Friday, May 24, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

ማኅበራዊማኅበራዊ ኃላፊነትን መወጣት ወይስ ገጽታ ግንባታ?

ማኅበራዊ ኃላፊነትን መወጣት ወይስ ገጽታ ግንባታ?

ቀን:

የቢዝነስ ኩባንያዎች እንቅስቃሴ ምን ያህል ኃላፊነት የተሞላበት ነው? የሚሰጡት አገልግሎት ወይም የሚያቀርቡት ዕቃ ዋጋስ ምን ያህል ነው? ለማኅበረሰቡ የሚጨምረው እሴት ምንድን ነው? የሚሉና መሰል ጥያቄዎች የኩባንያዎች የማኅበራዊ ኃላፊነት ጉዳይ ሲነሳ አብረው የሚነሱ ጥያቄዎች ናቸው፡፡

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የተለያዩ የግል ኩባንያዎች እንዲሁም የመንግሥት የልማት ድርጅቶችና ሌሎችም ወላጅ አልባ ሕፃናትን በማስተማርና በመርዳት፣ አረጋዊያንን በመደገፍ፣ ለጤና ተቋማት ድጋፍ በማድረግ ለተቸገሩ የትምህርት ዕድል በመፍጠርና በመሳሰሉት ማኅበራዊ ኃላፊነታቸውን ለመወጣት ሲሞክሩ እየታየ ነው፡፡ በተቃራኒው በተለያየ መንገድ በመገናኛ ብዙኃን ጭምር በተጮኸላቸው ዝግጅቶች ሁሉ እጃቸውን የሚያስገቡም አይታጡም፡፡

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ወላጅ አልባ ሕፃናትን በመደገፍ፣ ዛፎች እንዲተከሉ በማድረግ ለአካባቢ ጥበቃ አስተዋጽፆ ለማድረግ ይንቀሳቀሳል፡፡ ችግረኛ ለሆኑ ተማሪዎች የከፍተኛ ትምህርት ዕድል በመስጠት ቅድስት ማርያም ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ ማኅበራዊ ኃላፊነትን ከመወጣት አንፃር ይንቀሳቀሳል፡፡ ጊፍት ሪል ስቴት ከአንድ ዓመት በፊት የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማኅበር ለሚያሠራው ሕንፃ ገቢ ማስገኛ አዘጋጅቶት ለነበረው የኤስኤምኤስ ሎተሪ ሽልማት ይሆን ዘንድ 650 ሺሕ ብር የሚገመት ቤት መለገሱ ይታወሳል፡፡ በሌላ በኩል የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ 70 ሚሊዮን ብር በሚገመት ወጪ የአንገት በላይ ሕክምና ማዕከል  አስገንብቶ ለቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል ሚሌኒየም ሜዲካል ኮሌጅ ሊያበረክት መሆኑ፣ ግንባታውም በሚቀጥለው ዓመት እንደሚጀመር ታውቋል፡፡ እነዚህ ለአብነት ያህል ይጠቀሱ እንጂ በተለያየ ዘርፍ ማኅበራዊ ኃላፊነታቸውን ለመወጣት እየተንቀሳቀሱ ያሉ ተቋማት አሉ፡፡ ምንም እንኳ ከእንቅስቃሴዎች ጋር በተያያዘ ጥያቄዎች የሚነሱ ቢሆንም፡፡ 

- Advertisement -

የዚህ ዓይነቱ ማኅበራዊ ኃላፊነት (Corporate Social Responsibility) ሀሳብ መሠረት ቢዝነሦች የሚንቀሳቀሱት ከማኅበረሰቡ ጋር ባላቸው ማኅበራዊ ውል ነው የሚለው አስተሳሰብ ነው፡፡ በዚህ ውል መሠረት መንቀሳቀስ ደግሞ የቢዝነሶች ምላሽ ሁልጊዜም ለተቋቋሙለት ዓላማ ወይም ለባለአክሲዮኖች ብቻ ሳይሆን ለአጠቃላይ ማኅበረሰቡ እንዲሆን ግድ ይላል፡፡

ላለፉት አምስት ዓመታት በየዓመቱ ለተወሰኑ ቀናት አቅም ለሌላቸው ሕሙማን የነፃ የምርመራ አገልግሎት እየሰጠ የሚገኘው የውዳሴ ዳያግኖስቲክ ማዕከል ሥራ አስኪያጅና ባለቤት አቶ ዳዊት ኃይሉ ይህ የቢዝነሶች ማኅበራዊ ኃላፊነት የውዴታ ግዴታ ነው ይላሉ፡፡

እሳቸው እንደሚሉት ማኅበራዊ ኃላፊነት ማለት ከተቋቋሙበት ዓላማ፣ ከወሰዱት ኃላፊነት በላይ ሆኖ መገኘት ነው፡፡ ስለዚህም ምንም እንኳ ለትርፍ የተቋቋመ ማዕከል ቢሆንም የማኅበረሰቡን ችግር ለመፍታት የበኩላቸውን አስተዋጽኦ ማበርከት ስላለባቸው ይህን ማድረግ የሚያስችላቸውን ፕሮጀክት ቀርፀው መንቀሳቀስ ከጀመሩ ዓመታት ተቆጥረዋል፡፡

ከሦስት ዓመታት በፊት ማዕከሉ በሚገኝበት አራዳ ክፍለ ከተማ ኗሪዎች የሆኑ የቀበሌ መታወቂያቸውን በመያዝ 20 በመቶ የምርመራ ወጪ እንዲቀንስላቸው የሚያስችል አሠራር ዘርግተዋል፡፡ ማዕከሉ በዚህ ዓመት ከጳጉሜ 1 እስከ 6 ቀን 2007 ዓ.ም. ከ500 በላይ ለሚሆኑ ነፃ የምርመራ አገልግሎት ለመስጠት ዝግጅቱን አጠናቅቋል፡፡ በዚሁ ክፍለ ከተማ ኗሪ የሆኑ የስልክ ጥሪ በማድረግ ነፃ የአምቡላንስ አገልግሎት ማግኘትም ይችላሉ፡፡

ይህ የማዕከሉ ማኅበራዊ ኃላፊነትን የመወጣት ተሞክሮ ሌሎችም ሊከተሉት የሚገባ እንደሆነ የሚናገሩት አቶ ዳዊት ዕርምጃው አክሳሪ ሳይሆን አትራፊ መሆኑን ይገልጻሉ፡፡ ‹‹እንደ ኪሳራ ሳይሆነ ወደፊት እንደሚመነዘር ሀብት ነው የምናየው›› ይላሉ፡፡ የማዕከሉን ፈለግ በመከተል ከዚህ ቀደም ሁለት የግል ሆስፒታሎች ለሚገኙበት ክፍለ ከተማ ኗሪዎች የአሥር በመቶ የምርመራ ክፍያ ቅናሽ ማድረግ ጀምረው የነበረ ቢሆንም ብዙም ሳይገፉበት እንደተውት አቶ ዳዊት ያስታውሳሉ፡፡ ይህንንና መሰል አጋጣሚዎችን በመጥቀስ ማኅበራዊ ኃላፊነትን መወጣት ዲሲፕሊን የሚጠይቅ እንደሆነ ያስረዳሉ፡፡

የኩባንያዎች ማኅበራዊ ኃላፊነትን የመወጣት እንቅስቃሴ ገና በጅምር ላይ ያለ ቢሆንም እንደ ኢትዮጵያ አየር መንገድ፣ ኢትዮ ቴሌኮም፣ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክና ሌሎችም የግል ኩባንያዎች በተቀናጀና ቀጣይነት ባለው መንገድ ማኅበራዊ ኃላፊነታቸውን ቢወጡ ትልቅ ለውጥ ይመጣል የሚል ጠንካራ እምነት አላቸው፡፡

እሳቸው እንደሚሉት የዚህ ዓይነቱ ማኅበራዊ ኃላፊነት ቢዝነሶች ላይ ብቻ ማተኮር የለበትም፡፡ ይልቁንም ከግለሰብ መጀመር አለበት ‹‹ምክንያቱም ግለሰቦች ናቸው ኋላ የኩባንያዎች ኃላፊዎች ሆነው የሚመሩት፡፡ አሁን የማኅበራዊ ኃላፊነት አስተሳሰብ ባልዳበረበት ሁኔታ ግን ነገሩ ለሥራ አስኪያጆችም ለውሳኔ ከባድ ይሆናል›› ይላሉ፡፡

አንድ ስማቸው እንዲገለጽ ያልፈለጉ የማኅበራዊ ሳይንስ ባለሙያ የቢዝነሶች ማኅበራዊ ኃላፊነትን የመወጣት ነገር ሲነሳ ኩባንያዎቹ ሀብት ያፈሩት እንዴት ነው? እንቅስቃሴአቸው ሕጋዊ ነው? ግብርስ ይከፍላሉ ወይ የሚሉና ሌሎችም ጥያቄዎች ሊነሱ ይገባል ይላሉ፡፡

እሳቸውም እንደ አቶ ዳዊት ሁሉ የኩባንያዎች ማኅበራዊ ኃላፊነትን የመወጣት ዕርምጃ ገና የመጀመሪያ ደረጃ ላይ ያለ መሆኑን ቢስማሙም በኩባንያዎቹ ላይ ብዙም ተስፋ አይጥሉም፡፡ ‹‹ቢዝነስ የሚሠሩበት መንገድ ሀቀኝነት የጐደለው በመሆኑ፣ ማኅበራዊ እሴት የሚያስጨንቃቸውም ስላልሆኑ ከትርፋቸው አንስተው ለማኅበረሰቡ ይሰጣሉ ብሎ ማሰብ ያስቸግራል፡፡ አነሳሳቸው እንቅስቃሴአቸውም ማኅበራዊ ኃላፊነትን ከመወጣት የራቀ ነው›› ይላሉ፡፡

ከአቅማቸው ወይም ከዓመታዊ ትርፋቸው አንፃር ሲታይ በምን ያህል ደረጃ ተንቀሳቅሰዋል? የሚለው ጥያቄ ውስጥ ሊወድቅ ቢችልም ማኅበራዊ ኃላፊነታቸውን እየተወጡ ያሉ ኩባንያዎች መኖራቸውን በመጥቀስ ለባለሙያው ጥያቄ አቅርበንላቸው ነበር፡፡ መልሳቸው ‹‹የብዙዎቹ የገጽታ ግንባታ ሥራ ነው፡፡ የተለያዩ ተቋማትን መጥቀስ ይቻላል፡፡ ለአገልግሎት የሚጠይቁት ክፍያና ገቢ የሚሰበስቡበት መንገድ በማጤን ማኅበራዊ ኃላፊነታቸውን ለመወጣት የሚያወጡትን ወጪ ከትርፋቸው ጋር በማነፃፀር እውነቱን ማወቅ ይቻላል፡፡›› የሚል ነበር፡፡ ይህ ነጥባቸውን ለማስረዳት መንግሥታዊ ያልሆኑ አገር በቀል በጎ አድራጐት ማኅበራትን ዓመታዊ በጀትና ክንውን ትርፋማ የሚሏቸው ኩባንያዎች ከትርፋቸው ቢሰጡ ከሚሉት በጣም አነስተኛ ገንዘብ ጋር ያነጻጽራሉ፡፡

11 ሚሊዮን የሚሆኑ የኩላሊት ሕመምተኞችን (ከ30 – 40 ሺሕ የሚሆኑት ጽኑ ሕመምተኞች ናቸው) መነሻ በማድረግ ከፍተኛ ወጪ የሚጠይቁትን የኩላሊት እጥበትና ንቅለ ተከላ ሕክምናዎች የመስጠትን ዓላማ እውን ለማድረግ ከተዘረጉ የገቢ ማሰባሰቢያ መንገዶች አንዱ የሆነው የ8085 ኤስኤምኤስ አገልግሎት ነው፡፡ ይህን የአገሪቱን ትልቅ የጤና ችግር ለመቅረፍ ከሚገኘው ገቢ ኢትዮ ቶሌኮም 40 በመቶ፣ ገቢዎችና ጉምሩክ 15 በመቶ ብሔራዊ ሎቶሪ 15 በመቶ የገቢ ድርሻቸውን መስጠታቸውን የ8085 ኤስኤምኤስ አገልግሎት አማካሪና የማርኬቲንግ ኃላፊ አቶ መላኩ ተሰማ ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡ ረቡዕ ነሐሴ 20 ቀን 2007 ዓ.ም. በይፋ የተጀመረው አገልግሎት ለሁለት ወራት የሚቆይ ይሆናል፡፡

እስካሁን (ነሐሴ 21) ድረስ ከግማሽ ሚሊዮን ብር በላይ የሚገመት የቁሳቁስና የገንዘብ ዕርዳታ ማግኘታቸውን የሚናገሩት አቶ መላኩ እስካሁን ያገኙት ምላሽ አበረታች መሆኑን ይገልጻሉ፡፡ ‹‹ባለሀብቱ፣ አገልግሎት ሰጭ ድርጅቱ እያተረፈ ያለው እዚህ አገር ላይ ነው፡፡ ሀብቱ ንብረቱ የተጠበቀው ሥራውም ዕለት በዕለት ሳይስተጓጐል የቀጠለው አገሪቱ ሰላም በመሆኗ ኅብረተሰቡ ሰላማዊ በመሆኑ ነው፡፡ ስለዚህ የዚህን ማኅበረሰብ ችግር ለመፍታት አስተዋጽዖ የማድረግ ኃላፊነት አለበት›› ይላሉ፡፡

እሳቸው እየመሩት ካሉት ከዚህ እንቅስቃሴ ባሻገር በጥቅሉ የቢዝነሶች ማኅበራዊ ኃላፊነትን የመወጣት ዕርምጃ ግን አጥጋቢ አይደለም ብለው ያምናሉ፡፡ የዚህ ዓይነት ኃላፊነት አለብን ብለው የሚያምኑ ጥቂት ቢዝነሶች እንደሆኑ፤ ስለዚህም ማኅበራዊ ኃላፊነታችሁን ተወጡ የሚል ጥያቄን የሚመለከቱት ከሞላ ጐደል የልመና ያህል እንደሆነ ያስባሉ፡፡ ዘላቂ ያልሆነ ይልቁንም ዓይን የበዛባቸው ዝግጅቶች ላይ የመረባረብ ነገር ይበዛል ይላሉ፡፡    

አቶ መላኩ እንደሚሉት ማኅበራዊ ኃላፊነት ኩባንያዎች በአጋጣሚ በአንድ ጊዜ ብቻ ሳይሆን በተቀናጀና ከዓመት ትርፋቸው የተወሰነውን መድበው የሚወጡት መሆን አለበት፡፡ ይህ ማኅበራዊ ኃላፊነት ሙሉ በሙሉ ኩባንያዎች መልካም ፍቃድ ላይ የተመሠረተ ብቻ ሳይሆን መንግሥት በተለያየ መንገድ የሚከታተለው መሆን ይኖርበታል፡፡ ለምሳሌ መንግሥት ለኩባንያዎች ቅድሚያና ድጋፎች ሲያደርግ የኩባንያዎቹ ማኅበራዊ ኃላፊነትን መወጣት ከግምት ውስጥ ሊገባና ሊመዘን ይገባል፡፡

በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ሶሲዮሎጂ ዲፓርትመንት ተባባሪ ፕሮፌሰር ኢዛና አምደወርቅ  ማኅበራዊ ኃላፊነት (Corporate Social Responsibility) ቢዝነሶች በራሳቸው ተነሳሽነት ለሚንቀሳቀሱበት አካባቢ፣ ለአነስተኛ ቢዝነሶች የሚያደርጉት ድጋፍ ነው ይላሉ፡፡ ባደጉት አገሮች ይህ ኃላፊነት ቢዝነሶች ከፈለጉ ይወጡት ተብሎ ለራሳቸው የሚተው ሳይሆን በተወሰነ መልኩ ቁጥጥር የሚደረግበትም ነው፡፡ ለምሳሌ ቢራ የሚያመርት ኩባንያ ውኃ ጥበቃ፣ መኪና አምራች ደግሞ አካባቢ ጥበቃ ላይ እንዲሠሩ እንደሚደረግ ይገልጻሉ፡፡ ኩባንያዎች ለዚህ ወይም ለዚያ የበጐ አድራጐት ሥራ ይሄን ያህል አዋልን ሲሉ ታክስ ይቀነስላቸዋል፡፡ በጥቅሉ የቢዝነሶች የማኅበራዊ ኃላፊነት ሙሉ በሙሉ በእነሱ መልካም ፍቃድ ላይ የተመሠረተ ሳይሆን ወረቀት ላይ ባለ ነገር የሚመራበት ደረጃ ላይ ደርሷል፡፡

በእኛ አገር የቢዝነሶች ማኅበራዊ ኃላፊነት የሚለው ሀሳብ በራሱ ብዙ አይታወቅም፡፡ በዚህ ረገድ የሚንቀሳቀሱ ኩባንያዎች በመኖራቸው ጭላንጭል መኖሩን የሚገልጹት ተባባሪ ፕሮፌሠሩ ቢዝነሶች እየተስፋፉ ትልልቅ ኩባንያዎች እየተፈጠሩ ያሉበት በመሆኑ የቢዝነሶች ማኅበራዊ ኃላፊነትን መወጣት ትኩረት ሊሰጠው የሚገባበት ጊዜ መሆኑን ይናገራሉ፡፡ ለሚኖሩበት ወይም ለኖሩበት አካባቢ፣ የተቸገረና የሚያውቁትን መርዳትና የመሳሰሉት ዓይነት ማገዞች መኖራቸው ባህላዊ ሀብት ማጋራት መኖሩን እንደሚያሳይ ያስረዳሉ፡፡ በተቃራኒው በተቀናጀና ዘላቂነት ባለው መንገድ የቢዝነሶች ማኅበራዊ ኃላፊነትን የመወጣት ሁኔታ ደካማ መሆኑን ይጠቁማሉ፡፡

የአቶ መላኩን አስተያየት የሚጋሩት ተባባሪ ፕሮፌሠር ኢዛና ዘላቂ ያልሆኑ ይልቁንም በዓልንና መሰል ዝግጅቶችን መሠረት ያደረጉ የገንዘብ ድጋፍ የመስጠት አዝማሚያ በኩባንያዎች ዘንድ እንደሚስተዋል ይገልጻሉ፡፡ ‹‹ግለሰቦች ታመሙ ወይም ተቸገሩ ወይም ለዚህ ዝግጅት እየተባለ ገንዘብ መስጠት በራሱ መልካም ነገር ቢሆንም ይህ አካሔድ ዘላቂ አይሆንም›› ይላሉ፡፡ በተቃራኒው በጠንካራ ጐን ለአብነት ከጠቀሷቸው መካከል ኩባንያዎች ለሕዳሴው ግድብ የሚያደርጉት ድጋፍ፣ አንድ ብር ለአንድ ወገን ላይ ያደረጉት ተሳትፎና የመሳሰሉት ይገኙበታል፡፡  

ኩባንያዎች በምን መንገድ ሀብት ሰብስበው ከትርፋቸው ላይ ማኅበራዊ ኃላፊነት ይወጣሉ የሚለው ርዕዮተ ዓለምን መሠረት ያደረገ ዓለም አቀፍ ክርክር መሆኑን ተባባሪ ፕሮፌሠሩ ይጠቁማሉ፡፡ የሚያስማማው ነገር ኩባንያዎች በተነጣጠለና ባልተደራጀ መልኩ ሳይሆን በተቀናጀና በተጠናከረ እንዲሁም ዘላቂ እንዲሆን በሚያስችል መልኩ ማኅበራዊ ኃላፊነታቸውን የሚወጡበት ሁኔታን ማመቻቸት ነው፡፡

 

    

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የማዳበሪያ አቅርቦትና ውጣ ውረዱ

በቅፅል ስሙ “The Father of Chemical Warfare” እየተባለ የሚጠራው...

የኢትዮጵያ ልማት ባንክ የትርፍ ምጣኔውን ከ70 በመቶ በላይ አሳደገ

ከሁለቱ መንግሥታዊ ባንኮች መካከል አንዱ የሆነው የኢትዮጵያ ልማት ባንክ...