የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በ15ኛው ዙር ሊዝ ጨረታ በአዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ ባወጣው ቦታ፣ በከተማው ታሪክ ከፍተኛውን የመጫረቻ ዋጋ ያቀረበው ኩባንያ የሚጠበቅበትን ክፍያ በመፈጸም ውል መፈጸሙ ታወቀ፡፡
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በአዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ መርካቶ ይርጋ ኃይሌ የገበያ ማዕከል አካባቢ 242 ካሬ ሜትር ቦታ በሊዝ ጨረታ ለማስተላለፍ በወጣው ጨረታ፣ ስኬት ኢንተርናሽናል ኩባንያ በከተማው ታሪክ ከፍተኛ የመጫረቻ ዋጋ ማቅረቡን መዘገባችን ይታወሳል፡፡
ስኬት ኢንተርናሽናል ለዚህ ቦታ በካሬ ማትር 355,550 ብር ያቀረበ ሲሆን፣ ይህ ዋጋ በዝዋይ ኢንተርናሽናል ትሬዲንግ ተይዞ ከነበረው ክብረ ወሰን የሰበረ ዋጋ በ50,555 ብር ብልጫ አለው፡፡
ስኬት ኢንተርናሽናል ባለፈው ሳምንት መጨረሻ ከጠቅላላ ዋጋው 20 በመቶ ቅድሚያ በመክፈል፣ ከአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የመሬት ባንክና ማስተላለፍ ጽሕፈት ቤት ጋር ውል መፈራረሙ ታውቋል፡፡
ከስኬት ኢንተርናሽናል ጋር ተወዳድሮ ተሸናፊ የሆነው ኩባንያ ያቀረበው የመጫረቻ ዋጋ ምንም እንኳ አሸናፊ መሆን ባይችልም፣ በከተማው ታሪክ ትልቁ የመጫረቻ ዋጋ ነው፡፡
ሁለተኛ የወጣው የቲዘዘኒ አክሲዮን ማኅበር ለዚህ ቦታ 355 ሺሕ ብር በካሬ ሜትር አቅርቧል፡፡ ከዚህ ቦታ በመቀጠል በ15ኛው ዙር ከፍተኛ ዋጋ የቀረበው እዚያው አዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ የወጣ ቦታ ነው፡፡
ይህ ቦታ መርካቶ ቦምብ ተራ አካባቢ የሚገኝ ሲሆን፣ በ11ኛው ዙር ሊዝ ጨረታ ለውድድር ቀርቦ በወቅቱ በከተማው ታሪክ ከፍተኛ ዋጋ የቀረበለት ነበር፡፡
449 ካሬ ሜትር ስፋት ላለው ለዚህ ቦታ፣ ዝዋይ ኢንተርናሽናል ትሬዲንግ በካሬ ሜትር 305 ሺሕ ብር ቢያቀርብም፣ በወቅቱ ያቀረበው ይህ ከፍተኛ ዋጋ አነጋጋሪ በመሆኑና በኩባንያው ላይ ተፅዕኖ በመፍጠሩ የተወሰኑ የኩባንያው ባለአክሲዮኖች የቀረበው ዋጋ እነሱን የማይመለከት መሆኑን በማስታወቃቸው፣ አክሲዮን ማኅበሩ ውል ሳይፈጽም ቀርቷል፡፡ ይህ ቦታ በ15ኛው ሊዝ ጨረታ በድጋሚ ቀርቦ ዝዋይ ኢንተርናሽናል ትሬዲንግ ካቀረበው ዋጋ ዝቅ ቢልም ከፍተኛ የሚባል ዋጋ ቀርቦለት ነበር፡፡
ለዚህ ቦታ አንደኛ በመሆን በካሬ ሜትር 286,500 ብር ያቀረበው ኤቲኤኤ ኮንስትራክሽን ኩባንያ ነው፡፡ ነገር ግን ይህ ኩባንያ ምክንያቱ ለጊዜው ግልጽ ባይሆንም፣ እስካለፈው ዓርብ ድረስ ውል መግባት ቢኖርበትም ውል አለመፈጸሙ ታውቋል፡፡
ለዚህ ቦታ ሁለተኛ ተወዳዳሪ በመሆን በካሬ ሜትር 262,000 ብር ያቀረበው ያረፈደ ትሬዲንግ አክሲዮን ኩባንያ ነው፡፡
የአዲስ አበባ አስተዳደር አሸናፊ ኩባንያዎች ይፋ ከተደረጉበት አሥር የሥራ ቀናት ውስጥ ውል ካልፈጸሙ፣ ሁለተኛ ከወጡ ኩባንያዎች ጋር ይዋዋላል፡፡ ነገር ግን ከአሥር ቀናት በተጨማሪ የሦስት ቀናት ማስጠንቀቂያ ጊዜ የሚሰጥ በመሆኑ፣ በዚህ ሳምንት እስከ ረቡዕ ነሐሴ 22 ቀን 2007 ዓ.ም. ድረስ ኩባንያው የመዋዋያ ጊዜ እንዳለው የአስተዳደሩ ባለሙያዎች አስረድተዋል፡፡
ነገር ግን ከረቡዕ በኋላ ውል ያልፈጸሙ አሸናፊ ተጫራቾች፣ ለተጠባባቂ ተወዳዳሪዎች ዕድላቸውን አሳልፈው እንደሚሰጡ መረጃዎች አመልክተዋል፡፡ የከተማው አስተዳደር ሰኔ 15 ቀን 2007 ዓ.ም. ያወጣው 15ኛው ሊዝ ጨረታ ከሐምሌ 15 እስከ ሐምሌ 17 ቀን 2007 ዓ.ም. ድረስ መከፈቱ ይታወቃል፡፡
ውጤቱ ነሐሴ 9 ቀን 2007 ዓ.ም. የተገለጸ ሲሆን፣ ውጤቱ ከተገለጸ በኋላ ባሉት አሥር የሥራ ቀናት ውል የፈጸሙት ግማሽ ያህል ተጫራቾች ብቻ መሆናቸው ታውቋል፡፡