Monday, December 4, 2023
- Advertisment -
- Advertisment -

ሕዝብ ከኢሕአዴግ ጉባዔ የሚጠብቀው ተግባራዊ ዕርምጃ ነው!

ኢሕአዴግ አሥረኛ ጠቅላላ ጉባዔውን  በመቐለ ከተማ ካለፈው ዓርብ ነሐሴ 22 ቀን 2007 ዓ.ም. ጀምሮ በማካሄድ ላይ ይገኛል፡፡ ይህ ጉባዔ “ሕዝባዊ አደራን በላቀ ዕድገትና ትራንስፎርሜሽን” በሚል መሪ ቃል የሚካሄድ በመሆኑ፣ የኢትዮጵያ ሕዝብ ከኢሕአዴግ የሚጠብቃቸው ተግባራዊ ዕርምጃዎች አሉ፡፡ ሕዝቡ ለዓመታት ሲንከባለሉ የመጡት የመልካም አስተዳድር ዕጦት፣ የማስፈጸም ብቃት ማነስና ሙስና ላይ ተግባራዊ ዕርምጃ እንዲወሰድ ይጠብቃል፡፡

በ1983 ዓ.ም. በወርኃ ጥር በትግራይ ክልል በቆላ ተምቤን የተካሄደው የኢሕአዴግ የመጀመርያው ጉባዔ፣ የደርግ መንግሥትን ውድቀት ለማፋጠን የትጥቅ ትግሉ ተጠናክሮ እንዲቀጥል ውሳኔ ማሳለፉ ይታወሳል፡፡ በስድስት ወራት ውስጥም ውሳኔውን በተግባራዊ ዕርምጃ ማረጋገጡ አይዘነጋም፡፡ ከዚያም በኋላ በተካሄዱ የድርጅቱ ጉባዔዎች በተለይም በልማት ላይ የተላለፉት ውሳኔዎች በአገሪቱ ከፍተኛ የሆነ እመርታዊ ለውጥ ማምጣታቸው ይታወሳል፡፡ ኢሕአዴግ ጨከን ብሎ ተግባራዊ ዕርምጃዎች በወሰደባቸው መስኮች፣ በተለይም በፀረ ድህነት ትግሉ አመርቂ የሆኑ ውጤቶች መመዝገባቸውን ማንም ማስተባበል አይችልም፡፡ ተግባራዊ ዕርምጃ ሲወሰድ ውጤቱም በገሐድ ይታያልና፡፡

ከልማቱ ጎን ለጎን መቀላጠፍ የሚገባቸው ጉዳዮች እየተዘነጉ ወይም ችላ እየተባሉ ግን በአገር ላይ ጉዳት እየደረሰ ነው፡፡ እነዚህ ችግሮች የሚያስከትሉት ጉዳት የተሠራውን እንዳልተሠራ በማድረግ፣ በበርካታ አገራዊ ፋይዳ ባላቸው መሠረታዊ ጉዳዮች ላይ ጥላቻውን እያጠሉ ነው፡፡ አገሪቱ በመንገድ፣ በባቡር፣ በኃይል ማመንጫ፣ በቴሌኮም፣ በጤና፣ በትምህርትና በመሳሰሉት መሠረታዊ ልማቶች ያስመዘገበቻቸው ድሎች በዓለም ዙሪያ ገጽታዋን እየለወጡ ነው፡፡ ዝናቸውም በዓለም አቀፍ ሚዲያዎችም እያስተጋባ ነው፡፡ ነገር ግን ተግባራዊ ዕርምጃ ያልተወሰደባቸው ችግሮች ደግሞ የምሬት ማስተጋቢያ እየሆኑ ነው፡፡

ኢሕአዴግ በተለያዩ ጉባዔዎቹም ሆነ በልዩ ልዩ መድረኮች በተለይ የመልካም አስተዳደር ዕጦትና ሙስና አላላውስ እንዳሉ በስፋት አውስቷል፡፡ ሕዝብን በቢሮክራሲ የሚያማርሩ ተቋማትና ግለሰቦች መብዛት፣ በፍትሕ ሥርዓቱ ውስጥ የሚታዩ ችግሮች አስጨናቂ መሆን፣ ብቃት የሌላቸው ሹማምንት መብዛትና የማስፈጸም ብቃት መዳከም፣ ሙስና የአገርም ሆነ የሥርዓቱ ጠንቅ መሆን፣ ወዘተ ብዙ ተብሎባቸዋል፡፡ አሁን ዋናው አስፈላጊውና አንገብጋቢው ጉዳይ በችግሮቹ ላይ መነጋገር ብቻ ሳይሆን ተግባራዊ ዕርምጃ ነው፡፡ ችግሮቹ ከሚነገርላቸው በላይ ተግባራዊ ዕርምጃ ይሻሉ፡፡

የመልካም አስተዳደር ዕጦት፣ የማስፈጸም አቅም ማነስና ሙስና የአገሪቱን ሕዝብ እያስጨነቁ ባሉበት በዚህ ወቅት በተለያዩ የኢኮኖሚ፣ የፖለቲካና የማኅበራዊ ጉዳዮች ላይ ዕቅድ መንደፍ ብቻውን ውጤት አያመጣም፡፡ ሕዝቡ በተለይ በሁለተኛው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ለማሳካት በሚደረገው ርብርብ ላይ ተሳትፎው ሊያድግና የሚፈለግበትን አስተዋጽኦ ማበርከት የሚቻለው መብቱ ተጠብቆለት፣ ግዴታውን ለመወጣት የሚያስችለው ከባቢ ሲፈጠርለት ነው፡፡ የአገር ውስጥ ባለሀብቱም ሆነ የውጭ ኢንቨስትመንቱ የልማቱ አጋዥ የሚሆነው የመልካም አስተዳደር ዕጦት መገለጫ የሆኑት ያልተገቡ ተግባራት በተግባር ሲወገዱና ሙሰኞች አደብ ሲገዙ ነው፡፡

ኢሕአዴግ በአሥረኛው ጠቅላላ ጉባዔው ወቅት በተለያዩ ጉዳዮች ላይ ሲመክር የመልካም አስተዳደር ዕጦትና ሙስና በተግባር እንዴት እንደሚወገዱ አፅንኦት ሊሰጥባቸው ይገባል፡፡ ከምክክሩ ባሻገር ለተግባራዊ ዕርምጃው የሚረዱ የመፍትሔ ሐሳቦችን በመቀበል ተግባራዊ ለመሆን ትኩረት መስጠት አለበት፡፡ ኢሕአዴግ በእነዚህ አሳሳቢና አንገብጋቢ ጉዳዮች ላይ ሥር ነቀል ለውጥ ካላካሄደ፣ የሚታቀዱ የልማት አጀንዳዎች ችግር ይገጥማቸዋል፡፡ ድርጅቱ ህልውናውን አስጠብቆ መጓዝ የሚችለው አገርን ችግር ውስጥ የሚከቱ ችግሮችን ከመሠረታቸው ማስወገድ ሲችል ብቻ ነው፡፡ የኢኮኖሚው ዕድገት ባለሁለት አኃዝ ሆኖ መቀጠል የሚችለው ሕዝቡ እርካታ አግኝቶ ሰላምና መረጋጋቱ ሲቀጥል ነው፡፡ ለዚህ ደግሞ ተግባራዊ ዕርምጃ የግድ ነው፡፡

ኢሕአዴግ የሚመራው መንግሥት ያከናወናቸው በርካታ አወንታዊ ተግባራት ቢኖሩም፣ በተሳሳቱ መረጃዎችና ሪፖርቶች ምክንያት የሚያጠፋቸውም ብዙ ናቸው፡፡ በተለይ ያልተሠራውን እንደተሠራ አድርጎ የማቅረብ፣ ሕዝቡ እየተበደለ አሁን ገና ፀሐይ እንደወጣለት አድርጎ መዋሸት፣ ቅሬታዎችና አቤቱታዎችን ማፈን፣ በተድበሰበሱ ግምገማዎች ንፁኃንን ማሸማቀቅና ሙሰኞችን አዝሎ መዞር፣ ወዘተ በስፋት እየታየ ነው፡፡ ከእነዚህ በተጨማሪ ዜጎችን ማስፈራራት፣ ማሸማቀቅና ብሎም አገራቸውን ጥለው እንዲሰደዱ የሚያደርጉ አጓጉል ተግባራትን የሚፈጽሙ ሕገወጦችን ዝም ማለት የሕዝብ ምሬት ምንጮች ናቸው፡፡ ሥር ነቀል ለውጥ ይካሄድባቸው፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ በአሥረኛው የኢሕአዴግ ጠቅላላ ጉባዔ የመክፈቻ ንግግራቸው ላይ የጠቀሱት፣ የኪራይ ሰብሳቢነት ፖለቲካዊ ኢኮኖሚ በተለይ በከተሞች አካባቢ በስፋት መቀጠሉ አሳሳቢ ነው፡፡ ይህ በተጠናከረ ኔትወርክ የሚመራ እኩይ ተግባር እንደ ሰደድ እሳት እየተዛመተ በመሆኑ፣ በጠንካራ ተግባራዊ ዕርምጃ ካልተወገደ ጦሱ ለአገር ነው የሚተርፈው፡፡ ችግሩ በስፋት መኖሩን ማመን እንዳለ ሆኖ፣ ከሥር መሠረቱ ለመናድ ተግባራዊ ዕርምጃ ለመውሰድ መነሳት የወቅቱ ጥያቄ ነው፡፡ በቡድን የተደራጁ ኃይሎች ሙስናን በአገሪቱ ላይ እያነገሡ በመሆናቸው ቁርጠኛ መሆን ይጠይቃል፡፡ ይህ ዕርምጃ ከተገታ ግን ውጤቱ ከሚታሰበው በላይ አደገኛ ነው፡፡

የብቃት ማነስ በየቦታው መታየት የማስፈጸምን አቅም ተፈታትኖታል፡፡ ኢሕአዴግ በተለያዩ ጊዜያት የማስፈጸም ብቃት ችግር እንዳለበት ሲናገር ተደምጧል፡፡ ዕርምጃ ሲወስድ ግን አይታይም፡፡ የመጀመሪያው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ አፈጻጸም በዚህ ጉባዔ በጥልቀት እንደሚገመገም ተነግሯል፡፡ በእርግጠኝነት መናገር የሚቻለው በዕቅዱ አፈጻጸም ውስጥ ከሚታዩ ችግሮች አብዛኞቹ የሚከሰቱት በማስፈጸም አቅም ማነስ ነው፡፡ ከወረዳ ጀምሮ እስከ ፌዴራል ትልልቅ መሥሪያ ቤቶች ድረስ በአፈጻጸም ደካማነት የሚመዘገቡ አሳዛኝ ውጤቶች ብዙ ናቸው፡፡ ብዙዎችም በሐሰተኛ ሪፖርቶች ይቀባባሉ፡፡ በመንግሥት የውሳኔ አሰጣጥ ላይም ብዥታ ይፈጥራሉ፡፡ ይህም ከፍተኛ የሆነ ሥር ነቀል ለውጥ ያስፈልገዋል፡፡ በአገር ህልውና ቀልድ የለም፡፡ በአስቸኳይ፡፡

የኢሕአዴግ አሥረኛ ጠቅላላ ጉባዔ ከስኬቶች በላይ ከፍተኛ ትኩረት የሚያስፈልጋቸውን ችግሮች በጥልቀት ይገምግም፡፡ ሐሰተኛ መረጃዎችንና ሪፖርቶችን ያጋልጥ፡፡ ሕገወጥነትን የሚያበረታቱ ተግባራትን ያውግዝ፡፡ የመልካም አስተዳደር ፀር የሆኑ ተግባራትን ይዋጋ፡፡ የሕግ የበላይነትን የሚፃረሩ ተግባራትን ያስወግድ፡፡ ፍትሕ የሚያዛቡትን ያስወግድ፡፡ በኔትወርክ ተሳስረው አገር የሚበዘብዙትን ሙሰኞች ያባር፡፡ ብቃት የሌላቸውን ያሰናብት፡፡ ለዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታና ለሰብዓዊ መብት አጠባበቅ የማይበጁ አሠራሮችን በቃ ይበል፡፡ ከንግግር በላይ ለተግባር ቅድሚያ ይስጥ፡፡ የኢሕአዴግ ጉባዔ ለተግባራዊ ዕርምጃ ቆራጥ ይሁን!

 

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች

በዓለም አቀፍ ደረጃ ሕይወታቸውን በኤድስ ምክንያት ላጡ ሰዎች 35ኛ ዓመት መታሰቢያ

ያለፍንበትን እያስታወስን በቁርጠኝነት ወደፊት እንጓዝ - በኧርቪን ጄ ማሲንጋ (አምባሳደር) በየዓመቱ...

እዚያ ድሮን… እዚህ ድሮን…

በዳንኤል ካሳሁን (ዶ/ር) ተዓምራዊው የማዕበል ቅልበሳ “በሕግ ማስከበር” ዘመቻው “በቃ የተበተነ...

ለፈርጀ ብዙ የማንነት ንቃተ ህሊናችን የሚጠቅሙ ጥቂት ፍሬ ነገሮች

በበቀለ ሹሜ ከጨቅላነት ጅምሮ ያለ የእያንዳንዳችን የሰብዕና አገነባብ ከቤተሰብ እስከ...

በሲሚንቶ ፋብሪካ ላይ የታየው ተሞክሮ በሌሎች ምርቶች ላይም ይስፋፋ!

ሰሞኑን በኢትዮጵም ሆነ በአፍሪካ ደረጃ ግዙፍ ስለመሆኑ የተነገረለትን የለሚ...
spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

የአስተሳሰብና የአስተዳደር ዘይቤ ለውጥ ያስፈልጋል!

ኢትዮጵያ ውስጥ ሕዝቡን በጋራ አስተሳስረው የሚያኖሩ በጣም በርካታ ማኅበራዊ እሴቶች አሉ፡፡ እነዚህ ለዘመናት ከትውልድ ወደ ትውልድ ሲሸጋገሩ የኖሩ እሴቶች አገር ለማቆም ትልቅ አስተዋፅኦ ነበራቸው፣...

ድጋፍና ተቃውሞ እኩል ይስተናገዱ!

ኢትዮጵያ ውስጥ ለረዥም ዓመታት ለመንግሥት ከሚቀርቡ ጥያቄዎች መካከል አንዱ የመብት መከበር ጉዳይ ነው፡፡ ዜጎች ተፈጥሯዊም ሆኑ ሕጋዊ መብቶቻቸው እንዲከበሩላቸው ለመንግሥት ጥያቄ ሲያቀርቡ፣ ጥያቄው የቀረበለት...

ፖለቲካዊ ችግሮች ፖለቲካዊ መፍትሔ ይፈለግላቸው!

መንግሥት ከኦነግ ሸኔ ጋር በታንዛኒያ ዳሬሰላም ከተማ ሲያካሂድ የነበረው ንግግር ያለ ውጤት መጠናቀቁን ካስታወቀ በኋላ፣ በኦሮሚያ ክልልም ሆነ በሌሎች ቦታዎች ሰላም ለማስፈን የነበረው ተስፋ...