Thursday, September 21, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ኪንና ባህልኮሜዲያኖቹ ከማዝናናት ባሻገር

ኮሜዲያኖቹ ከማዝናናት ባሻገር

ቀን:

በገዥና ሻጭ ግርግር የሚታወቀው መርካቶ ባለፈው ሳምንት ከወትሮው የተለየ ድባብ ተላብሶ ነበር፡፡ ከአፍሪካ በስፋት ትልቁ መገበያያ እንደሆነ በሚነገርለት መርካቶ፣ ወደአሥር የሚጠጉ ኮሜዲያኖች የጫማ መጥረጊያ ሳጥን ይዘው ተገኝተው ነበር፡፡ በረከት በቀለ (ፍልፍሉ)፣ ደምሴ ፈቃዱ፣ አሰፋ ተገኝ፣ ዓለማየሁ ጌታቸው፣ ቤተልሔም ጌታቸው (ቤቲ ዋኖስ)፣ ስንታየሁ ክፍሌ፣ ዓብይ ሳህሌና ተፈሪ መንግሥቱ ከኮሜዲያኑ ጥቂቱ ናቸው፡፡ ኮሜዲያኖቹ መርካቶ ውስጥ እየተዘዋወሩ ጫማ የጠረጉ ሲሆን፣ ዓላማ አድርገው የተነሱት ለሙዳይ የበጎ አድራጎ ድርጅት ገንዘብ ማሰባሰብን ነበር፡፡ ኮሜዲያኖቹ ‹‹ችግርንም ጫማንም አብረን እንጠርጋለን›› የሚል መሪ ቃል አንግበው ስለ ድርጅቱ አስተዋውቀዋል፡፡ ሙዳይ በዋነኛነት በሴቶችና ሕፃናት ላይ ያተኮረ የተራድኦ ድርጅት ሲሆን፣ የተቋቋመው በወ/ሮ ሙዳይ ምትኩ ነው፡፡

ሙዳይ ከመመሥረቱ አስቀድሞ በ1993 ዓ.ም. ወ/ሮ ሙዳይ ከአንድ ግለሰብ ጋር ፍሬሽ ኤንድ ግሪን አካዳሚ የተባለ ትምህርት ቤት ትከፍታለች፡፡ በትምህርት ቤቱ ይማሩ የነበሩት ዝቅተኛ ከፍተኛም ገቢ ካላቸው ቤተሰቦች የተገኙ ሕፃናት ነበሩ፡፡ ከጊዜ ወደ ጊዜ በተማሪዎቹ መካከል ያለው የኢኮኖሚ ልዩነት የመማር ማስተር ሒደቱ ላይ ያጠላ ጀመር፡፡

የተሻለ ገቢ ያላቸው ቤተሰቦች ልጆቻቸው ከችግረኛ ተማሪዎች ጋር መማራቸውን ስላልወደዱት ቅሬታ ማሰማት ጀመሩ፡፡ አቅማቸው ያልቻለ ቤተሰቦች ወርሐዊ ክፍያ ያቋርጡ ነበር፡፡ የተሻሉቱ ልጆቻቸው ከችግረኛ ተማሪዎች ተለይተው እንዲማሩ ጥያቄ አቀረቡ፡፡ ወ/ሮ ሙዳይ ችግረኛ ተማሪዎች ክፍያ ባለመክፈላቸው፣ ንፁህ ባለመልበሳቸውና በምሳቃቸው ጥሩ ምግብ ባለመቋጠራቸው ከትምህርት ቤቱ እንዲባረሩ ማድረግ አልተዋጠላትም፡፡ በውሳኔአቸው ከሸሪኳ ጋር ተለያይተው ትምህርት ቤቱ በነፃ አገልግሎት የሚሰጥበት ሆነ፡፡

የተማሪዎቹ ጥያቄ ግን በነፃ መማር ብቻ አልነበረም፡፡ ምግብ፣ ልብስ፣ መጠለያና ሌሎችም መሰል ፍላጎቶቻቸውን ለማሟላት የቤተሰቦቻቸው አቅም አይፈቅድም፡፡ ድርጅቱ ተማሪዎቹን መመገብ፣ መማርያ ቁሳቁሶቻቸውን ማሟላት እንዲሁም በሌላም መንገድ መደጎም የጀመረውም ለዚሁ ነበር፡፡ ድጎማው ከተማሪዎቹ በተጨማሪ እናቶቻቸውን (ከእናቶቻቸው ጋር የተለያዩትን ደግሞ ኃላፊነቱን የወሰዱ ሴት አሳዳጊዎቻቸውን) ያቀፈ ነው፡፡ ሴቶቹ ለራሳቸውና ለልጆቻቸው ምግብ ያበስላሉ፤ ድርጅቱ ለሚኖሩበት ቤት ይከፍልላቸዋል፣ የዕደ ጥበብ ሙያ እያስተማረ ራሳቸውን የሚችሉበት መንገድ ያመቻቻል፡፡ ድርጅቱ ለአካል ጉዳተኞና በኤችአይቪ ለተያዙ ሴቶችም ድጋፍ ያደርጋል፡፡

ሙዳይ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ለዓመታት የሰጠ ሲሆን፣ ከ2005 ዓ.ም. ጀምሮ ፈቃድ አግኝቶ እየተንቀሳቀሰ ይገኛል፡፡ አሁን በድርጅቱ የሚረዱ ሰዎች ቁጥር 739 ደርሷል፡፡ የቁጥሩ መጨመር ወ/ሮ ሙዳይን ይከብዳት ጀመር፡፡ ያለውንን ፍላጎት ማሟላትም በአንዲት ሴት ጥረት የሚዘለቅ አልሆነም፡፡

ወ/ሮ ሙዳይ ገንዘብ ለማግኘት ለገጣፎ አካባቢ ከብት እያረባች ትሸጣለች፡፡ የተወሰኑ ልጆችን ለአጭር ጊዜ ስፖንሰር የሚያደርጉ ግለሰቦችና ተቋሞች ቢኖሩም፣ ቋሚ የገቢ ምንጭ የላቸውም፡፡ ነገሮች ከአቅሟ በላይ ሲሆኑ የተለያዩ አካሎች ለዕርዳታ እጃቸውን እንዲዘረጉ መጠየቅ ጀመረች፡፡

ጥያቄ ካቀረበችባቸው መድረኮች አንዱ በድርጅቱ ግቢ የተዘጋጀው የቡሔና አሸንዳ ክብረ በዓል ነው፡፡ በዓሉ ላይ የተገኙ ኮሜዲያኖች ግቢውን ከጎበኙ በኋላ ገንዘብ ለማሰባሰብ እንደ መጀመርያ ዕርምጃ የወሰዱት በድርጅቱ አካባቢ እየተዘዋወሩ ሆያ ሆዬ መጨፈርን ነበር፡፡ ኮሜዲያኖቹ በቀጣይ መርካቶ፣ ቦሌና ኤግዚቢሽን ማዕከል ጫማ ጠርገዋል፡፡

ከኮሜዲያኖቹ አንዱ በረከት በቀለ (ፍልፍሉ) እንደሚለው፣ ዋነኛ ዓላማቸው ስለሙዳይ ድርጅት ግንዛቤ መፍጠር ነው፡፡ ስለ ድርጅቱ የሚያውቁ ሰዎች ሲበራከቱ ብዙዎችን መድረስ እንደሚቻል ያምናል፡፡ ‹‹ወደ እኛ የመጣችው፤ ልጆቹ ሊበተኑ ሲሉ፤ ነው ሰዎች እንዲረዷቸው ለማነሳሳትም ጫማ ለመጥረግ ወስነናል፤›› ይላል፡፡

ኮተቤ መምህራን ኮሌጅ አካባቢ የሚገኘው ድርጅቱን የጎበኘነው ቅዳሜ ዕለት ነበር፡፡ አብዛኞቹ በድርጅቱ የሚረዱ ሕፃናት ትምህርት ባለመኖሩ በየቤታቸው ናቸው፡፡ በግቢው የነበሩ ሕፃናት እዚህም እዚያም ተሰብስበው በጨዋታ ተጠምደዋል፡፡ እናቶቻቸው ደግሞ ምግብ ለማብሰል ተፍተፍ ይላሉ፡፡ ከማብሰያቸው በቅርብ ርቀት ልጆቻቸው ከነርሰሪ እስከ ሰባተኛ ክፍል የሚማሩባቸው ክፍሎች ይገኛሉ፡፡

ክፍሎቹ እጅግ ጠባብ ናቸው፡፡ ያሉበት ሁኔታ ለተማሪዎች የሚመች አይመስልም፡፡ ከክፍሎቹ አንዱ የተማሪዎች ኮምፒውተር ክፍል ነው፡፡ አንድ ግለሰብ የለገሷቸው ጥቂት ኮምፒውተሮች እርስ በርስ ተደጋግፈው ለልጆቹ አገልግሎት ይሰጣሉ፡፡ ሌላው ክፍል ቤተ መጻሕፍት ሲሆን፣ መጻሕፍት በየመደርደሪያው  ታጭቀውበታል፡፡ መጻሕፍቱ በድርጅቱ የተገዙና ሌሎች ተማሪዎች የተገለገሉባቸው ናቸው፡፡

ከመማሪያ ክፍሎቹ በበለጠ ለሕፃናት ተማሪዎች የተዘጋጀው ማረፊያ ክፍል ያረጀ ነው፡፡ ሕፃናት በምሳ ሰዓታቸው በሚያርፉበት ክፍል ያሉት ፍራሾች አርጅተዋል፡፡ ክፍሉ 52 ለሚሆኑ የነርሰሪና ኪንደር ጋርደን ተማሪዎች ስለማይበቃ ተጨናንቀው እረፍት እንዲወስዱ ይደረጋል፡፡

በአንድ እጇ ምግብ እየሠራች በሌላኛው እጇ ደግሞ የሦስት ዓመት ሴት ልጇን ታቅፋለች፡፡ ሰናይት ካሳ የሁለት ልጆች እናት ነች፡፡ ወደ ድርጅቱ ያመራችው ከአምስት ዓመት በፊት ነበር፡፡ ሁለተኛ ልጇን ልትወልድ ወራት ሲቀሯት ባለቤቷ ጥሏት እንደሄደ ትናገራለች፡፡ በተመላላሽ ሠራተኛነት ተቀጥራ ትሠራ የነበር ቢሆንም ከልጅ ጋር መሥራት አዳገታት፡፡ የእሷና የልጆቿን የዕለት ጉርስ መሸፈንና የቤት ኪራይም መክፈል አቃታት፡፡ ሴት ልጇን በአደራ የምትሰጠው የዕርዳታ ድርጅት ስትፈልግ ወቅት ከወ/ሮ ሙዳይ ጋር ተገናኙ፡፡  

አሁን የመጀመርያ ልጇ በድርጅቱ ትምህርት ቤት የሰባተኛ ክፍል ተማሪ ነው፡፡ እሷም የሸክላ ሥራ ሥልጠና ወስዳ የተለያዩ ቁሳቁሶች ትሠራለች፡፡ በድርጅቱ የሚረዱ ሴቶች ሥራዎች ገበያ ላይ ሲውሉ ገዥ ቢኖራቸውም የሚፈለገውን ያህል ገቢ እንደማያስገኙ ትናገራለች፡፡ አሁን ያለው የኑሮ ውድነትም ድርጅቱን አላላውስ እንዳለው በሐዘኔታ ትገልጻለች፡፡

‹‹ስቸገር ጎዳና ላይ መውጣት ሁሉ አስቤ ነበር፤ አሁን እኔም ልጆቼም መጠለያ አግኝተናል፤›› የምትለው ሰናይት፣ ወ/ሮ ሙዳይን ‹‹የደሃ እናት›› በማለት ትጠራታለች፡፡ ድርጅቱ የገጠመው የገንዘብ እጥረት እያሳሰባት ነው፡፡ ድርጅቱን የሚደግፉ ሰዎች ካልተገኙ እንደ እሷ ሁሉ መጠጊያ የሌላቸው ሴቶችና ሕፃናት እንደሚበተኑ ታስረዳለች፡፡

ከትምህርት ቤቱ አጠገብ ሰናይትና የተቀሩት ሴቶች የዕደ ጥበባት ሥልጥና የሚወስዱበት ቅጥር ግቢ ይገኛል፡፡ ሴቶቹ የሸክላ ሥራ፣ የልብስ ስፌትና የሽመና ሥልጠና ይወስዳሉ፡፡ በተለያየ ዲዛይን የባህል ልብሶች ያዘጋጃሉ፡፡ በድርጅቱ ሴቶች የተሠሩ ልብሶች በቅርቡ በአቢሰኒያ የሥነ ጥበብና ሞዴሊንግ ትምህርት ቤት ተመራቂዎች ተለብሰው ለዕይታ ቀርበው ነበር፡፡ የቤት ውስጥ መገልገያ ቁሳቁሶችም ያመርታሉ፡፡ የተመልካችን ዕይታ በበለጠ የሚስቡት ከዘንባባ የሚያዘጋጇቸው ምርቶች ናቸው፡፡ የዘንባባ ዝንጣይ ከጥበብ ጋር አዋህደው መጋረጃ፣ የጠረጴዛ ልብስና ቦርሳ    ይሠራሉ፡፡

የድርጅቱ የዕደ ጥበባት ግቢ ተቆጣጣሪ አቶ መኳንንት ሽመልስ እንደሚለው፣ ቁሳቁሶች በትዕዛዝ የሚያሠሩና ለገበያ የቀረቡ ምርቶቻቸውን ከድርጅቱ ሱቅ የሚሸምቱ ሰዎች አሉ፡፡ ምርቶቻቸውን በየሱቁ በማቅረብ ገበያቸውን ቢያሰፉ ድርጅቱን በመጠኑ እንደሚደጉሙ ይገልጻል፡፡ የሚሠሩበት ቦታ መጥበቡ በሚፈልጉት መጠን እንዳያመርቱ እንዳገዳቸውም ያስረዳል፡፡

‹‹ተጨማሪ መሥሪያ ቦታና መሣሪያ ቢኖረን ተረጂዎችን ባጠቃላይ ማሳተፍ እንችላለን፤ አሁን 12 ሴቶችን በዘንባባ ሥራ፣ ስድስት ሴቶችን በሸክላ ሥራና 12 ሴቶችን በሽመና እናሳትፋለን፤›› ይላል፡፡ ድርጅቱን በገንዘብ፣ በዓይነት፣ በሐሳብም የሚደግፉ ሰዎች ቢገኙ መልካም ነው ይላል፡፡

በግቢው ከሚኖሩ ሕፃናት አንዷ የ14 ዓመቷ ታዳጊ እየሩስ አበበ፣ የሰባተኛ ክፍል ተማሪ ስትሆን ወደ ድርጅቱ የወሰዷት ወላጅ እናቷ ናቸው፡፡ ‹‹ቤተሰቦቼ የተዘበራረቀ ሕይወት ይኖሩ ነበር፤ ሲለያዩ ከእህቴ ጋር መኖር ጀመርኩ፤ እህቴ ግን ትመታኝ ነበር፤›› ትላለች ስላለፈ ሕይወቷ ስትናገር፡፡ እናቷ ወደ ድርጅቱ ካመጧት በኋላ ትምህርቷን እዛው እየተከታተለች ትገኛለች፡፡

‹‹ያለነው ችግር ላይ ነው፡፡ ወ/ሮ ሙዳይን የሚረዷት ሰዎች ቢገኙ ደስ ይለኛል፤›› ትባላለች፡፡ ደራሲ የመሆን ህልም ያላት ታዳጊዋ ሁሉም ሰው በአቅሙ እንዲረባረብ ትጠይቃለች፡፡

ሌላዋ በድርጅቱ የምትረዳው እናት ወይንሸት ደመቀ የሁለት ልጆች እናት ናት፡፡ የተወለደችው ሸዋሮቢት ሲሆን፣ ወደ አዲስ አበባ የመጣችው ከባለቤቷ ጋር ነበር፡፡ ባለቤቷ ግን ከጥቂት ዓመታት በኋላ አብሯት አልዘለቀም፡፡ በሰው ቤት ሠራተኝነት ብትቀጠርም ሥራዋ ከልጆቿ ጋር አልሆነም፡፡ የመጨረሻ አማራጯም መለመን ሆነ፡፡ እሷና ልጆቿ ማደሪያ አጥተው የተንከራተቱባቸውን ቀናት ታስታውሳለች፡፡

እናትና አባቷ ከዚህ ዓለም በሞት ሲለዩ ወንድምና እህቶቿም አገር ለቃ በመውጣቷ ተቀይመዋት ሊረዷት ፈቃደኛ አልሆኑም፡፡ አሁን ከልጆቿ ጋር ለምትኖርበት ቤት ድርጅቱ ይከፍልላታል፡፡ ምግብ ለምታበስልበትም ወርሐዊ ደመወዝ ይቆረጥላታል፡፡ ‹‹ልጆቼን ከመበተን ተርፌአለሁ፤ ልጆቼ ትልቅ ቦታ እንደሚደርሱ ተስፋ አደርጋለሁ፤ ከ700 በላይ ሰዎችን አንድ ሰው ማስተዳደር አይችልምና ድጋፍ እንሻለን፤›› ትላለች፡፡

ኮሜዲያን ዓለማየሁ ጌታቸው ጫማ በመጥረግ ከተሳተፉት ኮሜዲያኖች አንዱ ነው፡፡ ድርጅቱ ቋሚ የሆነ የገቢ ምንጭ ያለው አለመሆኑ አጣብቂኝ ውስጥ እንደከተታቸው ይናገራል፡፡ ጫማ ጠርገው ያገኙት ገንዘብ ተረጂዎችን እስከዘለቄታው ለማስተዳደር ባይበቃም፣ በተለያየ መንገድ ሰው እንዲረዳቸው ማነሳሳታቸውን ይገልጻል፡፡ ኮሜዲያኖቹ ኮሚቴ አዋቅረው ዕርዳታው የሚቀጥልበትን መንገድ እያቀዱ እንደሆነም ይናገራል፡፡

ኮሜዲያን ቤተልሔም ጌታቸው (ቤቲ ዋኖስ) ስለድርጅቱ ሁኔታ ግንዛቤ መፍጠር መቻላቸውን ትልቅ ቦታ ትሰጠዋለች፡፡ መርካቶ ውስጥ እየተዘዋወሩ ሲጠርጉ ከየኔቢጤ እስከ ባለሀብቶች ድረስ ድጋፍ እንዳደረጉላቸው ትናገራለች፡፡ ‹‹የኪነ ጥበብ ባለሙያዎች አንድ ነገር ቢገጥመን ቀድሞ የሚደርስልን ሕዝቡ ነው፤ እኛም ለሕዝቡ መድረስ አለብን፤›› ትላለች፡፡ በቅስቀሳቸው ብዙ ሰው ወ/ሮ ሙዳይና ድርጅቱ ያሉበትን አሳሳቢ ሁኔታ እንደተገነዘበና ለመርዳት እንደተነሳሳ ታምናለች፡፡

ወ/ሮ ሙዳይ እንደምትናገረው፣ የተረጂ ሴቶች፣ ሕፃናትና አካል ጉዳተኞች ቁጥር ሲጨመር ከተለያዩ ግለሰቦችና ተቋማት እየተበደረች ፍላጎታቸውን ማሟላት የግድ ሆኖባታል፡፡ አሁን ግን ብድሮቿን የምትከፍልበት አቅም አጥታለች፡፡ ለድርጅቱ ኪራይ በወር 52,000 ብር ትከፍላለች፡፡ በሌላ በኩል የኤችአይቪ ሕሙማን ደግሞ የተለየ እንክብባቤ ይሻሉ፡፡

‹‹እኔ ከአቅሜ በላይ ሆኗልና መላው የኢትዮጵያ ሕዝብ ይርዳኝ የሚለውን መልዕክቴን ኮሜዲያኖቹ አስተላልፈውልኛል፤›› ትላለች፡፡ በእሷ እምነት፣ በአንድ ማኅበረሰብ ውስጥ ሴቶች ለጥቃት የሚጋለጡበት ዕድል ሰፊ ነው፡፡ ይህን ችግር ለመቅረፍ ለጀመረችው እንቅስቃሴ ሁሉም ሰው ኃላፊነት ተሰምቶት ዕገዛ ቢያደርግ ለውጥ እንደሚመጣ ታምናለች፡፡ ኮሜዲያኑ ጫማ ሲጠርጉ የብዙዎችን ትኩረት እንደሳቡና ስለድርጅቱ በማሳወቅ ድጎማ እንዳስገኙ ትናገራለች፡፡

እሷ እንደምትናገረው፣ ለውጪ አገር ዜጎች ባህላዊ ቡና አፈላል፣ እንጀራ አገጋገርና ሌላም ሥራዎችን እያስጎበኙ ገንዘብ ያገኛሉ፡፡ ሐሳቧን በመደገፍ የወር አስቤዛ ለመግዛት ብድር ስትጠይቅ ፈቃደኛ የሆኑ የአካባቢው ነጋዴዎችም ጥቂት አይደሉም፡፡ እሷ ግን ከተረጂነት ተላቃ ድርጅቱ ራሱን የሚችልበትን ቀን ትናፍቃለች፡፡ ‹‹ከሁሉም በላይ ቅድሚያ የምንሰጠው ለዕለት ጉርሳቸው ነው፤ ከዚያ በኋላ ትምህርትና ሌሎችም ፍላጎቶችን ማሟላት ይቀጥላል፤›› የምትለው ወ/ሮ ሙዳይ፣ ማንኛውም ዓይነት ድጋፍ እንዲደረግላቸው ጥሪ በማቅረብ ነው፡፡

 

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ባለሙያዎች ኮሚሽን ሪፖርት ምን ይዟል?

ለአሜሪካ ድምፅ አማርኛ ዝግጅት የስልክ አስተያየት የሰጡ አንድ የደንበጫ...

መንግሥት በአማራ ክልል ለወደሙ የአበባ እርሻዎች ድጋፍ እንዲያደርግ ተጠየቀ

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በአማራ ክልል የተፈጠረው ግጭትና አለመረጋጋት በቢዝነስ...

አምናና ዘንድሮ!

እነሆ መስከረም ጠብቶ በአዲስ መንፈስ ተሞልተን መንገድ ጀምረናል። ‹‹አዲስ...