ዋና ከተማዋን አዲስ አበባን ጨምሮ በመላ አገሪቱ በተንሰራፋው የኤሌክትሪክ ኃይል መቆራረጥ ምክንያት በተለያዩ የሥራ መስኮች የተሰማሩ ዜጎችና የውጭ ባለሀብቶች እየተማረሩ ነው፡፡ የኃይል አቅርቦቱ በተደጋጋሚ መቆራረጥም ተስፋ እያስቆረጣቸው ነው፡፡ ይህ ጉዳይ የሚመለከተው የኤሌክትሪክ አገልግሎት መሥሪያ ቤትም ሆነ በከፍተኛው ዕርከን ላይ ያለው የመንግሥት አካል መፍትሔ መፈለግ አበት፡፡ በኃይል አቅርቦት ላይ የሚስተዋለው ችግር አገሪቱን በከፍተኛ መጠን ኪሳራ እያስከተለባት ነው፡፡ የሕዝቡንም ኑሮ እያቃወሰ ነው፡፡
አገሪቱ አንደኛውን የዕድገትና የትራንስፎርሜሽን ዕቅድ አጠናቃ ወደ ሁለተኛው እየገባች ነው፡፡ መንግሥት የግል ባለሀብቱ ከአገልግሎትና መሰል ዘርፎች ይልቅ በማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ ውስጥ እንዲገባ እየጎተጎተ ነው፡፡ የውጭ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንትም በሰፊው እየተጣራ ነው፡፡ ነገር ግን የኃይል አቅርቦት መስተጓጎሉ አላላውስ እያለ ነው፡፡ የኃይል አቅርቦቱ ጉዳይ መፍትሔ አግኝቶ በሙሉ ኃይል መንቀሳቀስ የማይቻል ከሆነ አገሪቱ በእጅጉ ትጎዳለች፡፡
በአሁኑ ጊዜ በማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ ውስጥ ያሉ የአገር ውስጥም ሆኑ የውጭ ኢንቨስተሮች በኃይል መቆራረጥ ምክንያት መሥራት እንዳቃታቸው በአደባባይ እየተናገሩ ነው፡፡ ኃይል የሚለቀቅበት ጊዜ በማነሱ ምክንያት በምርት ላይ ችግር እንደፈጠረባቸው፣ በከፍተኛ ወጪ ጄኔሬተሮችን ቢተክሉም የማምረቻ ዋጋ እየጨመረባቸው በመቸገራቸው ተወዳዳሪ መሆን እንዳቃታቸው በምሬት እየገለጹ ነው፡፡ ግንባታቸውን ያጠናቀቁ ፋብሪካዎችም በኃይል እጥረት ምክንያት ሥራ መጀመር እንዳልቻሉ በተደጋጋሚ ተሰምቷል፡፡ በአበባ ዘርፍ የተሰማሩ ባለሀብቶችም በኃይል እጥረትና መቆራረጥ ምክንያት፣ ለውጭ ገበያ የሚያቀርቧቸው ምርቶች እየተበላሹ ለኪሳራ መዳረጋቸውን ይናገራሉ፡፡ ጄኔሬተር ቢተክሉም የማምረቻ ዋጋ ንሮባቸዋል፡፡
በመካከለኛ፣ በአነስተኛና በጥቃቅን የሥራ ዘርፎች የተሰማሩ ዜጎችም የችግሩ ሰለባ ናቸው፡፡ ወፍጮ ቤቶች፣ ጋራዦች፣ የብረትና የእንጨት መሥሪያዎች፣ የውበት ሳሎኖች፣ ዳቦ ጋጋሪዎች፣ ሆቴሎችና ሬስቶራንቶች፣ ማተሚያ ቤቶች፣ ወዘተ የችግሩ ተጠቂዎች ናቸው፡፡ በመኖሪያ ቤቶች የሕፃናት ምግብ ማዘጋጀትና ሕሙማንን መንከባከብ አስቸጋሪ ሆኗል፡፡ ጄኔሬተር ለመጠቀም አቅም የሌላቸው የጤና ማዕከላትም አገልግሎታቸው እየተስተጓጎለ ነው፡፡ ከኃይል እጥረቱና መቆራረጡ በተጨማሪ በድንገት የሚለቀቅ ከፍተኛ መጠን ያለው ኃይል የዜጎችን ንብረት እያወደመ ነው፡፡
የቀድሞው የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ኮርፖሬሽን ለሁለት ተከፍሎ የአገልግሎቱ ዘርፍ ማኔጅመንት ለህንዱ ኩባንያ መሰጠቱ ይታወሳል፡፡ ይህ ኩባንያ ባለፉት ሁለት ዓመታት ያመጣው ለውጥ በተጨባጭ ምን እንደሆነ ሳይታወቅ፣ በቅርቡ ኮንትራቱ አብቅቶ ስንብት እንደተደረገለት ተሰምቷል፡፡ መንግሥት ኮንትራቱን ሲሰጥ ይጠብቅ የነበረው ለውጥ ተገኝቷል? የተገኘው ለውጥ ተገምግሟል? ወይስ ልፋቱ ሁሉ ከንቱ ነበር? የሚመለከተው አካል በዚህ ላይ በይፋ ያለው ነገር ስለሌለ ምላሽ ይጠበቃል፡፡ በሕዝብ በኩል ያለው ግን ምሬትና ተስፋ መቁረጥ ነው፡፡
መንግሥት ችግሩን እንደሚያውቅና ለመፍትሔው እየሠራ መሆኑን እየተናገረ ነው፡፡ በአዲስ አበባ የኤሌክትሪክ ኃይል ሥርጭቱን ለማዘመን እየሠራ መሆኑን ገልጿል፡፡ ከፍተኛ በጀት እንደተያዘም እንደዚሁ፡፡ ከተለያዩ የኃይል ማመንጫዎች ኃይል ለማግኘት ግንባታዎችን እያካሄደ መሆኑ ይታወቃል፡፡ ነገር ግን ከመቼውም ጊዜ በላይ እያደገ ያለውን የኃይል ፍላጎት የሚመጥን ሥራ እየተሠራ ነው ወይ? በሁለተኛው የዕድገትና ትራንስፎትሜሸን ዕቅድ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው አምራች ኢንዱስትሪዎች እንደሚገቡ እየታወቀና በርካታ የኢንዱስትሪ ዞኖች እየተዘጋጁ በፍጥነት መንቀሳቀስ ለምን አቃተ? የኃይል አቅርቦት ችግር በዚህ ሁኔታ ከቀጠለ ዕቅዱን እንዴት ማሳካት ይቻላል?
ሌላው ቀርቶ የውጭ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንትን ከሚስቡ የትኩረት ነጥቦች መካከል የኃይል አቅርቦት አስተማማኝነት አንዱ ነው፡፡ ከዚህ ቀደም በማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ የተሰማሩ ኢንቨስተሮች እየተማረሩ አዳዲሶችን ለመሳብ መሞከር አስቸጋሪ ነው፡፡ የአገር ውስጥ ባለሀብቱንም ይህንን ደካማ የኃይል አቅርቦት ይዘህ ገብተህ ካልተቸገርክ ማለት የዋህነት ነው፡፡ መንግሥት ዙሪያ ገብ ችግሮችን ፈትሾ በፍጥነት ካልተንቀሳቀሰ አገሪቱ የማትወጣው ችግር ውስጥ ትገባለች፡፡
የአገሪቱ ኤክስፖርት ገቢ የማያወላዳ በመሆኑ ምክንያት የውጭ ምንዛሪ አቅርቦት እያሽቆለቆለ ነው፡፡ አምራቾች በሙሉ ኃይላቸው አምርተው ጥራት ያለው ነገር ገበያው ውስጥ ይዘው መግባት ካልቻሉ የኤክስፖርት ገቢውም እየቀነሰ ይሄዳል፡፡ የዓለም ገበያ በአሁኑ ጊዜ የማያስተማምን እየሆነ ነው ያለው፡፡ በዓለም ላይ እያንዣበበ ያለውን የኢኮኖሚና የፋይናንስ ቀውስ በብቃት መመከት የማይችል አገር ይንኮታኮታል፡፡ ይህም ያሳስባል፡፡
ለዚህ መፍትሔው ደግሞ በተለይ አምራች ኢንዱስትሪው በኃይል መቆራረጥና በተለያዩ ምክንያቶች የሚደርሱበትን የማምረቻ ዋጋ ንረቶችን ማስወገድ ነው፡፡ በናረ ዋጋ የሚመረት ማንኛውም ዓይነት ምርት በዓለም ገበያ ተወዳዳሪ መሆን አይችልም፡፡ በተለይ ጨርቃ ጨርቅ፣ ቆዳ፣ አበባ፣ ወዘተ የመሳሰሉ የኤክስፖርት ምርቶች ከፍተኛ ትኩረት ይሻሉ፡፡
መንግሥት የኃይል ማመንጫ ግድቦችን፣ የንፋስና የጂኦተርማል ፕሮጀክቶችን በማከናወኑ ችግሮችን ለመፍታት እየተጋ መሆኑን ቢገልጽም፣ ፍጥነት ያስፈልገዋል፡፡ እነዚህ መሠረተ ልማቶች በብዛትና በጥራት እየተከናወኑ ጎን ለጎን ደግሞ በአነስተኛ ደረጃ ኃይል የሚያመርቱ ኩባንያዎችን ማሳተፍ ይጠበቅበታል፡፡ እነዚህ ኩባንያዎች በብዛት ሥራ እንዲጀምሩ ቢደረግ ጠቀሜታቸው የጎላ ይሆናል፡፡ የመኖሪያ ሥፍራዎችንና የማምረቻ አካባቢዎችን መለያየት፣ ለኃይል ብክነት የሚያጋልጡ አሠራሮችን ማስወገድ፣ በሚመለከተው የአገልግሎት መሥሪያ ቤት ውስጥ ኃላፊነትና ተጠያቂነትን ማስፈን፣ ወዘተ ትኩረት ያስፈልጋቸዋል፡፡ አሁን እየታየ ባለው ሁኔታ ግን የኃይል አቅርቦት መቆራረጥ ተስፋ አስቆራጭ ሆኗል!