Monday, July 22, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

የተመረጡ ፅሑፎች

እንዲህማ አይጨፈርብንም!

ጉዞ ከሽሮሜዳ ወደ ሜክሲኮ፡፡ በወርኃ ነሐሴ መገባደጃ የጥንቱ ሽሮሜዳ እንጦጦ ተራራ ሥር መሽጎ በጠዋት በረሃ ሆኗል፡፡ ያ የድሮ አጥንት ድረስ የሚሰማ ቅዝቃዜ ጠፍቶ ወበቁ ጃኬት ወይም ኮት ያስወልቃል፡፡ ገና በማለዳው ላባቸውን እያንቸረፈፉ ጎዳናው ላይ የሚያዘግሙት ወጣቶች ሳይቀሩ ‹‹ድሮ በዚህ ጊዜ…›› ቢባሉ ቅዥት እንደሚመስላቸው አያጠራጥርም፡፡ ከላይ ታች የሚለው መንገደኛ ያለፈውን ዘመን ከአሁኑ ጋር እያነፃፀረ ሲያዘግም፣ ከአየር ንብረት ለውጡ ባልተናነሰ የሰው ልጅ ባህሪ ለውጥ እንደሚያሳስበው ፊቱ ላይ ያሳብቃል፡፡ ዛሬ ይዘንባል ሲባል የከረረ ፀሐይ ሲወጣ፣ የፀሐይም መክረር አናትን እየበሳ ድንገት ያልታሰበ ዝናብ ሲጥል፣ ደህና የተባለው ሰው አይሆኑ ሆኖ አጓጉል ሲፈጽም ይስተዋላል፡፡ በመንገዱ ላይ የሚታየው የአየርና የሰው ልጅ መለዋወጥ ልዩ ጥናት የሚያስፈልገው ክስተት እየሆነ ሁሉም ይጓዝበታል፡፡

ታክሲ መያዣው ቦታ ላይ ቀጥ ብለው ተሠልፈው ለጉዞ ከተዘጋጁት መሀል አንዷ፣ ‹‹ዝናቡ ጠብ አልል ብሎ ፀሐይ ያሳርረናል፡፡ ታክሲው ቶሎ መጥቶ እንዳንሳፈር እጥረቱ ያጉላላናል፡፡ ሥራ አረፈድሽ የሚለኝ አለቃዬ አሳሬን ያበላኛል፡፡ እንዲያው የቸገረ ነገር…›› እያለች ስታማርር የሞተሩ ጩኸት ከበርበሬ ወፍጮ የማይተናነስ አሮጌ ሚኒባስ ከች አለ፡፡ በአስተናባሪው አማካይነት ገብተን ቦታችንን ያዝን፡፡ ታክሲው ከአሁን አሁን ይንቀሳቀሳል ብንልም ሾፌሩ ከምኔው የት እንደገባ አልታወቀም፡፡ ምን ሾፌሩ ብቻ ወያላውም ጠፍቷል፡፡ ‹‹ወይ ዘንድሮ? ወደ ላይ እያንጋጠጥን እንጮኃለን እንጂ፣ ትልቅ ችግር ያለው እኮ እታች ነው፡፡ እዚህ አጠገባችን…›› በማለት አንዱ የዕለቱን የታክሲ ‹ቀደዳ› ሲጀምር የቸኮሉ ተሳፋሪዎች አጉተመተሙ፡፡ ድምፃቸው እንደ ንብ መንጋ ‹እውውው› እያለ ምን እንደሚሉ ባይሰማም እያማረሩ መሆናቸውን በቀላሉ መረዳት ይቻላል፡፡

ከየት እንደመጣ ያልታወቀው ከተፎ ወያላ ተንደርድሮ መጥቶ በሩን ዘግቶ ገባ፡፡ ብብቱ ሥር የሸጎጠውን በፌስታል የተጠቀለለ ነገር አውጥቶ የራሱ መቀመጫ ሥር ሲሸጉጥ፣ ሾፌሩም በሩን ብርግዶ ገብቶ ሞተሩን ቀሰቀሰው፡፡ እንደ ወፍጮ የሚንተከተከው ሞተር ታክሲውን ካርገፈገፈው በኋላ ጉዞ ተጀመረ፡፡ ‹‹ስማ እባክህ? እኛ የሥራ ሰዓት ረፍዶብናል አንተ መቼም ቢሆን የማይረካ ሱስህን ለመሸመት ታቆመናለህ?›› ብሎ አንድ ጎልማሳ ወያላው ላይ እፈጠጠበት፡፡ ወያላውም አፍጥጦ እያየው፣ ‹‹እንዴት ነው ነገሩ? ኧረ ሰውዬው በጠዋት ደህና ነገር ተናገር፡፡ ራስህ ተነጅሰህ ሌላውን አትነጅስ…›› እያለ የሸጎጠውን ፌስታል አውጥቶ ከውስጡ አፈስ አድርጎ አፉ ውስጥ መሰገው፡፡ ‹‹ኧከከከ…አሁንማ ከአንተ ጋር ማን ይነጋገራል? ሰው በጠዋት አፉን በቁርስ ያሟሻል እንጂ ይኼንን አሀዱ ብሎ ይጀምራል?›› ብሎ ጎልማሳው እጁን ሲያጣፋ በወያላው ተስፋ መቁረጡ ያስታውቅ ነበር፡፡ ደግነቱ ወያላው መልስም አልሰጠው፡፡

ወያላው ከሸጎጠበት ያወጣውን ለስላሳ አፉ ውስጥ የከተተውን ነገር እያወራረደበት ‹‹ሒሳብ ወጣ ወጣ›› ማለት ሲጀምር ሁሉም እጁን ወደ ኪሱና ወደ ቦርሳው ላከ፡፡ ለጊዜው ዝምታ ሰፈነ፡፡ ዝምታው አልቆየም፡፡ እንደ ብራ መብረቅ የሚያስተጋባ የሞባይል ስልክ ጩኸት ሲሰማ የስልኩ ባለቤት ሦስተኛ ወንበር ላይ ተቀምጦ፣ ‹‹አንተ የማትረባ ሰይጣን!›› ብሎ ሲያንባርቅ ዞር ዞር ብለን አየነው፡፡ ሰውየው ከድምፁ ሻካራነት በተጨማሪ እንደ እድር ጥሩምባ ነፊ እየጮኸ ስለሚያወራ ከታክሲው አሮጌ ሞተር ጋር ተጋግዞ ጆሯችንን አደነቆረው፡፡ ‹‹በቀደም ዕለት የሰጠሁህን ሳትመልስ እንደገና 100 ብር አምጣ ስትለኝ አታፍርም? በል በል ሁለተኛ እንዳትደውል…›› ብሎ ሰልኩን ሲዘጋው አተነፋፈሱ የታመመ ፈረስ ይመስል ነበር፡፡ ከአንዳንዱ ሰው ባህሪ የበለጠ አፈጣጠሩ ራሱ ግርም ያደርጋል፡፡ ‹‹ምን ዓይነቱ ነው ይኼ ደግሞ? 100 ብር ቁም ነገር ሆኖበት ነው እንዴ እንዲህ የሚንጨረጨረው?›› ሲል ወያላው ሰማነው፡፡ ደግነቱ ሰውዬው አልሰማውም፡፡

ከመጨረሻው ወንበር ብሶት ይሰማል፡፡ የብሶቱን አቅጣጫ ተከትለን ጆራችንን ስንቀስር፣ ‹‹እኔ እኮ የሚገርመኝ ሲነገራቸው ከርመው ይቆዩና ደርሶ አዲስ ይመስል ሕዝብ ሕዝብ ማለታቸው ነው፡፡ ሕዝብ እኮ የማያውቀው፣ የማይሰማውና የማይታዘበው ነገር የለም…›› ትላለች አንዷ ኮረዳ፡፡ አጠገቧ የተቀመጠው ሸበላ፣ ‹‹ሕዝብ ቀጣሪ እነሱ ደግሞ ተቀጣሪ መሆናቸውን ረስተው እንደፈለጉ ሲጋልቡት ከርመው ይቅርታ ገለመሌ ማለታቸውስ አይገርምም?›› እያለ ሲነጫነጭ ስለምን እንደሚያወራ ግልጽ ባይሆንም፣ ያው የፈረደበት መንግሥት እየተከተከተ መሆኑ የገባን መስለናል፡፡ ባይመስለንስ ምን ይለናል? ‹‹ሕዝብ በስሙ እየተነገደበት የፖለቲከኞች መቀለጃ መሆኑ አያናድድም?›› የሚል ድምፅ ቢሰማም ዝምታው ገነነ፡፡

ቆይቶ ግን ነገሩ የገባው የሚመስል ነገር ግን በጥበባዊ አገላለጽ ጨዋታ የጀመረ አንድ ጎልማሳ፣ ‹‹በአገራችን ደንበኛ ንጉሥ ነው የሚል አጉል ወሬ አለ፡፡ የትም ሂዱ ደንበኛ ንጉሥ ሳይሆን ገባር ሆኖ ነው የምታገኙት፡፡ መብራት ኃይል ቆጣሪ ለመጠየቅ ወይም የተቋረጠ ኃይል ለማስቀጠል ሂዱ አምጣ ነው፡፡ ውኃ ክፍል ሂዱ ያው አምጣ ነው፡፡ መንጃ ፈቃድ ለማውጣት ሂዱ በእጅ ካልሆነ አይሆንም ይባላል፡፡ የንግድ ፈቃድ ምዝገባ፣ የንግድ ምልክት ስያሜና የብቃት ምዝገባ ያው ነው፡፡ የግንባታ ፈቃድና ማዘጋጃ ቤታዊ አገልግሎት ጉቦ ነው፡፡ በየቦታው ስትሄዱ አምጡ ነው፡፡ አሁንማ ጅብ በቀን የተለቀቀ ይመስላችኋል…›› እያለ ሲንጨረጨር የድምፁ ማስገምገም ያንን አሮጌ የታክሲ ሞተር አስከነዳው፡፡ ‹‹ዝም ብለው ሕዝብ ሕዝብ ቢሉ ዋጋ የለውም፡፡ የሾሙትን ሳይቆጣጠሩ፣ ሳይገስፁና ሳይቀጡ በባዶ ሕዝብ ማለት ከንቱ ነው…›› አለ፡፡ አቤት የምሬት ብዛቱ?

‹‹መጥኔ ለዚህች አገር…›› የሚሉት መሀል  ወንበር ላይ የተቀመጡ አንዲት እናት ናቸው፡፡ አጠገባቸው የተቀመጠች ቀዘባ፣ ‹‹ምነው ማዘር?›› ስትላቸው፣ ‹‹ምነው ሸዋ አይገባሽም እንዴ? ነው ወይስ አጠገቤ ተቀምጠሽ በሐሳብ አሜሪካ ገብተሻል ሲሉ?›› ተሳፋሪዎች አውካኩ፡፡ ‹‹የዚህች አገር ችግር እኮ የሚጀምረው ከራሳችን ነው፡፡ እስቲ ሹማምንቱን እዩዋቸው፡፡ የእኛው አይደሉ?  ጠፍጥፎ የሠራቸው ማን ነው? ይኼው ኅብረተሰብ፡፡ ኅብረተሰባችን ለሐሳብ ልውጥጥና ለክርክር ግልጽ ነው ወይ? ይኼ ዓይነ አፋር ሕዝብ ችግሩን አምቆ፣ ብሶቱን ውጦ፣ ምሬቱን ደብቆ እየኖረ የደላው ሊመስል ይፈልጋል፡፡ ከእሱ ውስጥ የወጡት ደግሞ ችግር ሲፈጠር መፍትሔ ለመፈለግ ከመሯሯጥ ይልቅ ለመሸፋፈን ይጣደፋሉ፡፡ ሕዝቡ ቸግሮታል ሲባሉ ‹ዕድገቱ ያመጣው ነው› ይላሉ፡፡ አስተዳደራዊ በደል አላስኖረው ብሎታል ሲባሉ ‹በፊውዳልና በደርግ ጭቆና ሥር ኖሮ አይደል እንዴ?› ብለው ይሟገታሉ፡፡ ሹማምንቱን የፈጠራቸው ሕዝብ በእነሱ ተመልሶ ሲማረር ይገርመኛል…›› አሉ እማማ፡፡ በአነጋገራቸው የተገረመ የሚመስል ወጣት፣ ‹‹ሐርቫርድ ነበሩ እንዴ?›› ሲላቸው፣ ‹‹እባክህ ከእኛ የተረፈ ነው…›› ብለው ንግግራቸው ሲገቱ አጀብ ከማለት ሌላ ምን መባል ነበረበት?

ሾፌሩ ለወያላው፣ ‹‹የኢሕአዴግ ጠቅላላ ጉባዔ እዚህ ታክሲ ውስጥ ነው እንዴ የሚካሄደው?›› እያለ በማሾፍ ሲስቅ፣ ‹‹ኢሕአዴጎቹ ራቅ ብለው ስብሰባ ስለያዙ የእኛ ታክሲ ደግሞ ጊዜያዊ ስቱዲዮ ሆኖል፤›› አለው ወያላው፡፡ ሾፌሩ በኋላ ትዕይንቱ መመልከቻ መስተዋቱ እያጨነቆረ፣ ‹‹ቃለ ጉባዔ ብትይዝ እኮ ለማታ ቴሌቪዥን ዜና ሥርጭት ይጠቅም ነበረ፤›› እያለ ሲስቅ ወያላው፣ ‹‹ኧረ አሁንም በኤፍኤም ሬዲዮ የቀጥታ ሥርጭት ከታክሲያችን እየተደመጠ ነው፤›› እያለ አሾፈ፡፡ ይኼኔ አዛውንቷ፣ ‹‹አንቺ ምን አለብሽ፣ ሮብ ዓርብ የለብሽ….››ሲሉ ሰማናቸው፡፡ ‹‹አንተ ማነህ ወያላው! ስለአገር ጉዳይ በቁምነገር ሲወራ እናንተ የምትቀልዱት ለምን እንደሆነ ይገባሃል?›› ብለው ሲጠይቁት፣ ‹‹ማዘር ይንገሩኝ እስኪ ለምን ይሆን እባክዎ?›› በማለት ጥያቄ አቀረበላቸው፡፡ ‹‹ከዕለት ኑሮ በላይ አታስቡማ፡፡ ይመሻል ይነጋል የሚባል ከንቱ ኑሮ የምትመሩ እናንተ አይደላችሁ? ለአገር የሚያስብማ በረጂሙ አስቦ ለረጂሙ ጉዞ የሚሆን ነገር ያመቻቻል፡፡ የእናንተ ቢጤው ግን እዚያው በላች እዚያው ሞተች ዓይነት ነው …›› ሲሉ ሳቅ በሳቅ ሆንን፡፡

ወደ መዳረሻችን ተቃርበናል፡፡ ወያላው በነገር አርጩሜ ተገርፎ አርፎ ተቀምጧል፡፡ ሾፌሩ በአላየሁም አልሰማሁም ድምፁን አጥፍቷል፡፡ ከአዛውንቷ አጠገብ የተቀመጠችው ቀዘባ፣ ‹‹ማዘር ፖለቲከኛ ነበሩ እንዴ?›› አለቻቸው፡፡ ‹‹ሰማሽ ልጄ ካርል ማርክስ የሰው ልጅ ማኅበራዊ እንስሳ ነው ማለቱን አልሰማሽም?›› ሲሉ ደነገጥን፡፡ እንዴ? ካርል ማርክስ? በእኚህ አዛውንት አንደበት? አዛውንቷ እየሳቁ፣ ‹‹ባናርስም እናጠምዳለን አሉ፡፡ እስከ አንገታችን ባንነከርበትም እኛም አንድ ሰሞን ሶሻሊስት ነበርን፡፡ እንደነገሩም አንብበናል፡፡ አሁን የሚያናድደው እኮ ሳያነብ የሚተቸው ነው፡፡ ፌስቡክ ላይ አላያችሁም? በተለይ ሐበሻ የተጻፈለትን ሳያነብ የሰው ‹ኮሜንት› እያነበበ የሚተች? ‹ላይክ› እና ‹ሼር› የሚደረግ የማይለይ? ወይ አገሬ ኢትዮጵያ? ስንቶች ብራና ሠርተው፣ ቀለም አዘጋጅተው ስንትና ስንት ድርሳናት በጻፉበት አገር የሚያነብ ጠፋ …›› እያሉ ተብሰከሰኩ፡፡

‹‹ፓርላማ ሰብሰባ ላይ ጥቂቶች በፖሊሲ ጉዳይ ላይ የጦፈ ክርክር ሲያደርጉ፣ ብዙኃኑ እንቅልፋቸውን ይለጥጣሉ፡፡ በአገር መሠረታዊ ጉዳዮች ላይ ጥልቅ ጥናትና ምርምር ሳይደረግ ያልበሰሉ ጽሑፎች ይታተማሉ፡፡ አጓጉል ትንተናዎች ይሰጣሉ፡፡ ያለ በቂ ዕውቀት፣ የሥራ ልምድና ዝግጅት ሥልጣን ላይ ይወጣና ያዙኝ ልቀቁኝ ይባላል፡፡ ከዚያስ አስተዳደራዊ ጉድለት አለ ሲባል ስድብ ይጀመራል፡፡ እየተቧደኑ የሰረቁ ሌቦች አገር ሲዘርፉ ጩኸቱ ሲበረክት የሚገረፈው ሌላ ነው …›› እያሉ ቆይተው፣ ‹‹ይኼንን ሁሉ የሚያናግረኝ ፖለቲካ ሳይሆን ያገባኛል ባይነት ነው …›› ብለው ሳይጨርሱ ወያላው ‹ወራጅ› ብሎ አሰናበተን፡፡ እኛን አዛውንት አጅበን ከታክሲው ስናወርዳቸው፣ ‹‹ያገባኛል ባይነት በሌለበት ኅብረተሰብ ውስጥ ግልጽነትና ተጠያቂነት ኖረው አያውቁም፤›› አሉን፡፡ አንዱ ችኩል ወጣት፣ ‹‹እማማ አልገባኝም?›› ሲላቸው፣ ‹‹ይኼንን ቴሌቪዥን አላየህም? የሻዕቢያ ተላላኪዎች በስደተኝነት ስም ሲደነፉበት? የስንትና ስንት ወገኖቻችንን ደም የገበርንበትን የአገር አንድነት ተጋድሎ ሻዕቢያ በጓሮ በር ሲያራክስብን አላየህም? በወኪለቹ አማካይነት የመገንጠል ጦርነቱን 54ኛ ዓመት በገዛ ቴሌቪዥናችን እየደነፋ ሲያከብርበት አላየህም?›› ሲሉት፣ ‹‹እንዲህማ አይጨፈርብንም!›› በማለት ደነፋ፡፡ እኛም በሐዘን አንገታችንን እየነቀነቅን በየፊናችን ተበታተንን፡፡ መልካም ጉዞ!

Latest Posts

- Advertisement -

ወቅታዊ ፅሑፎች

ትኩስ ዜናዎች ለማግኘት