በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት (ተመድ) ሥር አይፒሲሲ ተብሎ የሚጠራውን የዓለም አቀፍ የተመራማሪዎች ተቋም በምክትል ሊቀመንበርነት ለመምራት፣ የኢትዮጵያ መንግሥት ለመጀመርያ ጊዜ የራሱን ዕጩ ማቅረቡ ታወቀ፡፡
ለዕጩነት የቀረቡትም በብሔራዊ ሚቲዎሮሎጂ ኤጀንሲ እያገለገሉ የሚገኙት ዶ/ር ድሪባ ቆሪቻ ናቸው፡፡
አይፒሲሲ (Inter-governmental Panel on Climate Change) ከ196 አገሮች በላይ አባል የሆኑበት ተቋም ነው፡፡ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት በዓለም አቀፉ ሚቲዎሮሎጂ ኤጀንሲ በጥምረት የተቋቋመና በሺዎች የሚቆጠሩ ሳይንቲስቶችን ምርምር በመገምገም፣ ለመንግሥታት ሪፖርት እንዲያቀርብ ታስቦ የተመሠረተው በ1992 ዓ.ም. ነው፡፡
ድርጅቱ በአየር ለውጥና በሚያስከትላቸው ጉዳቶች፣ በሳይንሳዊ መንገድ የተሠሩ የጥናት ግኝቶችንና ለሚቀጥሉት አንድ መቶ ዓመታት የሚስተዋለውን የአየር ንብረት ለውጥን በመተንበይ፣ ለተመድ አባል አገሮች መሪዎችና ፖለቲከኞች አጋዥ የሆኑ የፖሊሲ ቀረፃና ውሳኔ የሚያገለግሉ የመረጃ ግብዓቶችን ያቀርባል፡፡
በዕጩነት የቀረቡት የ48 አመቱ ዶ/ር ድሪባ የዶክትሬት ዲግሪያቸውን ኖርዌይ ከሚገኘው በርገን ዩኒቨርሲቲ በአየር ትንበያ ሳይንስ ያገኙ ሲሆን፣ ካለፉት ሦስት ዓመታት ጀምሮ በአይፒሲሲ የኢትዮጵያ ወኪል በመሆን በማገልገል ላይ ይገኛሉ፡፡
ዕጩው የትንበያ ባለሙያ ከኢትዮጵያ በተጨማሪ ምሥራቅ አፍሪካንም በመወከል ለውድድሩ ቢመረጡም፣ ከሰባት የአፍሪካ አገሮች ዕጩዎች ፉክክር እንደሚኖርባቸው ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡
አይፒሲሲ ከዋናው ሊቀመንበር ሥር ሦስት ምክትል ሊቃነ መናብርት አሉት፡፡ በመጪው ጥቅምት ወር በክሮሺያ በሚካሄደው ምርጫ የሚያሸንፉ ከሆነ ዶ/ር ድሪባ በተቋሙ ሥር ‹ዎርኪንግ ግሩፕ አንድ› የሚባለውንና በሺዎች የሚቆጠሩ ተመራማሪዎች ያቀፈውን ቡድን ይመራሉ ተብሏል፡፡
ይኼንኑ ቡድን ላለፉት ሰባት ዓመታት ሲመሩት የነበሩት ስዊዘርላንዳዊው የአካባቢ ፊዚክስ ሳይንቲስቱ ፕሮፌሰር ቶማስ ስቶከር ናቸው፡፡ ፕሮፌሰሩ ራሳቸውን ለዋና ሊቀመንበርነት ተወዳዳሪ አድርገው አቅርበዋል፡፡ በአይፒሲሲ አባል አገሮችም በመዞር የምረጡኝ ዘመቻ የጀመሩት ፕሮፌሰር ስቶከር፣ ባለፈው ሳምንት በኢትዮጵያ ጉብኝት በማድረግ ከመንግሥት ባለሥልጣናት ጋርም ተወያይተው ነበር፡፡