Tuesday, November 28, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ዝንቅበቤጂንግ በመካሄድ ላይ ባለው 15ኛው የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና ላይ በ200 ሜትር የተወዳደረው...

በቤጂንግ በመካሄድ ላይ ባለው 15ኛው የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና ላይ በ200 ሜትር የተወዳደረው ጃማይካዊው ዩዜን ቦልት

ቀን:

በቤጂንግ በመካሄድ ላይ ባለው 15ኛው የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና ላይ በ200 ሜትር የተወዳደረው ጃማይካዊው ዩዜን ቦልት ለአገሩ ወርቅ ካስገኘ በኋላ ደስታውን በሚገልጽበት ወቅት እየተከታተለ ሲቀርጸው የነበረው ቻይናዊ ጋዜጠኛ ተሽከርካሪ ጋር ተጋጭቶ በወደቀበት ሰዓት

****

የደመና ትንቢት

 

ደመና ሲዳምን

 

‹‹ሊዘንብ ነው መሰል››

(እንዲህ ታስባለህ)

ደመናው ይዘንባል

ወይ ደግሞ ይቀራል

በደመናው መሀል ፀሐይ ትወጣለች

ይህች የወጣች ፀሐይ

ከደመና አርግዛ

ዝናብ ትወልዳለች

ወይ ታስወርዳለች

በመወለድ እና በማስወረድ መሀል

ሰው ይሉት የሰው ቃል

እውነት አርግዞ

እብለትን ይወልዳል

ለምን

በዚህ በአፍ ዘመን

እውነትን መናገር በአህዛብ መሀል

 

ልጡንም ያስርሳል መቃብር ያስምሳል

ከማስወረድ አልፈህ ተወልደሀልና

አንተ ግን ዝም በል

ደመና ሲዳምን

‹‹ሊዘንብ ነው መሰል››

ይህን አታብሰልስል

በለምን አትቁሰል

ለ‹‹ለምንህ?›› ደግሞ

ለምኑን ልንገርህ

እንዴቱን ላስረዳህ

ደመናን ‹‹ጨለማ››

ፀሐዩንም ‹‹ዝናብ››

ከሚለው አህዛብ

አውቀህ ተለይተህ

እውነትን የምትወልድ

እውነትን አርግዘህ

‹‹ሰው›› የተባለው ሰው

ሰውየው አንተ ነህ!

ሰለሞን ሳህለ ‹‹ያማል›› 2007 ዓ.ም.

****

ዳላስ ሙዚቃ ቤት

ፍቅረኛህን ‹‹ማሀሙድ ጋር ጠብቂኝ›› ስትላት ተሳስታ ማዶ ተሻግራ ከጠበቀችህ እድለኛ ናት፡፡ ካንተ በላይ የሚያስደስቷትን ሙዚቃዎች እየሰማች ነው ማለት ነው፡፡ ከዳላስ ሙዚቃ ቤት፡፡ ይህ ቤት የየመን ዝርያ ባላቸው ሐበሾች የተያዘ ነው፡፡ ከፒያሳ ፍቅር እንዲይዝህ ከሚያስችሉ አዚሞች አንዱ ነው፤ ዳላስ፡፡

በማለዳ ፒያሳ ከመጣህ በነ‹‹ያኒ›› ዜማ ትታደሳለህ፡፡ በሩቅ ምሥራቅ ረቂቅ ሙዚቃዎች ትፈወሳለህ፡፡ ረፋድ ላይ ፒያሳ ከደረስክ በነ መሀመድ ወርዲ፣ በነ አህመድ ሙስጠፋ፣ በነ ከማል ተርባስ በነ ሳይድ ከሊፋ ሱዳንኛ ዜማ ትደንሳለህ፡፡ በሱዳን ዜማ ለመደነስ አትሽኮርመም እንኳን አንተ ጠቅላይ ሚኒስትርህም ደንሰዋል፡፡

ከቀትር በኋላ ፒያሳን ከረገጥክ ደግሞ ዳላስ በብሉይ የእንግሊዝኛ ሙዚቃዎች አቅልህን ያስትሃል፡፡ በነ ሳም ኩክ፣ በነ ሬይ ቻርለስ፣ በነ ኢታ ጀምስ፣ በነ ዶና ሰመር፣ በነ ዳያና ሮዝ፣ በነ ማርቪንጌ፣ በነ ቲና ቻርለስ፣ በነ ሮድ ስቴዋርት ዜማዎች ትሰክራለህ፤ ትሳከራለህ፡፡ ደግሞ ማምሻ ላይ እነ ዶን ዊሊያምስ፣ እነ አለን ጃክሰን፣ እነ ሩኒ ሚልሳፕ፣ እነ ዶሊ ፓርተን፣ እነ ኬኒ ሮጀርስ በአገረ-ሰብ ሙዚቃ አለምህን ያስቀጩኻል፡፡

ዳላስ ብሉይ በኾኑ ነገር ግን በሚጣፍጡ ሙዚቃዎች የፒያሳን ዜጎች የማዝናናት ተግባር ላይ የተሰማራ ለትርፍ ያልተቋቋመ ድርጅት ይመስለኛል፡፡ ዛሬም ድረስ ሳይታክት ጆሮ ገብ ሙዚቃዎችን ያስኮመኩማል፡፡ በነፃ!

ከዚህ ቤት የሚደመጡ ሙዚቃዎች ዘፋኞቹ በሕይወት የሌሉ ወይም ደግሞ ዘፋኞቹ ራሳቸው የረሷቸው ሙዚቃዎች ሊሆኑ ይችላሉ፡፡ ‹‹ኦልዲስ-በት-ጉዲስ››፡፡ ታዲያ በቲቪ የምታውቀው ጥቃቅንና አነስተኛ ጀማሪ ዘፋኝ እዚህ ዳላስ ሙዚቃ ቤት አካባቢ ሲያንዣብብ ካየኽው አንድ ነገር ጠርጥር፡፡ ሊከትፍ ወይ ሊመነትፍ ነው፡፡

ዳላስ በብሉይ ሙዚቃዎች በይበልጥ ይታወቅ እንጂ በዓለም ላይ ዝናው ከፍ ያለ የሮክ፣ የጃዝ፣ የብሉዝ ወዘተ ሙዚቀኛን ሲዲ በመያዝም ይታወቃል፡፡ ዳላስ ገብተህ በትክክል የዘፈን ስም ከጠራህ ሲዲው ያለምንም ጥርጥር ይሰጥኻል፡፡ ድንገት እንኳ ሲዲው አልቆ ቢኾን ስለ አቀንቃኙ አንዳንድ ማብራሪያዎች ተሰጥቶህ ሌላ ጊዜ ብትመለስ ግን ሲዲው ከነልባሱ እንደሚዘጋጅልህ ተነግሮህ ነው የምትሰናበተው፡፡ ዳላስ ከተወለደ ጀምሮ ሙዚቃ አድናቂን አስቀይሞ አያውቅም፡፡ ሙዚቃ በእውቀት የሚነገድበት ቤት ነው፡፡

በነገርህ ላይ እዚያ አካባቢ የሚሠሩ የታክሲ ወያላዎች ዳላስ ሙዚቃ ቤት ተፅዕኖ ስላሳደረባቸው ይመስለኛል ተሳፋሪ ሲጠሩ ራሱ በዜማ ነው፡፡ የወያላዎቹን ድምፅ በደንብ አስተውህ ካዳመጥከው ሙዚቃዊ ቅላፄ አለው፡፡ ይስረቀረቃል፡፡ ‹‹22 ካዛንቺስ…መገናኛ!!!…መገናኛ ካዛንቺስ 22!!፣ 5ኪሎ…ቅድስተማርያም…አምስት ኪሎ!!!››

ፒያሳ ከመጣህ እንደ ወይን እያደር የሚጣፍጥ ዘፈኖችን ከዳላስ ሙዚቃ ዘወትር ትኮመኩማለህ፡፡ አምስት ሳንቲም ሳትከፍል፡፡ በዚህ ዘመን አንድን ሙዚቃ ሦስት ታክሲ ውስጥ ተከፍቶ ከሰማኸው እጅ እጅ ማለት እንደሚጀመር አንተም ሳትገነዘብ የቀረህ አይመስለኝም፡፡ የድሮ ሙዚቃ ግን ውብ ነው፡፡ ሄዶ ልብህ ላይ ነው የሚቀመጠው፡፡ አይጎረብጥህም፡፡ ካላመንከኝ ፒያሳ ዳላስ ሙዚቃ ቤት ደጅ ላይ ተሰየም፡፡

አንድ ድረ-ገጽ አንባቢዬ ዳላስ ሙዚቃ ቤትን እንዴት ገለጸው መሰለህ፤ ‹‹The soundtrack of Piassa››

መሐመድ ሰልማን ‹‹ፒያሳ›› 2004 ዓ.ም.

****

ምህረት

 

        ግርማዊ ንጉሠ ነገሥት መልካም ፈቃዳቸው ሆኖ የነፃነትን በዓል ምክንያት በማድረግ ከዚህ በታች ዝርዝራቸው ለሚገኘው እስረኞች የእስር ቅናሽና ሙሉ ምህረት አድርገዋል፡፡

1ኛ ከአዲስ አበባ ወህኒ ቤት………..29

2ኛ ከሐረር ጠቅላይ ግዛት …………42

3ኛ ከአሩሲ ጠቅላይ ግዛት ………….1

4ኛ ከበጌ ምድር ጠቅላይ ግዛት………5

5ኛ ከወለጋ ጠቅላይ ግዛት……………3

6ኛ ከጎሞ ጎፋ ጠቅላይ ግዛት…………2

በድምሩ ለሰማኒያ ሁለት ሰዎች ምህረት ተደርጓል፡፡

ሚያዝያ 9 ቀን 1943 ዓ.ም. አዲስ ዘመን ጋዜጣ

  •  

የወርቅ ሜዳሉን ለታክሲ አሽከርካሪ የከፈለው ፖላንዳዊ

በቻይና ቤጂንግ እየተካሄደ ባለው 15ኛው ዓለማቀፍ አትሌቲክስ ሻምፒዮና በአሎሎ ውርውራ የወርቅ ሜዳል ያገኘው ፖላንዳዊ፣ ደስታውን በመዝናናት ለማሳለፍ ወደ መጠጥ ቤት ጎራ ይላል፡፡ አመሻሹን ሲጠጣና ሲዝናና ቆይቶ ወደ ሆቴሉ የተሳፈረውም በታክሲ ነበር፡፡ ሆቴሉ ሲደርስም ለቻይናዊው ታክሲ አሽከርካሪ የወርቅ ሜዳሉን ሰጥቶት ይወርዳል፡፡

ፖላንዳዊው ፖውል ፋጃክ የወርቅ ሜዳሊያው እንደጠፋበት የተረዳው ጠዋት ከእንቅልፉ ሲነቃ ነው፡፡ ወዲያውም ለፖሊስ ደውሎ ያሳውቃል፡፡ ቢዝነዝ ኢንሳይደር እንደዘገበው፣ በአሎሎ ውርወራ የዓለም ክብረወሰንን የሰበረው ፋጃክ በስካር መንፈስ ነበር የወርቅ ሜዳሉን ለታክሲ ሾፌሩ የሰጠው፡፡ የቤጂንግ ፖሊሶች ባደረጉት ክትትል የታክሲ ሹፌሩ ተገኝቶ የወርቅ ሜዳሉን መልሷል፡፡ ‹‹የወርቅ ሜዳሉን የሰጠኝ እንደ ክፍያ ነው ሰርቄ አልወሰድኩም፤›› ሲልም ተናግሯል፡፡

ፋጃክ ግን ሳላውቅ ካንገቴ አውልቆ ወስዷል፣ ሰከረ የተባልኩትም ስም ማጥፋት ነው ብሏል፡፡ በቤጂንግ ሻምፒዮናውን ለመከታተል ከፖላንድ ያቀኑ ጋዜጠኞች ግን፣ ፋጃክ 80.88 ሜትር በመወርወር የወርቅ ሜዳልያውን ባገኘበት ዕለት ምሽት ለመዝናናትና ደስታውን ለመግለጽ ወጣ ማለቱንና መጠጣቱን ዘግበዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ለሲኒመር ትሬዲንግ አ/ማ አባላት በሙሉ የጠቅላላ ጉባኤ የስብሰባ ጥሪ

ለሲኒመር ትሬዲንግ አ/ማ አባላት በሙሉ የጠቅላላ ጉባኤ የስብሰባ ጥሪ ሲኒመር ትሬዲንግ...

የባህር በር በቀጣናዊ ተዛምዶ ውስጥ

በበቀለ ሹሜ መግቢያ በ2010 ዓ.ም. መጋቢት ማለቂያን ይዞ ዓብይ አህመድ በጠቅላይ...

ሥጋት ያስቀራል ተብሎ የሚታሰበው የጫኝና አውራጅ መመርያ

በአዲስ አበባ ከተማ በሕገወጥ መልኩ በመደራጀት ማኅበረሰቡ ላይ እንግልትና...

ማወቅ ወይስ አለማወቅ – ድፍረት ወይስ ፍርኃት?

በአሰፋ አደፍርስ ወገኖቼ ፈርተንም ደፍረንም የትም አንደርስምና ለአገራችን ሰላምና ክብር...