ከነሐሴ 22 ቀን እስከ ነሐሴ 25 ቀን 2007 ዓ.ም. በመቐለ ከተማ የሰማዕታት አዳራሽ አሥረኛ ጠቅላላ ጉባዔውን ያካሄደው ኢሕአዴግ፣ የመልካም አስተዳደር ጉድለት የህልውና ጉዳይ በመሆኑ የሞት ሽረት ትግል እንደሚያደርግ ወስኗል፡፡ ከዚህ ቀደም በተደረጉ የተለያዩ ስብሰባዎች የመልካም አስተዳደር ችግር እንዳለ ከመግለጽ ባለፈ፣ ተጨባጭ ዕርምጃዎች እንዳልወሰደ በራሱ ላይ ግለ ሒስ ያካሄደው ኢሕአዴግ፣ አሁን ግን ችግሩ እየተባባሰ ስለመጣ በአጭር ጊዜ ለመቅረፍ ያስችለኛል ያለውን ፍኖተ ካርታ አዘጋጅቼያለሁ ብሏል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ ትኩረት የሚያደርግባቸው አራት ጉዳዮች የመሬት፣ የግብር አሰባሰብ፣ የመንግሥት ግዥና የኮንትራት አስተዳደር መሆናቸውን አስታውቋል፡፡ የድርጅቱን ውስጣዊ ጥንካሬና ድክመትም እንደሚፈትሽ፣ በሕዝብ ተሳትፎ ላይ የተመሠረተ አመራር እንደሚሰጥም ገልጿል፡፡ በምሥሉ ላይ የሚታዩት ከፍተኛ የኢሕአዴግ ባለሥልጣናት የድርጅቱ አመራር ምርጫ ተካሂዶ ውጤት በመጠባበቅ ላይ በነበሩበት ወቅት ነው፡፡ ዝርዝር ዘገባው ለመመልከት እዚህ ላይ ይጫኑ፡፡
ሰለሞን ጐሹ እና የማነ ናግሽ