ሰሞኑን አነጋጋሪ ከሆኑ ዜናዎች አንዱ ሦስት አሜሪካውያንና አንድ እንግሊዛዊ ፈረንሣይ ውስጥ ባቡር ላይ ጥቃት ሊያደርስ የነበረን አሸባሪ መግታታቸው ነው፡፡ ከአምስተርዳም ወደ ፓሪስ ይጓዝ በነበረ ባቡር ውስጥ መሣሪያ ታጥቆ የነበረውን አሸባሪ፣ ራሳቸውን ለአደጋ አጋልጠው በመታገል የብዙዎችን ሕይወት የታደጉት ግለሰቦች ለተጋድሎአቸው ከፈረንሣይ መንግሥት የአገሪቱን እጅግ ትልቅ ሽልማት አኝግተዋል፡፡ በተለያዩ አገሮች ዘርፈ ብዙ የሽልማት ዓይነቶች አሉ፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥም የተለያዩ ክንውኖችን በማስመልከት ከመሪዎች የሚበረከቱ ሽልማቶች አሉ፡፡ ማኅበረሰቡም በባህላዊ መንገድ ጀግኖችን ሲያወድስ ኖሯል፡፡
በአገሪቷ የሽልማት አሰጣጥ ታሪክ በመንግሥታዊ ተቋሞች ደረጃ ከሚጠቀሱት መካከል የቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ የሽልማት ድርጅት አንዱ ነው፡፡ ባይዘልቅም የኪነ ጥበባትና መገናኛ ብዙኃን ድርጅትንም ማንሳት ይቻላል፡፡ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ደግሞ በግል ተቋሞች፣ በሙያ ማኅበራት አንዳንዴም በግለሰቦች ሽልማት ሲሰጥ ይስተዋላል፡፡ በልዩ ልዩ ዘርፎች ሽልማት በመስጠት ብቅ ብቅ ያሉ ብዙ ቢሆኑም የዘለቁት ጥቂቱ ናቸው፡፡
ስለሽልማት ሲነሳ ብዙዎች ጥያቄ የሚሰነዝሩበት ጉዳይ በማን መሰጠት አለበት? የሚለውን ነው፡፡ አንዳንዶች በመንግሥታዊ ተቋማት ብቻ እንዲሰጥ ሲሹ፣ ሌሎች ለአንድ ሙያ በቀረቡ አንዳንዴም በገለልተኞች መሰጠቱን ይደግፋሉ፡፡ ሽልማት መሰጠት ያለበት ዕውቅና ባለው ተቋም ብቻ እንደሆነ የሚገልጹ አስተያየት ሰጪዎች፣ በሽልማት ሰጪዎች ላይ ጥያቄ ያላቸው ግለሰቦች የተበረከተላቸውን ሽልማት ለመቀበል ፈቃደኛ ያልሆኑባቸውን አጋጣሚዎች ያጣቅሳሉ፡፡ ለሽልማት የሚሰጠው ክብር በሰጪዎቹ አሠራር ጥራት የሚወሰን እንደሆነ የሚያምኑም አሉ፡፡
በተያያዥ ለአንድ ሽልማት የሚታጩ ግለሰቦች ወይም ተቋማት የሚለዩበት መስፈርት ላይ እና በዳኝነት ሒደት ግልጽነትና ፍትሐዊነት ዙሪያም ጥያቄ ይነሳል፡፡ ምንም እንኳን በተለያየ ዘርፍ የላቀ አስተዋጽኦ ያላቸውን ማወደስ ከግለሰቦቹ ባለፈ አገራዊ ፋይዳው የጎላ ቢሆንም፣ ሽልማቱን የሚሰጡ ተቋሞች የተነሱበት ዓላማ መፈተሽ እንዳለበት የሚያምኑ አሉ፡፡
በዚህ ረገድ የብዙዎች ሥጋት የሆነው ሙያተኞችን መሸለም ኃላፊነታችን ብለው በአግባቡ የሚሠሩ እንዳሉ ሁሉ፣ ሒደቱን እንደ ቢዝነስ የወሰዱትም መኖራቸው ነው፡፡ ገንዘብ ተኮር የሆኑ ተቋሞችና ሽልማት በመስጠት አንድ የሙያ ዘርፍ እንዲጎለብት የሚተጉ ተቋሞች መለየት እንዳለባቸው እሙን ነው፡፡ ሽልማት ለአበርክቶ ምስጋና የሚቀርብበት ከመሆኑ ባሻገር በአንድ ሙያ ጤናማ ፉክክር በመፍጠር ለተሻለ ሥራ የሚያነሳሳ ነው፡፡ ይህንን ከግምት በማስገባትም ሽልማቶች በአግባቡ እንዲካሄዱ በሚመለከታቸው ተቋሞች ቁጥጥር ይደረጋልን? የሚል ጥያቄ ማንሳት ይቻላል፡፡
በሌላ በኩል በአገሪቱ በቂ ሽልማት ሰጪ ተቋሞች እንደሌሉ ይነገራል፡፡ ካለው የሙያ ስብጥርና የባለሙያዎች ቁጥር አንፃር በበቂ ሁኔታ ሽልማት እየተሰጠ እንዳልሆነም ይገለጻል፡፡ ከሽልማት ሰጪዎች መካከል በአግባቡ የሚሠሩ በሕዝብ ተቀባይነት ስለሚያገኙ ዘለቄታ እንደሚኖራቸውና መስመራቸውን የሳቱት ጊዜ እንደሚሽራቸው ያምናሉ፡፡
የበጎ ሰው ሽልማት የተጀመረው ከሁለት ዓመት በፊት ነበር፡፡ በልዩ ልዩ ሙያ የተሰማሩ ግለሰቦች ለማኅበረሰቡ ባበረከቱት አስተዋጽኦ ተወዳድረው እንደሚሸለሙ የበጎ ሰው ሽልማት ሰብሳቢ ዲ/ን ዳንኤል ክብረት ይናገራል፡፡ ‹‹በጎ ሰው ማለት ከግል ጥቅሙ በዘለለ ለአገርና ለወገኑ የሠራ ሰው ነው፤›› ይላል፡፡ በተለያዩ አካባቢዎች የሚኖሩ ግለሰቦች በሕዝብ ከተጠቆሙ በኋላ የሽልማቱ አዘጋጅ ኮሚቴ በሚመድባቸው ዳኞች አሸናፊዎች ይለያሉ፡፡
እሱ እንደሚለው፣ ለአገርና ለሕዝብ በሙያቸው መልካም ነገር ያደረጉና ማኅበረሰባዊ ኃላፊነታቸውን የተወጡ ሰዎች ዕውቅና ሊሰጣቸው ይገባል በሚል ነው ሽልማቱ የተጀመረው፡፡ መነሻ ያደረጉት ኖቤል ፕራይዝን ሲሆን፣ በሌሎች አገሮች ታላላቅ ሥራ የሠሩ ሰዎች እንደሚሸለሙና በኢትዮጵያ ይህ አካሄድ እንደማይስተዋል ይገልጻል፡፡
ዘንድሮ ጋዜጠኝነት፣ ሳይንስና ቴክኖሎጂ፣ መንግሥታዊ ኃላፊነትን በብቃት መወጣትን ጨምሮ አሥር ዘርፎች አሉ፡፡ በሕዝብ የተጠቆሙት 220 ሰዎች ሲሆኑ፣ 45ቱ ለመጨረሻ ዙር አልፈዋል፡፡ እንደ ዲ/ን ዳንኤል ገለጻ፣ በውድድሩ አንድ ሰው ሙያውን ተጠቅሞ ለማኅበረሰቡ ያበረከተው አስተዋጽኦ ከግምት ይገባል፡፡ ከሙያዊ ልቀት በላይ ግለሰቡ ለአገር ወይም ለሚኖርበት አካባቢ የሠራው ሥራ መመዘኛ መስፈርታቸው ነው፡፡ ተወዳዳሪዎቹ ሕዝብ በሙያቸው የሚያውቃቸው ወይም በአንድ አካባቢ ብቻ የሚታወቁ ሊሆኑ እንደሚችሉና ሲሸለሙ ዓርአያ ይሆናሉ በሚል እምነት እንደሆነ ይናገራል፡፡ ስለሚጠቆሙት ሰዎች ሚና በሚኖሩበት አካባቢ ወይም በሥራ የሚያውቋቸው ይጠየቃሉ፤ በሥራዎቻቸው ያስመዘገቡት ለውጥም ይገመታል፡፡
በጎ ሰው የዳኞቹን ማንነት አያስታውቅም፡፡ ዳኞቹ ተወዳዳሪዎች በሚቀርቡበት ሙያ ልምድ ያላቸው እንደሆኑ የሚናገረው ዲ/ን ዳንኤል፣ ማንነታቸውን አለማሳወቅ ከተወዳዳሪዎች ጋር መቀያየም እንዳይፈጠር ይረዳል ይላል፡፡ በኢትዮጵያ ስለግለሰቦች አበርክቶ ወይም አስተዋጽኦ ያለው መረጃ ውስን በመሆኑ በውድድሩ መካተት ያለባቸው ግለሰቦች የማይካተቱበት አጋጣሚ ሊፈጠር እንደሚችል ይናገራል፡፡ ‹‹ስህተት ሊፈጠር ይችላል፤ ስህተት ይፈጠራል ብሎ አለመሥራት ግን አይቻልም፤ አሠራሩን በሒደት ወደ ተሻለ ብቃት ከፍ ማድረግ ይመረጣል፤›› ይላል፡፡
በዲ/ን ዳንኤል ዕይታ፣ በአገሪቱ መንግሥታዊ ሽልማት፣ ተቋማዊ ሽልማትና በማኅበረሰቡ የሚሰጥም ሽልማት መኖር አለበት፡፡ አገሪቱን በሚወክል መንግሥት ለባለሙያዎች ሽልማት መሰጠቱ እንደሚጠቅም ገልጾ፣ ተቋሞችም ሕጋዊ መሠረትና ወጥ አሠራር መያዝ እንደሚገባቸው ይናገራል፡፡ በአገሪቱ ያሉ ሽልማቶች ችግር ቀጣይ አለመሆናቸውና በሚጀመሩበት አቅም አለመካሄዳቸው እንደሆነ ያምናል፡፡ ‹‹ሽልማቶች መጀመራቸው መጠላት የለበትም፤ ተነሳሽነቱ ጥሩ ቢሆንም ዓላማቸው እንዲስተካከል ገንቢ አስተያየት ሊሰጣቸው ይገባል፤›› ይላል፡፡
ፎረም ፎር ኢንቫይሮመንት በአካባቢ ጥበቃና እንክብካቤ ላይ የሚሠራ ድርጅት ሲሆን፣ ድርጅቱ ለሰባት ዓመታት በዘርፉ የሚሠሩ ግለሰቦችን፣ የሙያ ማኅበራትን፣ መንግሥታዊ ድርጅቶችን፣ የግል ተቋሞችንና ሌሎችንም እያወዳደረ ሸልሟል፡፡
የድርጅቱ ሥራ አስኪያጅ አቶ ዮናስ ገብሩ እንደሚናገሩት፣ ድርጅቱ ስለተፈጥሮ ሀብት ጥበቃ ቅስቀሳ ከሚያደርግባቸው መንገዶች አንዱ ማበረታቻ ሽልማት መስጠት ነው፡፡ ለተማሪዎች፣ ለአርሶ አደሮች፣ ለአርብቶ አደሮችና ለአካባቢ ጥበቃ ትኩረት ለሚሰጡ አካባቢዎች የሚሰጠውን አረንጓዴ ሽልማት የሚያበረክቱት የቀድሞው ፕሬዚዳንት ግርማ ወልደ ጊዮርጊስ ነበሩ፡፡ ሽልማቱ ብዙዎች በአካባቢ ጥበቃ አገር ውስጥ የሚሠሩት ሥራ ታውቆ ዓለም አቀፍ መድረኮች እንዲያገኙ አግዟል ይላሉ፡፡
አቶ ዮናስ እንደሚሉት፣ አቶ ግርማ በተፈጥሮ ጥበቃ ያበረከቱትን አስተዋጽኦ ተመርኩዘው ሽልማቱን እንዲሰጡ መርጠዋቸዋል፡፡ ‹‹ፕሬዚዳንት ከመሆናቸው በፊትም የተፈጥሮ ተቆርቋሪ ነበሩና ለሽልማቱ ትክክለኛ ሰው ነበሩ፤ ሽልማቱ በእሳቸው መሰጠቱ ተቀባይነቱንም ያጎላዋል፤›› ሲሉ ይገልጻሉ፡፡
የሽልማቱ ዕጩዎች የሚዳኙት በባለሙያዎች ሲሆን፣ ባለድርሻ አካላትም አስተያየት እንደሚሰጡበት ያስረዳሉ፡፡ እሳቸው እንደሚሉት፣ ሽልማት ስለአንድ ዘርፍ ዕውቀት ባላቸው ሲሰጥ ቦታ ያገኛል፡፡ ሽልማት ለመስጠት ብቻ ተብሎ በዘፈቀደ መጀመር እንደሌለበት የሚገልጹት አቶ ዮናስ፣ ‹‹ሽልማት እንዲሁ ከተሰጠ ክብሩ ወርዶ ተራ ነገር ይሆናል ተሸላሚውም ቦታ አይሰጠውም፤ በዘርፉም ለውጥ አያመጣም፤›› ይላሉ፡፡
ከኪነ ጥበብ ዘርፍ በሙዚቃና ፊልም የሚሸልመው ለዛ አምስተኛ ዙሩን በቅርቡ ያካሂዳል፡፡ በየዓመቱ ለሕዝብ የሚደርሱ ሥራዎች፣ ሕዝብ በሚሰጠው ድምፅ ተወዳድረው አብላጫውን ያገኙት ይሸለማሉ፡፡ የለዛ አዘጋጅ ብርሃኑ ድጋፌ፣ ውድድሩ በዋነኛነት በሕዝብ ድምፅ ቢዳኝም የባለሙያዎች ምዘና የሚካተትባቸው ዘርፎች መኖራቸውንም ይናገራል፡፡ ሙዚቃ ነክ ዘርፎች ሙሉ በሙሉ ከሕዝብ በሚገኝ ድምፅ ይወዳደራሉ፡፡ ሙዚቃዎች በተለያየ አጋጣሚ ለአድማጭ ስለሚደርሱ ሕዝብ ሰፊውን ድርሻ ቢወስድም፣ ፊልም ተደራሽነቱ ውስጥ በመሆኑ የባለሙያ ድምፅ ይታከልበታል ይላል፡፡
የውድድሩ ዳኞች ተዓማኒ እንደሆኑና የሕዝቡ ምርጫ ሒደትም ግልጽ እንደሆነ ያስረዳል፡፡ በመጀመርያው ዙር ድረ ገጽ ላይ ከተካተቱ ባለሙያዎች ለአንዱ ድምፅ ሲሰጥና ቁጥሩ ሲጨምር ስክሪን ላይ ይታያል፡፡ አንድ ሰው ከአንድ ስልክ ወይም ኮምፒውተር ከአንዴ በላይ ድምፅ መስጠት እንደማይችልና ሰዎች ጥያቄ ለሚያቀርቡ ሁሉም ተወዳዳሪዎች የሚያገኙት ድምፅ ይፋ እንደሚሆን ብርሃኑ ይገልጻል፡፡
‹‹በአንድ ዓመት ውስጥ ጥሩ ለሠራ ባለሙያ ዕውቅና ለመስጠት ያለመ ሽልማት ነው፤ ሽልማቱ የኪነ ጥበብ ባለሙያዎች በሕዝቡ ተወደው መመረጣቸውን በማሳየት ለተሻለ ሥራ ያነሳሳል፤›› ሲል ስለሽልማቱ ይናገራል፡፡ በእሱ እምነት፣ ሽልማት ስለሚሰጡ ተቋሞች ጥያቄ ከተነሳ አሠራራቸውን በመመርመር የተሻለ አቅጣጫ ማመላከት ይቻላል፡፡ ያሉት ሽልማት ሰጪዎችም በቂ እንዳልሆኑ ይናገራል፡፡ ሕዝብና ባለሙያዎች ቦታ መሰጠት ያለበት ለየትኞቹ እንደሆነ ስለሚገነዘቡ፣ ፈር የያዘ አካሄድ ያላቸው ይዘልቃሉ ሲልም ያክላል፡፡
ሌላው አስተያየት ሰጪ አምና ሥራ የጀመረው የኢትዮጵያ የዓመቱ ምርጥ ስፖርተኞች ሽልማት ድርጅት መሥራችና ሥራ አስኪያጅ ሳምሶን ከተማ ነው፡፡ በስፖርት የላቀ ብቃት ላሳዩና አመርቂ ውጤት ላስመዘገቡ ስፖርተኞች የሚሰጠው ሽልማት፣ እግር ኳስ ተጫዋቾችን፣ ሯጮችን፣ አሠልጣኞችንና ሌሎችምን ያካትታል፡፡ ሳምሶን እንደሚገልጸው፣ በዓለም አቀፍ ደረጃ በርካታ ሽልማቶች የሚያገኙ ኢትዮጵያውያን ስፖርተኞችን ለመሸለም የተነሳ ድርጅት ነው፡፡
ስፖርተኞች በአንድ ዓመት ውስጥ ባስመዘግቡት ውጤት መሠረት በድርጅቱ ታጭተው የስፖርት ጋዜጠኞች ድምፅ እንዲሰጡ ይደረጋል፡፡ በጋዜጠኞች ከተመረጡ ስፖርተኞች መካከል ሕዝቡ ድምፅ ይሰጥና የመጨረሻው ዙር አሸናፊዎች ይለያሉ፡፡ ዘንድሮም በጋዜጠኞች የተመረጡ ስፖርተኞች ሕዝብ ድምፅ እንዲሰጥ የቀረቡ ሲሆን፣ በቀጣዩ ዓመት አሸናፊዎቹ ይሸለማሉ፡፡
‹‹ስፖርት ውጤቱ በግልጽ ይታያል፤ የውድድር መለኪያውም ስፖርተኞች የሚያስመዘግቡት ውጤት ነው፤›› የሚለው ሳምሶን፣ ለጉዳዩ ቅርበት ያላቸው የስፖርት ጋዜጠኞች እንደሆኑና ሕዝቡ በራሱ ድምፅ የሚመርጠው ስፖርተኛ ቅሬታ እንደማያስነሳ ያምናል፡፡ ስፖርተኞችን መሸለማቸው ስፖርቱን ለማሳደግ እንደሚረዳም ይናገራል፡፡
በማንኛውም ዘርፍ ላሉ ባለሙያዎች ሽልማት የሚሰጡ ተቋሞችን የሚከታተል አካል እንደሚያስፈልግና መንግሥት ዕውቅና መስጠት እንደሚገባውና ሽልማቶች ሲሰጡ ለሕዝብ ተሳትፎ ከፍተኛ ቦታ ቢሰጥ ውጤቱ ፍትሐዊ እንደሚሆንም ይገልጻል፡፡
በፍቃዱ ዓባይ የእናት ማስታወቂያ ድርጅት ሥራ አስኪያጅ ሲሆን፣ ብራና የተሰኘ በንባብ ላይ ያተረኮ የሬዲዮ መርሐ ግብርም ያዘጋጃል፡፡ ድርጅቱ በ2004 ዓ.ም. በረዥም ልቦለድ፣ በአጭር ልቦለድ፣ በግጥምና ሌሎችም የሥነ ጽሑፍ ዘርፎች የዓመቱ ምርጥ ተነባቢ መጽሐፍ በሚል ሽልማት ሰጥቶ ነበር፡፡ ደራሲያን ሥራዎቻቸውን እንዲያስገቡ ጥሪ በማድረግና ገበያ ላይ ያሉ መጻሕፍትንም በማሰባሰብ ለውድድር አቅርበው ነበር፡፡ የከፍተኛ ተቋሞች መምህራን፣ ደራሲያንና ሐያሲያን ውድድሩን ዳኝተዋል፡፡ አድልኦ እንዳይፈጠር በሚል መጻሕፍቱ በኮድ እንደተወዳደሩና የዳኞቹ ማንነት ውድድሩ ከተጠናቀቀ በኋላ እንደተገለጸ ይናገራል፡፡
ውድድሩ ግን ከአንድ ዓመት በላይ መዝለቅ አልቻለም፡፡ በፍቃዱ የሚያስቀምጠው ዋነኛው ምክንያት የበጀት እጥረት ነው፡፡ በአንድ ዓመት የሚወጡ መጻሕፍትን ማሰባሰብና ለዳኞች ማቅረብ ቀላል እንዳልሆነ ይገልጻል፡፡ ሽልማቱ በተቀናጀ መልኩ እንደሚጀመር ተስፋ ቢያደርግም፣ ድጋፍ የሚሰጥ የተጠናከረ ተቋም አለመኖሩን ይተቻል፡፡
በእሱ ዕይታ፣ ሽልማት በመስጠት ዜጎችን ማበረታታት ያለባቸው የመንግሥት ተቋሞች ኃላፊነታቸውን እየተወጡ አይደለም፡፡ በዚህ ምክንያት የግል ተቋሞች ጣልቃ ገብነት አስፈላጊ ቢሆንም፣ ባልተገባ መንገድ ለሚሠሩ ግለሰቦች ክፍተት መፈጠሩን ይናገራል፡፡ ኃላፊነት ተሰምቷቸው ጊዜና ገንዘባቸውን መስዕዋት የሚያደርጉ ሽልማት ሰጪዎች እንዳሉ ሁሉ ገበያ ተኮርና ያላግባብ ገንዘብ ለማግኘት የሚንቀሳቀሱ መኖራቸው በሽልማት ጽንሰ ሐሳብ ላይ ጥላ ያጠላል ይላል፡፡ በፍቃዱ በሽልማት ዘርፍ የሚመለከታቸው የመንግሥት ተቋሞች እጃቸውን ማስገባት እንዳለባቸው በአጽንኦት ይናገራል፡፡
በጉዳዩ ላይ ሪፖርተር ያነጋገራቸው የሕግ ባለሙያ በአንድ ማኅበረሰብ ማሞገስም መኮነንም አስፈላጊ እንደሆነ ይገልጻሉ፡፡ ሽልማት ተቋማዊ ቢደረግ መልካም ቢሆንም፣ የግድ በመንግሥት መሰጠት የለበትም፡፡ በሌሎች አገሮች ያለውን ተሞክሮ በመመርኮዝ ጥያቄው ሽልማቱ በማን ተሰጠ? ሳይሆን ተሸላሚዎች የሚመለመሉበት መንገድ ነው ይላሉ፡፡ ሽልማት የሚሰጥ ተቋም የሚያወዳድርበት ቋሚ መስፈርት እንደሚያስፈልገው ሸላሚው በሕዝብ የሚታመንበት መርሕ ያለው መሆን እንዳለበትና የማያሳማው ወጥ የሆነ አሠራርም ሊኖረው እንደሚገባ ይገልጻሉ፡፡
‹‹ሕጉ አትሸልሙ አይልም፤ የተቋሞች አሠራር ፍትሐዊ ከሆነ ሽልማቱን የሚያገኘው ማን ይሆን? ብሎ ሕዝቡም በጉጉት ይጠባበቃል፡፡ አለበለዚያ ግን ዋጋ ያጣል፤›› ይላሉ የሕግ ባለሙያው፡፡
ባለሙያዎችን ለመሸለም ከሞከሩ የመንግሥት ተቋሞች የባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር ይጠቀሳል፡፡ ከኪነ ጥበቡ ባለሙያዎች ተመርጠው ለውድድር ቢቀርቡም ሳይሸለሙ ሒደቱ ተቋርጧል፡፡ በባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር የባህል ኢንዱስትሪ ልማትና ትብብር ዳይሬክተር አቶ ደስታ ካሳ እንደሚሉት፣ ሽልማቱ ያልተሰጠው ለሚኒስትሮች ምክር ቤት የተላከው የተሻሻለው የባህል ፖሊሲ ባለመፅደቁ ነው፡፡ አሁን ላይ ሽልማት የመስጠት ኃላፊነት ያለው የኢትዮጵያ የሽልማት ድርጅት ተቋቁሞ መተዳደሪያ ደንብ ተዘጋጅቶለታል፡፡
የተሻሻለው የባህል ፖሊሲ ከፀደቀ በድርጅቱ መተዳደሪያ ደንብ የተጠቀሱትን መንገዶች በመጠቀም ሽልማቱ ይካሄዳል ይላሉ፡፡ ደንቡ ላይ የበርካታ ባለሙያዎች አስተያየት እንደተካተተና በተለያየ ዘርፍ ያሉ ባለሙያዎችም በስፋት በሽልማቱ የሚካተቱበትን መንገድ እንደሚፈጥር አቶ ደስታ ይናገራሉ፡፡ ከዚህ ቀደም የነበሩ መንግሥታዊ ሽልማቶች የነበራቸውን ሒደት በመፈተሽ የሽልማት ድርጅቱ ደንብ መቃኘቱንም ገልጸዋል፡፡