Tuesday, January 31, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜናየአዲስ አበባ አስተዳደር የካቢኔ ሹም ሽር ሊያደርግ ነው

የአዲስ አበባ አስተዳደር የካቢኔ ሹም ሽር ሊያደርግ ነው

ቀን:

–  የንግድ ቢሮ ኃላፊ አይቀጥሉም

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በቅርቡ ባካሄደው ግምገማ ዝቅተኛ የሥራ አፈጻጸም አስመዝግበዋል በተባሉ የካቢኔ አባል መሥሪያ ቤት ከፍተኛ ባለሥልጣናት ሹም ሽር ሊያካሂድ መሆኑ ተሰማ፡፡

ብዛት ያላቸው መሥሪያ ቤቶችን ይነካል በተባለው ሹም ሽር በሕግ ተጠያቂ የሚሆኑ ባለሥልጣናት እንደሚኖሩ ለጉዳዩ ቅርበት ያላቸው የከተማው አስተዳደር ከፍተኛ ባለሥልጣን ለሪፖርተር ተናግረዋል፡፡

ባለፈው ወር ከስምንት ቀናት በላይ በወሰደው ግምገማ እነዚህ ችግሮች እንዳሉባቸው የተገለጹላቸው የከተማው ባለሥልጣናት አምነው ተቀብለው ችግራቸውን ለማስተባበል ከመሞከር ይልቅ፣ አሻፈረኝ በማለታቸው ወደፊት ለሥራ እንቅፋት እንደሚሆኑ የአዲስ አበባ ኢሕአዴግ ጽሕፈት ቤት ድምዳሜ ላይ መድረሱ ተመልክቷል፡፡

በተለያዩ ችግሮች ተዘፍቀዋል የተባሉት የአስተዳደሩ መሥሪያ ቤቶች በርካታ ቢሆኑም፣ የጎላ ችግር ታይቶባቸዋል ከተባሉት መካከል የአዲስ አበባ መሬት ልማትና ማኔጅመንት ቢሮና በሥሩ የሚገኙት ሰባት ኤጀንሲዎች እስከ ወረዳ ድረስ ያለው መዋቅር፣ የአዲስ አበባ አቅም ግንባታ ቢሮ፣ የአዲስ አበባ ጥቃቅንና አነስተኛ ልማት ኤጀንሲ ይገኙበታል፡፡

ምንጮች እንደገለጹት ከመሬት ጋር የተያያዙ ችግሮች ወጥ በሆነ መንገድ ለመፍታት የተሠሩ ሥራዎች መልካም ቢሆኑም፣ በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር አሁንም በመሬት ጉዳዮች ላይ የሚሠሩ ተቋማት ሙስናና የመልካም አስተዳደር ችግሮች ይታያሉ ተብሏል፡፡

እነዚህን ችግሮች ለመቅረፍ አመራሩ ብዙ ርቀት መሄድ ባለመቻሉ የባለሥልጣናት ሹም ሽር ማካሄድ አስፈላጊ ሆኖ ተገኝቷል በማለት ምንጮች አስረድተዋል፡፡

ሌላኛው የሹም ሽር ትኩረት በአቅም ግንባታ ቢሮ ላይ ያነጣጠረ እንደሚሆንም ተጠቁሟል፡፡ የአቅም ግንባታ ቢሮ በከተማው ውስጥ በሚገኙ መሥሪያ ቤቶች ሪፎርም ማካሄድ የሚጠበቅበት ቢሆንም፣ ቢሮው በሚፈለገው መጠን ሥራውን ማካሄድ አልቻለም ተብሎ መገምገሙን ምንጮች ተናግረዋል፡፡ በቢሮው የሚገኙ ባለሥልጣናት ሹም ሽር እንደሚካሄድባቸው ተገልጿል፡፡ በጥቃቅንና አነስተኛ ልማት ኤጀንሲም ተመሳሳይ ችግሮች ከመንፀባረቃቸው በተጨማሪ በኃላፊዎቹ ዘንድ ሒስ የመቀበል ግትርነት ይስተዋላል ተብሎ ጠንከር ያለ ግምገማ መካሄዱ ታውቋል፡፡ በዚህ ምክንያትም በኤጀንሲው፣ በክፍለ ከተማና በወረዳ በሚገኙ መዋቅሮቹ ላይ ሹም ሽር ይካሄዳል ተብሎ ይጠበቃል፡፡

በከተማው ንግድ ቢሮ ላይ የጎላ ችግር ባይጠቀስም የቢሮው ኃላፊ አቶ ሺሰማ ገብረ ሥላሴ ለትምህርት ወደ ቻይና የሚጓዙ በመሆናቸው፣ ለንግድ ቢሮ አዲስ ኃላፊ ይሾምለታል ተብሎ ይጠበቃል፡፡

አቶ ሺሰማ የትምህርት ዕድል እንደተመቻቸላቸው አረጋግጠው፣ ከንግድ ቢሮ መሰናበታቸውን ተናግረዋል፡፡ በ2005 ዓ.ም. በተካሄደው ምርጫ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደርን ቁልፍ የተረከቡት አቶ ድሪባ ኩማ በሥልጣን በቆዩባቸው ዓመታት የካቢኔ ሹም ሽር አላደረጉም፡፡ የአቶ ድሪባ ካቢኔ በአብዛኛው በቀድሞው ከንቲባ አቶ ኩማ ደመቅሳ የአስተዳደር ዘመን የነበረ ነው፡፡

የአቶ ድሪባ ካቢኔ በመሠረተ ልማት ግንባታዎች ከሞላ ጎደል ተሳክቶለታል ቢባልም፣ በመልካም አስተዳደርና በሙስና ቅሬታ እየቀረበበት ይገኛል፡፡ ከንቲባ ድሪባ በሰኔ 2007 ዓ.ም. ለምክር ቤቱ ባቀረቡት ሪፖርት የመልካም አስተዳደርና የአገልግሎት አሰጣጥ ችግሮችን ለመፍታት ጥረት እየተደረገ ቢሆንም፣ አሁንም ችግሩ በሚፈለገው ደረጃ ባለመፈታቱ ቀጣይ ትኩረት የሚሻ ጉዳይ ይሆናል ማለታቸው ይታወሳል፡፡

የመልካም አስተዳደር ችግር ሰሞኑን በተካሄደው አሥረኛው የኢሕአዴግ ድርጅታዊ ጉባዔ ላይም ጎልቶ የወጣ ሲሆን፣ በተለይ ችግሩ በሚንፀባረቅበት አዲስ አበባ የተለየ ዕርምጃ እንደሚወሰድ እየተነገረ ነው፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የገጠር መሬት ማሻሻያና የመሬት ባለቤትነት ጥያቄ በኢትዮጵያ

በኢትዮጵያ ከቅርብ ወራት ወዲህ መሬትን በተመለከተ ጠንከር ያሉ የለውጥ...

በፖለቲከኞች እጅ ያለው ቁልፍ

ኢትዮጵያ በተለይ ካለፉት አምስት ዓመታት ወዲህ ሰላሟ መረጋጋት አቅቶታል፡፡...

የኤክሳይስ ታክስ ረቂቅ አዋጅ ፓርላማው ያፀደቀውን አዋጅ የሚጥሱ ድንጋጌዎችን በማካተቱ እንዳይፀድቅ ተጠየቀ

ሰሞኑን ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የቀረበው የኤክሳይስ ታክስ ማሻሻያ...

በፀጥታ ችግር ሳቢያ ከተለያዩ አካባቢዎች ተፈናቅለው አማራ ክልል የገቡ ዜጎች ቁጥር 800 ሺሕ መድረሱ ተነገረ

በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል 112 ሺሕ ተማሪዎች ከትምህርት ገበታ ውጪ...