Monday, September 25, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ዓለምአውሮፓውያንን ለሁለት የከፈለው የስደተኞች ማዕበል

አውሮፓውያንን ለሁለት የከፈለው የስደተኞች ማዕበል

ቀን:

በየቀኑ በሺዎች የሚቆጠሩ ስደተኞች የአውሮፓ ድንበርን ለማቋረጥ ደጅ ይጠናሉ፡፡ ሆኖም ወደ አውሮፓ አገሮች መዝለቁ ፈተና ነው፡፡ አንዳንዶቹ አገሮች በስደተኛ ካምፕ ሲያስቀምጡና ጥገኝነትን ሲፈቅዱ፣ አንዳንዶቹ ደግሞ በራቸውን ዝግ የሚያደርጉ ጠንካራ የስደተኛ ፖሊሲ አውጥተዋል፡፡ ይህም የአውሮፓ አባል አገሮች መሪዎችን ለውዝግብ ዳርጓል፡፡

በአንድ የጋራ ፖሊሲ የሚተዳደሩት የአውሮፓ ኅብረት አባል አገሮች፣ በየቀኑ የሚጐርፉትን ስደተኞች ጉዳይ ለመዳኘት ወጥ አቅጣጫ ማስቀመጥ ተስኗቸዋል፡፡ ጀርመን ሁሉም አባል አገሮች ስደተኞች በተወሰኑ የአውሮፓ አገሮች ላይ የፈጠሩትን ጫና እንዲካፈሉ ሐሳብ ብታቀርብም፣ በሁሉም አገሮች ተቀባይነት አላገኘችም፡፡ ፈረንሳይና እንግሊዝ ከጀርመን ጐን በመቆም ስደተኞች የሚስተናገዱበትን አኳኃን በተመለከተ አዲስ የጋራ ፖሊሲ እንዲወጣ ግፊት ቢያደርጉምና በተደጋጋሚ ስብሰባ ቢቀመጡም፣ ከሌሎቹ አገሮች በጐ ምላሽ አላገኙም፡፡ በመሆኑም መስከረም 3 ቀን 2008 ዓ.ም. የአውሮፓ ኅብረት አባል አገሮች አስቸኳይ ስብሰባ በብራሰልስ ለማድረግ ወስነዋል፡፡ ስብሰባው ስደተኞች በተወሰኑ አገሮች ላይ የሚፈጥሩትን ጫና ለማቃለል የሚያስችልና ሁሉም አገሮች ችግሩን የሚካፈሉበትን የጋራ ስትራቴጂ ለመንደፍ ያለመ ቢሆንም፣ ሐሳቡ ከወዲሁ እክል እየገጠመው ነው፡፡

ጣሊያን፣ ግሪክና ጀርመን ስደተኞች በተለይ የሚጐርፉባቸው የአውሮፓ አገሮች ናቸው፡፡ ትንሽ በምትባለው የግሪክ ሌስቦስ ደሴት ብቻ 13 ሺሕ ስደተኞች ይገኛሉ፡፡ ከሊቢያ ሜዴትራኒያን ባህርን በማቋረጥ የጣሊያን ወደብን ያጨናነቁና ባህር የበላቸውም በሺዎች የሚቆጠሩ ናቸው፡፡ ከአውሮፓ አገሮች ትልቁን የስደተኞች ቁጥር የምታስተናግደው ጀርመን፣ በተያዘው ዓመት ብቻ ከ800 ሺሕ በላይ የፖለቲካ ጥገኝነት ጠያቂዎችን ልታስተናግድ እንደምትችል አሳውቃለች፡፡ ይህ ካለፈው ዓመት ጋር ሲነፃፀር በአራት እጥፍ ጨምሯል፡፡ በጀርመን እ.ኤ.አ. በ2015 የፖለቲካ ጥገኝነት የጠየቁ ስደተኞች ቁጥር በአውሮፓ አባል አገሮች ጥገኝነት ከጠየቁት 43 በመቶውን ይይዛል፡፡

የጀርመኗ መራሂተ መንግሥት አንገላ መርከል፣ በአገራቸውም ሆነ በሌሎች አገሮች ላይ ስደተኞች እያደረሱ የሚገኙትን ጫና ሁሉም እንዲጋሩ ጥሪ አቅርበዋል፡፡ ‹‹አውሮፓውያን እርስ በርሳቸው እንደሚረዳዱ ሁሉ ይህንን ለሌሎችም ማድረግ አለባቸው፡፡ ድጋፋችንን አሁን ማሳየት አለብን፣ በፍጥነት!›› ሲሉም ተናግረዋል፡፡  

አውሮፓውያን ግን መርከል እንዳሉት ተባባሪ ሆነው አልተገኙም፡፡ አልጄዚራ እንደዘገበው፣ የተወሰኑ የአባል አገሮቹ ተወላጆች ‹‹ጫናው እኛ በምንከፍለው ታክስ ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ ያመጣል፤›› ሲሉ፣ ሃንጋሪ ደግሞ ማንኛውም ስደተኛ ወደ አገሯ እንዳይገባ፣ የፖለቲካ ጥገኝነት የሚጠይቁም በጠንካራ መሥፈርቶች እንዲያልፉ አድርጋለች፡፡ ከዚህ ባለፈም ስደተኞች ድንበሯን እንዳያቋርጡ አጥር ለመገንባት በዝግጅት ላይ ነች፡፡ አጥሩ የሚገነባውም ከሰርቢያ በሚያዋስናት ድንበር ሲሆን፣ ይህም ከሰርቢያም ሆነ ሰርቢያን አቋርጠው ወደ ሃንጋሪ የሚገቡ ስደተኞችን ለማገድ ያስችላታል፡፡

የሃንጋሪ መንግሥት ቃል አቀባይ ዞልታን ኮቫስ ‹‹ሕገወጥ ስደተኞችን ለመግታት ደንብና ሥርዓት ማበጀት አለብን፤›› ብለዋል፡፡

ፈረንሳይ ግን በሃንጋሪ ዕርምጃ ላይ ተቃውሞዋን ሰንዝራለች፡፡ የፈረንሳይ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሎረንት ፋቢዮ፣ ‹‹ጨካኞች ናቸው፡፡ ሃንጋሪ የአውሮፓ አካል ናት፡፡ የራሳችን የሆነ እሴት አለን፡፡ ስደተኞች ላይ አጥር በማጠር ግን እሴቶቻችንን ልናከብር አንችልም፤›› ሲሉ ለኢሮፕ 1 ሬዲዮ ጣቢያ ተናግረዋል፡፡

አውሮፓ በስደተኞች መጥለቅለቋ ምሥራቅና ምዕራብ አውሮፓን በሐሳብ ልዩነት ከፍሏል፡፡ በተለይ ስደተኞችን በኮታ መከፋፈል የሚለው አጀንዳ ላይ ለመስማማት አልቻሉም፡፡ ጀርመንን ጨምሮ አንዳንድ የኅብረቱ አባል አገሮች የኮታ ሥርዓት ለመዘርጋት ሐሳብ ቢያቀርቡም፣ ተቀባይነት አላገኙም፡፡ እንደ ሃንጋሪ ሁሉ ስሎቫኪያም ሐሳቡን ውድቅ አድርጋለች፡፡ የስሎቫኪያ ጠቅላይ ሚኒስትር ሮበርት ፊኮ፣ አገራቸው መቼውንም ቢሆን ኮታ በሚለው ሐሳብ እንማትስማማና ስደተኞችንም እንደማትቀበል አሳውቀዋል፡፡ ‹‹አንድ ቀን ከዓረቡ ዓለም የተሰደዱ 100 ሺሕ ሰዎች በስሎቫኪያ ቢገኙ ለአገራችን ችግር ነው፡፡ ይህን ችግር ስሎቫኪያ እንድትሸከም አልፈልግም፤›› ብለዋል፡፡ ንግግራቸውም በፖላንድ፣ በቼክ ሪፐብሊክና በሃንጋሪ ድጋፍ አግኝቷል፡፡

አውሮፓ በተያዘው የአውሮፓውያን ዓመት ከዚህ ቀደም ከነበረው በተለየ ሁኔታ በስደተኞተ ተጨናንቃለች፡፡ ከዚሁ ጐን ለጐን የጋራ የፖለቲካ ጥገኝነት ጥያቄ ማስተናገጃ ስትራቴጂ አለመኖር ችግሩን በተወሰኑት አገሮች ላይ አባብሶታል፡፡ በመሆኑም ስደተኞቹ ጠንካራ ኢኮኖሚ ወዳላቸውና የፖለቲካ ጥገኝነት ጥያቄያቸው በቀላሉ ተቀባይነት ወደሚያገኝበት ምዕራብና ሰሜን አውሮፓ እንዲጓዙ አስገድዷል፡፡ ይህ ደግሞ በተወሰኑት አገሮች ላይ ጫና ፈጥሯል፡፡

በአገሮቹ ላይ ጫናውን ከመፍጠር ባለፈም፣ ስደተኞች በባህርና በየብስ እንዲሁም በማጓጓዣ መኪኖች ላይ ሕይወታቸው እያለፈ ነው፡፡ ባለፈው ሳምንት ብቻ ከ100 በላይ የስደተኞች አስከሬን ከባህር ማውጣታቸውን የሊቢያ ባለሥልጣናት አሳውቀዋል፡፡ ሟቾቹም አውሮፓ ለመግባት የሚጠባበቁ ነበሩ፡፡ ሊቢያ ይህንን ከማሳወቋ በፊትም በኦስትሪያ በተሳቢ ተሽከርካሪ ውስጥ የተጫኑ 71 ስደተኞች ሞተው ተገኝተዋል፡፡

የኦስትሪያ የአገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስትር ጆሃና ማይክሊትነር፣ ‹‹በኦስትሪያ ሞተው የተገኙ 71 ስደተኞች ጉዳይ ለአውሮፓ አገሮች ማንቂያ ደወል ነው፡፡ አውሮፓውያን የስደተኞችን ችግር ለመቅረፍ እጅ ለእጅ መያያዝ አለባቸው፤›› ብለዋል፡፡

በተያዘው ዓመት በአሥር ሺዎች የሚቆጠሩ ስደተኞች ለችግር ተጋልጠዋል፡፡ በአውሮፓ የተሻለ ኑሮ ፍለጋ ተሰደዋል ተብለው ከሚገመቱት ውስጥም 2,500 ያህሉ ባህር ውስጥ ሰጥመው ሞተዋል፡፡

አብዛኞቹ ስደተኞች በየአገራቸው ከሚገኝ ጦርነት፣ ብጥብጥና እስር በመሸሽ ወደ አውሮፓ የሚሰደዱ ናቸው፡፡ ሶሪያና አፍጋኒስታንን ጨምሮ ከ300 ሺሕ በላይ ስደተኞችም ጉዞዋቸውን ወደ አውሮፓ አድርገዋል፡፡ የሜዲትራኒያንን ባህር ካቋረጡት ውስጥ 2,636 ሞት መመዝገቡንና ብዙዎችም ጠፍተው መቅረታቸውን የስደተኞች ዓለም አቀፍ ቢሮ አሳውቋል፡፡

ከምሥራቅ አፍሪካ እንዲሁም ብጥብጥ ከነገሠባቸው የዓረብ አገሮች ወደ አውሮፓ የሚጐርፉ ስደተኞች ቁጥር ከቀን ወደ ቀን እየጨመረ ነው፡፡ ጣሊያንና ግሪክ አብዛኛው የስደተኛ መዳረሻ አገሮች ቢሆኑም፣ የስደተኞች ጉዳይ በአጠቃላይ ለአውሮፓ ራስ ምታት ሆኗል፡፡ የአባል አገሮቹ መሪዎችም በስደተኞች አቀባበል ዙሪያ ከስምምነት መድረስ አልቻሉም፡፡ በመሆኑም መስከረም 3 ቀን 2008 ዓ.ም. በብራሰልስ ለመምከር ቀጠሮ ይዘዋል፡፡ የስደተኞች ማዕበል በአውሮፓ የፈጠረውን ቀውስ በኮታ ሲስተም ለመፍታት የአውሮፓ አባል አገሮች መሪዎች ከስምምነት ይደርሱ ይሆን? በአውሮፓ በሻንገን ቪዛ መጠቀምን ማገድ ወደተወሰኑ አገሮች የሚደረግን እንቅስቃሴስ ይገታው ይሆን? የብዙዎች ጥያቄ ነው፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የቤት ባለንብረቶች የሚከፍሉትን ዓመታዊ የንብረት ታክስ የሚተምን ረቂቅ አዋጅ ተዘጋጀ

በአዋጁ መሥፈርት መሠረት የክልልና የከተማ አስተዳደሮች የንብረት ታክስ መጠን...

እንደ ንብረት ታክስ ያሉ ወጪን የሚያስከትሉ አዋጆች ከማኅበረሰብ ጋር ምክክርን ይሻሉ!

የመንግሥትን ገቢ በማሳደግ ረገድ አስተዋጽኦ እንዳላቸው የሚታመኑት የተጨማሪ እሴት...

ለዓለምም ለኢትዮጵያም ሰላም እንታገል

በበቀለ ሹሜ ያለፉት ሁለት የዓለም ጦርነቶች በአያሌው የኃያል ነን ባይ...