Sunday, April 21, 2024
- Advertisment -
- Advertisment -

ግልጽ ደብዳቤ በአገር ውስጥና በውጭ ለምትገኙ ኢትዮጵያውያን

በኤፍሬም ይስሐቅ (ፕሮፌሰር)

የተወደዳችሁ ወንድሞቼና እህቶቼ!

“እንደ ወንድሞችና እህቶች ሆነን በጋራ ለመኖር መማር አለብን፣ አልያም እንደ ሞኞች ሆነን ሁላችንም እናልቃለን” – ማርቲን ሉተር ኪንግ

 የምንወዳት ኢትዮጵያ አገራችን ከጥንት ጀምሮ የሰላምና መቻቻል አገር መሆኗ ይታወቃል፡፡ ግሪካውያን፣ ዕብራውያን፣ ፋርሳውያንና ነቢዩ መሐመድ፣ ስመ ጥር ምሁራን (ምናልባትም የፕሮቴስታንት እምነት መሥራች ራሱ ማርቲን ሉተርን ጨምሮ) ኢትዮጵያ ተቻችለውና ተከባብረው በሰላም የሚኖሩባት አገር መሆኗን መስክረዋል፡፡

እ.ኤ.አ. ከ1987 እስከ 2009 በሲሪላንካ በነበረው የእርስ በርስ ጦርነት የተፈጠረውን ከፍተኛ ሥነ ልቦናዊ ጉዳት አስመልክቶ በሲሪላንካ ዩኒቨርሲቲ ተማሪ ዓምና የቀረበ የዶክቶሬት መመረቂያ ጽሑፍ ላይ የፈታኞች ኮሚቴ አባል ነበርኩኝ፡፡ በጥናቱ ላይ የአንድ አኃዛዊ መረጃ እንደሚጠቁመው በውጊያው ተሳታፊ የነበሩ ወታደሮች ሳያካትት ከ100 ሺሕ በላይ ሲቪሎች በግጭቱ ሕይወታቸው ጠፍቷል፡፡ ጽሑፉን አንብቤ እንደተረዳሁት ከሆነ የግጭቱ መሠረታዊ መነሻ በታሚል፣ ሲንሃልና ሙር መካከል በተፈጠረ ከፍተኛ የዘር ጥላቻ ነበር፡፡

ከመነሻው ጀምሮ የሰዎችን ማንነትና ክብር ለማራመድ ታስቦ የነበረውን  ያለመታደል ሆኖ በጥቂት የፖለቲካ ሰዎች ምክንያት የማንነት የበላይነትና ጥላቻ ፍልስፍና በሕዝቡ ላይ በመዝራት የመንግሥት የሥራ ቅጥርና አሠራር አድሏዊ የተሞላበት መሆኑ ከጊዜ በኋላ የተነሱ የመገንጠል ፍላጎቶችና በጎሳዎች መካከል የተፈጠረን ከፍተኛ የዘር ጥላቻና ፍርኃት ምክንያት በተፈጠረ ግጭት ሰዎች ሕይወታቸውን አጥተዋል፤ ንብረት ወድሟል፡፡

በአሁኑ ወቅት የምወዳቸው የአገሬ ሰዎች እርስ በርሳቸው ስድብና ጥላቻን የሚያንፀባርቁ ቃላት ሲወራወሩ ሳይ ትግራይ ይሁን ኦሮሞ፣ አማራ ይሁን ከሌሎች የአገሬ ቋንቋ ተናጋሪዎች ክፉ ነገር ስሰማ በጣም ተከፍቻለሁ፡፡ እኔ መቆጣት የምችል ሰው ባልሆንም ዛሬ ላይ ያለው የአገሬ ሁኔታ ሳይ እጅግ አስቆጥቶኛል፡፡ እኛ ኢትዮጵያውያን እርስ በርሳችን በጥላቻ ስንናቆር እኛን መጉዳት ለሚችሉ የውጭ ጠላቶቻችን ምቹ ሁኔታ እንፈጥርላቸዋለን፡፡

በአሁኑ ጊዜ ማዮ በተባለ ታዋቂ ክሊኒክ የባህል ብዝኃነት በጤናው መስክ ያለው አስፈላጊነት ላይ ንግግር ለማድረግ ተጋብዤ ነው ያለሁት፡፡ አብዛኛዎቹ ያገኘኋቸው የጤና ባለሙያዎች ጥላቻ ከካንሰር ጋር የሚነፃፀር መጥፎ በሽታ መሆኑን ከእኔ ጋር ይስማማሉ፡፡ ጥላቻ ሊታከም የሚገባ ክፉ በሽታ ነው፡፡ ይህ ካልሆነ ጥላቻን የተሸከመው ሰው ራሱን ያጠፈዋል፡፡ ጥላቻ ያለበትን ሰው የአዕምሮና የነርቭ ሥርዓቱን ያዛባዋል፣ በእርግጥ ዕድሜውንም ያሳጥረዋል፡፡

በአጭሩ ጥላቻ ያለብን ሰዎች ከሌሎች ይልቅ እኛን የበለጠ ይጎዳል፡፡ በተቃራኒው ፍቅርና መከባበር አዕምሮንና የነርቭ ሥርዓትን ያረጋጋል፡፡ አንዳንድ የማውቃቸው የሥነ ልቦና አዋቂዎች ሰውን ከመጉዳት ይልቅ ሰዎችን በማበረታታት የሕይወት አማራጮች እንዲኖሩዋቸው ያደርጋል፡፡ በእርግጥም ለሰው ልጅ በጎ ነገር መሥራትና ስለ ወደፊት ብሩህ ተስፋ ማሰብ በሰዎች ዘንድ ደስታና የተሟላ መንፈሳዊ ሕይወት ይፈጥራል፡፡

በአገራችን ያሉ ሁሉም ሃይማኖቶች ፍቅርንና መተዛዘንን ያስተምራሉ፡፡ ታላላቅ የአይሁድ፣ የክርስትናና የእስልምና ነቢያት ስለ ፍቅርና መተዛዘን አስተምረዋል፡፡ ሁሉም ራስህን ብቻ ሳይሆን ጎረቤትህንም ጭምር ውደድ ብለው ይሰብካሉ፡፡ ኢየሱስ ሳይቀር “ጠላትን እንደ ራስህ ውደድ” ብሎ አስተምሯል፡፡ ሰውን መጥላት ለማንኛውም ቅን ኢትዮጵያዊ አስቀያሚ አስተሳሰብ ነው፡፡

በወለጋ በ1940ዎቹ መጀመርያ የቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተማሪ በነበርኩበት ወቅት በእግርና በበቅሎ ተጉዣለሁ፡፡ በ1950ዎቹ መገባደጃና 1960ዎቹ መግቢያ የኢትዮጵያ ብሔራዊ የትምህርት ዘመቻን (የፊደል ሠራዊት) በዳይሬክተርነት (ጀኔራል ታደሰ ብሩን በመተካት) በመራሁበት ወቅት በደቡብና ምሥራቅ ኢትዮጵያ፣ እንዲሁም በሰሜኑ የአገራችን ክፍል አክሱም፣ ላሊበላና ጎንደር ተዘዋውሬአለሁ፡፡ በ1950ዎቹ አጋማሽ በሐርቫርድ ዩኒቨርሲቲ የዶክትሬት ምርምሬን ባካሄድኩባቸው በገጠር አካባቢ በደረስኩባቸው ቦታዎች ያገኘሁት ሰው ሁሉ  የዋህ፤ ሰው ወዳድንና ቸር ነበር፡፡ በዚህን ጊዜ አንድም ከኔ በላይ ላሳር የሚል፣ በጥላቻ የተሞላና አክብሮት የጎደለው ሰው አላጋጠመኝም፡፡ አንድም ጊዜ  ኦሮሞ፣ አማራ ወይም ትግራይ ወይም ከሌሎች የአገራችን ቋንቋ ተናጋሪ ሰው መሆኔን የጠየቀኝ ሰው አላስታውስም፡፡ ሁሌም በጉዞዬ ይገጥመኝ የነበረው “ደከመህ? ርቦሃል? ቤት ገብተህ ቡና መጠጣት ትፈልጋለህን?” የሚሉ ነበሩ፡፡ አብዛኞዎቹ ሰዎች ደሃዎች ነበሩ፡፡ ይሁን እንጂ ነፍሳቸውና መንፈሳቸው ከእኛ በጥላቻና በቁጣ ከተሞላነው ሰዎች በላይ ባለፀጎች ነበሩ፡፡

 በመካከላችን የፖለቲካ ልዩነቶች መኖራቸው አይካድም፡፡ መፍትሔ የሚያስፈልጋቸው ትልልቅ ችግሮች አሉን፡፡ አንዳንዶቻችን በሰላም ዙሪያ ተግተን በመሥራት ላይ የምንገኝ ሰዎች ዕቅድ አውጥተን ከመንግሥትና ተቃዋሚ ኃይሎች ጋር አሁን ለተከሰቱ ችግሮችና ግጭቶች መፍትሔ ለመፈለግ እየተንቀሳቀስን እንገኛለን፡፡ በእኔ አስተሳሰብ አደገኛ በሆነ ችግራችን “ጥላቻ” ብዬ በምጠራው ጉዳይ ላይ በማተኮር ከአዕምሯችን ፍቀን ለማስወገድ እንደ ወንድምና እህት በጋራ ቁጭ ብለን በሰከነ መንፈስ የአገራችን ችግሮች መፍታት ይገባናል፡፡

በአገራችን የጠንካራና እውነተኛ ዴሞክራሲ መኖርን የማይፈልግ ሰው የለም፡፡ ሆኖም እውነተኛ ዴሞክራሲና ፖለቲካዊ ስምምነት በጥላቻና በቁጣ ሳይሆን በተረጋጋ ውይይትና አክብሮት በተሞላበት ንግግር የሚገኝ ነው፡፡ ከዚያ በኋላ ሁሌም በጋራ የምንኖርበት “ስምምነት” መመሥረት እንችላለን፡፡

ወንድሞቼና እህቶቼ! ወቀሳ ካበዛሁባችሁ እባካችሁ ይቅር በሉኝ፡፡ የጥላቻ መልዕክትን እያስተላለፋችሁ ያላችሁ ሰዎች ጭምር እወዳችኋለሁ፡፡ ዘርን መሠረት ካደረገ ጥላቻና ቁጣ ተመልሳችሁ ኃይላችሁን ለፍቅርና ደግነት እንድታውሉ ፀሎቴ ነው፡፡ ራሳችንን ጎሳን መሠረት ካደረገ ጥላቻ ነፃ አድርገን የተለያዩ ማኅበረሰቦች የሚወክሉ ወጣቶችና ሴቶች ጠንካራ ተሳትፎና ጥምረት በመፍጠር እውነተኛ ዴሞክራሲ እንዲሠርፅ ማድረግ ያስፈልጋል፡፡

በተጨማሪም የምንወዳትን የጋራ ቤታችን ገንብተን በአንድነት ሆነን የጋራ ጠላቶቻችን የሆኑትን ድህነት፣ በሽታና ኋላ ቀርነት መዋጋት አለብን፡፡  እርስ በርስ የምንፈቃቀርና የምንከባበር ሕዝቦች መሆናችንን ለአፍሪካ ተምሳሌት እንሁን፡፡ አምላክ በሰላሙ መንገድ እንድንጓዝ ልቦናና ማስተዋል ይስጠን፡፡

ከአዘጋጁ፡- ፕሮፌሰር ኤፍሬም ይስሐቅ የጥንት ሴማዊ ቋንቋዎችና ሥልጣኔዎች እንዲሁም የአፍሪካ/ ኢትዮጵያ ቋንቋዎችና ሃይማኖት ሊቅ ናቸው፡፡ በፕሪንስተን ኒው ጀርሲ የሴማዊ ጥናቶች ተቋም ዳይሬክተር እንዲሁም የኢትዮጵያ የሰላምና ልማት ማዕከል የቦርድ ወንበር ናቸው፡፡ ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እንገልጻለን፡፡

spot_imgspot_img
- Advertisment -

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

Related Articles