Tuesday, November 28, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊበመንገድ ዲዛይን ለውጥ የሚፈናቀሉ ለከንቲባ ጽሕፈት ቤት ቅሬታ አቀረቡ

በመንገድ ዲዛይን ለውጥ የሚፈናቀሉ ለከንቲባ ጽሕፈት ቤት ቅሬታ አቀረቡ

ቀን:

–  የአዲስ አበባ መንገዶች ባለሥልጣን ጋራዥ ከከተማ ሊወጣ ነው

የአዲስ አበባ ከተማ መንገዶች ባለሥልጣን ከአፍሪካ ኅብረት እስከ ኦሎምፒያ ድረስ የሚገነባው የመንገድ ዲዛይን ተከልሶ በሌላ አቅጣጫ እንዲጓዝ መደረጉ ቅሬታ አስነሳ፡፡ ለሁለተኛ ጊዜ በተከለሰው የመንገድ ዲዛይን ከቤት ንብረታቸው የሚፈናቀሉ የኦሎምፒያ አካባቢ ነዋሪዎች ቅሬታቸውን ለከንቲባ ጽሕፈት ቤት አቅርበዋል፡፡

ነዋሪዎቹ ለከንቲባ ጽሕፈት ቤት ባቀረቡት ቅሬታ መንገዱ ለሁለተኛ ጊዜ ቢከለስም፣ የክለሳው ምክንያቶች የመንገዱን ዘለቄታዊ ጥቅም ታሳቢ በማድረግ ሳይሆን የተለያዩ ግለሰቦችንና ድርጅቶችን ለመጥቀም ነው ብለዋል፡፡

ነዋሪዎቹ ባቀረቡት ቅሬታ የመጀመርያው የመንገድ ዲዛይን የተቀየረው የአዲስ አበባ ከተማ መንገዶች ባለሥልጣን ጋራዥ እንዳይነካ ለማድረግ ነው ብለዋል፡፡ ከመንገዱ ዲዛይን መረዳት እንደሚቻለው፣ በአጭር ርቀት ውስጥ የመንገዱን አቅጣጫ ለማዞር መሞከሩንና ሁለተኛው ዲዛይን ክለሳ ደግሞ የተወሰኑ የግለሰብ ወሰኖችን ላለመንካት በሚመስል ሁኔታ፣ ከመጀመርያው ዲዛይን የተለየ ሳይሆን መለወጡን ቅሬታቸው ያመለክታል፡፡

‹‹ሁለተኛው ዲዛይን ተግባራዊ ቢደረግ የመንገዱን ጠመዝማዛነት ከማባባሱም በላይ፣ ከተማዋ ደረጃውን ያልጠበቀ የቶፖግራፊ ገጽታ እንዲኖራት ያደርጋል፡፡ መንገዱን የሚጠቀሙ ተሽከርካሪዎች በቀላሉ ለአደጋ እንዲጋለጡም ያደርጋል፤›› በማለት ቅሬታ አቅራቢዎች ለከንቲባ ጽሕፈት ቤት ባቀረቡት አቤቱታ ገልጸዋል፡፡

የኦሎምፒያ አፍሪካ ኅብረት መንገድ የአፍሪካ መሪዎችን ጨምሮ የዓለም አቀፍ ልዑካን የሚጓጓዙበት በመሆኑ መንገዱ በትክክል ቢሠራ ጠቀሜታ ይኖረዋል በማለት የሚገልጹት ቅሬታ አቅራቢዎች፣ የመንገዱ አቅጣጫ ያለበቂ ምክንያት እንዲቀየር በመደረጉ የመንገዱ የተወሰነው ክፍል ከ350 ሜትር ርዝመት ወደ 610 ሜትር ከፍ እንዲል ማድረጉን የነዋሪዎቹ ቅሬታ ያመለክታል፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ መንገዶች ባለሥልጣን ዋና ሥራ አስኪያጅ ኢንጂነር ፍቃዱ ኃይሌ ይህንን ቅሬታ አይቀበሉትም፡፡ እሳቸው ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ የመንገዱ ዲዛይን ለውጥ ከጋራዡ ጋር የሚገናኝ አይደለም፡፡

‹‹እኛ ይህንን የሚያህል ቦታ በመሀል ከተማ ለጋራዥ ሥራ ማዋል ስለሌለብን ተለዋጭ ቦታ እንዲሰጠን አድርገናል፤›› በማለት ገልጸው፣ ‹‹ከከተማ ውጪ አዲስ ጋራዥ ከሠራን በኋላ ቦታውን ለአዲስ አበባ መሬት ልማትና ማኔጅመንት ቢሮ እናስረክባለን፤›› በማለት የዲዛይን ለውጡ ከጋራዡ ጋር የሚያገናኘው ነገር እንደሌለ አስረድተዋል፡፡

ከኦሎምፒያ ወደ መስቀል ፍላወር በሚወስደው መንገድ ላይ የሚገኘው የመንገዶች ባለሥልጣን ጋራዥ 26 ሺሕ ካሬ ሜትር ስፋት አለው፡፡ በአሁኑ ወቅት ባለሥልጣኑ ከከተማ ለመውጣት ባቀረበው ጥያቄ 47 ሺሕ ካሬ ሜትር ቦታ ተሰጥቶታል፡፡ ኢንጂነር ፍቃዱ በ2008 ዓ.ም. ግንባታ በማካሄድ መሀል ከተማ የሚገኘውን ጋራዥ እንደሚለቁ አስታውቀዋል፡፡

የመንገድ ዲዛይኑ ሊለወጥ የቻለው የአዲስ አበባና ዙሪያዋ ኦሮሚያ ልዩ ዞን የጋራ ማስተር ፕላን ጽሕፈት ቤት እያዘጋጀ ባለው አዲስ ማስተር ፕላን መሠረት እንደሆነም ገልጸዋል፡፡

ቀድሞ የነበረው የመንገድ ዲዛይን መንገዱ በ20 ሜትር ስፋት እንዲገነባ የሚፈቅድ ቢሆንም፣ አዲሱ ማስተር ፕላን የመንገድ ስፋቱ እስከ 30 ሜትር እንዲያድግ አድርጓል፡፡ በዚህ መሠረት የአቅጣጫ ለውጡ እንደሚያስፈልግ በመታመኑ የተለወጠ ነው በማለት ለቅሬታ አቅራቢዎች ምላሽ ሰጥተዋል፡፡

ከልደታ ፀበል እስከ ቄራ ድረስ ያለው የዚህ መንገድ ክፍል የሆነ 1.8 ኪሎ ሜትር መንገድ ግንባታ ተጠናቋል፡፡ ቀሪው ስድስት ኪሎ ሜትር መንገድ ግንባታ በመካሄድ ላይ ሲሆን፣ በቅርቡ ኦሎምፒያ አካባቢ ሲደርስ በመንገድ ዲዛይን ለውጡ ቅሬታ ያቀረቡ ነዋሪዎች እንዲነሱ ይደረጋል ተብሏል፡፡

 

 

 

 

                                                                                                                             

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ለሲኒመር ትሬዲንግ አ/ማ አባላት በሙሉ የጠቅላላ ጉባኤ የስብሰባ ጥሪ

ለሲኒመር ትሬዲንግ አ/ማ አባላት በሙሉ የጠቅላላ ጉባኤ የስብሰባ ጥሪ ሲኒመር ትሬዲንግ...

የባህር በር በቀጣናዊ ተዛምዶ ውስጥ

በበቀለ ሹሜ መግቢያ በ2010 ዓ.ም. መጋቢት ማለቂያን ይዞ ዓብይ አህመድ በጠቅላይ...

ሥጋት ያስቀራል ተብሎ የሚታሰበው የጫኝና አውራጅ መመርያ

በአዲስ አበባ ከተማ በሕገወጥ መልኩ በመደራጀት ማኅበረሰቡ ላይ እንግልትና...

ማወቅ ወይስ አለማወቅ – ድፍረት ወይስ ፍርኃት?

በአሰፋ አደፍርስ ወገኖቼ ፈርተንም ደፍረንም የትም አንደርስምና ለአገራችን ሰላምና ክብር...