያሳጥረዋል፡፡ በዚህ መሀል ግን ሁሉም ሐሳቦች ላይጠናቀቁ ይችላሉ፡፡ ነገር ግን በእርግጠኝነት የሚቀረውን ልዩነትና ርቀት ያሳጥረዋል፡፡ ሁሉንም ነገር በአጭሩ ከቋጨው እጅግ መልካም ነው፡፡ የተወሰኑትን ከቋጨም እንዲሁ መልካም ነው፡፡ ምክንያቱም ቀጣዩ ስብሰባና ውይይት ደግሞ የቀረውን ስለሚቋጨው ማለት ነው፡፡ ስለዚህ ሁልጊዜም ቢሆን ቀናና የወደፊቱን የምንመለከት መሆን አለብን፡፡ አንድ ጉዳይ በእንጥልጥል ቢቆይ ትልቅ ቸግር እንደተፈጠረ አድርገን መመልከት የለብንም፡፡ ራሳችንንም በዚህ ማጠርና ማደናቀፍ አይጠበቅብንም፡፡ እንዲህ ያለው ነገር ተፈጥሯዊና በየትኛውም የዓለም ክፍል በተለያዩ ጉዳዮች አማካይነት ሊፈጠር የሚችል ክስተት ነው፡፡ እንዲህ ያለውን ጉዳይ ለማረቅ ደግሞ ጊዜን፣ ጥረትንና የጋራ መግባባትን የሚጠይቅ ነው፡፡

ሪፖርተር፡-  በቅርቡ የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትርን ጨምሮ በርካታ የዓለም መሪዎች በታደሙበት ግብፅ አዲሱን የስዊዝ ካናል ማስፋፊያ ፕሮጀክት አስመርቃለች፡፡ ፕሮጀክቱ አገሪቱን ከስምንት ቢሊዮን ዶላር በላይ አስወጥቷል፡፡ ከዚህ አንፃር ፕሮጀክቱ ለግብፃውያን የሚሰጠውን ኢኮኖሚያዊ ጥቅምና በአካባቢው የሚኖረውን የጂኦፖለቲካል ተፅዕኖ እንዴት ይገልጹታል?

አምባሳደር መሐመድ፡- ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ በመገኘታቸው ከፍተኛ ክብርና ኩራት ይሰማናል፡፡ ይህ ፕሮጀክት የተለያዩ ገጽታዎች አሉት፡፡ የመጀመሪያው በግብፃውያን የተለየ ምልክታዊ ገጽታ አለው፡፡ የመጀመሪያው ስዊዝ ካናል እ.ኤ.አ. በ1869 ሲመረቅ ለመጠናቀቅ የፈጀበት ጊዜ አሥር ዓመት የነበረ ሲሆን፣ በሥራውም ከ120,000 በላይ ግብፃውያን ሕይወታቸውን አጥተዋል፡፡ አሁን ግን ይህ ፕሮጀክት የተጠናቀቀው በአንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ ነው፡፡ አጠቃላይ የፕሮጀክቱን ወጪ የሸፈኑት ደግሞ ግብፃውያን ዜጎች ብቻ ናቸው፡፡ ሦስተኛው ገጽታ ደግሞ ፕሮጀክቱ የተከናወነበት አጠቃላይ የክልሉ ሁኔታ ነው፡፡ ፕሮጀክቱ በምቹና ደህና የሚባል ጊዜም ላይም አይደለም የተከናወነው፡፡ ፕሮጀክቱ የተከናወነው በተዘበራረቀና በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ ነው፡፡ የመካከለኛው ምሥራቅ አካባቢን በምንመለከትበት ጊዜ በርካታ አለመረጋጋቶች፣ ብጥብጦች፣ እንዲሁም የሽብር ጥቃቶች እዚህና እዚያ እየተከሰቱ ነው፡፡ ሆኖም ግብፅ በውስጥም በውጭም ያለባትን ተፅዕኖ ተቋቁማ ይህን ፕሮጀክት መገንባት መቻሏ በራሱ ለግብፃውያንም ሆነ ለመላው ዓለም ትልቅ መልዕክት ነው፡፡ ወደ ኢኮኖሚው ጠቀሜታው ስንመጣ ፕሮጀክቱ የሚጠቅመው ግብፅን ብቻ አይደለም፡፡ አፍሪካዊ ወንድሞቻችንንና መላውን ዓለም ነው፡፡ ምክንያቱም ይህ ዓለም አቀፍ የመርከቦች መተላለፊያ ነው፡፡ በዚህ መስመር የግብፅ ንግድና መርከቦች ብቻ አይደለም የሚተላለፉት፡፡ የዓለምና የአኅጉሪቱ ንግድ ጭምር ይጓጓዝበታል፡፡ በእርግጠኝነት ከኢኮኖሚው ጥቅም ተጠቃሚ የሚሆኑት የአኅጉሪቱና የዓለም አቀፍ ንግድ ናቸው፡፡ ለእዚህም ነው ፕሮጀክቱ ‹ከግብፅ ለዓለም የተበረከተ› የሚል ስያሜ የተሰጠው፡፡

ሪፖርተር፡- ምንም እንኳን እርስዎ ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታውን ቢገልጹም፣ በአንፃሩ ደግሞ ፕሮጀክቱ ከአሥር ዓመት በኋላ ይደርስበታል ወደተባለው የ13.3 ቢሊዮን ዶላር ገቢ ግምት ሊደርስ አይችልም በማለት የሚተቹና የሚጽፉ በርካታ የዘርፉ ተንታኞችና ባለሙያዎች አሉ፡፡ እርስዎ ትችቱን እንዴት ያዩታል?

አምባሳደር መሐመድ፡- በግልጽ ለመናገር ነገሮችን ከዓላማቸው አንፃር መመልከት አለብን፡፡ ከዓላማቸው አንፃር ማየት አለብን ስንል ደግሞ የተለያዩ ሐሳቦችንና አመለካከቶችን ማስተናገድ አለብን ማለት ነው፡፡ በርካታ የፕሮጀክቱ አድናቂዎችና ደጋፊዎች አሉ፡፡ በተቃራኒው ደግሞ ፕሮጀክቱ ላይ የሰላ ትችት የሚያዥጎደጉዱም እንዲሁ አሉ፡፡ ሁለቱንም እኩል መውሰድ ይኖርብናል፡፡ ነገር ግን ከላይ የዘረዘርኳቸውን ጠቀሜታዎች ከግምት ውስጥ ስናስገባ ለግብፃውያን ይህ ፕሮጀክት ትልቅና ከፍተኛ ውጤት ነው፡፡ ሌላው ገጽታ ኢኮኖሚያዊ አስተዋፅኦ የሚለው ነው፡፡ ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ የሚባለው ነገር በመላምት ያለ ነገር ሳይሆን፣ በመሬት ላይ ያለ ነገር ነው፡፡ ፕሮጀክቱ ተከፍቶ አገልግሎት መስጠት ከጀመረ የተቆጠሩት ጥቂት ሳምንታት ናቸው፡፡ ምንም እንኳን ከተመረቀና አገልግሎት መስጠት ከጀመረ ገና ጥቂት ሳምንታት ቢሆኑም፣ በሥፍራው የሚተላለፉ የመርከቦች ቁጥር ጨምሯል፡፡ ቁጥሩ የጨመረ የመርከብ ምልልስ ማለት ደግሞ ገቢ ማግኘት ማለት ሲሆን፣ በዚያው ልክ ለዓለም አቀፍ ንግድ መፋጠንም አስተዋጽኦ ማበርከት ማለት ነው፡፡ ይህ ደግሞ ከማንም የተደበቀ አይደለም፡፡ ዜጎች ካናሉን መመልከትና የትራፊክ መጠን መጨመር አለመጨመሩን መታዘብ ይችላሉ፡፡ ስለዚህ መጨመር ካለ ገቢው ይጨምራል፡፡ የግብፃውያን የትርፍ ድርሻም እንዲሁ ይጨምራል፡፡ ስለዚህ የኢኮኖሚውን ጠቀሜታ በጊዜ ሒደት የምናየው ይሆናል፡፡ ከፍተኛ የሆነው የፕሮጀክቱ ጠቀሜታ ወደፊት የሚመጣና የሚታይ ይሆናል፡፡

ሪፖርተር፡- ስለዚህ ከአሥር ዓመት በኋላ ለመድረስ የተተነበየው ቁጥር ላይ ለመድረስ የሚያስችል ዕድል አለ እያሉኝ ነው?

አምባሳደር መሐመድ፡- ይመስለኛል፡፡ ተስፋ አደርጋለሁ፡፡ ጊዜ የሚያሳየን ይሆናል፡፡ ምክንያቱም መጨረሻ ላይ ምንም ነገር ሊደበቅ አይችልም፡፡ በጊዜ ሒደት ይህ ነገር ይሆናል አይሆንም የሚለውን እንመለከታለን፡፡

spot_img
- Advertisement -

ትኩስ ጽሑፎች

ተዛማጅ ጽሑፎች

- Advertisement -
- Advertisement -