Monday, March 4, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

የድሬ ኢንዱስትሪዎችና የሞጆ ቆዳ ፋብሪካ ከፍተኛ ባለአክሲዮን የባንክ ሒሳባቸውና አክሲዮናቸው ታገደ

ተዛማጅ ፅሁፎች

–  የፋብሪካው ሠራተኞች ሥጋታቸውን ገልጸዋል

ታዋቂው ነጋዴ ሐጂ በዳዳ ጫሊ ጅሩ ከፍተኛ ባለድርሻ የሆኑባቸው ድሬ ኢንዱስትሪዎች ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር፣ ሞጆ ቆዳ ፋብሪካ አክሲዮን ማኅበር፣ ቦረን ሪል ስቴትና ድሬ ኃይላንድ አክሲዮን ማኅበር አክሲዮኖችን ለሦስተኛ ወገን እንዳይሸጡና እንዳይተላለፉ ታግደው እንዲቆዩ ፍርድ ቤት ትዕዛዝ ሰጠ፡፡

የፌዴራል የመጀመርያ ደረጃ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ ሁለተኛ ፍትሐ ብሔር ችሎት ነሐሴ 13 ቀን 2007 ዓ.ም.  የሰጠውን ጨምሮ ውሳኔ በተለያዩ ጊዜያት በሰጠው ትዕዛዝ በወጋገን ባንክ፣ በአዋሽ ኢንተርናሽናል ባንክ፣ በኢትዮጵያ ንግድ ባንክና በተለያዩ ቅርንጫፍ ባንኮች የተቀመጠ ገንዘብና አክሲዮንም ካለ ታግዶ እንዲቆይ ትዕዛዝ አስተላልፏል፡፡

የታዋቂው ነጋዴ ሐጂ በዳዳ አክሲዮኖችና ገንዘብ እንዲታገዱ ምክንያት የሆነው፣ ለ50 ዓመታት የትዳር አጋራቸው መሆናቸውን የገለጹት ወ/ሮ ልኬለሽ ያዴሳ ለፍርድ ቤት ባቀረቡት የፍች ጥያቄ ምክንያት ነው፡፡

ወ/ሮ ልኬለሽ በተሻሻለው የቤተሰብ ሕግ አንቀጽ 81 መሠረት የፍች ውሳኔ እንዲሰጣቸው ያቀረቡት፣ ሐጂ በዳዳ ትዳራቸውን አክብረው መኖር ሲገባቸው ቤታቸውን ጥለው በመውጣት ከጋብቻ ውጪ ከሌላ ሰው ጋር መኖር መጀመራቸውን በመግለጽ መሆኑን ክሱ ያስረዳል፡፡

ሐጂ በዳዳ በራሳቸው፣ በባለቤታቸውና በአራት ልጆቻቸው በተቋቋመው 112.9 ሚሊዮን ብር ዋጋ ካለው ድሬ ኢንዱስትሪዎች አክሲዮኖች ውስጥ 86,580 አክሲዮን ወይም 86.5 ሚሊዮን ብር ድርሻ ያላቸው መሆኑን ሰነዶች ያስረዳሉ፡፡

ከፕራይቬታይዜሽንና የመንግሥት የልማት ድርጅቶች ተቆጣጣሪ ኤጀንሲ የገዙት ሞጆ ቆዳ ፋብሪካም ከ25 በላይ ባለአክሲዮኖች ያሉት ሲሆን፣ ከፍተኛ ድርሻ ያላቸው ሐጂ በዳዳ መሆናቸውን ሰነዶች ያስረዳሉ፡፡

ባለቤታቸው ባቀረቡት የፍች ጥያቄ ክስ ምክንያት የባንክ ገንዘባቸውና አክሲዮኖቻቸው የታገደባቸው ሐጂ በዳዳ፣ ለፍርድ ቤቱ ምላሽ ሰጥተዋል፡፡

ሐጂ በዳዳ ለፍርድ ቤቱ በሰጡት ምላሽ ከባለቤታቸው ጋር መስማማት ባለመቻላቸው ለ50 ዓመታት የጠበቁትን ትዳራቸውን ለመተው መገደዳቸውን ገልጸዋል፡፡ ከራሳቸው ይልቅ ለቤተሰባቸውና ለአገራቸው ዕድገትና ልማት በማሰብ ሁሉን ነገር ሆነው ፋብሪካዎች ማቋቋማቸውንና ከ1,200 በላይ ሠራተኞች እንዳሏቸው አስረድተዋል፡፡ ከ350 ሚሊዮን ብር በላይ ልዩ ልዩ ብድር እንዳለባቸውም ገልጸዋል፡፡ ፍች ለጠየቁት ባለቤታቸው በ2,310 ካሬ ሜትር ቦታ ላይ የተገነባ መኖሪያ ቤትና ሦስት ሚሊዮን ብር በመስጠት ትዳራቸው ሳይፈርስ ለየብቻ እንዲኖሩ በማቀድ በሰላም እየኖሩ መሆናቸውንም አስረድተዋል፡፡

በሸሪዓ ሕግ መሠረት ሌላ ሰው በማግባት ልጆች ወልደው እየኖሩ መሆኑንና ከሳሽ ባለቤታቸውን ጨምሮ ሁሉም ሰው የሚያውቅ መሆኑን አስረድተዋል፡፡ በመሆኑም እንዲከፋፈሉና ትዳር እንዲፈርስ የተጠየቀው አግባብ ባለመሆኑ ክሱ ተሰርዞ እንዲሰናበቱ ጠይቀዋል፡፡ ሐጂ በዳዳ ባቀረቡት ሌላ አቤቱታ ከ350 ሚሊዮን ብር በላይ የተለያዩ ዕዳዎች እንዳለባቸው በድጋሚ ጠቅሰው፣ በገቢና በወጪ ንግድ ላይ ተሰማርተው ለአገሪቱ ከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ እያስገቡ መሆኑን በመግለጽ፣ ፍርድ ቤቱ ወደ ክርክር እንዲገቡ የሚያደርግ ከሆነ ክርክሩ በዝግ እንዲሆን ፍርድ ቤቱን ጠይቀው ነበር፡፡ ፍርድ ቤቱ ግን አልተቀበላቸውም፡፡

ሐጂ በዳዳ በበኩላቸው በወ/ሮ ልኬለሽ ያዴሳ ስም በአዋሽ ኢንተርናሽል ባንክ የተቀመጠ ገንዘብ በአራዳ ሕንፃ ሁለተኛ ፎቅ ላይ ያለ የኤሌክትሮኒክስ መደብር፣ በኦሮሚያ ክልል ደቡብ ምዕራብ ሸዋ ዞን ሰዴን ሶዶ ወረዳ አሌ አበባን ቀበሌ የሚገኝ ንብረትና ድሬ ኢንዱስትሪዎች ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር ግቢ ውስጥ የሚገኝ መጋዘን ውስጥ ያለ ንብረት ታግዶ እንዲቆይ ጠይቀው፣ የፌዴራል የመጀመርያ ደረጃ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ ሁለተኛ ፍትሐ ብሔር ችሎት ዕግድ ጥሏል፡፡

በድርጅቶቹ ከፍተኛ ባለድርሻ ሐጂ በዳዳና የአክሲዮን ድርሻና የባንክ ባለቤት ሒሳብ ላይ ፍርድ ቤቶች የሚጥሉት ዕድግ እንዳስፈራቸው የሞጆ ቆዳ ፋብሪካ አክሲዮን ማኅበር መሠረታዊ ሠራተኞች ማኅበር  ገልጿል፡፡ ባለሀብቱ ፋብሪካውን ከገዙት በኋላ ውጤታማ እየሆነ እንደሚገኝ የገለጸው ማኅበሩ፣ 992 ቋሚና ጊዜያዊ ሠራተኛ በፋብሪካው መኖሩን ገልጾ፣ በተለይ በባንክ ሒሳብ ላይ ዕግድ በመጣሉ የላብ አደሩ ደመወዝ እንዴት እንደሚከፈል ሥጋት እንደገባው አመልክቷል፡፡ ችግሩ የፋብሪካ ሠራተኞቹ ብቻ ሳይሆን ከ5,000 በላይ የሚሆኑ ቤተሰቦቻቸውም ጭምር መሆኑን ጠቁመው፣ የሚመለከተው አካል ችግሩን በቀላሉ እንዲፈቱት እንዲያደርግ ጠይቀዋል፡፡ ፍርድ ቤቱ ውሳኔ ለመስጠት ለጥቅምት 3 ቀን 2008 ዓ.ም. ቀጠሮ ሰጥቷል፡፡

  

 ,

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች