Sunday, March 26, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊየሕይወት ልምድ የተሰነቀላቸው

የሕይወት ልምድ የተሰነቀላቸው

ቀን:

‹‹በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ከተራ ኦፊሰርነት ተነሥቼ ምክትል ፕሬዚዳንት ሆኜ በማገልገል ላይ እገኛለሁ›› ያሉት በመጪው ዓመት ዩኒቨርሲቲ ለመቀላቀል በዝግጅት ላይ ለሚገኙ 2,500 ለሚሆኑ ሴት ተማሪዎች ዘር ኢትዮጵያ ባዘጋጀው የሽኝት ፕሮግራም ላይ የሕይወት ተሞክሯቸውን ለማካፈል የተገኙት ወ/ሮ መሊካ በድሪ ነበሩ፡፡

ዓርብ ነሐሴ 22 ቀን 2007 ዓ.ም. በአፍሪካ ኅብረት አዳራሽ በተዘጋጀው ፕሮግራም የሕይወት ልምዳቸውን ለማካፈል የተገኙት ወ/ሮ መሊካ በዕድሜያቸው ያሳለፏቸውን ውጣ ውረዶችና ስኬቶችን ለተማሪዎቹ አስቃኝተዋል፡፡ እሳቸው እንደገለጹት ተወልደው ያደጉት አዲስ አበባ ሲሆን፣ የአንደኛ ደረጃ ትምህርታቸውን በአባድር አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተከታትለዋል፡፡ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን ደግሞ በየካቲት 12 የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት አጠናቅቀዋል፡፡ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በኢኮኖሚክሥ የመጀመሪያ ዲግሪ አላቸው፡፡ በባህር ማዶም ተጨማሪ ትምህርት ተከታትለዋል፡፡

በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ለረጅም ዓመታት እንዳገለገሉ የሚናገሩት ወይዘሮዋ እናትነትና በሥራው ዓለም ተወዳዳሪ ሆኖ መቆየት ‹‹እጥፍ ድርብ ልፋት አለው›› በማለት ተማሪዎቹ መጠንከር እንደሚገባቸው ተናግረዋል፡፡ ከመደበኛ ሥራቸው ባሻገርም በተለያዩ የበጐ አድራጐት ሥራዎች ላይ እንደሚሳተፉ ገልጸዋል፡፡ እ.ኤ.አ. በ2013 አሶሴሽን ኦፍ ውሜን ኢን ቢዝነስ ባዘጋጀው በ(Women of excellence Award) ዕውቅና ከተሰጣቸው አምስት ሴቶች መካከል መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡ በተጨማሪም በ2014 በደቡብ አፍሪካ ጁሀንስበርግ ላይ ሲኢኦ ኮሚዩኒኬሽን ባዘጋጀው (African most influential woman in business) በመንግሥት አስተዳደር ዘርፍ ዕውቅና አግኝተዋል፡፡

እንደ ወ/ሮ መሊካ ሁሉ የሕይወት ተሞክሯቸውን ያካፈሉ በመከላከያ ሚኒስቴር ብርጋዲየር ጀነራል ዘውዴ ኪሮስ፣ የኬኤምዲ ኢትየጵያ መሥራችና ዋና ሥራ አስፈጻሚ ዶ/ር ቦጋለች ገብሬ፣ አርቲስት ደስታ ሐጐስ ይገኙበታል፡፡ የሽኝት ፕሮግራሙ የተዘጋጀላቸው ተማሪዎች በአዲስ አበባ ከሚገኙ ትምህርት ቤቶች የተውጣጡ ሲሆን ከፍተኛ የዩኒቨርሲቲ መግቢያ ነጥብ ያስመዘገቡም ናቸው፡፡ የፕሮግራሙ ዓላማ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማትን የሚቀላቀሉ ሴት ተማሪዎች በካምፓስ ቆይታቸው በሴትነታቸው የሚያጋጥሟቸውን ፈተናዎች በብቃት መወጣት እንዲችሉ አቅጣጫ የማመላከት ነው፡፡

ለተወሰኑ ሴት ተማሪዎች የገንዘብ ድጋፍ ሲያደርግ የቆየው ዘር ኢትዮጵያ ዘንድሮ ለአምስተኛ ጊዜ በተደረገው የሽኝት ፕሮግራም ተማሪዎቹ በዩኒቨርሲቲ ቆይታቸው ለሚያስፈልጓቸው አንዳንድ ወጪዎች መሸፈኛ መጠነኛ ገንዘብ ሲሰጥ መቆየቱን የዘር ኢትዮጵያ መሥራችና ዳይሬክተር አቶ ያሬድ ግርማ ይናገራሉ፡፡

በመጪው ጥቅምት 2008 ዓ.ም. ከተመሠረተ አንድ ዓመት የሚሞላው ዘር ኢትዮጵያ ቪዥን ፎር ጀነሬሽን በተባለ በዩኒቨርሲቲ የሚገኙ ሴቶችና ሕፃናት ላይ ይሠራ ከነበረ ድርጅት ጋር የተቋቋመ ነው፡፡ ዘር ኢትዮጵያ በሚል የሴቶችን ጉዳይ በተናጥል ለመሥራት ራሱን ችሎ የተቋቋመው በቅርብ ነበር፡፡ እስካሁን 500 ለሚሆኑ ሴት የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች የገንዘብ ድጋፍ ሲያደርግ ቆይቷል፡፡ በመጪው ዓመትም የተማሪዎችን ቁጥር በእጥፍ ለማሳደግ ማቀዱን አቶ የሬድ ተናግረዋል፡፡ በተጨማሪም 32 የሚሆኑ የፎቶ ኮፒ ማሽኖችን ለአገልግሎት በማዘጋጀት በተቋሙ ለታቀፉት ተማሪዎች ነፃ አገልግሎት የሚያገኙበትን ዝግጅት አጠናቅቋል፡፡

30 የሚሆኑ ሴት ተማሪዎችን ከዘንድሮ ክረምት ጀምሮ በሥራ እንዲሰማሩ በማገዝ ራሳቸውን እንዲችሉ ድጋፍ አድርጓል፡፡ በዕለቱ ‹‹የታላቋ ሴት የክብር ሽልማት›› የተዘጋጀ ሲሆን፣ ከመከላከያ ሠራዊት ብርጋዴር ጀነራል ሣምራ ዩኒስ ሽልማቱን አግኝተዋል፡፡  

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ለፋይናንስ ዘርፉ ብቃት ያለው የሰው ኃይል የማፍራት የቤት ሥራን የማቃለል ጅማሮ

የአገሪቱ የፋይናንስ ዘርፍ እያደገ ለመሆኑ ከሚቀርቡ ማስረጃዎች ውስጥ  የግል...

የምድር ባቡርን የሚያነቃቃው የመንግሥት ውሳኔ

በኢትዮጵያ ወደብ አልባነት ላይ የተደመረውን የሎጀስቲክስ ችግር ለመፍታት ግዙፍ...

የፓርላማ አባላት ስለሰላም ስምምነቱ አፈጻጸም ግልጽ መረጃ የለንም አሉ

‹‹ሕወሓትን ለፍረጃ አብቅተውት የነበሩ ጉዳዮች በአብዛኛው መልክ ይዘዋል›› ሬድዋን...