Tuesday, April 16, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ጊቤ ሦስት እስከ ጥቅምት ወር 561 ሜጋ ዋት እንደሚያመነጭ ተገለጸ

ተዛማጅ ፅሁፎች

በበርካታ ዓለም አቀፍ ተቋማት ጫና ተፅዕኖ ውስጥ ያለፈው ጊቤ ሦስት የኃይል ማመንጫ ፕሮጀክት፣ እስከ ጥቅምት ወር 2008 ዓ.ም. ድረስ 561 ሜጋ ዋት እንደሚያመነጭ ተገለጸ፡፡

ሪፖርተር ያነጋገራቸው የውኃ፣ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስትሩ አቶ ዓለማየሁ ተገኑ፣ የኃይል ማመንጫ ፕሮጀክቱ በአሁኑ ወቅት ተርባይኖቹን እየሞከረ እንደሚገኝ ገልጸዋል፡፡

የኃይል ማመንጫ ፕሮጀክቱ እ.ኤ.አ. በ2006 የተጀመረ ሲሆን፣ በወቅቱ የነበረው ዕቅድ እስከ 2013 ድረስ ይጠናቀቃል የሚል ነበር፡፡ ይሁን እንጂ ፕሮጀክቱ የሚጠይቀውን 1.8 ቢሊዮን ዶላር ኢትዮጵያ እንዳታገኝ የተለያዩ የሰብዓዊ መብት አቀንቃኞች ግፊት አድርገዋል፡፡

ፕሮጀክቱ ኦሞ ወንዝ አካባቢና በኬንያ የቱርካና ወንዝን ተገን ያደረጉ ነዋሪዎችን የኢኮኖሚ ምንጭ ይጎዳል የሚሉ ቅሬታዎች ነበሩበት፡፡ ቅሬታዎቹን ከሚያነሱት ተቋማት መካከል አንዱ ‹ኢንተርናሽናል ሪቨርስ› የተባለው የኃይል ማመንጫ ግንባታዎች ተፅዕኖ ለማስወገድ የሚሠራ ዓለም አቀፍ ተቋም ነው፡፡

የኢትዮጵያ መንግሥት በወቅቱ ለፕሮጀክቱ የሚያስፈልገውን ገንዘብ ለማግኘት ከአውሮፓ ኢንቨስትመንት ባንክ፣ ከአፍሪካ ልማት ባንክና ከዓለም ባንክ የብድር ጥያቄዎችን አቅርቦ እንደነበር መረጃዎች ያስረዳሉ፡፡

በዚህ ምክንያት ፕሮጀክቱ በተያዘለበት ጊዜ መሠረት መገንባት አልቻለም፡፡ በፋይናንስ ችግር የተመታውን ይህንን ፕሮጀክት ከምዕራባውያን ተቋማት ጫና አላቆ ለማስቀጠል በመንግሥት የተያዘው አቅጣጫ ወደ ቻይና ማማተር ነበር፡፡

በመሆኑም በቬንደር ፋይናንሲንግ ስምምነት የቻይናው ኤሌክትሮ መካኒካል ኩባንያ 550 ሚሊዮን ዶላር በማቅረብ፣ የፕሮጀክቱን ኤሌክትሮ መካኒካል ሥራ ለመሸፈን ስምምነት ፈርሟል፡፡

ፕሮጀክቱ ይጠናቀቃል ተብሎ የተገመተው እ.ኤ.አ. በ2013 ቢሆንም፣ ሁለት ዓመታት ዘግይቶ ዘንድሮ በነሐሴ ወር የተርባይኖች ሙከራ ጀምሯል፡፡ የኃይል ማመንጫ ፕሮጀክቱ አሥር ተርባይኖች ሲኖሩት፣ የእያንዳንዳቸው የማመንጨት አቅም ደግሞ 187 ሜጋ ዋት መሆኑን መረጃዎች ያስረዳሉ፡፡

በአሁኑ ወቅት በአምስት ተርባይኖች ላይ ውኃ በመልቀቅ ሙከራ እየተካሄደ ነው ያሉት ሚኒስትሩ አቶ ዓለማየሁ፣ ኢንጂነሮቹ የሚወስኑ ከሆነ በአምስት ተርባይኖች ኃይል የማመንጨት ሥራ እስከ ጥቅምት ወር ይጀመራል ብለው እንደሚያስቡ ተናግረዋል፡፡ እርግጠኛውን ቀን ማስቀመጥ አስቸጋሪ እንደሚሆንም ጠቁመዋል፡፡

 ይህ ፕሮጀክት በሙሉ አቅሙ መሥራት ሲጀምር 1,870 ሜጋ ዋት ኃይል የሚያመነጭ ሲሆን፣ ከዚህ ውስጥ ለኬንያ 200 ሜጋ ዋት የመሸጥ ስምምነት መደረጉን መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡

 

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች