ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ላይ ሁለት ጥናቶችን ለማከናወን የተመረጠው የፈረንሣዩ ቢአርኤል ኢንጂነርስ ኩባንያ፣ በ15 ቀናት ውስጥ የጥናት የቴክኒክ ፕሮፖዛሉን ለሦስቱም መንግሥታት ለማቅረብ ተስማማ፡፡
ኩባንያው የጥናት የቴክኒክ ፕሮፖዛሉን በሐምሌ ወር በሱዳን በተካሄደው የኢትዮጵያ፣ የግብፅና የሱዳን የሦስትዮሽ ቴክኒክ ኮሚቴ ስብሰባ ላይ ማቅረብ ይጠበቅበት የነበረ ቢሆንም ይህንን ሳያደርግ ቀርቷል፡፡
ምክንያቱ ደግሞ በጥናቱ ላይ የፈረንሣዩ ኩባንያ ድርሻ፣ እንዲሁም ሁለተኛው ተባባሪ አጥኚ የኔዘርላንዱ ዴልታ ሬዝ ኩባንያ የሥራ ክፍፍል ግልጽ ስላልሆነለት እንደሆነ ተገልጿል፡፡
ባለፈው ሳምንት ከነሐሴ 14 ቀን 2007 ዓ.ም. ጀምሮ በአዲስ አበባ በተካሄደው የሦስቱ አገሮች የጋራ ቴክኒክ ኮሚቴ ስብሰባ ላይ ኩባንያው የቴክኒክ ፕሮፖዛሉን ያቀርባል ተብሎ ቢጠበቅም፣ በዚህ ስብሰባም አለማቅረቡን ለመረዳት ተችሏል፡፡
በዚህ ስብሰባም የፈረንሣዩ ኩባንያ የቴክኒክ ፕሮፖዛሉን ያላቀረበበት ምክንያት፣ አሁንም የሥራ ክፍፍሉ ግልጽ ባለመሆኑ እንደሆነ ሪፖርተር ያገኛቸው መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡
የሦስቱ አገሮች የጋራ ኮሚቴ በሚያዚያ ወር ባካሄደው ስብሰባው የፈረንሣዩ ኩባንያ ሁለት ጥናቶችን በበላይነት እንዲወስድ፣ እንዲሁም የኔዘርላንዱ ኩባንያ ተባባሪ አጥኚ እንዲሆን ወስኖ ነበር፡፡ የሥራ ክፍፍሉ ዝርዝር ውሳኔ የተወሰነው በሱዳኑ ስብሰባ ላይ ሲሆን፣ በዚህም መሠረት የፈረንሣዩ ኩባንያ የሁለቱ ጥናቶች ውል ተዋዋይና ሕጋዊ ኃላፊነት የሚወድቅበትና 70 በመቶ የሚሆነውን የጥናት ድርሻ የሚይዝ እንዲሆን ተወስኗል፡፡
የኔዘርላንዱ ኩባንያ ደግሞ 30 በመቶ የሚሆነውን የሥራ ድርሻ ለመፈጸም የሚያስችል የሰው ኃይል በማቅረብ ሥራውን በጋራ እንዲያከናውኑ ተወስኗል፡፡ ይሁን እንጂ የፈረንሣዩ ኩባንያ በድጋሚ የግልጽነት ጥያቄ በአዲስ አበባ ስብሰባ ላይ አቅርቧል፡፡
በዚህም መሠረት የኔዘርላንዱ ኩባንያ ዴልታ ሬዝ በጥናት ማኔጅመንት (አስተዳደር) ጉዳዮች ላይ መሳተፍ ይችላል ወይስ አይችልም የሚለው ሌላ አወዛጋቢ ጥያቄ እንደነበር የሪፖርተር ምንጮች ገልጸዋል፡፡
በግብፅ በኩል የዴልታ ሬዝ ባለሙያዎች በጥናት ማኔጅመንት (አስተዳደር) ሥራ ላይ እንዲሳተፉ ቢፈለግም፣ በኢትዮጵያ በኩል ግን ተቀባይነት አላገኘም፡፡ ሁለት ቀናት ከፈጀ ስብሰባ በኋላ በኢትዮጵያ በኩል የቀረበው ሐሳብ ተቀባይነት አግኝቶ የፈረንሣዩ ኩባንያ በተሰጠው የሥራ መመርያ መሠረት የቴክኒክ ፕሮፖዛሉን በ15 ቀናት ውስጥ እንዲያቀርብ ተስማምተዋል፡፡
ኩባንያው የቴክኒክ ፕሮፖዛሉን ማለትም ጥናቱን እንዴት እንደሚያካሂዱና የሥራ ድርሻ መዘርዝሮችን ካቀረበ በኋላ፣ የአገሮቹ የቴክኒክ ኮሚቴ አመራሮች የጋራ ስብሰባ መቼ እንደሚካሄድ ይወስናሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡
ሁለቱ ኩባንያዎች እንዲያጠኗቸው የሚፈለጉት ሁለት ጥናቶች አንዱ የኃይድሮሎጂ ሲሙሌሽን ሲሆን፣ ይህም ማለት የህዳሴው ግድብ የውኃ አያያዝና አለቃቀቅ በተለያዩ የዝናብ ወቅቶች ምን ያህል መሆን አለበት የሚለውን የሚመለከት ነው፡፡ ሁለተኛው ጥናት ደግሞ የህዳሴው ግድብ በዓባይ ተፋሰስ ላይ መገንባቱ በሱዳንና በግብፅ ላይ የሚያስከትለውን አካባቢያዊና ማኅበራዊ ተፅዕኖ መገምገም ነው፡፡