Tuesday, February 27, 2024
- Advertisment -
- Advertisment -

ከምስኪኑ የመንግሥት ሠራተኛ ለልማታዊው የመንግሥት ሠራተኛ

በታዲዮስ ገረመው ልዑል

ይድረስ ለአቶ ታዲዎስ ግንባር ቀደም ፈጻሚ ለጤናህ እንደምን ነህ? እኔ ትዕግሥቱንና ብርታቱን የሰጠኝ ፈጣሪ ይመስገን በጣም ደህና ነኝ፡፡

አቶ ታዲዮስ  በሕይወት አለህ? መኖርህን ከአቶ በላይ ማድቤት ትሁን መፀዳጃ ቤት መሆኗን በውል ከማትታወቀው ቤት የተከራየው የአንደኛ ደረጃ መምህር ደረጀ ነግሮኛል፡፡ ደረጀ ለምን ሻል ያለ ቤት አልተከራየም? ለምንስ ሕይወቱን በጥሩ ሁኔታ አልመራም? ትለኝ ይሆናል፡፡ ሆኖም ግን ከማገኛት የወር ደመወዝ ለኮንዶሚንየም ቆጥቦ ስላልበቃው አይደል ሻል ያለ ቤት ተከራይቶ መኖር ያልቻለው?

አቶ ታዲዮስ የምልህ መቼም አቶ የምትባለውን ማረግህን ስለምትወዳት ነው፡፡ አቶ ታዲዮስ የት ነው እየሠራህ ያለኸው? አቶ ኡመር የዛሬ ስምንት ዓመት ገደማ ወረዳ ጉዳይ ሊያስፈጽም በመጣበት ወቅት የወረዳው ሥራ አስፈጻሚ እንደነበርክ አጫውቶኛል፡፡ የደንቡንም ገንዘብ ስላልከፈለ ጉዳዩ እንዳልተፈጸመለት ነግሮኛል፡፡ ጉዳዩን ብትፈጽምለት አመሰግንህ ነበር፡፡ የመንግሥት ሠራተኛ ነው ብር ከየት አባቱ አምጥቶ ይክፈልህ ብለህ ነው ገንዘብ ካልተከፈለ ብለህ ጉዳዩን ያልፈጸምክለት? ደግሞስ አቅሙን ያገናዘበ ጥያቄ ለምን አላቀረብክለትም? የመንግሥት ሠራተኛው መብቱን ስለማይለምንና መብቱን ስለሚያስከብር መደራደሩ አያዋጣንም ብለህ ነው?

ይኸውልህ ጉዳዩ ሳይፈጸምለት ተጨማሪ ዓመታት አስቆጥሯል፡፡ ሰነድ አልባ ቤቱ አንዴ ሲፈርስበት መልሶ ሲሠራ እዚህ ደርሷል፡፡ ጊዜው እንዴት ሄዷል? አምስት ዓመታት አስቆጠረ፡፡ የምሥራቹን ልንገርህ? ሰነድ አልባ ካርታ ይሰጠዋል ተብሎ የአዲስ አበባ ማዘጋጃ ሕግ ስላወጣ የቤት ባለንብረት መሆኑ አይቀርም፡፡

አቶ ታዲዮስ የዛሬ ስድስት ዓመት በቢሮህ በተደረገው ግምገማ ደካማ ተብለህ ካለህበት ሥራ አስፈጻሚነት እንደለቀቅህና ወደ ክፍለ ከተማ እንደ ተሾምክ የቢሯችን ልጅ እግር የፅዳት ሠራተኛ ወ/ሪት ፀሐይ ነግራኛለች፡፡ ነገርን ነገር ያነሳዋል አይደል ፀሐይ ወደ መዝገብ ቤት አድጋለች፡፡ ደመወዟም ወደ 1,347 ብር ደርሷል፡፡ ፀሐይ ቤት ተከራይታ መኖር ጀምራለች፡፡ የ3,000 ብር የኮንዶሚንዬም ቤት ተከራይታለች፡፡ አይገርምም ከደመወዟ በላይ ኮንዶሚንዬም ስትከራይ? የቢሮው ሰው እንደሚያወራው ቀን ከሥራ ወጥታ ሌሊት ኑሮን ለመግፋት ሴተኛ አዳሪ ሁና እየሠራች ነው፡፡ የሚገርመው ቢሯችን ውስጥ ያሉ ሠራተኞችን በሙሉ በአለባበስ ቦንሳቸዋለች፡፡ ትንሽ የምትቀራረበው የሥራ አስኪያጁ የመልዕክት ሠራተኛ የሆነችው ቲቲ ብቻ ነች፡፡ ቲቲ 600 ብር ያልተጣራ ወርኃዊ ደመወዝ ታገኛለች፡፡ የምትጫማቸው ጫማዎች እያንዳንዳቸው ከ700 ብር በላይ ዋጋ ያወጣሉ፡፡

አንድ ቀን ደመወዝ ዘግይቶብን ምሳ የምንበላበት ገንዘብ ስላልነበረን ከቢሯችን ፊት ለፊት ቁጭ ብለን ‘ቫይታሚን ዲ’ እየተመገብን ሳለ ቲቲ በአጠገባችን አለፈች፡፡ ተመልሳም ሰላም አለችን፡፡ ማኪያቶ እንድንጠጣም ጋበዘችን፡፡ ምሳ እንዳልበላን ነገርናት፡፡ ለሁላችንም ምሳ ለቀቀችብን፡፡ ደስ አይልም? አመስግነናት ወደ ቢሯችን ስንሄድ የለበሰችውን አልባሳት በሙለ ስንደምረው አሥራ ዘጠኝ ሺሕ ብር ደረሰ፡፡ ሽቶ 1,000፣ የአንገት ሐብል ቢያንስ 5,000፣ የእጅ ካቴና ቢያንስ 3,000፣ የያዘችው ጋላክሲ ሞባይል ቢያንስ 12,000 ብር፡፡

አቶ ታዲዮስ ይህንን ገንዘብ በሙሉ ከየት አመጣችው ትል ይሆናል፡፡ ገምት መቼም አንተ እንደምትገምተው ሙስና ገንዘብ ለአለቃዋ የሚመጡ ሰዎች ለእሷም ገንዘብ ይሰጧታል ነው የምትለው፡፡ እንደዚህ ካሰብክ በጣም ተሳስተሃል፡፡ ሚስጥሩን ልንገርህ? አንድ ፓይለት ወንድም አላት፡፡ ከውጭ ዕቃ ያመጣለታልና ቲቲ እነዚህን ልብሶች በቢሮ የሥራ ሰዓት ከቢሮ ውጪም ሆነ ቢሮ ውስጥ መቸብቸብ ነው፡፡

አቶ ታዲዮስ ከአራት ዓመት በፊት የክፍላችን የሒሳብ ሠራተኛ አቶ ዋሲሁን በአካውንቲንግ በማዕረግ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ በሁለተኛ ዲግሪ ሲመረቅ ከነበሩ ግንባር ቀደም የመንግሥት ኃላፊዎች አንዱ እንደነበርክ ለእኔ ሳልሆን ከአንተ ጋር እኛ ቢሮ በነበርክበት ጊዜ የሰው ሀብት አስተዳደር ዳይሬክተር ሲናገር በጆሮዬ አዳምጫለሁ፡፡

መቼም አንተ ስለአቶ ዋሲሁን ታሪክ ሳልነግርህ ብቀር ሆድህን ያምሀል፡፡ አቶ ዋሲሁን ከተመረቀ በኋላ የንብረትና ግዥ አስተዳደር ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ሆኗል፡፡ ታዲያ አቶ ዋሲሁን የሚገኘው ደመወዝ ከ6000 ብር ባይበልጥም የተመሰከረለት ኪራይ ሰብሳቢ ሆኗል፡፡ ጨረታ ማፈን የሚታወቅበት ሥራው ነው፡፡ ባለፈው ቤቴል አካባቢ አምስት ሚሊዮን ብር ቤት መግዛቱንና የንግድ መኪና ኤሮ ትራከር መግዛቱን የመሥሪያ ቤታችን ሠራተኞች የምናውቀው ጉዳይ ነው፡፡

አቶ ታዲዮስ የዛሬ ሦስት ዓመት አካባቢ በዝቅተኛ ዋጋ ምግብ ከምንበላበት የክበብ ካፌ ቁጭ ብለን ከአቶ ዳውድ ጋር ምሳ ስንበላ፣ በዓይኔ በብረቱ ስለሲቪል ሰርቪስ ሪፎርም ንግግር ሲደረግ አይቻለሁ፡፡ ብለህ ብለህ ወደ ሲቪል ሰርቪስ ሚኒስቴር ተመለስክ ማለት ነው?

አቶ ታዲዮስ የዳውድ ጉዳይስ ብለህ እንዳትጨነቅ፡፡ አቶ ዳውድ የንብረት ክፍል ኃላፊ ሆኗል፡፡ ተመችቶታል፡፡ ከኪሎው በእጥፍ ጨምሯል፡፡ ከ80 ኪሎ በላይ ሆኗል፡፡ ከአንተ በስተቀር በውፍረት የሚበልጠው ያለ አይመስለኝም፡፡ ወደ ምግባሩ ስገባ ጥራታቸውን ያልጠበቁ ዕቃዎች ገቢ እንዲደረጉ ተባባሪ ነው፡፡ ብቻ ሀብታም መሆኑን ድፍን መሥሪያ ቤታችን ያወራል፡፡ ብዙ ጊዜ መሥሪያ ቤቱ ስለእኔ ምን ያዋራል? ብሎ ይጠይቀኛል፡፡ ጥሩ መረጃ ከሰጠሁት ምሳና ሲቸግረኝ ተመሳሳይ ጥያቄውን ጠይቆኝ ያልኩትን ገንዘብ ይወረውርልኛል፡፡

አቶ ታዲዮስ የዛሬ ሁለት ዓመት አካባቢም እንዲሁ በቴሌቪዥን ስለ ሲቪል ሰርቪስ ሪፎርም ሥልጠና ሲሰጥ አይቻለሁ፡፡ አብሮ አደግ ጓደኛዬ በመሆኔ ደስታ ይሰማኛል፡፡ አንዳንዴም ሺሕ ዘመን አይኖር ብዬ በአንተ እሸማቀቃለሁ፡፡

ታዲያ በንግግርህ ወቅት ሁለተኛው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ለሠራተኛው ትልቅ የደመወዝ ጭማሪ ይዞ እንደሚመጣና የመንግሥት ሠራተኛው የልማት ተጠቃሚ እንደሚሆን ስታወራ ሰምቻለሁ ልበል? አረጀሁ መሰለኝ መርሳት ጀምሬያለሁ፡፡

ታዲያ አቶ ታዲዮስ የሠራተኛው ችግር ስለማይገባህ በሳምንት ቢያንስ አንድ ጊዜ የጣፋጠ ምግብ አትብላ፡፡ ፁም፣ ፀልይ፡፡ አቶ ታዲዮስ እኔ በሞትኩ መንገር ያለብኝን ነገር ሳልነግርህ፡፡ ካስታወስከው በመሥሪያ ቤታችን ስብሰባ በሆነ ቁጥር ስለዕውነት የሚናገረው አቶ አገኘሁ እንግዳ በመኪና አደጋ ሞተ፡፡ ለምን ሞተ ትለኝ እንደሆነ ለፀረ ሙስና የሚቀርብ ሰነድ አለኝ አጋልጣለሁ ብሎ  በስብሰባ ላይ ተናግሮ ነበር፡፡ ታዲያ በሁለተኛው ቀን በመኪና አደጋ ሕይወቱን ለእውነት ሲል ስለእውነት አሳልፎ ሰጠ፡፡ አደጋ ያደረሰበት ሾፌር የውኃ ሽታ ሆኖ ቀረ፡፡

አቶ ታዲዮስ መቼም ከአንዱ መሥሪያ ቤት ወደ ሌላ መሥሪያ ቤት ሥራ ልቀይር ነበር፡፡ ሆኖም ግን ደመወዝ ይጨመርልኛል ብዬ እየተጠባበቅኩ ነው፡፡ የኑሮ ውድነቱ ራሴ ላይ ወጥቷል፡፡ ድህነቱ ተጫጭኖኛል፡፡ ትንሽ ትንሽ የምንቀሳቀሰው በደህናው ዘመን የሠራሁት ቤት ጉልበት ሆኖኛል፡፡ በእሱ እንደነገሩ እኖራለሁ፡፡

አቶ ታዲዮስ የመሥሪያ ቤታችን ጥበቃ አበጋዝ ያለኝን ላካፍልህ፡፡ አበጋዝ አራት ልጆቹን በ951 ጥቅል የወር ደመወዝ እያስተዳደረ ይገኛል፡፡ ደግነቱ በደጉ ዘመን ሁለት ክፍል የቀበሌ ቤት አግኝቷል፡፡ ታዲያ በዚህ ብር ቤተሰቡን እንዴት ያስተዳድር? ሳይንሳዊ የአመጋገብ ግኝት አበጋዝ ቀምሯል፡፡

ቁርስ

የአንደኛ ክፍልና የሦስተኛ ክፍል ተማሪዎች የሆኑት ልጆቹ እንዲመገቡ ያደርጋል፡፡

ምሳ

የስድስተኛና የዘጠነኛ ክፍል ተማሪ የሆኑት ልጆቹ እንዲመገቡ ያደርጋል፡፡

መክሰስ

ለሕፃናቱ በረዶ ይገዛላቸዋል፡፡

እራት

ሁሉም የቤተሰብ አባላት ያገኙትን ይቃመሳሉ፡፡

ታዲያ አቶ አበጋዝ አንጀቱን አስሮ በቀን አንድ ጊዜ ብቻ እየተመገበ በትዕግሥት የደመወዝ ጭማሪውን እየጠበቀ ይገኛል፡፡

አቶ ታዲዮስ ስለድህነት መቼም ባወራህ ምንም ስለማይገባህ የመንግሥት ሠራተኛ ትዕግሥተኛ ነው ብለህ ትርጉም የሌለው የደመወዝ ጭማሪ እንዳታደርግ፡፡

አቶ ታዲዮስ ሌላ ጊዜ ደብዳቤ ብልክልህ ስለማታነበው ዛሬ በደንብ አዳምጠኝ፡፡ የመንግሥት ሠራተኛ ለመሆን የተቀጠርኩበትን የመጀመሪያ የሥራ ቀኔን ረገምኩ፡፡ ለምን መሰለህ በታማኝነት ስትሠራ ሰው አይወድህም፡፡

አቶ ታዲዮስ አንድ የምሥራችና ሚስጥር ልንገርህ የ1ለ5 ግንባር ቀደም ፈጻሚ ሁኛለሁ፡፡ ይህ እንግዲህ የምሥራቹ ነው፡፡ መንግሥት በቀየሰው የልማት ሠራዊት ግንባታ ማዕቀፍ ስትሰበስብ ስለኪራይ ሰብሳቢነትና ስለመልካም አስተዳደር ታወራለህ፡፡ ትፋጫለህ፡፡ እውነት መስሎህ እውነት እውነቱን ካወራህ በየምክንያቱ ከመሥሪያ ቤቱ የምታገኘውን ጥቅማ ጥቅም አትጠብቅ፡፡ ግን የውሸት ሪፖርት በመቀመር ከጧት 2፡30 እስከ 11፡30 ሰባት ቢሮህ ከተገኘህ ግንባር ቀደሙ አንተ ነህ፡፡ ታዲያ እኔ ከጧቱ 2፡30 እስከ 11፡30 ሰዓት የምሠራው ሥራ ባይኖርም ስብሰባ መሰብሰብና የ1ለ5 ሪፖርት ማቅረብ፡፡ አለቀ በቃ ይህ ነው ለአገሪቱ ትልቅ ለውጥ የሚያመጣ፡፡

አቶ ታዲዮስ ጭንቅላቴ ሊፈነዳ ነው፡፡ ለ16 ዓመታት በመንግሥት ሠራተኝነት በመጀመሪያ ዲግሪ ተመርቄ 5,080 ብር የወር ደመወዝ ይከፈለኛል፡፡ ተቃጠልኩ ለማን አቤት ልበል? የአገሪቱ ሀብት በአግባቡ መጠቀም አለብን ብልም ሰሚ አላገኘሁም፡፡

አቶ ታዲዮስ ይህንን ደብዳቤ እንደጻፍኩልህ አንዱ ጓደኛዬ ደውሎ በሚኒስትር ማዕረግ በአማካሪነት መሾምህን ነገረኝ፡፡ ታዲያ ለዚች አገር የሚጠቅም ምክር እንድታቀርብ እጠይቅሃለሁ፡፡

አቶ ታዲዮስ የመንግሥት ሠራተኛው አካሉ በሥራ ቦታው ቢውልም አዕምሮው ግን ከሥራ ውጪ ነው፡፡ “People who leave their minds at home and bring their bodies to work will destroy us. ”  አይደል ለእኛ አገር የመንግሥት ሠራተኛ ነጮች የሚቃኙለት?

አቶ ታዲዮስ ሳልነግርህ እኛ መሥሪያ ቤት ክፍት የሥራ ቦታ ማስታወቂያ ከጋዜጣ ላይ የማያዩት የፋይናንስና የግዥ ሠራተኞች ብቻ ናቸው፡፡ ዓይነ ሥውሩ ክብሩም ቢሆን በጃኦስ ሶፍትዌር በመጠቀም በኢንተርኔት ክፍት የሥራ ቦታ ማስታወቂያ ይከታተላል፡፡ ክብሩ ኢንተርኔት ላይ የማይለቀቁ ክፍት የሥራ ቦታዎችን ብቻ የያዘ ክፍል በብሬል ስለማይወጣ፣ በተለያዩ ቦታዎች ተዘዋውሮ መሥራቱ እንደተገደበ ለሰብዓዊ መብት ኮሚሽን የደረሰበትን ችግር ማመልከቱን ነግሮኛል፡፡

አቶ ታዲዮስ ሰማያዊ የፐብሊክ ሰርቪስ ባስ ተመድቦልናል፡፡ እኛ የመንግሥት ሠራተኞችን በጣም እንደጠቀመን ለምታማክራቸው ሰዎች ንገራቸው፡፡ ግን የፅዳትና በሌሊት ሥራ የሚገቡ ሠራተኞች የአገልግሎቱ ተጠቃሚዎች ስላልሆኑ ሊታሰብበት ይገባል ብለህም አማክራቸው፡፡

አቶ ታዲዮስ ሆቴል የሚሠራው ጓደኛህ እንዴት ነው፡፡ አንድ ቀን የሆቴል ምርቃት ፕሮግራም ላይ ተሳትፌ ነበር፡፡  ጓደኛህ አምስት ጊዜ ተሸለመ፡፡ የሸለሙትንም ሰዎች ቢያንስ ሦስት ጊዜ ሸለመ፡፡ እነሱ ተሸላለሙ፡፡ ሠራተኛው ቢያንስ 100 ጊዜ አጨበጨበ፡፡ ያዘጋጁት ሰዎች ሲሸላለሙ ፕሮግራሙ አለቀ፡፡ ለምስኪኑ ሠራተኛ ምን ተረፈ፡፡ ለእኔ ግን በየጠረጴዛው ውስኪ ሲቀርብ ግማሽ ጠርሙስ  ጠጣሁ፡፡

አቶ ታዲዮስ ኢንጅነሩ ጓደኛህስ እንዴት ነው? የኮንዶሚኒዬም ቤቶች ሲመረቁ በቴሌቪዥን መስኮት ፊት ለፊት አይቸዋለሁ፡፡ ደረጃ አንድ የኮንተራክተር ፈቃድ በወንድሙ ስም እንዳወጣ አውቄያለሁ፡፡ ብቻ የሚሠራበትን ቦታ ሥራ ለመቀበያነት እንደሚጠቀምበት ከሚሠራበት መሥሪያ ቤት ሰምቻለሁ፡፡

ምነው አፈር በሆንኩ? እስካሁን ድረስ የትራፊክ ጓደኛህን ሳልጠይቅህ ቀረሁ፡፡ በኤፍኤም ሬዲዮ የተጠየቀው እንቆቅልሽ አያስታውሰኝ መሰለህ?

“መንገድ ላይ ቁጭ ብላ ሽንኩርት የምትልጥ?” የሚል ጥያቄ በኤፍኤም ሬዲዮ ተጠየቀ፡፡ አንድ መላሽ ቀጥታ በአየር ላይ ገባ፡፡ “ትራፊክ ፖሊስ” በማለት ምላሽ ሰጠ፡፡ በጣም ገረመኝ፡፡ አሁን አሁን ፖሊስም የወንጀል ምርመራ ሥራዎችን ሲሠራ እጅህ ከምን ማለት ጀምሯል፡፡ የጓደኛህ ሚኒባስ ታክሲ ገቢው ጨመረ ወይ? አቶ ታዲዮስ ነገርን ነገር ያነሳዋል አይደል? የትራፊኩ ፖሊስ ጓደኛ አቃቤ ሕጉ ጓደኛህ ደህና ነው ወይ? የአቃቤ ሕጉ ጓደኛ ዳኛው ጓደኛህስ እንዴት ነው? የጓደኛው ጓደኛ ጠበቃውስ እንዴት ነው?

እንደበፊቱ ጠበቃው፣ አቃቤ ሕጉ፣ ፖሊሱና ዳኛው አንድ ላይ ቢዝነስ በጋራ ይሠራሉ እንዴ? ወይስ በሕግ ጥላ ሥር መኖር ጀመሩ? መቼም እዚች አገር ተደራጅቶ ካልተሠራ ውጤታማ መሆን አልተቻለም፡፡ አያቴ አንዳንዴ እንደሚሉት፣

‘ካልተገኘ በቀር ቁና ሙሉ ቆሎ

ከጠፋ ጭብጦ

ፍትሕ ቀረ ቀልጦ’

አቶ ታዲዮስ እንግዲህ ከመንግሥት ሠራተኞች በሰላም፣ በምቾትና በድሎት የሚኖሩት እነዚህ አንተ የምታውቃቸው የአንተ ጓደኞች ብቻ ናቸው፡፡

አቶ ታዲዮስ እንቅልፋሙ ጓደኛህ እንዴት ነው? ፓርላማ ላይ የማንቀላፋት ሱስ ያለበትን ማለቴ ነው፡፡  በሚቀጥለው ደብዳቤ በጎ አድራጎት ኤጀንሲ ስለገቡ ጓደኞችህና ስለኤንጅኦ ደብዳቤ እጽፍልሃለሁ፡፡

ፈጣሪ ኢትዮጵያን ይባርክ!

 

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እየገለጽን፣ ጸሐፊውን በኢሜይል አድራሻቸው [email protected] ማግኘት ይቻላል፡፡

spot_imgspot_img
- Advertisment -

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

Related Articles