Saturday, December 2, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

የአፍሪካ አገሮች ተስፋ የተደረጉበትን የኢኮኖሚ ዕድገት የሚተነብየው ሪፖርት ይፋ ሆነ

ተዛማጅ ፅሁፎች

በመጪዎቹ አሥራ አምስት ዓመታት ውስጥ አብዛኞቹ ድሃ የአፍሪካ አገሮች ወደ መካከለኛ ገቢ ኢኮኖሚ እንደሚሻገሩ የሚተነብየው ሪፖርት ይፋ የተደረገው ነሐሴ 26 ቀን 2007 ዓ.ም. በአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን በተካሄደ ሥነ ሥርዓት ነበር፡፡

የአፍሪካ ኅብረት፣ ከዓለም የምግብ ፖሊሲ ምርምር ኢንስቲትዩት (ኢፍፕሪ) ጋር በመተባበር ባዘጋጀው ሥነ ሥርዓት ላይ ይፋ የተደረገው ሪፖርት እንደሚጠቁመው፣ በመጪዎቹ ዓመታት የአፍሪካን የኢኮኖሚ ዕድገት ገጽታ የሚቆጣጠሩ ክስተቶች እንደሚሆኑ ከተነገረላቸው መካከል ሰፊ የመሠረተ ልማት ክፍተቶች፣ የአየር ንብረት ለውጥ፣ ፈጣን ከተሜነት (ኧርባኒዜሽን) በወጣቶች የተሞላና ፈጣን የሕዝብ ቁጥር ዕድገት የአፍሪካ መጻዔ ከሚቆጣጠሩ ክስተቶች ውስጥ ተመድበዋል፡፡

የዓለም የምግብ ፖሊሲ ምርምር ኢንስቲትዩት በሚያስተባብረው ተቋም በኩል ይፋ የተደረገው ሪፖርት ‹‹አኑዋል ትሬንድስ ኤንድ አውትሉክስ›› የተሰኘ ዓመታዊ ሪፖርት ሲሆን፣ በየዓመቱ የሚከሰቱ ለውጦችንና ክንውኖችን በመተንተን የሚያቀርብ ነው፡፡ በዚህ መሠረት በአሁኑ ወቅት ኢትዮጵያን ጨምሮ ዝቅተኛ ገቢ ያላቸው ተብለው የሚታወቁ አፍሪካ አገሮች በአሥራ አምስት ዓመት ውስጥ ወደ መካከለኛ ገቢ ደረጃ ያድጋሉ በማለት ሪፖርቱ ትንታኔ አቅርቧል፡፡

ከዚህ ባሻገር እ.ኤ.አ. በ2050 ሁሉም የአፍሪካ አገሮች የመካከለኛ ገቢ ኢኮኖሚ እንደሚገነቡ ሲጠበቅ፣ በርካታ ፈተናዎችም እንደሚጋረጡባቸው በሪፖርቱ ተመልክቷል፡፡ ሪፖርቱ ነሐሴ 26 ቀን 2007 ዓ.ም. በአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን ይፋ የተደረገ ሲሆን፣ ለሦስት ቀናት በሚቆይ ውይይት እንደሚታጀብም ከአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን የተገኘው መረጃ ይጠቁማል፡፡

የግብርና ሚኒስትር ዴኤታውን አቶ ወንድይራድ ማንደፍሮን ጨምሮ አፍሪካ ኅብረት የገጠር ኢኮኖሚና የግብርና ኮሚሽነሯ ሮዳ ቱሚሲሜና ሌሎችም ኃላፊዎች ተገኝተዋል፡፡ በስብሰባውም አፍሪካ እያስመዘገበችው ያለው ፈጣን ኢኮኖሚ ዘላቂነት ላይ ያተኮረ ውይይት ይካሄዳል፡፡ በዓለም ሁለተኛ ፈጣን የኢኮኖሚ ዕድገት በማስመዝገብ ላይ የምትገኘው አፍሪካ፣ አሁንም በድህነትና በችጋር ውስጥ ለሚገኙ በርካታ ሚሊዮኖች ሕይወት መሻሻል መፍትሔ ሊሆን አላስቻለም፡፡ በመሆኑም ፖሊሲ አውጪዎች በእነዚህ ጉዳዮች በመምከር ለመጪዎቹ ዓመታት ስንቅ የሚሆኑ የመፍትሔ ሐሳቦችን ያመነጫሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች