Monday, July 15, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊ‹‹ፓርኪንሰን›› የዕድሜ ልክ ሕመም

‹‹ፓርኪንሰን›› የዕድሜ ልክ ሕመም

ቀን:

አቶ ቢያብል ጎበዜ የ72 ዓመት ዕድሜ ባለፀጋ፣ ባለትዳርና የሰባት ልጆች አባት ናቸው፡፡ ተወልደው ያደጉት ጎጃም ውስጥ ሲሆን፣ በኢሉ አባቦሩ ዞን በሚገኙ የተለያዩ የመንግሥት ከፍተኛ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች በመምህርነትና በርዕሰ መምህርነት አገልግለዋል፡፡ ከመንግሥት የትምህርት ተቋማት በጡረታ ከወጡ በኃላ አዲስ አበባ በሚገኙ ከዊንስ፣ አድማስና ኢትዮጲስ ኮሌጆች በዲንነት ሠርተዋል፡፡

ሁለቱም እጆቻቸውና መላው ሰውነታቸው ክፉኛ ይንቀጠቀጣሉ፡፡ በእንቅስቃሴ ላይም ሆነ ሌሊት ተኝተው መላ ሰውነታቸው ያለዕረፍት ይንቀጠቀጣል፡፡ ከዚህም ሌላ የመንቀሳቀስ ችግር አለባቸው፡፡ የሚንቀሳቀሱት በምርኩዝ ድጋፍና በሰው እየተረዱ ነው፡፡ አንድ ዕርምጃ ለመራመድ ምናልባትም ደቂቃዎች ሊፈጅባቸው ይችላል፡፡ የደረሰባቸውም የጤና ችግር ፓርኪንሰን ሕመም ይባላል፡፡ ሕይወታቸው ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ እንዳልነበረ አድርጎ ከቀየረው ፓርኪንሰን ጋር አብረው መኖር ከጀመሩ አምስት ዓመታት አስቆጥረዋል፡፡ በሽታው በጤናቸው ላይ ካደረሰው ቀውስ ባሻገር ለከፍተኛ የኢኮኖሚና ማኅበራዊ ችግሮች እንደዳረጋቸው አቶ ቢያብል ይናገራሉ፡፡

እ.ኤ.አ. በ1817 ‹‹የሚያንቀጠቅጥ ሕመም›› በሚል ስለሕመሙ በጻፈው በእንግሊዛዊው የቀዶ ሐኪም ዶ/ር ጀምስ ፓርኪንሰን ስም ተሰይሟል፡፡ የፓርኪንሰን ሕመም ጠቅላላ እንቅስቃሴንና ንግግርን የሚያውክ፣ በጊዜ ሒደትም አስከፊነቱ እየጨመረ የሚሄድ፣ ከአዕምሮ ጋር በተያያዘ የሚከሰት ችግር ነው፡፡ በብዛት የሚያጠቃውም ከ60 ዓመት በላይ የሆኑ ሰዎችን ነው እስካሁን የሕመሙ ማስታገሻ እንጂ መድኃኒት አልተገኘለትም፡፡

እንደ አቶ ቢያብል ያሉ የበሽታው ተጠቂዎች በሕይወት ለመቆየት አለማቋረጥ የማስታገሻ መድኃኒቱን መውሰድ ይኖርባቸዋል፡፡ ነገር ግን የመድኃኒቱ ዋጋ ለበርካቶች የማይቀመስ በመሆኑ መድኃኒቱን ለማግኘት ብዙ ይቸገራሉ፡፡

እንደ አቶ ቢያብል ገለጻ፣ በቀን ሁለት ጊዜ መድኃኒት ይውጣሉ፡፡ መድኃኒቱ ዋጋውም ከአቅማቸው በላይ ነው፡፡ ቤተሰቦቻቸው የሚተዳደሩት እሳቸው በሚያገኙት የጡረታ አበል ቢሆንም፣ አብዛኛው ወጪያቸው የሚውለው ለመድኃኒት ግዥ ላይ ነው  የቤት ኪራይ ለመክፈል ብዙ ይቸገራሉ፡፡ ያልተከፈለ ውዝፍ ዕዳም ተጠራቅሞባቸዋል፡፡ የሚበላ ቀለብ ጠፍቶ ከቤተሰቦቻቸው ጋር ይቸገራሉ፡፡

በአፍ የሚወሰድ አሥሩ ፍሬ መድኃኒት ዋጋው 75 ብር እንደሆነ፣ ከዚህም ሌላ ቤንዛሀክሶል የተባለ ተጨማሪ መድኃኒት እንደሚጠቀሙ፣ በአጠቃላይ ለመድኃኒት ግዥ ብቻ በወር እስከ 500 ብር እንደሚያወጡ፣ ይህም ሆኖ ግን ሁሉም መድኃኒቶች የሚያገለግሉት ለማስታገስ ብቻ እንደሆነና ተመራማሪዎች መድኃኒቱን ለማግኘት እየለፉ መሆኑን፣ ይህም ተስፋ እንደሰጣቸው ተናግረዋል፡፡

‹‹የመድኃኒቱ ዋጋ ውድ ከመሆኑ ባሻገር አልፎ አልፎ ከገበያ የሚጠፋበት ጊዜ አለ፡፡ ሊጠፋ የሚችለውም አንዳንድ መደኃኒት ቤቶች በርካሽ ዋጋ ገዝተው ይሸሸጉና እጥረት ሲፈጠር አውጥተው በውድ ዋጋ ይሸጡታል፤›› በማለት አርቲፊሻል እጥረት የሚፈጥሩ መድኃኒት ሻጮች መኖራቸውን ይናገራሉ፡፡

አቶ ታሊሞስ ዳታ የፓርኪንሰን ፔሸንትስ ሰፖርት ኦርጋናይዜሽን ኢትዮጵያ ዋና ሥራ አስኪያጅ ናቸው፡፡ እንደ ሥራ አስኪያጅ ገለጻ፣ ፓርኪንሰን ሕሙማን ካጋጠሟቸው በርካታ ችግሮች መካከል በዋናነት የሚጠቀሰው የመድኃኒት አቅርቦትና ሥርጭት፣ እንዲሁም የዋጋ ውድነት ነው፡፡ በመድኃኒቱም ዋጋ ውድነት ምክንያት እንዷን ፍሬ በአንድ ጊዜ መዋጥ ሲገባቸው ሰብረው ለሁለት ጊዜ የሚጠቀሙ አሉ፡፡ ችግሩ እየሰፋ ሲሄድ ለአካል ጉዳተኝነት እንደሚዳረግና በአካል ጉዳተኞች ዙሪያ የሚሠሩ ሴክተር መሥሪያ ቤቶችና ሎች ባለድርሻ አካላት በጉዳዩ ላይ ጣልቃ እንዲገቡ ጠይቀዋል፡፡

የፓርኪንሰን ሕመምተኛና የድርጅቱ መሥራች ወይዘሮ ክብራ ከበደ፣ ‹‹ሰዎች በፓርኪንሰን ሕመም መጠቃት የጀመሩት ጊዜ መቼ እንደሆነ አይታወቅም፡፡ በጣም ረዥም ጊዜ እንደሆነ ይገመታል፡፡ ምናልባትም የሰው ልጆች ሲፈጠሩ አብሮ የተፈጠረ ሳይሆን እንደማይቀር አንዳንድ ጥናቶች ይጠቁማሉ፤›› ብለዋል፡፡

ፓርኪንሰን ከጊዜ ወደ ጊዜ እየባሰበት የሚሄድና እንቅስቃሴ የሚያውክ ከባድ ከአዕምሮ ጋር የተያያዘ ሕመም ነው፡፡ በመላው ዓለም 10 ሚሊዮን የሚሆኑ ሰዎች ከፓርኪንሰን ጋር አብረው ይኖራሉ፡፡ በኢትዮጵያ ይህንን ጉዳይ አስመልክቶ የተደረገ ጥናት ባይኖርም አዲስ አበባ ውስጥ ብቻ ከ500 በላይ የፓርኪንሰን ሕሙማን እንዳሉ ይታመናል፡፡ እስካሁን በድርጅቱ ተመዝግበው በአባልነት የታቀፉት ግን 188 ብቻ ናቸው፡፡ ይህም ቁጥር ሆስፒታል ያልመጡትን፣ መጥተውም ያልተመዘገቡትን እንደማያካትት ወ/ሮ ክብራ ተናግረዋል፡፡

በጤና ጥበቃ ሚኒስቴር በሽታዎች መከላከልና መቆጣጠር ባለሙያ አቶ አበባው አየለ ፓርኪንሰን በኢትዮጵያ እምብዛም የማይታወቅ ቢሆንም ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራዎችን በተከታታይ በማከናወን ኅብረተሰቡ በሽታውን እንዲረዳው ማድረጉን ገልጸው፣ በየደረጃው ባሉ ጤና ተቋማት አገልግሎቱ የሚሰጥበትን አግባብና በዚህ ችግር የሚጠቁ ሰዎች ወደ ሕክምና ተቋም እየሄዱ ሕክምናውን የሚያገኙበትን መረጃ በመስጠት እየተንቀሳቀስን መሆኑን አስረድተዋል፡፡

በአዕምሮ ጤና ስትራቴጂ ውስጥ ፓርኪንሰን ከሚጥል በሽታ ጋር ተካትቶ በተደራጀና በተጠናከረ መልኩ የሕክምና አገልግሎት የሚሰጥበት ሁኔታ በማመቻቸት ላይ መሆኑንም ተናግረዋል፡፡ ፓርኪንሰን የማከም ሥራ በዋነኝነት የሚኒስቴሩ ድርሻ ቢሆንም ሌሎች ባለድርሻ አካላትም ሊተባበሩ እንደሚገባ ገልጸዋል፡፡

የፓርኪንሰን ምልክቶች የሰውነት ሚዛን መጠበቅ አለመቻል፣ መንቀጥቀጥ፣ እግር ለመራመድ መቸገር፣ ሰውነት ጨምድዶ መያዝ፣ ድብርት፣ የድምፅ ጥራትና መጠን መቀነስ፣ ድርቀት፣ እንቅልፍ ማጣት፣ የማሽተት ችግር ናቸው፡፡

ፓርኪንሰን ሕመም ተላላፊ እንዳልሆነ፣ በብዛት የሚያጠቃው ከ60 ዓመት በላይ ያሉን ወንዶችን ነው፡፡ አንድ ሰው ፓርኪንሰን ሲይዘው በፓርኪንሰን መያዙን ወዲያው ላይገነዘበው ይችላል፡፡ በፍፁም በፓርኪንሰን እያዛለሁ ብለው ሳይገምቱ ታማሚ ሆነው ሊገኙ ይችላሉ፡፡ መጣ ሄደት የምትል ትንሽ የእጅ መንቀጥቀጥ ተገንዝቦ ማን የአስቸጋሪው ሕመም ምልክት ናት ብሎ መገመት ይችላል?

ለምን ፈገግ እንደማይሉ ወይም ለምን ቀስ ብለው እንደሚራመዱ አያውቁት ይሆናል፡፡ የበሽታው ምልክት ሁሉ እንደ ተራ ነገር ሊቆጠር ይችላል፡፡ ምልክቶቹ እየበረቱና እየተደጋገሙ ሲሄዱ ብቻ ነው በጥርጣሬ ‹‹ምን ነክቶኝ ነው፡፡ መመርመር አለብኝ፤›› ብለው ሐኪም ማማከር የሚጀምሩት፡፡

የፓርኪንሰን ሕመም ደግሞ ዶፓሚን በሚባል የኬሚካል እጥረት የሚከሰት የሕመም ዓይነት ነው፡፡ የዶፓሚን እጥረት በምርመራ አይታይም፡፡ የሚታወቀውም ምልክቶቹን በማየት ነው፡፡ መንቀጥቀጥ፣ ሰውነት ጨምድዶ መያዝ፣ የሰውነት ሚዛን መሳት የመሳሰሉት የበሽታው መለያ ምልክቶች ናቸው፡፡

አንዳንድ ጊዜ የፓርኪንሰን ተጠቂው በዕረፍት ላይ በሚሆንበት ወቅት እጅ ብቻ ወይም እጅና እግር አንዳንድ ጊዜ ምላስና አገጭ ሊንቀጠቀጥ ይችላል፡፡ የሚንቀጠቀጠው እጅ ሥራ ሲሠራ ለምሳሌ ቡና ለመቀበል በሚዘረጋበት ጊዜ መንቀጥቀጡ ይቆማል፡፡ ወዲያው እጅ ሲያርፍ መንቀጥቀጡ ይጀምራል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ሚዲያው በሕዝብ የህሊና ችሎት ከተዳኘ በቂ ነው!

መሰንበቻውን ድንገት ሳይታሰብ ያለ ማስጠንቀቂያ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ...

የባህር በር ጉዳይ

በታምሩ ወንድም አገኘሁ ድሮ ድሮ ገና ልጅ ሆኜ ፊደል እንደቆጠርኩ...

አገሩ ፖለቲካዊ ስክነትና መደማማጥ ያስፈልገዋል

በንጉሥ ወዳጀነው    ኢትዮጵያ የሁላችንም የጋራ ቤት ነች፡፡ ‹‹ጥያቄዬ ተመለሰልኝ››፣...

የመንግሥት የሰብዓዊ መብት ተቋም ለምን የመንግሥት ሚዲያን ማስተማር አቃተው

በገነት ዓለሙ የአገራችን የ2016 የበጀት ዓመት መሰናበቻና የአዲሱ የ2017 በጀት...