የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ባካሄደው የቀበሌ ቤቶች ቆጠራ በስድስት ክፍላተ ከተሞች 140 ሺሕ ቤቶች እንዳሉት አረጋገጠ፡፡ በ1996 ዓ.ም. በተካሄደ ጥናት የከተማው አስተዳደር ከ150 ሺሕ በላይ የቀበሌ ቤቶች እንዳሉት ቢገለጽም፣ በአስተዳደሩ ዕውቅና ለመልሶ ማልማት ፕሮግራሞች የፈረሱ ቤቶች የመኖራቸውን ያህል በሕገወጥ መንገድ የግል ይዞታ የተደረጉ፣ ፈርሰው ከግል ይዞታ ጋር የተቀላቀሉ፣ ተስፋፍተው የተገነቡ፣ ወደ ግል ይዞታነት የተለወጡ በመኖራቸው በሕገጦች ላይ ዕርምጃ እንደሚወስድ ተገልጿል፡፡
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የቤቶች አስተዳደር ኤጀንሲ ባለፈው ዓመት የጀመረውን ቆጠራ በተያዘው በጀት ዓመት አጠናቋል፡፡ በዚህ ቆጠራ በመሀል አዲስ አበባ በሚገኙት ቂርቆስ፣ አራዳ፣ አዲስ ከተማ፣ ልደታ፣ ጉለሌና የካ ክፍላተ ከተሞች 140 ሺሕ ቤቶች መኖራቸው ተገልጿል፡፡ በአራቱ የማስፋፊያ ክፍላተ ከተሞች ቦሌ፣ ንፋስ ስልክ ላፍቶ፣ ኮልፌ ቀራኒዮና አቃቂ ቃሊቲ አነስተኛ ቁጥር ያላቸው የቀበሌ ቤቶች አሉ ተብሏል፡፡
የከተማው አስተዳደር ምን ያህል ቤቶች እንዳሉት በመረጃ ለማወቅ፣ መረጃውንም አውቆ ካርታ እንዲወጣላቸው፣ በሕገወጥ መንገድ በተያዙት ላይም ዕርምጃ ለመውሰድ መረጃ እንዲሰበሰብ ወስኗል፡፡
በዚህ መሠረት አስተዳደሩ ከ140 ሺሕ ትንሽ ከፍ የሚሉ ቤቶች እንዳሉት ያረጋገጠ ሲሆን፣ የቤቶች አስተዳደር ኤጀንሲ ምክትል ሥራ አስኪያጅና የቤት ርክክብና ማስተላለፍ ዋና ሥራ ሒደት መሪ ወ/ሮ አፀደ ዓባይ ለሪፖርተተር እንደገለጹት፣ ያሉት የቀበሌ ቤቶች ካርታ ይወጣላቸዋል፡፡
‹‹ለቀበሌ ቤቶቹ ካርታ እየተዘጋጀ ነው፡፡ ካርታው የሚዘጋጀው በኤጀንሲው ስም ነው፡፡ ለሕገወጥ ድርጊት በተጋለጡት ላይ ደግሞ የማስተካከያ ዕርምጃ ይወሰዳል፤›› ብለዋል፡፡