Monday, December 4, 2023
- Advertisment -
- Advertisment -

ኢሕአዴግ የገባው ቃል በተግባር ይደገፍ!

ኢሕአዴግ ቃልና ተግባሩ አልገናኝ እያሉ ዓመታት ተቆጥረዋል፡፡ ስኬቶቹን እያገዘፈ፣ ችግሮቹን እየሸፋፈነ የዘለቀው ኢሕአዴግ በጣም ቢረፍድም አሁን ወደ ቀልቡ የተመለሰ ይመስላል፡፡ በመልካም አስተዳደር ዕጦት፣ በሙስናና በፀረ ዴሞክራቲክ ተግባራት ምክንያት ሕዝቡ እየደረሰበት ያለው ፈተና እንደተሰማው በአደባባይ ተናግሯል፡፡ ኢሕአዴግ ከዚህ ቀደም እየተሸፋፈነም ቢሆን እነዚህን ችግሮች ቢያምንም፣ አሁን ግን ችግሮቹ እንደማያላውሱት የተረዳ መስሏል፡፡ እነዚህን ሕዝብ የሚፈታተኑ ችግሮችን ከሥር መሠረታቸው እንዳለሁ ብሏል፡፡ ነገር ግን የተገባው ቃል በተግባር ካልተደገፈ ልፋቱ ሁሉ የከንቱ ከንቱ ነው፡፡

ኢሕአዴግ ሕዝቡ ላይ የተጫኑ ፈተናዎችን አስወግዳለሁ ማለቱና በግልጽ በራሱ ላይ ሒስ በማካሄዱ አበጀህ መባል አለበት፡፡ የችግሮቹን ግዝፈት በማመን የተደረገው ግምገማ ጥሩ ነው፡፡ ነገር ግን ድርጅታዊ የማጥራት ሥራውን ከማከናወን ጎን ለጎን ሕዝቡን በሚገባ ማዳመጥ ተገቢ መሆኑን ሊያሰምርበት ይገባል፡፡ በተሳሳቱ ሪፖርቶች ላይ ተመሥርቶ በአገር ህልውና ላይ ውሳኔ የሚያስተላልፈው ኢሕአዴግ ሕዝባዊ ነኝ ለማለት የሚያስችለው ቁመና ላይ መገኘት አለበት፡፡ ኢሕአዴግ ለሕዝብ ወገንተኛ ነኝ ለማለት የሚችለው ሕዝቡን ማዳመጥ ሲጀምር ነው፡፡ የሕዝቡን ተሳትፎ የገደበና የአለቅነት ሚናውን የማይቀበል ሥርዓት ዕድሜ እንደሌለው በአፅንኦት መገንዘብ አለበት፡፡ በተግባርም ማሳየት ይኖርበታል፡፡ የተገባው ቃል በተግባር ካልተደገፈ ውኃ ቅዳ ውኃ መልስ ነው የሚሆነው፡፡ የአገርና የሕዝብን ህልውና ከራሳቸው ጥቅም በታች አሳንሰው የሚያዩ ውስጡ የተሰገሰጉ ኃይሎች በተግባራዊ ዕርምጃ ይታረሙ፡፡ ካልሆነም ይወገዱ፡፡ ለዚህም ተግባር ይቅደም፡፡

ኢሕአዴግ በእስካሁን ቆይታው ምን ያህል የመሪነት ሚናውን ተወጥቷል የሚለው ጉዳይ በቃለ ነቢብ ወይም በንድፈ ሐሳብ መተንተን ሳይሆን፣ በተግባር መሬት ላይ ወርዶ ተጨባጩን ሁኔታ መገምገም ተገቢ ነው፡፡ ሕዝቡ በመልካም አስተዳደር ዕጦት ተጎድቷል፣ በሙስና ተንገብግቧል፣ ሰብዓዊ ክብሩና ነፃነቱ ተጎሳቁሏል ሲባል በኢሕአዴግ አመራር ውስጥ ያሉትን በሙሉ ይመለከታል፡፡ ችግሩ እታች ነው ያለው እየተባለ በአመራሮች ግዴለሽነት የደረሰው ችግር መፍትሔ ይፈልጋል፡፡ በመሆኑም ኢሕአዴግ ራሱን መፈተሽ ያለበት ከላይ ወደ ታች ነው፡፡ በተግባር፡፡

በአሥረኛው የኢሕአዴግ ጠቅላላ ጉባዔ ላይ የተንፀባረቀው የመልካም አስተዳደር ችግሮችን ለመፍታት ከላይ እስከ ታች ያለው አመራር በቁርጠኝነት ተግቶ መሥራት እንዳለበት ነው፡፡ ይኼ ጥሩ ውሳኔ ነው፡፡ ነገር ግን ድርጅቱ ውስጥ የመሸጉ አደገኛ ግለሰቦች በቡድን ተሳስረው ስለሚገኙ እያንዳንዱ አባል በሚገባ ተብጠርጥሮ መፈተሽ አለበት፡፡ በየደረጃው ባሉ መንግሥታዊ መዋቅሮች ውስጥ ሆነው የድርጅቱን አባልነት ሕዝብ ለመበደል፣ ሙስና ለማስፋፋት፣ ዜጎችን ለማሸማቀቅና ያልተገቡ ተግባራትን ለመፈጸም የሚጠቀሙበት ሞልተዋል፡፡ ለበላይ አካል ሐሰተኛ ሪፖርቶችንና መረጃዎችን እየላኩ ከፍተኛ በደል የፈጸሙ አሉ፡፡ ታች ወርደው የሕዝቡን አኗኗር የማያዩና በቀረበላቸው ሪፖርት ብቻ አመራር የሚሰጡ ሰነፎችም አሉ፡፡ ይህ በብርቱ ሊታሰብበት ይገባል፡፡ ቃል በተግባር ይደገፍ፡፡

በጉባዔው ላይ የሕዝብ ተሳትፎ ጉዳይ ተነስቷል፡፡ ሕዝብ ከችግሩ የሚያላቅቀው የመፍትሔ አካል መሆን አለበት ሲባል፣ የይስሙላ ተሳትፎ አይደለም የሚፈለገው፡፡ በኢሕአዴግ ቋንቋ ‹ኪራይ ሰብሳቢ› የሚባሉት ኃይሎች በስመ አደረጃጀትና በሐሰተኛ የሚዲያ ዘገባዎች እየተረዱ፣ ትክክለኛውን የሕዝብ ምሥል በማጥፋት አገሪቱን የፕሮፓጋንዳ መናኸሪያ አድርገዋታል፡፡ ኢሕአዴግ ውስጥ ትግል የሌለ እስኪመስል ድረስ ‹የጠራ መስመር ባለቤት› እያሉ ገደል ይከቱታል፡፡ ሕዝቡንም የመከራ ገፈት ቀማሽ ያደርጉታል፡፡ ከአመራር ጀምሮ እስከ ታችኛው እርከን ድረስ ኢሕአዴግ ውስጥ የመሸጉ ኃይሎች ከጥቅማቸው ውጪ ምንም ነገር ስለማይታያቸው ሕዝቡንም አገሪቱንም እያጠፉ ነው፡፡ ሕዝብን የማያዳምጥ መንግሥት የሚያደምጠው ስለሌለ ለሕዝብ ተሳትፎ ትኩረት ይሰጥ፡፡ ለዚህ ደግሞ የአገርና የሕዝብ ፍቅር ያላቸው አባላት ጠንክረው ይውጡ፡፡ ፀረ ሕዝቦችን ይዋጉ፡፡ በተግባር፡፡

ሕዝቡ መልካም አስተዳደር የለም፣ ፍትሕ የለም፣ ሰብዓዊ መብት አይከበርም፣ ሙስና እንደ ሰደድ እሳት ተስፋፍቷል፣ በየደረጃው ያሉ ሹማምንት አምባገነን ሆነዋል፣ ወዘተ እያለ ሲጮህ መደመጥ አለበት፡፡ ‹የፀረ ሕዝቦችና የኪራይ ሰብሳቢዎች አሉባልታ ነው› እየተባለ የሕዝቡ ብሶት ሲታፈን፣ ለተለየ አመለካከት ቦታ ሲነፈግ፣ በመንግሥት ቁጥጥር ሥር ያለው ሚዲያ አድሎአዊ ሲሆን፣ ጉቦኛ ሹማምንት በሥልጣናቸው ያላግባብ እየጠቀሙ ሲበለፅጉ፣ ፍትሕ እንደ ሰማይ ሲርቅ፣ መብት መጠየቅ ወንጀል ሲሆን፣ ወዘተ እንዴት ነው ሞጋች የሆነ ኅብረተሰብ መፍጠር የሚቻለው? ምክንያታዊነት ወደ ዳር እየተገፋ ፅንፈኛ ደጋፊና ተቃዋሚ የአገሪቱን ፖለቲካ ምኅዳር እያበላሸ ምን ዓይነት ሥርዓት ነው የሚገነባው? ተግባራዊ ምላሽ ያስፈልጋል፡፡

ኢሕአዴግ የመልካም አስተዳደር ችግሮችን ለመቅረፍ ጊዜ የለም የሚለው ምክንያት ቦታ የለውም ማለቱ ጥሩ ነው፡፡ የልማትና የመልካም አስተዳደር ጥያቄ የህልውና ጉዳይ እንደሆነ አስምሮበታል፡፡ ከዚህ በፊትም ዴሞክራሲ ቅንጦት ሳይሆን የህልውና ጉዳይ ነው ማለቱ አይዘነጋም፡፡ አሁን የሚያስፈልገው ግን በተግባር የታጀበ ቁርጠኝነት ነው፡፡ ቁርጠኝነት የሌለበት ፉከራና ቀረርቶ የትም አያደርስም፡፡ በመሆኑም ኢሕአዴግ በመጀመሪያ ራሱን ያጥራ፡፡ ውስጡ የተሰገሰጉ ኃላፊነት የማይሰማቸው፣ ሕዝብ የሚያንገላቱ፣ ሰብዓዊ መብት የሚጥሱ፣ ከማረም ይልቅ ለማጥፋት የሚቅበዘበዙ፣ በሐሰት ዕውነታን የሚያድበሰብሱና ሕዝባዊ ወገንተኝነት የሌላቸው በቃችሁ ይባሉ፡፡ በተግባር፡፡

የኢሕአዴግ አንዱ ትልቁ ችግር ከተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር ያለው የተበላሸ ግንኙነት ነው፡፡ እነዚህ በሰላማዊ መንገድ ተደራጅተውና አማራጭ ፖሊሲዎች ይዘው የሚታገሉ ኃይሎችን በፀረ ሕዝብነት መፈረጁ መቆም አለበት፡፡ በተግባር ባያደርገውም ድሮ እንደሚለው ግማሽ መንገድ ድረስ ተጉዞ በአገር ጉዳይ ላይ ሊያነጋግራቸው ይገባል፡፡ በማይግባባበት የፖሊሲ ልዩነት ላይ የራሱን አቋም እያራመደ፣ በጋራ ብሔራዊ ጉዳዮች ላይ ግን የውይይትና የድርድር መድረኮች በመፍጠር የተዘጋጋውን በር መክፈት አለበት፡፡ የጥላቻና የፅንፈኝነት ፖለቲካ ለአገሪቷ ስለማይጠቅም የፖለቲካ ምኅዳሩ ይከፈት፡፡ ተቃዋሚዎችን ማሰር፣ ማንገላታትና ለስደት መዳረግ ይቁም፡፡ ይህም በተግባር ይረጋገጥ፡፡

ኢሕአዴግ አሥረኛውን ጉባዔውን ሲያጠናቅቅ መላ አባላቱና አመራሩ ለድርጅቱ ውሳኔዎች ተግባራዊነት እንዲረባረቡ ጥሪ አቅርቧል፡፡ የሕዝቡን አደራ ለመወጣት ከፍተኛ ጥረት መደረግ እንዳለበትም አሳስቧል፡፡ ያለ ሕዝቡ ተሳትፎም የትም መድረስ እንደማይችል አስታውቋል፡፡ ለሕዝቡ የገባውን ቃል አክብሮ ወደ ተግባር የሚገባ ከሆነ ምሥጋና ይቸረዋል፡፡ ነገር ግን ወደ ተግባር መለወጥ ካልቻለ ጠቡ ከሕዝብ ጋር ነው፡፡ የሕዝቡን ማዕበላዊ ቁጣ ማቆምም አይቻልም፡፡ ከጉባዔው መልስ በቁርጠኝነት ተንቀሳቅሶ ሕዝቡን እያሳተፈ ተግባራዊ ዕርምጃ ካልወሰደ ውጤቱን ያየዋል፡፡ እንደተባለው ቃል በተግባር ከተደገፈ ግን ጠቀሜታው የላቀ ይሆናል፡፡ ለዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታም መሠረት ይጣላል፡፡ ዜጎች በእኩልነት የሚኖሩባት የበለፀገችና ዴሞክራሲያዊት አገር ትፈጠራለች፡፡ ይህ ምኞት ዕውን እንዲሆን ኢሕአዴግ የገባው ቃል በተግባር ይደገፍ!

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች

በዓለም አቀፍ ደረጃ ሕይወታቸውን በኤድስ ምክንያት ላጡ ሰዎች 35ኛ ዓመት መታሰቢያ

ያለፍንበትን እያስታወስን በቁርጠኝነት ወደፊት እንጓዝ - በኧርቪን ጄ ማሲንጋ (አምባሳደር) በየዓመቱ...

እዚያ ድሮን… እዚህ ድሮን…

በዳንኤል ካሳሁን (ዶ/ር) ተዓምራዊው የማዕበል ቅልበሳ “በሕግ ማስከበር” ዘመቻው “በቃ የተበተነ...

ለፈርጀ ብዙ የማንነት ንቃተ ህሊናችን የሚጠቅሙ ጥቂት ፍሬ ነገሮች

በበቀለ ሹሜ ከጨቅላነት ጅምሮ ያለ የእያንዳንዳችን የሰብዕና አገነባብ ከቤተሰብ እስከ...

በሲሚንቶ ፋብሪካ ላይ የታየው ተሞክሮ በሌሎች ምርቶች ላይም ይስፋፋ!

ሰሞኑን በኢትዮጵም ሆነ በአፍሪካ ደረጃ ግዙፍ ስለመሆኑ የተነገረለትን የለሚ...
spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

የአስተሳሰብና የአስተዳደር ዘይቤ ለውጥ ያስፈልጋል!

ኢትዮጵያ ውስጥ ሕዝቡን በጋራ አስተሳስረው የሚያኖሩ በጣም በርካታ ማኅበራዊ እሴቶች አሉ፡፡ እነዚህ ለዘመናት ከትውልድ ወደ ትውልድ ሲሸጋገሩ የኖሩ እሴቶች አገር ለማቆም ትልቅ አስተዋፅኦ ነበራቸው፣...

ድጋፍና ተቃውሞ እኩል ይስተናገዱ!

ኢትዮጵያ ውስጥ ለረዥም ዓመታት ለመንግሥት ከሚቀርቡ ጥያቄዎች መካከል አንዱ የመብት መከበር ጉዳይ ነው፡፡ ዜጎች ተፈጥሯዊም ሆኑ ሕጋዊ መብቶቻቸው እንዲከበሩላቸው ለመንግሥት ጥያቄ ሲያቀርቡ፣ ጥያቄው የቀረበለት...

ፖለቲካዊ ችግሮች ፖለቲካዊ መፍትሔ ይፈለግላቸው!

መንግሥት ከኦነግ ሸኔ ጋር በታንዛኒያ ዳሬሰላም ከተማ ሲያካሂድ የነበረው ንግግር ያለ ውጤት መጠናቀቁን ካስታወቀ በኋላ፣ በኦሮሚያ ክልልም ሆነ በሌሎች ቦታዎች ሰላም ለማስፈን የነበረው ተስፋ...