Wednesday, June 19, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

ልናገርየተዘነጉ አጽሞች መርገም እንዳይሆኑብን

የተዘነጉ አጽሞች መርገም እንዳይሆኑብን

ቀን:

በሐናንያ መሐመድ (አፋር)

መዘንጋት እንዴት ያናዳል፡፡ ግን መዘንጋት እንዴት ይፈጠራል? በብዙ ባልና ሚስቶች መካከል ረሳኝ የሚል ቅሬታ በግልጽም ሆነ በአሽሙር ይሰነዘራል፡፡ ተዘነጋሁ፣ ተረሳሁ ብሎ የሚያስበው ሰው ለሽማግሌዎችም ሆነ ዘነጋኝ ለሚለው ሰው ማስረዳት ይከብደዋል፡፡ ‹‹ለወሬ የማይመች›› እንዲሉ ይሆንና ነገሩ ሕመሙ የሚገባው ለተዘነጋው ብቻ ይሆናል፡፡ በእርግጥ አንዳንድ ጊዜም እራሳችን በራሳችን በምንሰጠው ግምት የተዘነጋን ሊመስለንም ይችላል፡፡ ከመሬት ተነስቶ ‹‹ኧረ ጣል ጣል አደረግከኝ›› የሚልህ  ሰውም ይገጥማል፡፡ አንዳዱ ደግሞ ለምንም ሳይፈልግ ‹‹ጠፋህ›› ይላል፡፡ ‹‹መቼ ፈለግከኝ?›› ቢባል መልስ የለውም፡፡

ይኼኛው መዘንጋት ግን ከእነዚህ ይለያል፡፡ ምክንያቱም ነጮችን ያንበረከኩ፣ በቅኝ ያልተገዛን ብለን አፋችንን ሞልተን እንድንናገር ያደረጉ ጀግኖች አርበኞችን መርሳታችን ነው፡፡ ለመሆኑ  የአርበኞችን ቀን ስናከብር ምን አስበን ይሆን?  ዓመቱን ሙሉ ጠፍታችሁ አንድ ቀን ብቻ ነው የምታስቡን? እነማን ናችሁ እናንተ ቢሉንስ? ልጆቻችሁ ነን የምልበት ድፍረትና ወኔ ይኖረን ይሆን? በማይጨው የሚገኙ አጽሞችን ለዓመታት ዘወር ብለን ሳናያቸው መቅረታችን እያበሳጫቸው ቢሆንስ? ዘራፍ … የምን ማስመሰል ነው ሁሌ ዓመት ሲደርስ፣ እልፍ ፋኖ ሞቶ አንጀት የሚያደርስ…. እያሉ ቢፎክሩስ?

- Advertisement -

በኮረፌዋ የምትታወቀውን ከተማ ኮረምን ስናልፍ ታሪካዊዋን ማይጨው ከተማን እናገኛለን፡፡ እንግዲህ ማይጨው ሲነሳ የኢጣሊያን ጦርነት ወደ አዕምሮአችን ብቅ ማለቱ አይቀርም፡፡ ኢጣሊያንን ስናስብ ደግሞ የዓደዋ ድል ድቅን ይልብናል፡፡ ስለማይጨው ለማውራት ስለ ዓደዋ ጦርነት ማውራት ግድ ይለናል፡፡ ታሪክን ስንመዝ ባንዳ (አገር ከሀዲ) ሰዎችንም እናስባለን፡፡ በተቃራኒውም ጀግና አርበኞችን እናሳታውሳለን፡፡

ዘመኑ በቅኝ ግዛት አፍሪካን እንደ ቡና ቁርስ አውሮፓውያኖች ቆራርሰው የተቀራመቱበት ጊዜ ነበር፡፡ እንደ እግር ኳስ ምድብ ኢትዮጵያ የደረሰቻት ለኢጣሊያ ነበር፡፡ ኢጣሊያም በጦሯ ታጅባና ተዘጋጅታ በባንዳና በፕሮፖጋንዳ ታንፃ ኢትዮጵያን የራሷ ለማድረግ ፋሽሽታዊ አዋጅ አወጀች፡፡ በነጫጭባ አገሩ መደፈሯን የሰማው ኢትዮጵያዊ ሁሉ ጨርቄን ማቄን ሳይል ጦሩን እየሰበቀ ከአራቱም ማዕዘን ወደ ትግራይ ተመመ፡፡ እናት አገራቸውን እንደ ሚስታቸው፣ እንደ ፍቅረኛቸውና እንደ ነፍሳቸው የሚወዱ አባት አርበኞች ስንቃቸውን ቋጥረው በፉከራና በቀረርቶ የኢጣሊያን ጦር አንበረከኩት፡፡

በነገራችን ላይ ይህን ማውራት የፈለግኩበት ምክንያት አብዛኛዎቻችን የሩቁን እንጂ የአገራችን ወይም የራሳችን ነገር ከማወቅም ሆነ ከመስማት ሸፍተናል፡፡ የአገራችንን ወይም የማንነታችንን ጉዳይ ከማወቅ ይልቅ የእነሮናልዲኒሆና የእነቢዮንሴን ታሪክ መተንተን ይቀናናል፡፡ የምግብ ምርጫቸውን ሳይቀር ሳይቀር የኬጂ ተማሪዎች በቀላሉ ያስረዱናል፡፡  ባለፈው ሰሞን ከጓደኞቼ ጋር ስንጫወት ስለአደፍርስ፣ ፍቅር እስከ መቃብርና መሰል መጻሕፍት ሳወራቸው በጣም ተናደዱብኝ፡፡ ‹‹አትደውከን… አትረብሸን… አታሰልቸን… አሁን ብናነበው እኮ ምንም የሚጠቅም ነገር የለውም…›› በማለት እየተቀባበሉ ሳቁብኝ፡፡ ተሰማኝ፡፡ እንዳልደብራቸው ስለምን ማውራት ነበረብኝ? ለእነሱ የሚጠቅመው መጽሐፍስ ምን ዓይነት ይሆን?

አንድ ጊዜ በአንድ ሬዲዮ ጣቢያ ማንኛውም ሰው ደውሎ የሚያደንቀውን እንድናገርና አስተያየቱን እንዲሰጥ ይደረጋል፡፡ ከዚያም አንዷ ደውላ ማንን እንደምታደንቅ ስትጠየቅ ‹‹አልበርት አንስታይንን›› አለች:: የፕሮግራሙ አዘጋጆችም እስኪ ከአልበርት አንስታይን ሥራዎች አንዳንድ ነገር ንገሪን ሲሏት ወድያው ስልኳን ዘጋች፡፡ ከዚህ የምንረዳው ነገር ስለማናውቀው ነገር ማውራት ከመውደዳችን በተጨማሪ፣ የራሳችንን ፋኖ ትተን የሰው አገር ፖለቲከኞችን ማድነቅ፣ የራሳችንን የጥበብ ሰው ትተን የማናውቀውን ባዕድ ለማምለክ ሩብ ጉዳይ እስከሚቀረን መንጀባረር የተለመደ እየሆነ ስለመጣ ነው፡፡

የቀድሞ ነገሥታቶቻችንን ክብር ብናውቅ ለማንም በከንቱ አናደገድግም ነበር፡፡ የአማርኛ ፊልም አላይም የሚሉህ ብዙ ወጣቶችን እናውቃለን፡፡ ደግሞ የኢትዮጵያ ልቦለድ፣ ደግሞ የኢትዮጵያ ኮሜዲ፣ የኢትዮጵያ….. ይሉሃል፡፡ የዚነት ሙሃባን ዘፈን ማድመጥ ‹ፋራነት›፣ የሲሊንድዮንን መስማት ‹መሠልጠን› የሚመስላቸው ጉብሎች ሥፍር ቁጥር የላቸውም፡፡ ይሁን ግዴለም! በዚህ ሁሉ መካከል ማንነቱን ጠብቆ የሚኖር ትውልድም ስላለ ብለን በተስፋ መጽናናት ይሻለናል፡፡ አለዚያማ በንዴት ብንታመም በቀላሉ የምንታከምበት ሆስፒታል  አናገኝም፡፡ ምክንያቱም ዶክተሩ  በግሉ የሚሠራበት ክሊኒክ ይቀጥረንና አራግፎን ይልከናል፡፡ ይሁን ግዴለም!!!!

ምንም እንኳን እንደሚገባ ባናከብረውም ዛሬ እኛ ሁሌ በዘፈናችን፣ በታሪካችን፣ በጭውውት መካከል በኩራት የምንናገረውን ኢጣሊያኖችን ደግሞም እስከ ዓለም ዳርቻ ድረስ ያሸማቀቃቸውን ገድል በዓደዋ ተራራና ሜዳ ላይ በኢትዮጵያ ጀግና አባት አርበኞች ትኩስ ደም ተፈጸመ፡፡ ያኔ የዓለምን ሕዝብ ያስገረመው ድሉ ብቻ ሳይሆን፣ ጥቁሮች ነጮችን ለመጀመርያ ጊዜ ማሸነፋቸው ጭምር ነበር፡፡ ዛሬ እኛ ቢገባንም ባይገባንም አባቶች የሚወዷት አገራቸውን ከጠላት ወረራ ጠብቀው እስከ ክብሯ አወርሰውናል፡፡

እንዲህም ሆነ፡፡ ኢጣሊያ ከመጋቢት 23 እስከ መጋቢት 26 ቀን 1928 ዓ.ም.  ድረስ በተካሄደው ጦርነት የዓደዋውን ቁጭት ተበቀለችን፡፡ የዓደዋው ጦርነት ለማይጨው ድል መደረጋችን ለኢጣሊያውያን ትልቅ ተሞክሮ ሆኗቸው አልፎ ነበርና፡፡ በማይጨው ጦርነት  እጅግ ዘመናዊ መሣሪያዎችና የጦር አውሮፕላኖችን ከመጠቀማቸውም በላይ፣ በዓለም አቀፍ የተከለከለ መርዛማ ኬሚካልም እንዲጠቀሙ ለኢጣሊያኖች ፍርኃታቸው ድፍረት ሆኖላቸዋል፡፡ በዚህም ጦርነት የብዙ ሺሕ ጀግኖች ኢትዮጵያውያን ሕይወት ሊቀጠፍ ችሏል፡፡ ለኢጣሊያ የድል ጀንበር ፈገግ ያለችላት ጊዜ ያኔ ነበር፡፡ ከዚህ አሳዛኝ እልቂት በኋላ ነበር የኢትዮጵያ አርበኞች ‹‹ዱር ቤቴ›› ብለው የሸፈቱት፡፡

ወደ ማይጨው ከተማ ልንገባ ጥቂት ሲቀረን ከኮረብታማው ቦታ በመፈራረስ ላይ ያለች ትንሽ ቤት እናያለን፡፡ ይህቺ ቤት ለዘመናት ታሪክ ሠርተው ያለፉ አባቶችን አክብራ ማረፊያ የሆነች ቢሆንም፣ ወደ ውስጥ ስንዘልቅ ግን ችላ የተባለ ነገር እንዳለ ለመገመት ያለ አስረጂ የዓይን እማኝ ለመሆን እንገደዳለን፡፡ አንዳንድ ጊዜ ወጪ የሚያስፈራን የሚጠቅም ነገር ለመሥራት ሲሆን ነው እንዴ? ብለን ራስን እንድንጠይቅ ያስገድዳል፡፡

ለምን እንደዚህ እንዳልኩኝ ታውቃለህ?  ጀግና አባቶቻችን እግራቸውን ለእሾህና ጠጠር፣ ግንባራቸውን ለፀሐይና ቁር፣  ነፍሳቸውን ለዘመናዊ የጦር መሣርያና ለሰው ልጆች ለተከለከለ ኬሚካል ያለስስት አሳልፈው ለእናት አገራቸው ሕይወታቸውን ገብረው ታሪክ ሆነው አልፈዋል፡፡ በዚች ትንሽ ቤት ውስጥ የብዙ አባቶች አጽም እግሮቻቸው ለብቻ፣ ጭንቅላቶቻቸው ለብቻ፣ እጆቻቸውና ሌሎች አጥንቶቻቸው ለየብቻ በመስታወት ውስጥ ታሪክ ሠርተው ታሪክ ሆነው እናያለን፡፡

እነ ቢትወደድ አሸናፊ (የግቢ ሚኒስቴር ዋና ጦር አዛዥ)፣ ደጃዝማች ወንድይራድ (የግቢ ሚኒስቴር ምክትል አዛዥ)፣ ደጃዝማች መንገሻ ይልማ (የፈረሰኛ ጦር አዛዥ)፣ ደጃዝማች አበራ ተድላ (የራያና አዘቦ ጦር አዛዥ)፣ ፊታውራሪ ነጋሽ ተስፋዬ (የወለጋ ጦር አዛዥ)፣ ግራዝማች ገብረ ጽዮን ወልደተክለ (መግለጫ ያልተጻፈለት)፣ ሻለቃ ታደሰ ሙሉጌታ (የመድፈኛ ጦር አዛዥ)፣ ሻለቃ ሺበሺ ደያሳ (የክብር ዘበኛ  ሻለቃ አዛዥ)፣ የመቶ አለቃ ትርፌ ተፈራ (የክቡር ዘበኛ የመቶ አዛዥ)፣ ባሻ ኤፍሬም (የክቡር ዘበኛ አንደኛ ባታሊዮን አዛዥ)፣ ባሻ ቸርነት (የክቡር ዘበኛ አምስተኛ ባታሊዮን አዛዥ)፣ ፶ አለቃ ትርፌ ወልደ ጻድቅ (ባልደረባ)፣ ወታደር ዳመኑ (ባልደረባ)፣ ወታደር ባቡ (ባልደረባ)፣  አቶ አምባዬ ተፈሪ (ገበሬ)…፡፡ ሃያ አራት የሚሆኑ ሰዎች የተሰውበትን ቦታና ቀን የሚያሳይ ስም ዝርዝር በእጅ በተጻፈ ወረቀት ከግድግዳ ላይ ተንጠልጥሎ እናገኛለን፡፡ እነዚህ ጀግና አርበኞችም ከተለያዩ የአገራችን ክፍል ያለ ምንም የቋንቋ፣ የብሔር፣ የሃይማኖትና የዘር ልዩነት ለጦርነቱ የዘመቱ ሲሆን የተሰውትም፣ ከ22/7/28 እስከ 24/7/28 ዓ.ም. ድረስ ነው፡፡ የወደቁበት ቦታም አዲ አዋሊዕ፣ አዱሽ ዓዲ፣ ጎርጉራ፣ ተጉለ በር፣ አዲ ቆልቋላ፣ አዲ አጋም፣ ሰውሒ፣ በተባሉ  ቦታዎች መሆኑን በዚያው  ቦታ ሰፍሮ ይገኛል፡፡

በአንድ ወቅት በቦታው ጥሩ ሙዝየምና ቤተ መጻሕፍት ለማሠራት በመንቀሳቀስ ላይ እንደሚገኝ የትግራይ ባህልና ቱሪዝም ቢሮ ገልጾ ነበር፡፡ ግን ይህ ከተባለ ዓመታት አልፈዋል፡፡ ነቃፊ ትውልድ አያድርገንና ኢትዮጵያን ከኢትዮጵያውያን ነፃ ላወጡ ሰማዕታት መታሰቢያ በየክልሉ የተሠሩትን ሙዚየሞች ጎብኝተን፣ ይህን ቦታ ስናይ ትዝብት ብቻ ሳይሆን ወኔ ካለን ንዴትም ጭምር ሊተናነቀን ይችላል፡፡  ምክንያቱም እነኚህ ጀግኖች ከወራሪ ፋሺስት ኢጣሊያ አገራችንን ነፃ ያወጡ ናቸውና፡፡ በዚህ ቦታ ታሪክ ሆነው ከተሰው አርበኞች ውጪ ማንም ታጋይ በዓለም አቀፍ በተከለከለ ኬሚካል መርዝ ተንገብግቦ አልሞተም፡፡ ማንም፣ አንድም፡፡ ለእነዚህ ሰዎች የሰጠነው ክብር በእርግጥ የሚገባ ነው? እነዚህ ጀግና አርበኞች ለሕይወታቸው ሳይሰስቱ ከወራሪው ፋሺስት ኢጣሊያ ነፃ ካወጡን እኛ አጽማቸውን ከሸረሪት ድር ነፃ ማውጣት እንዴት ያቅተናል? ኢትዮጵያዊያንን ከኢትዮጵያዊ ገዥ ነፃ ላወጣ  የምናወራውንና የምናደርገውን ያህል  ሲሶውን ያህል እንኳን ለእነዚህ አርበኞች ብናደርግ ምናለበት?

የውኃ አቁማዳ፣ በወንጋ የተሠራ ጌጣጌጥ፣ አቡጀዲ አልባሳት፣ ፊሻሌ ሽጉጥና ክላሽ ሳይቀሩ ክብር አግኝተው በየሙዝየሙ በክብር ሲቀመጡ ምነው ለአባቶቻችን አጽም ጀርባ መስጠት አሰኘን? ምን ይታወቃል ጣሊያኖች እኛን ስለሚያሳፍረን  እባካችሁን እንዲህ ዓይነት መታሰቢያ ሐውልት አትሥሩ ብለው ተማጽነውን ይሆን እንዴ? በእኔ በኩል እነዚህን አጽሞች መዘንጋት ሌላ መርገም እንዳይሆንብንም  እፈራለሁ፡፡

በእርግጥ ኢትዮጵያ እ.ኤ.አ. በ2015 የዓለም ምርጥ የቱሪዝም መዳረሻ እንድትሆን በየአውሮፓ ቱሪዝምና ንግድ ምክር ቤት ጠቅላላ ጉባዔ ተመርጣለች፡፡ ይህም መንግሥት ለቱሪዝም ኢንዱስትሪ መስፋፋት ያለውን ቁርጠኝነት እንደሚያሳይ ያመለክታል፡፡ ምንም እንኳን መደናነቅ እንደ ሰማይ ቢርቅብንም፡፡ ባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴርን ማመስገን ብቻ ሳይሆን እጅህን አይቆርጥመው በርታ ማለትም ይበጃል፡፡ ነገር ግን ይህ ቁርጠኝነት ሙሉ እንዲሆን ከተፈለገ የብሔር ብሔረሰቦች ጭፈራ፣ ውብ መልከዓ ምድሮችንና የተቀረፁ ድንጋዮችንና ቅርፃ ቅርፆችን ብቻ ሳይሆን የተከሰከሱ አጽሞችንም ልናስብ ይገባናል፡፡ እኛ ችላ ያልነውን ታሪክ ማን ሊንከባከብልን ይችላል? በቅርቡ እንኳን ሚሊዮን ብሮች አውጥተን የገነባናቸው ሐውልቶች የሉምን? ታድያ የእነዚህ የጀግና አርበኞችን አጽም ቦታ ለማስያዝ እንዴት እጃችን አጠረ? በማይጨው የሚገኙ አጽሞች መዘንጋታቸውን አፍ አውጥተው ባይናገሩም ሸረሪቶች ግን ሊጎበኝ ለሚሄድ ሰው በድራቸው ይናገራሉ፡፡

ቻይናውያን የማኦ ዜዱንግን አጽም በክብር አስቀምጠው ምን ያህል ለቱሪዝም እየተጠቀሙበት እንደሆነ  ለማወቅ ቻይና መሄድ አይጠበቅብንም፡፡ ወይም ቻይናዊ ሆነን እንድንውለድ አንገደድም፡፡ በምን ያህል ጥበቃና በምን ያህል ክብር ምን ያህል ገንዘብ እየዛቁበት እንደሆነ ለመረዳት ቀላል ነው፡፡ ቻይናውያን መሪያቸውንም አክብረው በቱሪዝም እያደጉ ይገኛሉ፡፡ እኛ ይህን እንዳናደርግ ማን ዓይናችንን ጋረደው? መልካም ነገር ለማሰብ ይደክመናል ልበል?

በቅኝ ገዥዎች ያልተንበረከክን ብለን ስንፎክር እስኪ የታለ መታሰቢያቸው? የታል የአጽማቸው ማደሪያ? ብንባል ምን እንመልስ ይሆን? ኦባማ እንደመጣ የጥቁር አርበኛ አባቶችን አጽም መጎብኘት እፈልጋለሁ ቢል ደፍረን እናስጎበኘው ነበር?  ለዚህ ነገር ተወቃሹ ማነው የሚለው አያሳስባችሁ፡፡ ሁላችንም ራሳችንን መጠየቅ  ቀላሉ ዘዴ ነው፡፡ የትኛው መምህር ነው ለተማሪዎቹ ታሪክን በአግባቡ የሚያስተምረው? የትኛውስ ተማሪ ነው ስለአገሩ ለማወቅ የሚፈልገው? የትኛው ወላጅ ነው ልጁ ማንነቱን አውቆ እንዲያድገለት የሚፈልገው? የትኛው ልማታዊ ባለሀብት ነው ቱሪዝም ላይ ገንዘቡን ማፍሰስ የሚፈልገው? ማንኛው ነጋዴ ነው ለአገሩና ለዜጋው የሚጨነቀው? የትኛው ብሔረሰብ ነው ኢትዮጵያዊነቱን ወዶ የሚንቆለጳጵሰው? የትኛው ባለሥልጣን ነው ለትውልድ የሚያወርሰውን ታሪክ ሠርቶ ማለፍ የሚፈልገው? ሁላችንም ራሳችንን እንፈትሽ፡፡

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እየገለጽን፣ በኢሜይል አድራሻቸው [email protected] ማግኘት ይቻላል፡፡  

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የንብረት ማስመለስ ረቂቅ አዋጅና የሚስተጋቡ ሥጋቶች

ከሰሞኑ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የቀረበው የንብረት ማስመለስ ረቂቅ...

የመጨረሻ የተባለው የንግድ ምክር ቤቱ ምርጫና የሚኒስቴሩ ውሳኔ

በአገር አቀፍ ደረጃ ደረጃ የንግድ ኅብረተሰቡን በመወከል የሚጠቀሰው የኢትዮጵያ...

ሚስጥሩ!

ጉዞ ከካዛንቺስ ወደ ስድስት ኪሎ፡፡ የጥንቶቹ አራዶች መናኸሪያ ወዘናዋ...