Wednesday, March 22, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊየተበሉ አደራዎች

የተበሉ አደራዎች

ቀን:

ከዓመታት በፊት ነው፡፡ ባህር ማዶ ለመውጣት የሚያስፈልጓቸውን ነገሮች ሁሉ አሟልተዋል፡፡ የቀራቸው ንብረታቸውን ቦታ ማስያዝ ብቻ ነበር፡፡ መኖሪያ ቤታቸውንም እንዲያስተዳድሩ ለሚቀርቧቸውና ታማኝ ለሚሏቸው ጎረቤታቸው በአደራ ሰጡ፡፡ ጎረቤታቸውም በእምነት የተረከቡትን ቤት በማከራየትና በመጠበቅ ያስተዳድሩ ጀመር፡፡

ከተወሰነ ጊዜ በኋላ በሥራ ምክንያት ክፍለ አገር ይኖር የነበረ የወካዮቹ ቤተሰብ መጣ፡፡ ባለቤቶቹም ከቤቱ የሚገኘውን ጥቅማ ጥቅም ያገኝ ዘንድ ቤቱን ከባለ አደራው ተረክቦ እንዲያስተዳድር ወሰኑ፡፡ በዚህ መሠረትም ቤቱን ከባለአደራው ለመረከብ ጥያቄ አቀረበ፡፡ ባለአደራው ግን በጀብለው አልሰጡትም፡፡ ይልቁኑ ቤቱ የግላቸው መሆኑን በመግለጽ አንዳችም የመብት ጥያቅ እንዳያነሳ ማስጠንቀቂያ ሰጡት፡፡ በመካከላቸው የተፈጠረውን ችግርም በሰፈር ሽምግልና ለመፍታት ተሞክሯል፡፡ ነገር ግን በአጭር መቋጨት አልተቻለም፡፡ ጉዳዩም ፍርድ ቤት ደረሰ፡፡

ሰዎች አስገዳጅ ሁኔታዎች ሲያጋጥማቸው ንብረቶቻቸውን ሦስተኛ ወገን እንዲያስተዳድረው አሳልፈው ይሰጣሉ፡፡ ይህም ሲወርድ ሲዋረድ የመጣ አሠራር ሲሆን ብዙ ጊዜ ሕጋዊ ውል ላይ ያልተመሠረተ ስለሚሆን ዋጋ ሲያስከፍል ይስተዋላል፡፡ በመተማመን ላይ የተመሠረተው ውክልና በሕግ የተመዘገበ ባለመሆኑ ባለቤትነቱን ለመካድ የተመቸ ሆነ፡፡

በአገሪቱ የረጅም ጊዜ ታሪክ ያለው የአደራ ውል ዛሬም በብዙ ሰዎች ዘንድ ይመረጣል፡፡ ጥቂት የማይባሉትም የተቀበሉትን አደራ እምነት ሳያጎድሉ ለማስተዳደር ሲሞክሩ፤ የተቀሩት ግን አላግባብ ጥቅም በመፈለግ አልያም ለሌላ አሳልፈው ሲሸጡ፣ ይዞታውን ሲቀይሩና የራሳቸው ሀብት እንደሆነ ሁሉ እንዳሻቸው ሲያዙበት ይስተዋላል፡፡ ባለንብረቶቹ በቅርበት የማስተዳደር ዕድሉ ኖሯቸው ከባለአደራው ለመረከብ በሚያደርጉት ጥረት የሚክዱበት አጋጣሚም ጥቂት አይባልም፡፡

በዚህም ብዙ ግጭቶች ይፈጠራሉ፡፡ ምንም እንኳ ሕጋዊ ውል ያልፈጸሙ ቢሆንም በሕግ ለመዳኘት ፍርድ ቤት የሚመላለሱ ጥቂት አይደሉም፡፡ ተካድን ሲሉ አቤቱታ የሚያቀርቡ ባለንብረቶችም የባለቤትነት ማስረጃ ለማቅረብ ላይ ታች በማለት ለአላስፈላጊ ወጪና እንግልት ሲዳረጉ ይስተዋላል፡፡

መተማመንን መሠረት አድርጎ የሚከወን ንብረት የማስተደደር ውክልና ትልቅ ማኅበራዊ ግምት የሚሰጠው መሆኑን የሕግ አማካሪና ጠበቃ አቶ ብሥራት ተክሉ ይናገራሉ፡፡ መተማመኑ በኅብረተሰቡ ዘንድ ያለውን ማኅበራዊ ትስስር የማያጎለብት ቢሆንም አልፎ አልፎ የሚፈጠረው ችግር ብዙዎችን ዋጋ እያስከፈለ እንደሚገኝ ይገልጻሉ፡፡

በብዛት በአገር ውስጥ ሀብት ያፈሩና ኑሯቸውን ከአገር ውጪ ያደረጉ ዳያስፖራዎች የችግሩ ሰለባዎች እንደሚሆኑ ያስረዳሉ፡፡ አብዛኛዎቹ ንብረት የማስተዳደር ኃላፊነቱን ለቤተሰቦቻቸው አልያም ለቅርብ ጓደኛቸው ይሰጣሉ፡፡ በመተማመን ላይ የተመሠረተ ስለሚሆንም ውል የመፈጸሙን ሁኔታ ወደጎን ይተውታል፡፡

‹‹በተለይም ባህር ማዶ በሚኖሩ ጥንዶች ንብረት ላይ በርካታ ችግሮች ያጋጥማሉ›› የሚሉት አቶ ብሥራት በአንድ ወቅት የገጠማቸውን እንዲህ ያስታውሳሉ፡፡ ጥንዶቹ ከአገር ሲወጡ ንብረታቸውን የማስተዳደር ኃላፊነት የሰጡት ለሚስት አጎት ነበር፡፡ ከጊዜ በኋላ ትዳራቸው ያልሰመረላቸው ጥንዶቹ በፍቺ ተለያዩ፡፡ የንብረት ክፍፍል በሚደረግበት ወቅት አገር ውስጥ የነበረው ንብረታቸው በክፍፍሉ አለመካተቱ ግጭት አስነሳ፡፡

የንብረቱ አስተዳዳሪ የነበሩት የሚስት አጎት ንብረቱን አሳልፈው ሸጠዋል፡፡ ይህም ከተሰጣቸው መብቶች መካከል ያልነበረ ሲሆን ጉዳዩ በሕግ እንዲታይላቸው የወሰኑት ተበዳይ ጉዳዩን ለሕግ አቤት አሉ፡፡

መሰል ገጠመኞች በቤተሰብ መካከል የሚፈጥሩትን ቅራኔ በመሸሽም ሌላ አማራጭ የሚወስዱ ጥቂት አይደሉም፡፡ በሕግ አግባብ ውልን መሠረት ያደረገ ውክልና በመስጠት ሥጋት የሆኑባቸውን መብቶች የሚያወጡ ብዙ ናቸው፡፡ ‹‹ውክልናውን ከሰጡ በኋላ ባልና ሚስቱ ለብቻቸው ተስማምተው መሸጥና መለወጥ የሚለውን አንቀጽ ያወጡታል›› ይላሉ፡፡

ሕጋዊ ውል ባልተፈጸመበት ሁኔታ በብዛት ካጋጠሙ የመብት ጥሰቶች መካከል ከአገር በወጡ ኤርትራውያንን ያጋጠሙ ችግሮች ይጠቀሳሉ፡፡

ከዓመታት በፊት በሁለቱ አገሮች መካከል በነበረው ግጭት በርካታ ኤርትራውያን እንዲወጡ ተገድደዋል፡፡ ብዙዎቹም ‹‹እንመለሳለን›› በሚል ተስፋ ቤት ንብረታቸውን በውክልና አገር ውስጥ ለሚኖር ቤተዘመድና የቅርብ ጓደኛ ቤትና ንብረታቸውን አደራ ሰጥተው ነበር፡፡ ቤት ንብረት ያላቸው ኤርትራውያን ንብረታቸው እንዲመለስ በወጣው አዋጅ መሠረትም ጥቂት የማይባሉት ተመልሰዋል፡፡ ብዙዎቹ ግን ‹‹አለ›› ብለው ያሰቡት ንብረት ተሽጦና ተለውጦ ጠብቋቸዋል፡፡ በዚህ ረገድ ያጋጠማቸውን ኬዝ አቶ ብሥራት እንዲህ ያስታውሳሉ፡፡

ግለሰቡ ሙሉ ንብረታቸውን ለሚስታቸው ትተው ኤርትራ ገቡ፡፡ ከዓመታት በኋላ የወጣውን አዋጅ ተከትሎም ወደ አገር ይመለሳሉ፡፡ ተስፋ የጣሉባቸው ንብረቶቻቸው ግን በቦታቸው አልነበሩም፡፡ ‹‹ሚስት ባለቤታቸው እንደሞቱ አልያም እንደጠፉ ሁሉ የልጆቻቸውን ውርስ ይጠይቃሉ፡፡ ጥያቄውም ተቀባይነት አግኝቶ ውርሱ ተላለፈላቸው፡፡ ይሁን እንጂ ውርሱን ሲቀበሉ ባልታወቀ ምክንያት በልጆቻቸው ስም አላስመዘገቡትም፡፡ ንብረቱ የራሳቸው እንደሆነ ሁሉ ያስመዘገቡት በስማቸው ነበር›› በማለት በጥንዶቹ መካከል የተፈጠረውንና ፍርድ ቤት ያቆማቸውን ግጭት መነሻ ያብራራሉ፡፡

እንደ አቶ ብሥራት ገላፃ ንብረቱ ለሌላ ሰው ተላልፎ የተሸጠ ሲሆን ገዢውም ለሌላ ወገን አሳልፎ ሸጦታል፡፡ መሰል ጉዳዮች ብዙ ሲሆኑ እስካሁን ንብረታቸውን ያላገኙ በርካታ ኤርትራውያን ይገኛሉ፡፡

አንዳንዴ በውልና ማስረጃ በተደገፉ ውክልናዎችም ባለቤትነትን የመካድና ሌሎች የማጭበርበር ድርጊቶች ያጋጥማሉ፡፡ ውሉ ላይ ከተዘረዘሩ የአስተዳዳሪው ኃላፊነቶች ላይ ተጨማሪ መብት የሚሰጥ አንቀጽ በመጨመር የተፈጸመ የማጭበርበር ድርጊት ያስታውሳሉ፡፡ ንብረቱን የማስተዳደር ኃላፊነት የተሰጣት ግለሰብ ሕግን መሠረት ያደረገ ውል ፈጽማለች፡፡ ነገር ግን በውልና ማስረጃ ጽሕፈት ቤት ተቀማጭ በተደረገው መረጃ ያልተካተተ መብት የሚሰጥ ኮፒ በእጇ ይገኛል፡፡ ይኸውም መሸጥና መለወጥ የተባለ አንቀጽ ያካተተ ሲሆን በጽሕፈት ቤቱ በሚገኙ ሁለቱ ኮፒዎች ላይ ያልነበረ ነው፡፡ ይህ የታወቀውም ግለሰቧ ንብረቱን ከሸጠች በኋላ በተነሳው የመብት ጥያቄ ነው፡፡ ድርጊቱ ያለፈቃድ ንብረት ሸጦ ከመጠቀም ባሻገር ‹‹ማንኛውም ግለሰብ በወከለው ሰው ስም የሚሰበሰበውን ገንዘብ ለወካዩ የመስጠት ግዴታ አለበት›› የሚለውን የሕግ ድንጋጌ የሚጥስም ነበር፡፡

በአደራ የሚተላለፍ የንብረት አስተዳደር በተለይ በቤተዘመድ መካከል ሲፈጸም በርከት ያሉ የመብት ጥሰቶች እንደሚያጋጥሙ አቶ ብሥራት ይናገራሉ፡፡ ብዙ ጊዜ ግን በመካከላቸው ቅራኔ ከመፍጠር ባለፈ ጉዳዩን ከሕግ ፊት አያቀርቡም፡፡ በቤተ ዘመድ ሽምግልና መፍታት ይመርጣሉ አልያም እንደዚሁ ተደባብሶ ይቀራል፡፡

የንብረት አስተዳደር ውክልና አጠቃላይና ልዩ ውክልና በሚል ለሁለት ይከፈላል፡፡ አጠቃላይ ውክልና በየሦስት ዓመቱ መታደስ ያለበት ሲሆን ውስን መብቶች ማከራየት፣ ማሳደስ የመሳሰሉትን ይይዛል፡፡ ልዩ ውክልና ሲሆን የተሰጠው ሥልጣን በግልፅ በውክልናው መስፈር አለበት፡፡ የመሸጥና የመለወጥ መብት የሚሰጠውም በልዩ ውክልና ውስጥ ነው፡፡ ከሕጉ አኳያ አንድ የንብረት አስተዳዳሪ በንብረቱ ላይ የሚወስናቸው ውሳኔዎች የወካዩን ጥቅም የማይነካ መሆን አለበት፡፡ አንድ መልካም ባለቤት ለቤቱ የሚያደርገውን ጥበቃ በአደራ ለተቀበለውም ንብረት ሊያደርግለት ይገባል፡፡ በዚህ መሠረት ጥቂት የማይባሉ ግለሰቦች ከሞላ ጎደል ኃላፊነታቸውን ሲወጡ የተቀሩት አግባብ ያልሆኑ ድርጊቶችን ይፈጽማሉ፡፡

በአገር ውስጥ የብዙዎች ራስ ምታት ሆኖ የቆየው የንብረት አስተዳደር በሌላው ዓለም ለዚሁ ዓላማ የተቋቋሙ ሕጋዊ ድርጅቶች በመኖራቸው ብዙም ችግር ሲሆን አይትይም፡፡ አክስዮን፣ ቦንድን ጨምሮ ልዩ ልዩ ተንቀሳቃሽና የማይንቀሳቀሱ ንብረቶች ያስተዳድራሉ፡፡ በአገር ውስጥም መሰል ተቋማት ብቅ ብቅ ማለት የጀመሩ ሲሆን ጥቂት ለማይባሉ ተጠቃሚዎች እፎይታ ፈጥሯል፡፡

ከአራት ዓመታት በፊት የተቋቋመው ‹ሆም ኢን አዲስ›› ንብረት ከሚያስተዳድሩ ድርጅቶች አንዱ ነው፡፡ የድርጅቱ መሥራችና ሥራ አስኪያጅ አቶ ሳሙኤል ኢዮብ ናቸው፡፡ አቶ ሳሙኤል ለበርካታ ዓመታት ባህር ማዶ ቆይተዋል፡፡ በቆይታቸው መልካም ባህል ብለው ያሰቡትን ንብረት የማስተዳደር ሥራ በአገር ውስጥ ቢተገብሩም የመጀመሪያዎቹን ዓመታት በድረገጻቸው አገልግሎቱ ምን ያህል ተፈላጊነት እንዳለው ሲያጠኑ ቆይተዋል፡፡ ‹‹በመጀመርያ በድረ ገጹ 40 የሚሆኑ ንብረቶች ለቀቅን፡፡ በየቀኑ ከ50 የሚበልጡ ክሊኮች እናገኝም ጀመር፤›› የሚሉት አቶ ሳሙኤል በዚህ መልኩ የአገልግሎቱን ተፈላጊነት ካረጋገጡ በኋላ ሥራውን አጠናክረው ገፉበት፡፡ ዛሬ ሆምኢን አዲስን ጨምሮ አገልግሎቱን የሚሰጡ ጥቂት የማይባሉ ተቋማት በአገር ውስጥ ይገኛሉ፡፡

አቶ ግዛው ተፈራ አገልግሎቱን ከተጠቀሙ ሰዎች መካከል ናቸው፡፡ አቶ ግዛው ኑሯቸው በአሜሪካ ነው፡፡ ‹‹ምናልባት በአገር ውስጥ የምኖርበት አጋጣሚ ከተፈጠረ›› በሚል ከዓመታት በፊት ላፍቶ አካባቢ ቤት ገንብተው ነበር፡፡ ነገር ግን በአገር ውስጥ ለመኖር ገና ዝግጁ አልነበሩምና ቤቱን የሚያስተዳድረው ወንድማቸው ነበር፡፡ በዚህ መልኩ ንብረታቸውን ማስጠበቅ ቢችሉም የግድ ወደ አገር እንዲመጡ የሚያስገድዳቸው አጋጣሚ ተፈጠረ፡፡ ወንድማቸውም ሞቱ፡፡

በአገር ውስጥ የመኖር ፍላጎታቸውን በማቆየትም ቤቱን ለመሸጥ አሰቡ፡፡ ይህንን ለመፈጸም ግን የግድ ወደአገር መግባት አልነበረባቸውም፡፡ ለጥቂት ጊዜያት ምን ማድረግ እንዳለባቸው ግር ብሏቸው የነበረ ቢሆንም ሪስኮም የተባለ ንብረት የማስተዳደር አገልግሎት የሚሰጥ ድርጅት አገኙ፡፡ ‹‹እንዲህ ያለ አገልግሎት በአገር ውስጥ ይኖራል ብዬ አልጠበኩኝም›› የሚሉት አቶ ግዛው አገልግሎቱን ለመጠቀም አላመነቱም ነበር፡፡ ድርጅቱን በአነጋገሩ በሦስተኛው ቀንም ሽያጩ ሊፈጸምላቸው ችሏል፡፡

ሪስኮም ቤት የማከራየት፣ የመሸጥ፣ ጥበቃ፣ ፅዳትና የመሳሉትን የንብረት ማስተዳደር ሥራዎች ይሠራል፡፡ አገልግሎቱንም በተለያዩ ድረገጾች የሚያስተዋውቅ ሲሆን፣ አገልግሎት መስጠት በጀመረበት ዓመት ውስጥ ጥቂት የማይባሉ ደንበኞች አፍርቷል፡፡

‹‹አጠቃላይ ባለቤቱ የሚሠራውን ሥራ እንሠራለን›› ያሉት የሪስኮም ድርጅት መሥራች ወይዘሮ መሰለች ብርሃን ናቸው፡፡ በኪራይ ቤቶች ኤጀንሲ ይሠሩ እንደነበር የሚናገሩት ወይዘሮ መሰለች በሥራ ገበታቸው ሳሉ በርካታ ውል የሌላቸው ውክልናዎች፣ ውላቸውን በተገቢው መፈጸም ያልቻሉ ግለሰቦች ክስ ይገጥማቸው እንደነበር ያስታውሳሉ፡፡ ሁኔታውን እንደማንኛውም ተመልክተው አላለፉም፡፡ ይልቁኑ ንብረታቸው በሦስተኛ ወገን እንዲተዳደርላቸው ለሚፈለጉ ግለሰቦች ግልጋሎት የሚሰጠውን ሪስኮምን አቋቋሙ፡፡

እስካሁን ማስተዳደር የቻሉት የመኖሪያ ቤቶችን ብቻ ሲሆን ከቀናት በፊት ግን አንድ ሕንፃ ለማስተዳደር ውል መግባታቸውን ይናገራሉ፡፡ ‹‹ከደንበኞች አድራሻቸውንና የቤት ቁጥር በመቀበል ቤቱን እናገኘዋለን›› በማለት ሒደቱን የስረዳሉ፡፡ የሚሰጡት አገልግሎትም የኪራይ ሲሆን አሥር በመቶ እንዲሁም ሽያጭ ሲሆን ሁለት በመቶ ክፍያ እንደሚቀበሉ ይናገራሉ፡፡

‹‹አገልግሎቱ ብዙ አልተለመደም›› የሚሉት ወይዘሮ መሰለች የደንበኞችን ፍላጎት ተከትለው ለማስፋፋት እንዳሰቡ ተናግረዋል፡፡

አብዛኞቹ የአገልግሎቱ ተጠቃሚዎች ዳያስፖራዎች ቢሆኑም አንዳንድ የአገር ውስጥ ነዋሪዎችን ማግኘት ተችሏል፡፡ ካፒቴን ሽመልስ ከበደ ይባላሉ፡፡ ለገጣፎ በሚገኘው ሲሲዲ የመኖሪያ መንደር ውስጥ ቤት አላቸው፡፡ ቤቱን የገነቡት በጡረታ ጊዜአቸው ሊኖሩበት አስበው የነበረ ቢሆንም በጡረታ ጊዜአቸው በሙያቸው የማስተማር ዕድል ስላገኙ ከከተማ አልወጡም፡፡ ቤቱን ለማስተዳደር በቂ ጊዜ ስለሌላቸውም የንብረት ማስተዳደር ግልጋሎት ከሚሰጡ ድርጅቶች ጋር ውል ፈርመዋል፡፡

አገልግሎቱን መጠቀም ከጀመሩ ዓመት አልፏቸዋል፡፡ የንብረት አስተዳዳሪዎቹ ቤቱን አከራይተውላቸዋል፡፡ ገንዘባቸውም ወሩን ጠብቆ ይደርሳቸዋል፡፡ ለዚህም ሁለት በመቶ የሚከፍሉ ሲሆን ግብር፣ ዕድሳትና ሌሎችም ልዩ ልዩ ጉዳዮችን የሚፈጽመው ድርጅቱ መሆኑን ይናገራሉ፡፡ ‹‹አገልግሎቱ በጣም አስደሳች ነው›› የሚሉት ካፒቴን አገልግሎቱ መስፋፋትና መበረታታት እንደሚገባው አስተያየት ይሰጣሉ፡፡

አገልግሎቱ በበቂ ባለመታወቁ የተለያዩ ድርጅቶች ገጠመኞችን ያስተናግዳሉ፡፡ ብዙዎቹ ሰዎች ገንዘብ ይዘን የምንጠፋ ይመስላቸዋል፡፡ የሚሉት የሆም ኢን አዲስ ሥራ አስኪያጅ አቶ ሳሙኤል አገልግሎቱ ካለመታወቁ ጋር ተያይዞ የሚከሰቱ ችግሮችን ለመሸሽ ሌሎች አማራጮችን እንደሚጠቀሙ ይናገራሉ፡፡ ንብረቱ የተሸጠበትን ዋጋና የቤት ኪራይ ገዢው ቀጥታ ወደ ባለቤቱ የባንክ ደብተር እንዲያስገባ ያደርጋሉ፡፡ ይሁን እንጂ በሌላ በኩልም ቢሆን የሸሹትን አጋጣሚ ከመጋፈጥ አልተረፉም፡፡ ጉዳዩ የአንድ ቤተሰብን የውርስ ንብረት የማስተዳደር ውል ነበር፡፡ አገልግሎቱን የሚያውቀው አንደኛው የቤተሰቡ አባል ሲሆን ውል ለመፈጸም አቶ ሳሙኤልን ይዞ ቤተዘመዶቹ ጋር ሄዱ፡፡ የገጠማቸው ግን ከጠበቁት የተለየ ነበር፡፡ ወጣቱ ሆነ ብሎ ንብረት ለማሸሽ የፈጠረው ሐሳብ እንደሆነ ቤተሰቦች በመጠርጠራቸው ግጭት ተፈጠረ፡፡

ከንብረት ማስተዳደር ጋር የሚነሱ ችግሮች በመላው አገሪቱ የሚስተዋሉ ቢሆንም ተቋማቱ አገልግሎቱን ከአዲስ አበባ ውጪ ላለው ኅብረተሰብ ማድረስ አልቻሉም፡፡ በብዛትም ቤት ማስተዳደር ላይ ብቻ የተወሰኑ ሲሆን ሌሎች ንብረቶችን ለማስተዳደር ቢሹም የሕዝቡ ግንዛቤ ሰፊ ባለመሆኑ አገልግሎታቸው እንዲወሰን አድርጓል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

[ክቡር ሚኒስትሩ ከሚያከብሯቸው አንድ የቀድሞ ጉምቱ ፖለቲከኛ ስልክ ተደውሎላቸው እያወሩ ነው]

አንዳንድ ነገሮች ቢያሳስቡኝ ነው ቀጠሮ ሳልይዝ ላወራህ የፈለኩት ክቡር...

የትግራይ ክልል የሽግግር አስተዳደር ምሥረታና የሰላም ስምምነቱ ሒደት

በትግራይ ክልል ጊዜያዊ የሽግግር መንግሥት ለመመሥረት ደፋ ቀና እየተባለ...

ጥራዝ ነጠቅነት!

ከሜክሲኮ ወደ ጀሞ እየሄድን ነው፡፡ የተሳፈርንበት አሮጌ ሚኒባስ ታክሲ...

አወዛጋቢነቱ የቀጠለው የአዲስ አበባ የጤፍ ገበያ

ሰሞኑን የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በጤፍ የተከሰተውን የዋጋ ንረት...