Sunday, April 2, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ንግድ ባንክ ለመጀመርያው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ የሚፈለገውን ያህል ገንዘብ አላቀረብኩም አለ

- ማስታወቂያ -

ተዛማጅ ፅሁፎች

–  ጠቅላላ ተቀማጭ ገንዘቡ 241.7 ቢሊዮን ብር መድረሱን አስታወቀ

የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በአምስት ዓመቱ የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ዘመን፣ ኢኮኖሚው እየተነቃቃ ከመሄዱ አንፃር ገበያው የሚፈልገውን የገንዘብ መጠን አለማቅረቡን አስታወቀ፡፡

የተፈለገውን ወይም ገበያው የሚፈልገውን ያህል ብድር ማቅረብ አለመቻሉንና ትልቅ ተግዳሮት ሆኖበት እንደነበር የገለጹት ኃላፊዎቹ፣ ባንኩ በአምስት ዓመቱ ዕቅድ 171.8 ቢሊዮን ብር ለማበደር አቅዶ የዕቅዱን 187 በመቶ 321.9 ቢሊዮን ብር ማቅረብ በመቻላቸውም ከፍላጎት አንፃር እንዳልተካካሰ አመልክተዋል፡፡ 158.3 ቢሊዮን ብር ከብድር ተመላሽ ለመሰብሰብ መቻሉንና የዕቅዱ 235.4 በመቶ መሆኑን አክለዋል፡፡ የተበላሸ ብድርም ከሁለት በመቶ በታች መሆኑን አስረድተዋል፡፡

ባንኩ በአምስት ዓመቱ ዕቅድ በተቀማጭ ገንዘብ፣ በውጭ ምንዛሪ፣ በብድር አሰጣጥና አሰባሰብ ክንውን፣ በጠቅላላ ሀብትና በትርፍ፣ በተደራሽነትና በደንበኞች ብዛት፣ በኤሌክትሮኒክ ባንኪንግና በሰው ኃይል ልማት ከፍተኛ ለውጥ ያስመዘገበ ቢሆንም፣ የገበያውን ፍላጎት በአገር ውስጥ ገንዘብም ሆነ በውጭ ምንዛሪ ሙሉ በሙሉ ለማሟላት ባለመቻሉ ፈታኝ ጊዜ ሆኖበት እንዳለፈ፣ ነሐሴ 21 ቀን 2007 ዓ.ም. በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ አስታውቋል፡፡

የባንኩ የቢዝነስ ዴቨሎፕመንት የሥራ ሒደት ባለቤት አቶ ይስሀቅ መንገሻና የኮሙዩኒኬሽን ሥራ አስኪያጁ አቶ ኤፍሬም መኩሪያ በጋራ እንደገለጹት፣ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ሁሉም ነገር አልጋ ባልጋ ባይሆንለትም ባደረገው ከፍተኛ እንቅስቃሴ ከአገር ውስጥና ከውጭ ገንዘቦችን በማሰባሰብ ረገድ የተሻለ የዕቅድ አፈጻጸም እንደነበረው አስረድተዋል፡፡

ፍላጎትና አቅርቦት ያልተጣጣመ እንደነበር ኃላፊዎቹ ጠቁመው፣ ገና ብዙ ቢቀረውም የቁጠባ ባህል ከአምስት በመቶ ወደ 22 በመቶ መድረሱን፣ በሰው ኃይል ልማት በኩልም እ.ኤ.አ በ2025 ዓለም አቀፍ ተቀባይነት ያለው እንዲሆን የልህቀት ማዕከል ከፍቶ በማሠልጠን ላይ መሆኑን ኃላፊዎቹ ገልጸዋል፡፡

ባንኩ በአምስት ዓመቱ ዕቅድ የተቀማጭ ሒሳብ ዕድገቱን 188.4 ቢሊዮን ብር ለማድረስ አስቦ፣ 241.7 ቢሊዮን ብር ማድረሱንና በየዓመቱ በአማካይ 34.4 በመቶ ለማሳደግ መቻሉን ኃላፊዎቹ ጠቁመዋል፡፡ በውጭ ምንዛሪ አፈጻጸሙ 28.1 ቢሊዮን ዶላር ለማግኘት አቅዶ 24.9 ቢሊዮን ዶላር ማግኘቱንም አክለዋል፡፡ የውጭ ምንዛሪው የተገኘው  ከወጪ ንግድና በውጭ ከሚኖሩ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ወደ አገር ውስጥ ከሚልኩት መሆኑንም ገልጸዋል፡፡

የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በዕቅዱ ዘመን ማብቂያ 25.8 ቢሊዮን ብር ለማትረፍ አቅዶ፣ 42.8 ቢሊዮን ብር ማትረፉንና 166 በመቶ አፈጻጸም እንዳለው ኃላፊዎቹ አስረድተዋል፡፡ በአምስት ዓመቱ ዕቅድ የመጀመሪያ ዓመት የባንኩ ጠቅላላ ሀብት 74.2 ቢሊዮን ብር፣ ካፒታሉም 5.5 ቢሊዮን ብር እንደነበር ያስታወሱት ኃላፊዎቹ፣ በዕቅዱ ማጠናቀቂያ ላይ ጠቅላላ ሀብቱ 303.6 ቢሊዮን ብር፣ ካፒታሉ ደግሞ 12.9 ቢሊዮን ብር መድረሱን ተናግረዋል፡፡ የጠቅላላ ሀብቱ ዕቅድ 209.7 ቢሊዮን ብር እንደነበር ጠቁመዋል፡፡

ንግድ ባንክ የደንበኞቹን ብዛት በዕቅዱ ዘመን መጨረሻ ላይ 10.7 ሚሊዮን ማድረሱን የገለጹት ኃላፊዎቹ፣ ዕቅዱ ሲጀመር የነበሩት ደንበኞች 2.2 ሚሊዮን የነበሩ ቢሆንም፣ በአማካይ በየዓመቱ 1.7 ሚሊዮን የአዳዲስ ደንበኞች ሒሳብ በመክፈት ደንበኞቹን ማብዛቱን ተናግረዋል፡፡ ባንኩ የዕቅዱ ትግበራ ሲጀመር 220 ቅርንጫፎች እንደነበሩት፣ በአምስት ዓመት ውስጥ 745 አዳዲስ ቅርንጫፎችን በመክፈት አሁን 965 ማድረሱን ኃላፊዎቹ ገልጸዋል፡፡ 886 ቅርንጫፎች በኔትወርክ የተገናኙ መሆናቸውንም አክለዋል፡፡

የአምስት ዓመቱ የባንኩ ኮርፖሬት ስትራቴጂካዊ ዕቅድ ሲጠናቀቅ በካርድ የባንክ አገልግሎት የሚጠቀሙ ደንበኞች ቁጥር 1.6 ሚሊዮን መድረሳቸውን፣ የሞባይል ባንኪንግ አገልግሎት ተጠቃሚዎች 579 ሺሕ፣ የኢንተርኔት ባንኪንግ አገልግሎት ተጠቃሚዎች ደግሞ 7,838፣ 644 ኤቲኤሞችና 1,866 የ“POS” መክፈያዎችን በተለያዩ አካባቢዎች ማቅረብ መቻሉን ኃላፊዎቹ አብራርተዋል፡፡ ባንኩ የነበረውን 8,117 የሰው ኃይል ወደ 22,908 ማድረሱንም አክለዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች