Wednesday, May 22, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

ዜናጃፓን የጣለችውን ማዕቀብ ካነሳች ከስድስት ዓመት በኋላ በቡና ጥራት አለመደሰቷን ይፋ አደረገች

ጃፓን የጣለችውን ማዕቀብ ካነሳች ከስድስት ዓመት በኋላ በቡና ጥራት አለመደሰቷን ይፋ አደረገች

ቀን:

–  ግዙፉ የቡና ኩባንያ የጥራት ውድድር እዚህ ያካሂዳል

ከስድስት ዓመት በፊት ወደ ጃፓን በተላከ የቡና ጆንያ ላይ በተገኘ የኬሚካል ቅሪት ሳቢያ ጃፓን ከኢትዮጵያ የሚላከውን ቡና አግዳ ብትቆይም፣ አሁንም በሚላክላት ቡና ላይ የጥራት ጉድለት እየታየ በመሆኑ የቀድሞውን ያህል እየገዛች አለመሆኗ ተገለጸ፡፡

በኢትዮጵያ የጃፓን ባለሙሉ ሥልጣን አምባሳደር ካዙሂሮ ሱዙኪ ሪፖርተር ላቀረበላቸው ጥያቄ በሰጡት ምላሽ፣ ከስድስት ዓመት በፊት በፀረ አረምና ፀረ ተባይ ኬሚካል ሳቢያ ጃፓን ትገዛው የነበረው ቡና ለተወሰነ ጊዜ ከተቋረጠ በኋላ መልሶ ማገገም ቢጀምርም፣ ከስድስት ዓመት በፊት ወደነበረበት ደረጃ ሊመለስ አልቻለም ብለዋል፡፡ ይህ ሊሆን የቻለው ደግሞ ጥራት ያለውና ከፍተኛ ደረጃ የተሰጠው ቡና ተብሎ የሚላከው ጥራቱም ደረጃውም ዝቅተኛ ከሆነው ጋር እየተደባለቀ በመገኘቱ እንደሆነ አምባሳደር ሱዙኪ ገልጸዋል፡፡ በዚህ ሳቢያም የሚፈለገውን ያህል ቡና ወደ ጃፓን መላክ ባይቻልም በየጊዜው እያደገ መምጣቱ ግን ተነግሯል፡፡

- Advertisement -

የግብርና ሚኒስቴር መረጃ እንደሚጠቁመው በዓመት ከ170 እስከ 190 ሺሕ ቶን ቡና ለዓለም ገበያ ይቀርባል፡፡ ከዚህ መጠን ውስጥ የጃፓን ድርሻ ግን ከአሥር በመቶ እንደማይበልጥ ለማወቅ ተችሏል፡፡ በአንፃሩ ከስድስት ዓመት በፊት ወደ ጃፓን ይላክ የነበረው የቡና መጠን ከጠቅላላው የኢትዮጵያ ኤክስፖርት እስከ 25 ከመቶ ይደርስ ነበር፡፡

የኬሚካል ንክኪውን ለማስቀረት የጃፓን ባለሙያዎች ወደ ኢትዮጵያ መጥተው በጃፓን መንግሥት ድጋፍ የላቦራቶሪ ማዕከል ተቋቁሞ አገልግሎት እየሰጠ ቢሆንም፣ ከፍተኛ ጥራት ያለው ቡና ከመደበኛው ቡና ጋር ተቀላቅሎ እየተላከ በመሆኑ፣ የኢትዮጵያ ቡና የጃፓንን የጥራት ደረጃዎች ማሟላት ተስኖት እንደሚገኝ አምባሳደሩ ይናገራሉ፡፡ ይህ ቢስተካከል ግን ከፍተኛ ዋጋ የሚያወጡ ጥራት ያላቸው ልዩ ቡናዎች በኢትዮጵያ እንደሚገኙ አምባሳደር ሱዙኪ አስታውቀዋል፡፡ ኢትዮጵያ ከጥሬ ቡና ባሻገር አገር ውስጥ የተቀነባበረ ቡና የመላክ ሐሳብ እንዳላት ያስታወሱት አምባሳደሩ፣ ይህንን ለማድረግ ግን አግሮ ፕሮሰሲንግ ኢንዱስትሪው መዳበር እንደሚኖርበት ገልጸዋል፡፡

በሌላ በኩል በዓለም ግዙፉ የቡና ኩባንያ የሆነው ዩሺማ ኮፊ ካምፓኒ ሆልዲንግ ግሩፕ (ዩሲሲ) በኢትዮጵያ የቡና ጥራት ላይ ያተኮረ ውድድር ሊያካሂድ መሆኑን ይፋ አድርጓል፡፡ ኩባንያው በጅማ ከተማ አቅራቢያ በሚገኙት በለጠና ጌራ አካባቢዎች የሚገኘውን የጫካ ቡና ሲገዛ መቆየቱም ይታወቃል፡፡ ኩባንያው በተደጋጋሚ በቡና ጥራት ላይ ከፍተኛ ጃፓናዊ ባለሙያ እያስመጣ ለአካባቢው አርሶ አደሮችና ቡና ላኪዎች ሥልጠና ሲሰጥ ቆይቷል፡፡ የኩባንያውን ማኅበራዊ ኃላፊነት የመወጣት ስትራቴጂ እንደሆነ በተነገረለት በዚህ እንቅስቃሴም፣ ወደፊት በቋሚነት ሊካሄድ ይችላል የተባለውን የቡና የጥራት ውድድር ለማካሄድ ከአገር በቀሉ መታድ የግብርና ልማት ኩባንያ (ካቡ ኮፊ በተባለው ምርቱ ይታወቃል) ጋር የጥራት ውድድር እያዘጋጀ ይገኛል፡፡

በመጪው ዓመት መጋቢት ወር ይካሄዳል የተባለው ውድድር 24 ሺሕ አምራቾችን የሚያሳትፍ ሲሆን፣ አሸናፊ የሚሆኑት የመጀመሪያዎቹ ስድስት ተወዳዳሪዎች ከመደበኛው የቡና ዋጋ ከአሥር እስከ 30 በመቶ ጭማሪ የሚደረግበት የስድስት ሺሕ ኩንታል ቡና ግዥ እንደሚፈጸምላቸው ኩባንያው አስታውቋል፡፡ ከጥር እስከ የካቲት ባለው ጊዜ ውስጥ ተወዳዳሪዎች ቡናዎቻቸውን ለውድድር ያቀርባሉ የተባለ ሲሆን፣ የመወዳደሪያ መሥፈርቶቹ ወደ ፊት ይፋ እንደሚደረጉ የዩሲሲ ኩባንያ ኃላፊዎች አስታውቀዋል፡፡

ጃፓን ከአሜሪካና ከጀርመን ቀጥላ በዓለም ሦስተኛ ቡና የምትገዛ አገር ስትሆን ከጣሊያን፣ ከፈረንሣይና ከእንግሊዝ በመቅደም በቡና ጠጪነት ከሚታወቁት አገሮች ተርታ ትመደባለች፡፡ ዩሲሲ ኩባንያ በበኩሉ በጃፓንና በእስያ ቡና ቆልቶ በማዘጋጀት ግንባር ቀደምነቱን ተቆናጧል፡፡ በዓለም ሰባተኛ ደረጃ መያዙን የኩባንያው ወኪሎች ይናገራሉ፡፡ በተለያዩ ዘዴዎች ቡና አዘጋጅቶ ለጃፓናውያን፣ ለእስያውያንና ለአውሮፓውያን የሚያቀርበው ይህ ኩባንያ ቡናን በዱቄትና በፈሳሽ መልክ እንደ ለስላሳ መጠጦች አሽጎ በማቅረብም ስሙ የሚጠራ ተቋም ነው፡፡ በጃፓን የቡና ማሠልጠኛዎችና የቡና ሙዚየም ያለው ዩሲሲ በእንግሊዝ፣ በስፔን፣ በኔዘርላንድስ፣ በስዊዘርላንድና በፈረንሣይ አምስት የቡና ማቀነባበሪያ ፋብሪካዎች አሉት፡፡ ከተመሠረተ 80ኛ ዓመቱ ላይ የሚገኘው ይህ ኩባንያ በሥሩ 62 ኩባንያዎችን በማቀፍ፣ በዓመት 185 ሺሕ ቶን ቡና በማገበያየት የ2.8 ቢሊዮን ዶላር ሽያጭ ያከናውናል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የማዳበሪያ አቅርቦትና ውጣ ውረዱ

በቅፅል ስሙ “The Father of Chemical Warfare” እየተባለ የሚጠራው...

የኢትዮጵያ ልማት ባንክ የትርፍ ምጣኔውን ከ70 በመቶ በላይ አሳደገ

ከሁለቱ መንግሥታዊ ባንኮች መካከል አንዱ የሆነው የኢትዮጵያ ልማት ባንክ...