Thursday, June 13, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

ማኅበራዊሸመታ የተጠናወታቸው

ሸመታ የተጠናወታቸው

ቀን:

ሽበት ጣል ጣል ያደረገበት ፀጉራቸውን ጥቅልሉ ሳይፈታ ወደ ኋላ አስይዘውታል፡፡ ያደረጉት ልጥፍ ጉትቻ ከፊት ቅርፃቸውና ከፀጉር አያያዛቸው ጋር ሄዷል፡፡ ቦርሳቸውን ከጫማቸው፣ ሱሪውን ከአላባሹ አዋደው የለበሱ በ50ዎቹ መጀመርያ ላይ የሚገኙ ሽቅርቅር ወይዘሮ ናቸው፡፡ ወጣ ያለ ቀለም ያለው ሀር መሳይ ሱሪና ሸሚዛቸው ለየት ያለ ነገር ግን ሳቢ የሆነ አለባበስ ነበር፡፡ የተቀቡት ውድ ሽቶም እንደዚሁ ከመደዴው የሚለያቸው ነው፡፡

የአንድ ልጅ እናት የሆኑት ወ/ሮ ሳባ መላኩ ከባለቤታቸው ጋር የተለያዩት ተጋብተው ብዙም ሳይቆዩ ከ30 ዓመት በፊት ነበር፡፡ መምህር ሆነው ለጥቂት ዓመታት ሠርተዋል፡፡ በአስተማሪነት ሙያ ያገኙት የነበረው ደመወዝ በቂያቸው አልነበረምና ሥራቸውን ወደ ጎን ብለው ወደ ጂቡቲ ተሰደዱ፡፡ በጂቡቲ በአንድ ቤተሰብ ውስጥ ለሙያቸው ቅርብ በሆነው በልጅ አስጠኝነት ተቀጠሩ፡፡ ቀጣሪዎቻቸው በሳምንት አንድ ቀን እንዲያርፉ ያደርጓቸው ነበር፡፡

ያቺን አንድ ቀን የሚያሳልፉት ከጓደኞቻቸው ጋር በመዝናናት፣ ወይም ተጨማሪ ሥራ በመሥራት አልነበረም፡፡ በዕረፍት ቀናቸው በእጃቸው ያለውን ገንዘብ ይዘው ገበያ ይወጣሉ፡፡ አልባሳት፣ የተለያዩ የቤት ውስጥ መገልገያ ዕቃዎች፣ ጌጣ ጌጦችና ሌሎችም ነገሮችን ይሸምታሉ፡፡ መጀመርያ አካባቢ የሚያስፈልጋቸውንና ቢኖረኝ ብለው የሚያስቡትን ነበር ይሸምቱ የነበረው፡፡ ቀስ በቀስ ግን ገበያ መውጣትና መሸመትን እንደ ጊዜ ማሳለፊያ፣ መዝናኛ፣ ብቸኝነታቸውን የሚረሱበት አጋጣሚ አድርገው ይጠቀሙበት ያዙ፡፡ ለአንድ ልጃቸውና ለወላጆቻቸው እንዲሁም ለሌሎች በቅርብ ለሚያውቋቸው ሁሉ ሳይቀር ዕቃ እየገዙ መላክ ሥራዬ አሉ፡፡ ጥሩ ነገር አይተው ማለፍ አይችሉም፤ ለራሳቸው ባይሆን እንኳ ለሌላ ሰው መግዛታቸው አይቀርም፡፡

- Advertisement -

‹‹የምገዛው ጥሩ ዕቃ፣ ኪስ በማይጎዳ ዋጋ ነው፡፡ ጥሩ ዕቃና አሪፍ ዋጋ ያለባቸውን አካባቢዎችም ለይቼ አውቃለሁ፡፡ የምሸምተውም በተመረጡ አካባቢዎች ነው፡፡ ጓደኞቼንም ይዤ እሄድ ነበር፤›› የሚሉት ወ/ሮ ሳባ ሽቅርቅርና ዘናጭ የሆኑበት ሚስጥር አብዝቶ መግዛታቸው ብቻ ሳይሆን ጥሩ ዕቃ ማወቅና የቱ ከየቱ ጋር ይሄዳል? የሚለውን አውቀው መልበሳቸው እንደሆነ ይናገራሉ፡፡

ማንኛውም ዓይነት ቀለም ያለው፣ ጥራት ያላቸው ውድ ጨርቆችና ውድ ውድ ብራንዶችን ያሰባስባሉ፡፡ አንዳንዶቹን የሚለብሱበት አጋጣሚ ጠባብ ቢሆንም ግን እንዲኖራቸው ስለሚፈልጉ ብቻ ይገዛሉ፡፡ መኖሪያ ቤታቸው ውስጥ የሚገኙ ሁለት ትልልቅ ቁምሳጥኖች ሞልተዋል፡፡ የተረፉትን አልባሳት በትልልቅ ሻንጣ ሞልተው ያስቀምጣሉ፡፡ ስካርፍና የውስጥ ልብሶች ሳይቀሩ ከሻንጣ በላይ ናቸው፡፡ ጫማዎቻቸውን ወደ ላይ ሁለት ሜትር ያህል ርዝማኔ ያለው ቁም ሳጥን እንኳ አልቻላቸውም፡፡

ያላቸውን የልብስ ቁጥር ፈጽሞ አያውቁትም፡፡ ሁሉም አልባሳት፣ መጫሚያዎችና ጌጣ ጌጦች ግን የሚለበሱበት የየራሳቸው ፕሮግራም አላቸው፡፡ ሐበሻ  ቤተ ክርስቲያን ለመሳም፣ የአዘቦት፣ የዓመቱ ትልልቅ በዓላት ሲኖሩ የሚለብሷቸው፣ ለሠርግ፣ ገዳም ሲሄዱ የሚጠቀሙዋቸው የአገር ባህል ልብሶች ሁሉ ለብቻ ናቸው፡፡ ቅዳሜና እሑድ፣ በሥራ ቀናት የሚለብሱትም የተለየ ነው፡፡ በሐዘን ጊዜ የሚለብሷቸው ልብሶች ለቀብር፣ ለሰልስትና ለተዝካር የተለያየ ነው፡፡ የዋና ፓንቶቻቸውም እንደዚሁ ከቁጥር በላይ ናቸው፡፡ የሚገዟቸውን ነገሮች ሁሉ በዚህ መልኩ ለተለያየ ተግባር ስለሚያስፈልጉኝ ነው እያሉ ወደ ሱስ የተጠጋ የመግዛት አመላቸውን በምክንያት የሚያደርጉት እንደሆነ ራሳቸውን ያሳምናሉ፡፡

ጓደኞቻቸው ጥሩ ዕቃ ስለሚያውቁ ወይዘሮዋን ሳያስከትሉ ወደ ገበያ መውጣት አይሆንላቸውም፡፡ ሊያጋዙ በሄዱበት አጋጣሚ ታዲያ ጥሩ ዕቃ ካገኙ ለሌላ ጉዳይ የያዙትን ገንዘብ አውጥቶ፣ ከሌላቸው ተበድሮ ከመግዛት ወደ ኋላ አይሉም፡፡ በቤት፣ በመኪናና በሌሎችም ወሳኝ የሽያጭ ድርጅቶች ሳይቀር አስተያየታቸውን የማይጠይቃቸው የለም፡፡ ለዓመታት ያዳበሩትን የመግዛት ፍቅር የሱስ ያህል የሆነባቸው ይመስላል፡፡

አብዛኞች በሚያገኙት ገንዘብ መጠን ነገሮችን በፕሮግራም ማስኬድን፣ አላስፈላጊ ወጪዎችን ከማውጣት ደግሞ መቆጠብ ተቀማጭ ማድረግን ይመርጣሉ፡፡ ለነገሩ ሁሉም ኑሮውን በዚህ መልኩ ቢመራ ምርጫው ነው፡፡ መተግበሩ ግን በተለያዩ ሁኔታዎች አስቸጋሪ ይሆናል፡፡ በብዛት ደባል ሱሶች ያለባቸው ገንዘብ በፕሮግራም መጠቀም ተራራ የመግፋት ያህል ከባድ ሊሆንባቸው እንደሚችል አይጠረጠርም፡፡ ከተለመዱት የአልኮል፣ የትምባሆ፣ የአነቃቂና አደንዛዥ ዕፆች ሱስ ባሻገር አዘውትረው የሚገዙ፣ የመግዛት አመላቸውን በፕሮግራም መገደብ የማይችሉ፣ በገበያ ማዕከላት፣ በየሱቁና በየቡቲኩ ካልገቡ ቅር የሚላቸው የመግዛት ሱስ ተጠናውቷቸው እንደሆነ ያስጠረጥራል፡፡

ከመጠን ያለፈ የመግዛት አመል ያለባቸውን ድርሳናቱ ‹‹ሾፓሆሊክ›› (Shopaholic) ይሏቸዋል፡፡ ሾፓሆሊክነት ሱስ ነው? አይደለም? በሚል በሁለት ጎራ የተከፈሉ ክርክሮች አሉ፡፡ ሱስ ነው የሚሉት ወገኖች አንድ ሰው ያለምክንያት አዘውትሮ ከመግዛት ራሱን መቆጣጠር ካልቻለ፣ አመሉ የሚያስገድደው ከሆነ መግዛት ሱስ ሆኖበታል ሾፓሆሊክ ሆኗል ማለት ነው ይላሉ፡፡ በሌላው ጎራ ያሉት ደግሞ ሾፓሆሊክነት ሱስ ሳይሆን አደገኛ ግን የግለሰቡ ፈቃድ ከታከለበት መቆጣጠር የሚቻል አመል ነው በማለት ይከራከራሉ፡፡ ይሁንና ሁለቱም ወገኖች ሾፓሆሊክነት በአንድም ይሁን በሌላ መልኩ ችግር መሆኑን ግን ይስማማሉ፡፡

አንዳንድ ጥናቶች እንደሚያሳዩት፣ አዲስ ነገር ግዙ ግዙ የሚያሰኝ ከፍተኛ መሻት የራሱ የሆነ ሳይንሳዊ መሠረት አለው፡፡ ሾፓሆሊክ የሆኑ ሰዎች አዲስ ነገር ሲገዙ አንጎላቸው ኢንደርፊንና ዶፓሚን የተባሉ ኬሚካሎችን ይለቃል፡፡ እነዚህ ኬሚካሎች ሰዎች ደስተኛ ስሜት እንዲያድርባቸው የማድረግ ባህሪ አላቸው፡፡ ይህ ነገር በተደጋጋሚ ጊዜ ሲከሰት አንጎል ኢንዶርፊንና ዶፓሚንን በመልቀቅ ሱስ ይጠመዳል፡፡ ደጋግሞ ለመልቀቅም ደጋግመው እንዲሸምቱ ያስገድዳቸው ይጀምራል፡፡

በዚህ መልኩ ሸመታን የሚያዘወትሩ ሰዎች በሆነው ባልሆነው በከፋቸውና ቅር ባላቸው ቁጥር አዲስ ነገር በመግዛት ደስተኛ ለመሆን ይሞክራሉ፡፡ ምርጥ ዕቃዎችን ፈልገው በመሸመት ሱስ የተጠመዱም አሉ፡፡ እነዚህ ሰዎች መጀመርያ ወደውና ከብዙ ዕቃዎች መካከል መርጠው የገዙትን ቆይተው ሊጠሉት ወይም የተሻለ ያልገዙት ነገር እንዳለ ስለሚሰማቸው ተመልሰው ወደ ገበያ ይሮጣሉ፡፡ ሌላ ምርጥ መስሎ የታያቸውን ይገዛሉ፡፡

አንዳንዶቹ ሾፓሆሊኮች ደግሞ የዕቃውን ዋጋ ዓይተው የሚማረኩ ናቸው፡፡  አንድ ነገር አስፈለጋቸውም አላስፈለጋቸውም በቅናሽ መሸጡ ብቻ እንዲገዙት ይገፋፋቸዋል፡፡ ብዙ ገንዘብ አውጥተው እንደሚዘንጡ ለሌሎች ማሳወቅ የሚፈልጉ ደግሞ ውድ የሆነና በሁሉም ዓይን ውስጥ የሚያስገባቸውን ነገር ሲሸምቱ ከፍተኛ ገንዘብ የሚያወጡ ናቸው፡፡ አብዝተው በመግዛታቸው የጥፋተኝነት ስሜት የሚሰማቸውና የገዙትን ሲመልሱ፣ እግረ መንገዳቸውን መልሰው ሌላ የሚገዙም አሉ፡፡ ሁሉም ነገር እንዲኖራቸው የሚፈልጉና ባገኙት አጋጣሚ አዲስ ነገር ለመግዛት ኪሳቸውን የሚዳብሱ ሾፓሆሊዎች አሉ፡፡ ከፍተኛ የመግዛት መሻት ያለባቸው እነዚህ ሰዎች በማንኛውም ቦታ ሆነው ቢያንስ በሳምንት አንዴ ወይም በተወሰኑ ቀናት ልዩነት አዲስ ነገር ለመግዛት ይገደዳሉ፡፡

የ28 ዓመቷ ዓይናለም አሥራትም በየሳምንቱ ቅዳሜ አዲስ ነገር ለመግዛት ወደ ደንበኞቿ ሱቅ ትሄዳለች፡፡ ቅዳሜን መደበኛ የግዥ ቀን አድርጋ ስለምትወስድ እንጂ በሌሎቹ የሳምንቱ ቀናት አትገዛም ማለት አይደለም፡፡ ዓይናለም 22 አካባቢ ልብስና ኮስሞቲክስ መሸጫ ሱቅ እንዳላት ትናገራለች፡፡ ለሱቋ የሚያስፈልጉትን ነገሮች ባህር ማዶ ሄዳ ስታመጣ ለራሷ የሚሆኑ አልባሳት ውድ ውድ ሽቶዎች ገዝታ ትመለሳለች፡፡

ነገር ግን ይህ ብቻ ስለማይበቃት ልትሸጥ ካመጣቻቸው ነገሮች የወደደቻቸውን ብድግ ከማድረግ አትቆጠብም፡፡ በራሷ ሱቅ የማታገኛቸውን ነገሮች ደግሞ ከጎኗ ከሚገኙ ሱቆች ትገዛለች፡፡ እያንዳንዱ የምትገዛቸው ሽቶዎች ከ3,300 እስከ 3,500 ብር ድረስ ዋጋ እንዳላቸው ትናገራለች፡፡ የገዛችው ሳያልቅ በላይ በላይ ስለምትገዛ ያሏትን የሽቶዎች ቁጥር አታውቀውም፡፡ ዲዎድራንትም እንዲሁ ፋሺን በመጣ ቁጥር ስለምትገዛ ምን ያህል እንዳላት አታውቅም፡፡ ሊፒስቲክና ሌሎች የመዋቢያ ግብዓቶች የምትገዛው ፋሸኑን እየተከተለች ስለሆነ ስብስቦቿ ብዙ ናቸው፡፡

‹‹ቀሚስ ለባሽ ነኝ፡፡ ነገር ግን ሱሪና ካናቴራዎችም በብዛት እገዛለሁ፡፡ አሪፍ ነገር ባገኘሁ ቁጥር አላልፍም፡፡ ጥራት ያለው ነገር ደስ ይለኛል፡፡ አንዳንዴ ዕቃውን ከወደድኩት የቻይናም ቢሆን እገዛለሁ፤›› አለች ከተወለደች 40 ቀን ያልሞላት አራስ ልጇን እያባበለች፡፡ ፋሸን መከተል እንደሚያስደስታት የምትናገረው ዓይናለም ሾፓሆሊክ ስለመሆን አትጨነቅም፡፡ ለሷ የወደደችውን መልበስና ማጌጥ ከምንም ነገር በላይ ነው፡፡ በየሳምንቱ ከምትገዛቸው አንዳንድ አልባሳትና ኮስሞቲክሶች ውጪ በሦስትና በአራት ወራት ልዩነት እስከ 7,000 ብር መድባ የምትሸምትበት መደበኛ ፕሮግራም አላት፡፡ ባየች ቁጥር የምትገዛቸው ነገሮች በሷ ዓይን ከቁጥር አይገቡም፡፡

የሚያስጨንቃት ነገር በፕሮግራም መግዛት ሳይሆን የትኛው ለየትኛው ፕሮግራም ወይም ዝግጅት ይለበሳል፣ የሚለው ጉዳይ ነው፡፡ አገዛዟ የሌላት እንዲኖራት ነገር እንዲኖራት ሳይሆን መግዛት ስለምትወድ ይመስላል፡፡ ‹‹ፀጉሬ በጣም አሪፍ ነው፡፡ ነገር ግን ሂውማን ሄር ፋሽን ስለሆነ ሂውማን እቀጥልበታለሁ፡፡ ከዓመት በፊት የገዛሁት 22 ኢንች ሂውማን ሄር ፋሽኑ ስላለፈበት ሌላ 24 ኢንች ገዝቻለሁ፤›› የምትለው ዓይናለም ወጪ ማብዛት የለብኝም ብላ ወስና እንደምታውቅ፣ ነገር ግን ብዙም እንዳልተሳካላት ትናገራለች፡፡ ለነገሩ ብዙም ችግር የሆነባት አትመስልም፡፡

ነግዳ ከወጪ ገቢ የምታገኘው በአማካይ 4,500 ብር አካባቢ ሲሆን፣ ይህ ግን እንዳሻት የምትገዛቸውን አልባሳትና የመዋቢያ ግብዓቶች ወጪን እንኳ የሚሸፈን አይደለም፡፡ ስለዚህም ቀሪ ወጪዋን የሚሸፍነው ባለቤቷ እንደሆነ ትናገራለች፡፡ ካላት የመግዛት ፍቅር የተነሳ ለባለቤቷ ለበዓላት አልያም ለሌላ ፕሮግራም ስጦታ የሚሰጣት የምትፈልገውን ነገር የምትገዛበትን ገንዘብ ነው፡፡

ለረዥም ጊዜ ገበያ ሳትወጣ የቆየችበት ጊዜ ልጇን ወልዳ የተኛችበት 40 የማይሞሉ ቀናት ናቸው፡፡ ልጇን ለመገላገል ሆስፒታል ከመግባቷ ሰዓታት አስቀድማ ግን ወደ ገበያ ሄዳ የአመሏን አድርሳለች፡፡ የልጇን ክርስትና አስታካም የ16,000 ብር የአገር ልብስ የመረጠችው ባለፈው ሳምንት ነበር፡፡

ፀጉሯን በቄንጥ አበጥራ፣ ጉትቻዋን ከለበሰችው ቡራቡሬ ካናቴራ አስማምታ የለበሰችው ሌላዋ የ31 ዓመቷ ማርታ ዋለልኝ ‹‹እኔ ለራሴ የማላደርገው ነገር የለም፡፡ ዓይቼ የወደድኩትን ሁሉ እገዛለሁ፡፡ ወደ ቤቴ ስገባም የሆነ ነገር ይዞ መግባት ደስ ይለኛል፤›› ስትል አንድም የወደደችውን ነገር ከመግዛት ወደ ኋላ እንደማትል ትናገራለች፡፡

በወር የምታገኘው 4,200 ብር ደመወዝ በብዛት ለራሷ የሆነ ነገር በመሸመት ነው የምታጠፋው፡፡ የምትገዛው የሚያስፈልጋትን ሳይሆን ዓይታ የወደደችውን ስለሆነ እሷም እንደ ሌሎቹ ፕሮግራም አታውቅም፡፡ እንዲያውም ፕሮግራም ማውጣት በራሷ ላይ ገደብ እንደማስቀመጥ ያህል ነው የሚሰማት፡፡ ‹‹የማደርገው የአገር ውስጥ ጫማ ነው፡፡ አንድ ጫማ እስከ 1,200 ብር እገዛለሁ፡፡ በአንዴ ሁለትና ከዚያ በላይ ነው የምገዛው፤›› አለች ብትገዛ ከስንት ጊዜ አንዴ ዙር ደርሶት ወደ ተጫማችው በእጇ እየጠቆመች፡፡

ተመላልሳ የምትገዛቸው ደንበኞቿ በተደጋጋሚ ስለምትጎበኛቸው ቅርርባቸው እንደ ሻጭና ደንበኛ ሳይሆን ወደ ቤተሰብነት ደረጃ ከፍ ብሏል፡፡ በበዓላት ጊዜ ከሱቃቸው የመረጠችውን አዲስ ዕቃ እንድትወስድ የሚፈቅዱላት ደንበኞች አፍርታለች፡፡ እሷ ግን ስጦታው ብቻ ስለማይበቃት ጨምራ ትገዛቸዋለች፡፡ የተጠናወታት የመግዛት አመል ወደ ሌሎች ጓደኞቿም አጋብታለች፡፡ የሷን ያህል ባይሆንም መግዛት ያዘወትሩ ጀምረዋል፡፡  

አዳዲስ የገበያ ሞሎችና ሱቆችን ስታይ የመጎብኘት ግዴታ ያለባት ይመስል ጎራ ማለት ታበዛለች፡፡ በዚያ አጋጣሚ የወደደችው ነገር ካለ ካላት ከፍላ ከሌላት ደግሞ ቀብድ ሰጥታ ትወስዳለች፡፡

የወንዶች አልባሳት መሸጫ ሱቆችን ሁሉ መጎብኘት ያስደስታታል፡፡ በዚያውም ለወንድ ጓደኛዋ የወደደችውን መርጣ ትገዛለታለች፡፡ ‹‹የቅርብ ዘመዱ አርፈው ሐዘን ላይ ነው፡፡ ለቅሶ መድረስና ማጽናናት አልቻልኩም፡፡ ስለዚህም ፒያሳ ከሚገኝ አንድ ሱቅ ሁለት የሐዘን ልብሶች ገዝቼ ሰጠሁት፤›› ትላለች፡፡ ምናልባት የራሷን ቤተሰብ ብትመሠረት አመሏን በመጠኑ ለመቀነስ እንደምትችል የምትናገረው ማርታ ገንዘብ ቆጥባ እንደማታውቅ፣ በባንክ የሚገባላትን ደመወዝ አውጥታ ሙሉ ለሙሉ እንደምትጠቀመው ስትናገር የምንተ እፍረቷን እየሳቀች ነበር፡፡

እርግዝናዋን እንደ ሸክም ሳይሆን እንደ ጌጥ ስትዋብበት የከረመችው ሳድሳዊት አብርሃም ደግሞ ከአሥር በላይ የሚሆኑ የነፍሰ ጡር ልብሶች ማቀያየር ሥራዋ ያደረገችው በእርግዝናዋ የመጀመርያ ወራት ጀምሮ ነው፡፡ የ3,000 ብር ደመወዝተኛዋ  ሳድሳዊት ደመወዟ የማያወላዳ ዓይነት ቢሆንም፣ በተወሰኑ ቀናት አዲስ ነገር ትገዛለች፡፡

አብዛኛውን ወጪዎቿን የሚሸፍኑላትም ባህር ማዶ የሚገኙ ዘመዶቿ አሁን ደግሞ ባለቤቷ ነው፡፡ ከሚልኩላት ገንዘብ ሌላ የሚጭኑላት ውድ ውድ ሽቶዎችና ብራንድ ልብሶች ተጨማሪ ከመግዛት የሚገድባት አይደለም፡፡ ‹‹የጓጓሁለትን ለመግዛት አልሳሳም›› የምትለው  ሳድሳዊት  ልብሶቿ ቁም ሳጥን ሞልተው በሻንጣ ቢታጨቁም ይበቃል ብላ መግዛቷን እንደማታቆም ስትናገር ሳትጨነቅ ነው፡፡ ሲበዛ አንስታ ለተቸገሩ ትሰጣለች እንጂ አለመግዛት እንደማትችል ትናገራለች፡፡ ላልተወለደች ልጇ ሳይቀር መግዛት ከጀመረች ቆየት ብላለች፡፡ ‹‹ምናልባት ወደ ልጄ ላደላ እችላለሁ እንጂ መግዛት አላቆምም፤›› ትላለች፡፡

ሾፓሆሊክ እሆን ይሆን? የሚለው ጉዳይ ሳያስጨንቃቸው እንዳሻቸው ያዩትን፣ የወደዱትን ሁሉ የሚሸምቱ እንደ  ሳድሳዊት  ያሉ ገዝተው መሽቀርቀርን ሥራዬ ብለዋል፡፡ እንደ ወ/ሮ ሳባ በቀልድ የተጀመረ የመግዛት ሱስ በጀት ከማናጋት ባለፈ በርካቶች ዕዳ ውስጥ እንዲገቡ፣ ተቀማጭ ብለው የሚያስቀምጡት መጠባበቂያ ገንዘብ እስኪያጡ ባዶ እጃቸውን እያስቀራቸው ይገኛል፡፡ ሾፓ ሆሊክነት ባደጉት አገሮች ክትትል የሚደረግለት ማኅበራዊ ችግር ነው፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

[ክቡር ሚኒስትሩ በመንግሥት የሚታወጁ ንቅናቄዎችን በተመለከተ ባለቤታቸው ለሚያነሱት ጥያቄ ምላሽ ለመስጠት እየሞከሩ ነው]

እኔ ምልህ? እ... ዛሬ ደግሞ ምን ልትይ ነው? ንቅናቄዎችን አላበዙባችሁም? የምን ንቅናቄ? በመንግሥት...

የመንግሥት የ2017 ዓ.ም በጀትና የሚነሱ ጥያቄዎች

የ2017 ዓመት የመንግሥት ረቂቅ በጀት ባለፈው ሳምንት መገባደጃ ለሚኒስትሮች...

ከፖለቲካ አባልነትና ከባንክ ድርሻ ነፃ የሆኑ ቦርድ ዳይሬክተሮችን ያካተተው ብሔራዊ ባንክ ያዘጋጃቸው ረቂቅ አዋጅና መመርያዎች

የኢትዮጵያ የብሔራዊ ባንክ የፋይናንስ ተቋማትን የተመለከቱት ድንጋጌዎችንና የባንክ ማቋቋሚያ...

የልምድ ልውውጥ!

እነሆ መንገድ ከቦሌ ሜክሲኮ። አንዱ እኮ ነው፣ ‹‹እንደ ሰሞኑ...