Sunday, June 23, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ልናገርየኢሕአዴግን ጆሮ የደፈነው ማነው?….

የኢሕአዴግን ጆሮ የደፈነው ማነው?….

ቀን:

በእንደርታ መስፍን

ስህተትን “ስህተት ነው!!!…….” ብሎ መናገር ስህተት የሆነበት ስህተት፡፡ ሕዝቡ ኢሕአዴግን ሲመርጥ የተጀመረውን የልማት አቅጣጫ እንዲያስቀጥል “አደራ!!!…..” እያለ እጅግ እየተንሰራፋ ያለውን የመልካም አስተዳድር፣ የፍትሕና የሙስና ችግሮችን እንዲፈታ በማስጠንቀቅም ጭምር ነው፡፡

እነዚህን ችግሮች ለመፍታት የአመራር ቆራጥነት ይጠይቃል፡፡ ለዚህም ነው ሕዝቡ ሰሞኑን የኢሕአዴግና አባል ድርጅቶቹን ጉባዔዎች በንቃት ሲከታተል የሰነበተው፡፡ የአመራር ለውጥ በማድረግ የተጠናከረ የፀረ ሙስና ዘመቻ ይጀምራል በሚል ተስፋ፡፡

ጉባዔዎቹ ሲጀመሩ ጠንከር ያሉ ትችቶች ይቀርቡ ስለነበር ለእነዚህ ህፀፆች ደግሞ በዋነኝነት የድርጅቱንና የክልል አመራሮችን የሚመለከቱ ስለነበሩ አንዳንዶቹ “ቆራጦች” “ለዚህ ሁሉ ስህተት እኔ ኃላፊነቱን እወስዳለሁ!!!…..” እያሉ የስንብት ደብዳቤ ያቀርባሉ የሚል ግምትም ነበረኝ፡፡ 

በጉባዔዎቹ የአቶ መለስ ዜናዊንና የአቶ ዓለማየሁ አቶምሳን ስም እየጠሩ “የሰማዕታቶቻችንን ቃል እንጠብቃለን!!!…..” የሚሉ ፉከራዎችን ስሰማ በቃ!!!…… ኢሕአዴግ አዲስ የጄት ሞተር ተገጥሞለት የህዳሴውን ጎዞ በተሻለ ፍጥነት የሚያስቀጥለው መስሎኝ ብዙ ጓጓሁ፡፡

ቆይ ቆይ!!!….. እዚሁ ጄት ላይ እንደተሳፈርን አየር ላይ ፍሬን እንያዝና አየር ላይ እንውረድ፡፡ እናም አየር ላይ ያሉ ጥያቄዎችን ላንሳ፡፡

እኔ የምለው የታጋይ ዓለማየሁ አቶምሳ አሟሟትን በተመለከተ የተሟላ መረጃ መቼ እንጠብቅ?……እነዚያ ጀግኖች ሰማዕታት ውድ ሕይወታቸውን አሳልፈው የሰጡት የመልካም አስተዳደር፣ ፍትሕና የሙስና ችግሮች በደርግ መቃብር ላይ እንዲያብቡ አይደለም፡፡ ወደ ጄታችን እንመለስ፡፡ ወደ ጉባዔዎቹ፡፡ በአብዛኛው ያሉት ችግሮች የተንፀባረቁባቸው “አንጀቴ ቅቤ ጠጣ!!!…..” የሚያስብሉ ጉባዔዎች ነበሩ፡፡ በተለይ የሕወሓት ጉባዔ ጠንከርና ረዘም ያለ ጊዜ የወሰደ ነበረ፡፡ የጉባዔዎቹ ማጠቃለያ ላይ ቀድሞ የነበሩትን አመራሮች በአብዛኛው እንዲቀጥሉ አድርገው እንደተለመደው፣ “ችግሮቹን ከሕዝባችን ጋር እንፈታለን!!!……” በሚል ዲስኩር ተዘጉ፡፡ ሕዝብ የአመራር ለውጥ እንደፈለገ እየገለጸ ድርጅቱ ባለህበት እርገጥን ለምን መረጠ?………. በተለይም የሕወሓቱ መረር ያለ ጉባዔ መደምደሚያው ያለውን አመራር በማስቀጠል እንዴት ሊጠናቀቅ ቻለ?……..የሕወሓት ጠቅላላ ጉባዔ ማዕከላዊ ኮሚቴ ሲመርጥ ያስተላለፈውን የሕዝቡን መልዕክት ማዕከላዊ ኮሚቴው ለምን ሰምቶ እንዳልሰማ ሆኖ ከሕዝብ ፍላጎት ጀርባ መቆምን ከጀለ?……..ብዙ ብዙ የታጀሉ ጥያቄዎችን መምዘዝ ይቻላል፡፡

 ጥቂት የማይባሉ ወዳጆቼ የጉባዔዎቹን አካሄድ በማየት እንደኔው አዳዲስ አመራሮችን ለማየት እንደጓጉ በሶሻል ሚዲያ ሲገልጹ ተመልክቻለሁ፡፡ ትርጉም ያለው የአመራር ለውጥ አለመደረጉን እየተመለከቱም “ጉባዔዎቻችን በድል ተጠናቀቁ!!!……” ምናምን እያሉ ሲያራግቡ አስተውያለሁ፡፡ የድል ትርጉሙ ተቀይሮ ከሆነ ሹክ በሉኝማ፡፡ ደርግ ወደ ሥልጣን ሊወጣ አካባቢ ነው አሉ፡፡ “ኃይለ ሥላሴ ወረዱ!!!……… አልወረዱም!!! ………..” ውዥንብር ነበረ፡፡ ሕዝብ በመንገድ ግራና ቀኝ ቆሟል፡፡ ያኔ እንደ ዘንድሮ ፊሽካ አልነበረም፡፡ (ቆዩኝማ!!!!…….. “ እነዚያ ፊሽካ ነፋን!!!….” እያሉ ሆዳችንን የነፉን የት ደረሱ?……….) አንዱ ጥሩንባ እየነፋ ከች አለ፡፡ “ጡጡጡጥ………ኃይለ ሥላሴ ከሥልጣን ወርዷል!!!!……..” እልልታው ቀለጠ፡፡ “ እልልል…………..ይኼ ሌባ!!!!…….” ንጉሡ የሆነ የወጥ ሌባ ነገር ተደርገው ተወገዙ!!!….. ጥቂት ቆይቶ ሌላ አንጋች ያስከተለ ግርማ ሞገሱ የሚያስፈራ ሰው በፈረስ ተቀምጦ ከተፍ አለ፡፡ “………ንጉሣችን ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ በዙፋናቸው ላይ ይገኛሉ!!!……..” እሱም ምታ ነጋሪት አለ፡፡

ሌላ እልልታ!!!………“እልልል………..ፀሐዩ ንጉሣችን ለዘለዓለም ይንገሥልን!!!! እልል……..”ቂቂቂቂቂቂቂ………….ምን ለማለት ፈልጌ ነው በቃ ተግባብተናል አይደል?!!!…….. ወደ ነፈሰበት መወዛወዝ ትዝብት ላይ ይጥላል፡፡ ከአንደኛው ወዳጄ ጋር ስንነጋገር፣ “ሁሉም ምርጫ የተከናወነው በፕሮሲጀሩ (በሥርዓቱ) መሠረት በመሆኑ ስህተት የለም!!!…….” እያለ ሲሞግተኝ ነበር፡፡ እኔ የምለው ወዳጄ!!!…… ‹ፕሮሲጀር› የሚባል የሕዝብ አለቃ አለ እንዴ?…… መኖሪያው የት እንደሆነ ጠቁሙኝማ፡፡ በሥነ ሥርዓቱ ውስጥ የሕዝብን ጥያቄ መመለስ አይቻልም?……..ለእኔ ምንም ምክንያትን አድርጎ ለሕዝብ ድምፅ ጆሮ አለመስጠት የስህተቶች ሁሉ ትልቁ ስህተት ነው፡፡

ሕዝቡ በመሠረታዊነት በሚያነሳቸው ችግሮች ላይ ለውጥ እንዲያመጡ የዓመታት ሥልጣን የተሰጣቸው ግን ምንም ተስፋ ያላሳዩ አመራሮች እንዲቀየሩ ከሕዝብ ይቀርብ የነበረው ጥያቄ ለምን በድርጅቱ ችላ ተባለ?………የሕዝቡ ፍላጎት ስህተት ነው!!!….. ከተባለ  የኢሕአዴግ አመራር የሚያውቀው ሕዝቡ ጋ ያልደረሰ መረጃ አለ ማለት ነው፡፡ ይኼን የማሳወቅ ኃላፊነት ድርጅቱ አለበት፡፡ ሕዝቡ በሚያውቃቸው መረጃዎች ተመርኩዞ የሚያነሳቸውን ጥያቄዎች ውሳኔዎቹን ግን ኢሕአዴግ የማክበር ግዴታ አለበት፡፡ አለቃው ሕዝብ ነውና!!!………ደርግ ሕዝብን አያዳምጥም ነበር፡፡ ደርጎች የራሳቸውን ሐሳብ የሕዝብ ፍላጎት አድርገው ራሳቸውን እያዳመጡ መጃጃላቸውን ያዩ ጥቂት ቆራጥ የሕዝብ ልጆች የሚሊዮኖችን ልብ ይዘው ጫካ ሲገቡ፣ ሕዝቡን መስለው በሕዝቡ ታቅፈው ጥቂት ግን እልፍ ሆነው ስለኖሩ የማይቻል የሚመስለውን ገርሰሰው ለድል በቁ፡፡ ዛሬስ?!!!!……..ኢሕአዴግ ስህተቶቹን መጠቆም ከአንድ ጠንካራ ደጋፊ አባል የሚጠበቅ ነው፡፡ በጭፍን መደገፍ ኢሕአዴግን ወደ ገደል እንደመገፍተር ይቆጠራል፡፡  

እኔ በግሌ ኢሕአዴግን እደግፋለሁ፡፡ እደግፋለሁ!!!….ማለት ግን ስህተት ተሠርቷል!!!….ብዬ ሳምን አልጠቁምም!!!….. በጭፍን ትክክለኛ ሥራ ነው!!!…. ብዬ እከራከራለሁ ማለት አይደለም፡፡ መተካካት በመርህ ደረጃ ትክክል ነው፡፡ ብቃት ያላቸው አመራሮች ሳይዘጋጁ በመተካካት!!!…… ሰበብ ነባሮቹ ታጋይ አመራሮች ቦታ እንዲለቁ መደረጋቸው ግን ስህተት ነበር ብዬ አምናለሁ፡፡ ተተኪ በብዛትና በጥራት አለማፍራታቸው የሚወቀሱበት ድክመታቸው ቢሆንም፡፡ ትናንት ጥቂቶች በበረሃ የትጥቅ ትግልና ነፃ በነበሩ አካባቢዎች ሕዝብን በማስተዳደር ተግባራት ጥራት ያለው የአመራር መተካካት ነበረ፡፡ ለድሉም ጉልህ አስተዋፅኦ አበርክቷል፡፡ ዛሬ ታዲያ ለምን አልተቻለም?……..ትናንት አመራርነት ለመስዋዕትነት መታጨት ነበረ፡፡ ለሕዝብ ነፃነት ሲል ደሙን ለማፍሰስ ዝግጁ የነበረ አመራር የነበረው ድርጅት ዛሬ የመልካም አስተዳደር፣ የፍትሕና የሙስና ችግሮችን ለመታገል ምነው አቅም እንደ ቁምጣ አጠረው?…….ኢሕአዴግ በጉባዔዎቹ እነዚህ ችግሮቼ ናቸው ብሎ በወፍራም ቀለም ለመጻፍና ችግሮቹን እንቀርፋለን!!!…. ምናምን የሚሉ ባለ ምናምን ነጥቦች የአቋም መግለጫ ለማውጣት ችግር የለበትም፡፡ ከዚያም እስከ ቀጣዩ ጉባዔ ድረስ ችግሮቹ ችግር ሆነው ይቀጥላሉ፡፡ በሌላ ጉባዔ ታሪክ ይደገማል፡፡

አዳዲስ አመራሮች በብዛት በጥራት ለምን አይታዩም?…….ኢሕአዴግ አሁን ቆም ብሎ ውስጣዊ ችግሮቹን የሚፈትሽበት ጊዜ ይመስለኛል፡፡ አንድ ብቃት ያለው ግለሰብ ከሥር ጀምሮ አቅሙን እያጎለበተና እያሳየ አገር ወደ መምራት ለመምጣት የሚያስችለው አሠራር በድርጅቱ ይኖር ይሆን?…….. “አለ!!!……” የሚል መልስ ከተሰጠ ታዲያ ሲስተሙ ላይ ማን ነው ችግር የሚፈጥረው?……….አንድ ግለሰብ ከቀበሌ የኢሕአዴግ ሴል አባልነት ጀምሮ የተለያዩ እርከኖችን ለማለፍ ቢያስብ በስመ የኢሕአዴግ አባልነት የግል ጥቅማቸውን ከሚያሳድዱ በሆዳቸው የሚያስቡ ካድሬዎች ጋር ይላተማል፡፡ የሚያየውን የመልካም አስተዳድርና የሙሰኝነት ችግርን አንስቶ ከተቻቸው በቃ!!!…… እሱ ፀረ ልማት ነው፡፡ “ፀረ ሕዝብ!!!….” የሚል ታርጋ ተለጥፎለት ይኮረኮማል፡፡ ተስፋ ቆርጦ አርፎ ይቀመጣል፣ ወይም ተገፍቶ ወደ ተቃዋሚው ጎራ ይቀላቀላል፡፡ ግለሰቡ አሠላለፉን በተቃዋሚነት ሲቀይር “እኛ ቀድመን አውቀነዋል!!!…….” ዓይነት ወሬ ያሰራጫሉ፡፡ የበላያቸውን ዓመኔታ ለማግኘት ምንም ከማድረግ አይመለሱም፡፡

የሰማዕታትን አደራ እንደሚጠብቁ ለሕዝብ ቁርጠኛ አገልጋይ እንደሆኑ በየመድረኩ ይደሰኩራሉ፡፡ ሕዝብ እያማረሩ እየዋሉ “ኅብረተሰቡ በመሰተንግዶው መሻሻል ደስታውን እየገለጸ ነው!!!……” ዓይነት ሪፖርት ለበላይ እርከን ይልካሉ፡፡ የበላይ አለቆቻቸውን ስሜት የሚገዛ የተፈበረከ ሪፖርት ያቀርባሉ፡፡ እላይ ያለውም ወረድ ብሎ ሪፖርቱን ለማረጋገጥ ራሱም በችግሮች የተተበተበ “በእከክልኝ ልከክልህ!!!…….” የተከረቸመ በመሆኑ ሪፖርቱን ማጣፈጫ ቅመም ጨምሮበት ከበላዩ ወዳለው እርከን ይልካል፡፡

አንድ ከሥር ያለ ፈጻሚ አካል ከበላይ የሚመጣ መመርያ ስህተትም ቢኖርበት “ይስተካከል!!!…….” ብሎ ለመጠየቅ ወኔው የለውም፡፡ መመርያውን ከነችግሮቹ ሲፈጽም ኅብረተሰቡ ቅሬታ ቢያነሳ ምን ቸገረው?……. እሱን የሚያስጨንቀው በዚህ መመርያ ተገን አድርጎ ደሃውን ኅብረተሰብ እያስለቀሰ የሚሰበስበው ገንዘብ ብዛት ነው፡፡ በደሙ ደርግን በጣለው ሕዝብ ላይ “በእኔ አውቅልሀለሁ!!!…..” ይጀነናል፡፡ ድርጅቱ ከሕዝቡ ቢነጠል ምን ገዶት?!!!……..ኧረ ምንም!!!!………… በግሉ ችግር የሚፈጠርበት ከመሰለው ገንዘቡን ያሸሽና ወደ ውጭ ይኮበልላል፡፡ በኢሕአዴግ ውስጥ ለሕዝብ ጥቅም ሲታገል እንደቆየና ከአቅሙ በላይ ሆኖበት እንደሸሸ ለፅንፈኛው ዳያስፖራ በመግለጽ “ጀግና!!!….” የሚል ማዕረግ ተሰጥቶት ሌላ የፖለቲካ ሕይወት ቁማር መጫወት ይጀምራል፡፡     

አዳዲስ አመራሮችን በጥራት አፍርቶ ለውጥ ባለመምጣቱ ኢሕአዴግን ስንተቸው አንዳንዶች ለምን ይበሳጫሉ?….. አንዳንዶችስ ልጆች ሆነን ከትምህርት ቤት ጓደኞቻችን ጋር ስንጣላ “ሰኔ 30 አገኝሀለሁ!!!….” እያልን እንደምናቅራራው ለምን ጥቃት እንደሚፈጽሙ በአደባባይ ይዝታሉ?……..

አዎ!!!….. የአመራር ለውጥ ለእነሱ ህልውናም አስጊ ነው፡፡ የለውጥ አለመኖር ዕፎይታ ሰጥቷቸዋል፡፡ ይኼ ጉዳይ ሲነሳ በሽታቸው ያገረሻል፡፡ ከአንዱ ጭፍን ካድሬ ጋር ስንወያይ፣ “ስደት የሕገወጥ ደላሎችና የኅብረተሰቡ ዕድገቱን የተከተለ ፍላጎት ውጤት ነው!!!……” አለኝ፡፡ እናም ጉንጭ አልፋ ክርክር ገጠምን፡፡

ክልሎች ምን ያህል ለኢንቨስትመንት ክፍት ናቸው?……የሥራ ዕድሎች እንዲፈጠሩ ምን ያህል ያበረታታሉ?……. የሕገወጥ ደላሎች አስተዋፅኦ እንደተጠበቀ ሆኖ በሥራ ፈጠራና ኢንቨስትመንት ዙርያ የመስተዳድር መዋቅሮች ችግር ለምን አልተጠቀሰም?…… ጥያቄዎቼን ለመመለስ አልፈለገም ወይም አልቻለም፡፡ እኔም ግልምጫውን አልቻልኩትምና ክርክሬን አቆምኩ፡፡ እሱ በልቶ በጠገበው እኔ በባዶ ሆዴ እንዳገሳለት ይፈልጋል፡፡

በመጨረሻም “ስደቱ ዕድገትን ተከትሎ የመጣ ነው!!!……” ያለኝ ትክክል እንደሆነ ተንትኜ አስረዳሁት፡፡ ላልገባቸው ፈትፍቶ እንዲያጎርሳቸውና እንዲገባቸው፡፡ ወዳጄ!!!……. አንተ ልክ ነህ፡፡ ሰው በልቶ ሲጠግብ ምግቡ እንዲዋሀድለት ወክ ማድረግ ይፈልጋል፡፡ ብዙ ስለሚበላ ብዙ መንገድ የእግር ጉዞ ያደርጋል፡፡ ስለዚህ የኢትዮጵያ መሬት ለወክ ስለማይበቃው ድንበር አልፎ ቢሄድ ይኼ ስደት ሊባል አይችልም፡፡ ረጅም ወክ ነው፡፡ ጥጋቡን ተከትሎ አድቬንቸር ለመሞከር በማሰብ በጀልባ ወደ ዓረብ አገሮችና  አውሮፓ ለመግባት ጉዞ የሚያደርጉ በዝተዋል፡፡ በበረሃዎች አድካሚ የእግር ጎዞ ማድረግ በባህር ከሻርክ ጋር መታገልም የአድቬንቸሩ አካል ነው፡፡ አንተ ልክ ነህ ልበልህና እስቲ ደስ ይበልህ፡፡ ኢሕአዴግ ሆይ!!!…. ዛሬም አልረፈደም፡፡ አመራር ላይ መሠረታዊ ለውጥ ሳይመጣ በጉባዔ የአቋም መግለጫ ጋጋታ የሚፈታ ችግር የለም፡፡ ከላይ አመራር ጀምሮ በጠንካራ ግምገማ ለውጥ ያስፈልጋል፡፡ አዳዲስ ተተኪ አመራሮች በማፍራት ላይ ትኩረት የሚጠይቅ ሥራ መሠራት አለበት፡፡  የሚቀርቡትን ሪፖርቶች እውነተኛነት ለማረጋገጥ ወደ ሕዝቡ ወርዶ መጠየቅ  ኑሮውን ኑሮ ችግሩን መቅመስን ይጠይቃል፡፡

ድሮ ድሮ ነው አሉ  ብልህ መሪዎች “እረኛ ምን አለ?!!!…..” ይሉ ነበር አሉ፡፡ በዘመናችን ደግሞ “ካድሬ ምን አለ?………” ይባላል አሉ፡፡ “አሉ!!!……” ነው፡፡ አሉን አሉ ማለት ራሱ “አሉ!!!…..” ነው፡፡ ኢሕአዴግ ሕዝብን እንዳያዳምጥ ጆሮው ላይ የተቀመጡትን ሆዳም ካድሬዎቹን አሽቀንጥሮ ይጣል፡፡ ምርጥ ጥቂቶች ካሉት ይበቃል፡፡ አለበለዚያ የጉባዔዎቹ የግለት ውጤት በዜሮ እንደተባዛ ይቀጥላል፡፡ የሕዝቡም ምሬት እስከ አንድ ቀን ይቀጥላል፡፡ እስከ አንድ ቀን!!!!

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እየገለጽን፣ ጸሐፊውን በኢሜይል አድራሻቸው [email protected] ማግኘት ይቻላል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

አስጨናቂው የኑሮ ውድነት ወዴት እያመራ ነው?

ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ የኑሮ ውድነት እንደ አገር ከባድ ፈተና...

‹‹ወላድ ላማቸውን አርደው ከደኸዩት ወንድማማቾች›› ሁሉም ይማር

በንጉሥ ወዳጅነው   የዕለቱን ጽሑፍ በአንድ አንጋፋ አባት ወግ ልጀምር፡፡ ‹‹የአንድ...

የመጋቢቱ ለውጥና ፈተናዎቹ

በታደሰ ሻንቆ ሀ) ችኩሎችና ገታሮች፣ መፈናቀልና ሞትን ያነገሡበት ጊዜ እላይ ...

ጥራት ያለው አገልግሎት መስጠት የሚያስችል ሥርዓት ሳይዘረጉ አገልግሎት ለመስጠት መነሳት ስህተት ነው!

በተለያዩ የመንግሥትና የግል ተቋማት ውስጥ ተገልጋዮች በከፈሉት ልክ የሚፈልጉትን...