አቶ ጌታቸው እንግዳ፣ የዩኔስኮ ምክትል ዋና ዳይሬክተር
በነሐሴ ወር ከሚከበሩት በዓላት አንዱ በወሩ አጋማሽ በተለይ ሴቶች ጎልተው የሚታዩበት የአሸንዳ በዓል ነው፡፡ ዘንድሮም እንደ አምና በተለያዩ የትግራይ፣ የዋግ ሕምራ፣ የላስታና መሰል አካባቢዎች ተከብሯል፡፡ ነሐሴ 16 ቀን 2007 ዓ.ም. በተለይ በመቐለ እና በዓብይ ዓዲ ከተሞች በአደባባይ ሲከበር፣ በክብር እንግድነት የተባበሩት መንግሥታት የትምህርት የሳይንስና የባህል ድርጅት (ዩኔስኮ) ምክትል ዋና ዳይሬክተር ኢትዮጵያዊው አቶ ጌታቸው እንግዳ ተገኝተው ነበር፡፡ በሁለቱም ከተሞች ባደረጉት ንግግርም የተመሠረተበትን 70ኛ ዓመቱን ለሚያከብረው ዩኔስኮ የአሸንዳ በዓል ልዩ ትርጉም እንደሚኖረው በምክንያትነት ያብራሩት፣ ‹‹የጾታ እኩልነትን ማረጋገጥና የአፍሪካ አህጉርን መደገፍ ድርጅቱ ቅድሚያ የሚሰጣቸው የትኩረት አቅጣጫ በመሆናቸው ነው፤›› በማለት ነበር፡፡ የአሸንዳ በዓል በዩኔስኮ የሰው ልጆችን ድንቅ የባህል ቅርስ በሚወክል የምዝገባ ሰነድ ውስጥ ተመዝግቦ ለማየት የየበኩላችንን ጥረት ማድረግ ይኖርብናል ያሉትን የአቶ ጌታቸው የተጣበበ ጊዜያቸውን በመሻማት ሔኖክ ያሬድ ከእርሳቸው ጋር ለአፍታ ቆይታ አድርጓል፡፡ አዲስ አበባ ከተማ ሽሮ ሜዳ ተወልደው ያደጉት አቶ ጌታቸው የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርታቸው በአመሀ ደስታ፣ ሁለተኛ ደረጃን በተፈሪ መኩንን ትምህርት ቤቶች ተከታትለዋል፡፡ በቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ዩኒቨርሲቲ አንድ ዓመት ከተማሩ በኋላ በተፈጠረው ረብሻ ከአገር ከወጡ 40 ዓመት አስቆጥረዋል፡፡ ገጸ ታሪካቸው እንደሚያሳየው፣ የማስትሬት (ኤምቢኤ) ዲግሪያቸውን ከለንደን ሲቲ ዩኒቨርሲቲ በተለይ በኢንተርናሽናል ባንኪንግና ፋይናንስ ላይ በመመሥረት ሲያገኙ፣ የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን (ቢኤ) ከማንችስተር ዩኒቨርሲቲ በኢኮኖሚክስ በማዕረግ አግኝተዋል፡፡ ቻርተርድ አካውንታንትም ናቸው፡፡ በሥራው ዓለም ዩኔስኮን በግንቦት 1996 ዓ.ም. ከመቀላቀላቸው በፊት በናይሮቢ (ኬንያ) የዓለም አቀፉ የቁም እንስሳት ምርምር ተቋም (ኢልሪ) የፋይናንስ፣ የሰው ሀብትና አስተዳደር ዳይሬክተር የነበሩ ሲሆን፣ በሮም (ጣሊያን) የተባበሩት መንግሥታት የእርሻ ልማት ዓለም አቀፍ ፈንድ (ኢፋድ) በኃላፊነት ሠርተዋል፡፡ ወደ ፓሪስ (ፈረንሣይ) የዩኔስኮ መቀመጫ ከዘለቁ 11 ዓመታት ያስቆጠሩት አቶ ጌታቸው፣ የመጀመሪያውን ስድስት ዓመት የሒሳብና የአስተዳደር ኃላፊ በመሆን ካገለገሉ በኋላ ምክትል ዋና ዳይሬክተርነቱን ከተረከቡ አምስት ዓመት ሞልቷቸዋል፡፡ ‹‹የሚቀጥለው ደግሞ በሒደት እናየዋለን›› ያሉት አቶ ጌታቸው ‹‹በሒደት እናየዋለን የሚለው አማርኛ አሁን ነው እየገባኝ የመጣው›› በማለት ከፈገግታ ጋር አውግተዋል፡፡
ሪፖርተር፡- የአሸንዳ በዓልን እንዴት አገኙት?
አቶ ጌታቸው፡- ስሜቴ ኃይለኛ ነው፤ በዚህ በዓል ላይ እንድገኝ በክቡር ሚኒስትሩ በመጋበዜ ደስተኛ ነኝ፡፡ አንደኛ በኢትዮጵያዊነቴ ከዚህ በፊት በቅጡ የማላውቀውን ባህል በቅጡ እንድረዳው፤ ኢትዮጵያ በጽሑፍ ብዙ ባህል አላት፣ ብዙ ቅርስ አላት፣ የሚባለውን በዓይን ተገኝቶ መገንዘብ ታላቅ ነገር ነው፡፡ እና ይህ ለእኔ ትልቅ ኩራት ሰጥቶኛል፡፡ ሁለተኛ ነገር ደግሞ ባለኝ የሥራ ኃላፊነት መሠረት፣ የዩኔስኮ ትልቁና ዋናው ዓላማው ባህሎችን ከትውልድ ወደ ትውልድ እየተጠበቁና እየዳበሩ እንዲሄዱ ማድረግ ነው፡፡ አንዱ በተቻለ መጠን የሌላውን ባህል እንዲያውቅ፣ በዚያም የተነሳ ሰላም እንዲሰፍን የማድረግ ሥራ ነው፣ የዩኔስኮ ትልቁ ሥራ፡፡ በዚያም የተነሳ የኢትዮጵያን ባህሎች ዓለም ላይ ማስተዋወቅ አንዱ የዩኔስኮ ግዳጅ ነው፡፡ በአጭር ጊዜ ውስጥ የአሸንዳ በዓል እንደመስቀል በዓል አከባበር የዩኔስኮ ምዝገባ ውስጥ ይገባል የሚል ተስፋ አለኝ፡፡ በግለሰብ ደረጃ የምችለውን ነገር ሁሉ አደርጋለሁ፡፡ እርግጠኛ ነኝ የመንግሥት አካላትም ተረባርበው በአጭር ጊዜ ውስጥ ሊያደርጉት እንደሚችሉ፡፡
ሪፖርተር፡- ኢትዮጵያ ከተዳሳሽ ቅርሶች ሌላ የማይዳሰሱ ቅርሶችን ለማስመዝገብ እየተንቀሳቀሰች ነው፡፡ በቅርቡ በጊዜያዊ መዝገብ ውስጥ ፊቼ ጫምባላላና የገዳ ሥርዓት ተይዘዋል፡፡ እነዚህንና ሌሎችን አልምታ ለማስመዝገብ ምን ተግዳሮት ሊገጥማት ይችላል?
አቶ ጌታቸው፡- ይህን ተግዳሮት የሚባለውን ነገር እኔ አሁን ካለሁበት ቦታ ላይ ሆኜ መናገር አልችልም፡፡ በእርግጠኝነት መናገር የምችለው ግን ከማውቀው የኢትዮጵያ ባህል፣ ከማውቀው የኢትዮጵያ ታሪክ አንፃር ዩኔስኮ ውሰጥ የተመዘገቡት የኢትዮጵያ የባህል ቅርሶች የሚዳሰሱትም ሆኑ የማይዳሰሱት በቂ አይደሉም፡፡ በእርግጥ በምዝገባ ቁጥር ከሄድን ኢትዮጵያ ዛሬ በአፍሪካ ደረጃ አንደኛ ቁጥር ላይ ነው ያለችው፡፡ ያ ግን በቂ አይደለም፡፡ እኛ የባህል ሙዚየም ነን፤ ሰዎች የተፈጠሩባት አካባቢ ነን፡፡ ብዙ ባህሎችን እንኳን የተቀረው ዓለም ቀርቶ እርስ በርሳችን የማናውቃቸው አሉ፡፡ እነዚህ ግን መሠረታዊ ማንነታችን የሚገልጹ ናቸውና በጊዜያዊ መዝገብ ላይ የተመዘገቡትም ሆኑ ሌሎች የሚመዘገቡት፣ መንግሥት አስፈላጊውን መዘጋጀት አድርጎ፣ የኤክስፐርቶችን ምክር ወስዶና ከዩኔስኮ ጋር ተመካክሮ እስካቀረበ ድረስ ይህንን ለማስመዝገብ የሚገጥም ችግር አይታየኝም፡፡ ይልቅስ የኢትዮጵያ መንግሥትም ሆነ ሌላ መንግሥት ያንን ማስታወስ ያለበት የባህል ቅርስ ዩኔስኮ መዝገብ ውስጥ ሲያስገባ የቁንጅና ውድድር አይደለም፡፡ እዚያ መዝገብ ውስጥ ሲያስገባ ዓለም እንዲያውቅለት ባህላችን ምን ይመስላል? የተፈጥሮ፣ የቅርሳ ቅርሱ፣ የሃይማኖቱ ወዘተርፈ የተባሉት ነገሮች በሙሉ ከግዳጅ ጋር ይመጣሉ፡፡ ያ ግዳጅ ማለት ደግሞ ያንን ባህል በሥርዓቱ የመጠበቅ፣ የተመዘገቡት ነገሮች እንዲታወቁ ማድረግ ነው፡፡ ዩኔስኮም ያንን እየተከታተለ ያልተሠራ ሥራ ካለ እንዲሠራ፣ በጣም የጎደለ ነገር ካለ ደግሞ ከመዝገቡ አውጥቶ አደጋ ላይ ናቸው የሚል መዝገብ ውስጥ እናስገባለን፡፡ ያ በዓለም ይታወቃል፣ በአስመዝጋቢውም መንግሥት ይታወቃል፣ በዚያ የተነሳ መንግሥት የግድ አስፈላጊው ዕርምጃ መውሰድ ይገባዋል ማለት ነው፡፡
ሪፖርተር፡- ኢትዮጵያ የማይዳሰሱ ቅርሶች (የኢንታንጀብል ሄሪቴጅ) ስምምነት ከፈረመች አሥር ዓመታት ሆኗል፡፡ በእነዚህ ዓመተት ውስጥ አንድ የመስቀል በዓል ብቻ ነው የተመዘገበው፡፡ በርካታ ብሔረሰቦች ያላት በሐውርታዊት አገር ሆና እያለች፣ እንደ ሌሎች የእስያ፣ የአፍሪካና የአውሮፓ አገሮች ብዙ ቅርስ ማስመዝገብ አልቻለችም፡፡ ለምሳሌ የጥምቀት በዓል ‹‹የአፍሪካ ጥምቀት›› (African Epiphany) እያሉ ይጠሩታል፡፡ እዚህ ላይ ያለው እንቅስቃሴ ውሱን ነው፡፡ ክፍተት አለ ይባላል፤ በዚህ ረገድ ዩኔስኮ የሚሰጠው ድጋፍ ሊኖር ይችላል?
አቶ ጌታቸው፡- ድጋፍ ይኖራልም፤ አለም፡፡ ከዚህ በፊትም አለ፤ ይቀጥላል፡፡ ክፍተት እንዳለ ዩኔስኮም ያውቃል፤ በተለይም የኢትዮጵያ መንግሥት፣ እዚህ ሥራ ላይ የሚሠሩት ባለሥልጣኖችም ሆኑ ድርጅቶች ብዙ ገና እንደሚቀር ይገባቸዋል፡፡ ከብዙ አገሮች በተሻለ መልክ ያስመዘገብናቸውና በጊዜያዊነትም ሆነ በቋሚነት የተመዘገቡ የማይዳሰሱ ቅርሶች አሉ፡፡ ግን ሌሎችም አሉን፡፡ አገራችን የባህል፣ የቅርስ ሙዚየም ነች ስንል በሺሕ የሚቆጠሩ የሚመዘገቡ ሀብቶች አሉ፡፡ በዚያ አንፃር ከተመለከትነው ገና ዳዴ እያልን ነው ማለት እችላለሁ፡፡ ያ ማለት ግን ሥራው አልተጀመረም ማለት አይደለም፤ የአቅም ክፍተት አለ፡፡ ችግሮችን በሥርዓቱ የመረዳት ችግር አለ፡፡ ይኼን የመሳሰሉት ችግሮች ለመቅረፍ በመንግሥት ብቻ ሳይሆን ኅብረተሰቡ ሊተባበር ይገባዋል፡፡ ይኼም ማለት እኔ ለባህሌ፣ ለአገሬ ለራሴ የሚለውን አስተሳሰብ ማምጣት ያስፈልጋል፡፡ የባህል ቅርሶች ማንነታችንን የሚገልጹ ናቸውና፡፡ የመንግሥት ኃላፊነት ብቻም አይደለም፣ የሁላችንም ኃላፊነት ነው፡፡ ክፍተቶችንም ለመቅረፍ ሁላችንም ተባብረን መሥራት ይኖርብናል፡፡ ሚዲያውም ሰው የማያውቀውን የማሳወቅ ኃላፊነት አለበት፡፡
ሪፖርተር፡- በየስፍራው ቅርሶች ይመዝገቡልን የሚል መነሳሳት አለ፡፡ የመመዝገቡ ፋይዳ ምንድነው ብለው ለሚጠይቁ ምን ልንላቸው እንችላለን?
አቶ ጌታቸው፡- መጀመሪያ ባህል ለአንድ ኅብረተሰብ ምንድነው? መመለስ ያለበት ጥያቄ ነው፡፡ ዋናው እዚህ ላይ ግንዛቤ የሚያስፈልገው አንደኛ ባህል የኅብረተሰብ ሙጫ ነው፡፡ ኅብረተሰብን አንድ የሚያደርግ፡፡ የምንነጋገረው ቋንቋ፣ የምንበላው ምግብ፣ የምናምንበት ሃይማኖት ወዘተርፈ፣ የምንጫወታቸው ሙዚቃዎች፣ የምናሳያቸው ቴአትሮች፣ አለባበሳችን እነዚህ ሁሉ ተደማምረው ነው አንድን ኅብረተሰብ፣ ያንን ኅብረተሰብ የሚያስመስሉት፡፡ ያ ኅብረተሰብ ደግሞ ሌላው ኅብረተሰብ እንዲረዳው፣ ራሱንም እንዲያስተዋውቅ፣ ተግባብቶ እንዲኖር እነዚህ ነገሮች በአገር ብቻ ሳይሆን በዓለም ደረጃ መታወቅ አለባቸው፡፡ ባለመቻቻልና ባለማወቅ ምክንያት ብቻ ዓለም ላይ ብዙ ጦርነቶች ተካሂደዋል፡፡ አሁንም እየተካሄዱ ነው፣ አንዱ መሣሪያችን ተግባብቶ የመኖርን ሐሳብ መሠረት ማስያዝ ነው፡፡ ይህ የሚሆነው ደግሞ እያንዳንዳችን የራሳችንም የሌላውንም ባህል ማወቅ ስንችል ነው፡፡ የእያንዳንዳችን ባህል ዓለም አቀፍ ዋጋ አለው፡፡ ለእኛ ብቻ አይደለም፤ ይህ የዓለም ሕዝብ ቅርስ ነው፡፡ ለዚህም ነው ሶሪያ ውስጥ ቤተ ክርስቲያኖችና መስጊዶች ሲፈርሱ የምንጮኸው፣ የምናወግዘው፡፡ ለኢትዮጵያ ሕዝብ ስለቅርስ ማስመዝገብ ፋይዳ በምናስረዳበት ጊዜ ቅድም እንዳልኩት የቁንጅና ውድድር ሳይሆን መሠረታዊ ዋጋ ያለው ማኅበራዊ ኃላፊነት ነው፡፡ ለእኛ ብቻ ሳይሆን ለሚቀጥለው ትውልድ፣ ከዚያም ቀጥሎ ለሚመጣው ትውልድ ይጠቅማል፡፡ ከእኛ በፊት የነበሩት ትውልዶች ይኸንን ቅርስ ባያቆዩት ኖሮ ዛሬ አሸንዳን እንደ አሸንዳ አናከብረውም ነበር፡፡ በቀላሉ ሊጠፋ ይችል ነበር፡፡ ያን የወረስነውን አሳልፎ የመስጠት ኃላፊነት አለብን፡፡ በዚያም ላይ የኢኮኖሚ ጥቅሞችም አሉ፤ ከቱሪዝም ኢንዱስትሪ መስፋፋት ጋር ተያይዞ ለኅብረተሰቡ የሚሰጠው ትልቅ የኢኮኖሚ ፋይዳ አለው፡፡ እሱም በአግባቡ ግንዛቤ ውስጥ ሊገባ ያስፈልጋል፡፡
ሪፖርተር፡- የተለያዩ አገሮች የሚጋሯቸው በአፍሪካም ሆነ በእስያ የተመዘገቡ የጋራ ቅርሶች አሉ፡፡ በእኛም ክፍለ አህጉር እንዲሁ፡፡ ትስስሩ እንዴት ይታያል?
አቶ ጌታቸው፡- በዓለም አቀፍ ደረጃ የእያንዳንዱን ኅብረተሰብ ባህል ማክበር ግዴታም ኃላፊነትም ነው፤ ያንን እስካደረግን ድረስ ድንበር ተሻጋሪ ባህሎችና ቅርሶች የሚመሩበት ዘዴ አለ፡፡ ቅርሶች ሕዝብን ያቀራርባሉ መግባባትንም ይፈጥራሉ፡፡ ከማያስፈልግ ጦርነት ከመግባት ሊያግዱን ይችላሉ፡፡ ያ እንግዲህ በነፃ ማሰብ ስንጀምር፣ መግባባት ላይ ስንደርስ፣ ከኔ ይባስ ስንባባል ነው፡፡ ሌላው ቀርቶ እንኳን በአንድ አገር ውስጥ የሚኖሩ ሰዎች ቀርቶ ከጎረቤት አገርም ኢትዮጵያ ሶሪያ ውስጥ ያለ አንድ ቅርስ ሲጠፋ ትቆጫለች፡፡ ያንን አስተሳሰብ ለማዳበር ነው ዩኔስኮ የተፈጠረው፡፡
ሪፖርተር፡- የዩኔስኮ 70ኛ ዓመት በምን መልኩ ማክበር ታስቧል? ኢትዮጵያም መሥራች ከመሆኗ አንፃር ምን የታሰበ ነገር አለ?
አቶ ጌታቸው፡- ዩኔስኮ ከተቋቋመ ዘንድሮ 70ኛ ዓመቱ ነው፡፡ ወደ ኖቨምበር ገደማ 195 አገሮች የሚሳተፉበት ጠቅላላ ጉባኤ ይኖራል፡፡ እዚያ ላይ የተለያዩ ዓይነት ዝግጅቶች ይኖራሉ፡፡ ለእያንዳንዱ መንግሥት ግብዣ ሰጥተናል፡፡ የኢትዮጵያም አመራሮች እዚያ ቦታ ላይ ትልቅ ሚና ይጫወታሉ የሚል ተስፋ አለን፡፡ ለጠቅላይ ሚኒስትራችን ግብዣ ሰጥተናል፡፡ እስካሁን ድረስ ከምናውቀው ይሳተፋሉ የሚል ተስፋ አለን፡፡ ከርሱ አልፎ ደግሞ ምናልባት ከተሳካ እኔ እስከማውቀው ድረስ የሉሲን ቅጂ (ሪፕሊካ) ለዩኔስኮ ለመስጠት ዓላማ አለ፡፡ እነዚህ ሁሉ ተደማምረው ከአብዛኛው አገር በተለየ መልኩ ለኢትዮጵያ ትልቅ ትኩረት (ቪዚቢሊቲ) ሊሰጥ የሚችል ኩነት (ኢቬንት) ይሆናል የሚል ግምት አለኝ፡፡ 70ኛው ዓመት በሚከበርበት ሰዓት አብረን ልናስባቸው የሚገቡ ብዙ ነገሮች አሉ፡፡ የዛሬ 67 ዓመት የዓለም አቀፍ የሰብአዊ መብት ሕግ ሲወጣ ከዩኔስኮ ሥራ ጋር ተያይዞ ነው፡፡ ትምህርትን የማስፋፋት ዓላማም እንዲሁ፡፡ እነዚህን የመሳሰሉት ተግባሮች ሁሉ አልተፈጸሙም፡፡ 70 ዓመት እንደሰው ዕድሜ ለአንድ ድርጅት ብዙ አይደለም፡፡ ዩኔስኮ ጡረታ የመውጣት ዓላማ የለውም፡፡ ይቀጥላል የሚል ተስፋ አለን፡፡ ግን በሚቀጥልበት ጊዜ ያልተጨረሱ ብዙ ሥራዎች አሉ፡፡ የጀመርናቸው፣ 70 ዓመት ታግለን አሁንም ውጤት ያላገኘንባቸው የሴቶች እኩልነት በሚመለከት፣ አፍሪካን ከሌላው ዓለም ደረጃ ላይ በኢኮኖሚም ሆነ በሶሻል ማድረስ ወዘተርፈ የምንተጋበት ይሆናል፡፡ ዘላቂ የልማት ግቦች መለኪያ የሚባለው ሰነድም በሚቀጥለው ወር ኒውዮርክ ላይ ውሳኔ ያገኛል፡፡ የአዲስ ምዕራፍ መጀመርያ ጊዜያችንም ይሆናል፡፡