እኛ ኢትዮጵያውያን ከገባንበት ቀውስ ውስጥ ለመውጣት ከእኛ በላይ ማንም እንደሌለ ማመን ይገባናል፡፡ ባዕዳን መጡም ሄዱም ከራሳችን በላይ በማንም መተማመን የለብንም፡፡ ኢትዮጵያውያን በታሪካቸው ለማንም ጥገኛ ሆነው አያውቁም፡፡ የጥገኝነት አስተሳሰብና ሥነ ልቦና የሌለው ሕዝባችን በታሪክ ያጋጠሙትን ፈተናዎች ያለፈው፣ በጠንካራ አንድነቱና ኅብረቱ ነው፡፡ በዚህ ዘመንም ይህ ጥሩ ልምድ ሊያገለግለን ሲገባ ባዕዳን ሥር መርመጥመጥ እየበዛ ነው፡፡ እኛ ውስጣችንን በድፍረት መፈተሽና የጎደሉንን ነገሮች ያለምንም መደባበቅ መነጋገር ስንጀምር፣ እንኳን ወደ ባዕዳን ልናንጋጥጥ ከእነ መፈጠራቸውም አናስታውሳቸውም፡፡ ከምንም ነገር በላይ ማመን ያለብን ነፃነታችን እጃችን ውስጥ መሆኑን ነው፡፡ ምክንያታዊ ሆነን በሠለጠነ መንገድ መነጋገር ከቻልን፣ መጀመርያ መግባባት ያለብን የሕግ የበላይነት እንዲሰፍን ነው፡፡ ሰላማዊና ሥልጡን ዴሞክራሲያዊ ትግል የሚፈልገው በሕግ የበላይነት ማመን ነው፡፡ የሕግ የበላይነት ሲኖር ሐሳብን በነፃነት መግለጽና መሰብሰብ፣ የሚፈልጉትን መደገፍና መቃወም ይቻላል፡፡ ሕግ እንዲከበር ሕጋዊ መሆን እንደሚያስፈልገው ሁሉ፣ ሕግ የሚጥሰውንም ፍትሕ ደጃፍ ለማቅረብ ይጠቅማል፡፡ ለአገር ህልውና ከልባቸው የሚያስቡ ይህንን ጉዳይ በጥሞና ሊያስቡበት ይገባል፡፡
አንድ አገር ሉዓላዊ ነው ሲባል የውስጥ ጉዳዩን ያለማንም ጣልቃ ገብነት የማከናወን መብቱን ማሳያ ነው፡፡ በእርግጥ አገሮች እርስ በርስ በሚያደርጓቸው ግንኙነቶች የሚጋሯቸው ወይም የሚተባበሩባቸው ጉዳዮች ሲኖሩ፣ ከውጭ ጉዳይ ፖሊሲያቸውም ይመንጭ ወይም ከራሳቸው አገራዊ ፍልስፍና አንፃር የሚያነጋግሯቸው በርካታ ጉዳዮች ይኖራሉ፡፡ የአንዱ አላስፈላጊ ተግባር ሌላውን የሚጎዳ ወይም ገጽታውን የሚያበላሽበት ከሆነ ችግሩ ሰፍቶ ሊቃረኑም ይችላሉ፡፡ ነገር ግን በዚህ በሠለጠነ ዘመን አገሮች ቢያንስ እ.ኤ.አ. በ1948 በወጣው የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ሁለንተናዊ የሰብዓዊ መብቶች ድንጋጌና በሌሎች መሰል ዓለም አቀፍ ስምምነቶች መሠረት ተግባራቸውን ካከናወኑ፣ በሁለትዮሽም ሆነ በባለ ብዙ ዘርፍ ግንኙነቶች የሚግባቡባቸው በርካታ መስኮች ይኖራሉ፡፡ ትልቁ ችግር ግን ኢትዮጵያን ጨምሮ በርካታ አገሮች፣ በተለይ በዴሞክራሲና በሰብዓዊ መብቶች ምክንያት በዓለም አቀፍ ደረጃ ሲወቀሱና ሲወገዙ መስማት የተለመደ ነው፡፡ ልማትን አስቀድሞ ዴሞክራሲን ችላ የሚል አገር በውስጡ ስምምነት ስለማይኖር፣ አገራችን ላለፉት ሁለት ዓመታት በላይ የገባችበትን ቀውስ ያስገነዝበናል፡፡ የአገር ህልውና አሳሳቢ ሁኔታ ውስጥ ገብቶ ሕዝብ ግራ በተጋባበት በዚህ ወቅት፣ ከገባንበት ማጥ ውስጥ ለመውጣት የብልህና የአስተዋይ ኢትዮጵያውያን ዕውቀትና ልምድ መፈለግ አለበት፡፡ በጨዋነትና በአስተዋይነት የታደለው የኢትዮጵያ ሕዝብ ሁለገብ ተሳትፎ ሲጨመርት ደግሞ፣ አገርን ወደ ትክክለኛው መንገድ መመለስ ይቻላል፡፡ ኢትዮጵያውያን ምሁራን፣ የአገር ሽማግሌዎች፣ የሃይማኖት መሪዎች፣ በተለያዩ የሙያ መስኮች የተሰማሩ ዜጎችና የመሳሰሉት እየተገፉ ወደ ውጭ ማፍጠጥ ግን ያስተዛዝባል፡፡ የአገር አለኝታ ልጆቿ እንጂ ማንም ሊሆን አይችልም፡፡
አገር የሚያስተዳድረው መንግሥት ሕግ ተከብሮ ዜጎች በነፃነት የሚኖሩበትን ዴሞክራሲያዊ አውድማ ማዘጋጀት ባለመቻሉ ብቻ፣ የሕዝብ ምሬት ከመጠን በላይ ሆኖ አገር ቀውስ አጋጥሟታል፡፡ ለዓመታት የተጠራቀሙ ብሶቶች ከቁጥጥር ውጪ ሆነው የንፁኃን ሕይወት ጠፍቷል፡፡ በአገር ላይ ከፍተኛ ውድመት ደርሷል፡፡ በመደበኛው የሕግ ማስከበር ሥርዓት አልተቻለም ተብሎ ከአንዴም ሁለቴ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ታውጇል፡፡ ይህ ሁሉ የሆነው በየደረጃው በመንግሥት ሥልጣን ላይ የተቀመጡ ሰዎች በፈጠሩት ችግር ነው፡፡ ሕዝብን ማዳመጥ ነውር እስኪመስል ድረስ በርካታ ጥፋቶች ተፈጽመዋል፡፡ የፖለቲካ ምኅዳሩ ተዘጋግቶ መተናፈሻ እስኪጠፋ ድረስ አገር የገባችበት ሥቃይ ይታወቃል፡፡ የፖለቲካውን ምኅዳር ለማስፋት ተብሎ ከተወሰዱ የቅርብ ጊዜ ዕርምጃዎች መካከል፣ ከፖለቲካ ጋር በተገናኘ የታሰሩ ሰዎችን መፍታትና ክስ ማቋረጥ ይገኝበታል፡፡ በሕግ የበላይነት ወይም ሌላው ቢቀር በሕገ መንግሥቱ ዋስትና የተሰጣቸው መሠረታዊ መብቶች ቢከበሩ ኖሮ አገር ለቀውስ አትዳረግም ነበር፡፡ በአግባቡ ልንጠቀምባቸው የሚገቡ ወርቃማ አጋጣሚዎች እንደ ዋዛ ቀልጠው፣ ያጋጠመው ቀውስ እንደ እሳት በሚጋረፍ ወቅት በቁጭት እንንገበገባለን፡፡ ነገር ግን የተበላሹ አጋጣሚዎችን እየተቆጨንባቸው ለአገር ህልውና ስንል ወደ ቀልባችን መመለስ ከቻልን አሁንም ዕድሉ አለ፡፡ ይህንን ጀግና፣ አስተዋይና ጨዋ ሕዝብ ይዞ ከልብ በመፀፀት መነሳት ያስፈልጋል፡፡ የአገር ጉዳይ ከምንም ነገር በላይ ስለሆነ ከልብ ይታሰብበት፡፡
ሥልጣንን ብቻ በማሰብ የሚደረጉ ፈራቸውን የሳቱ እንቅስቃሴዎች ውጤታቸው ዕልቂትና ውድመት መሆኑን የግድ ሶሪያና የመንን ወይም ሊቢያን መጥቀስ የለብንም፡፡ በነጋ በጠባ ዓለም አቀፍ ሚዲያው የዜና ርዕስ የሚያደርጋቸው የወደሙ አገሮች ለማንም አዲስ አይደሉም፡፡ ጤነኛ አዕምሮ ያለው ሰው ደግሞ ዓይኑ እያየ ለሥልጣን ሲል ብቻ የአገሩን ህልውና አሳልፎ ይሰጣል ተብሎ አይጠበቅም፡፡ አገር በተወሰኑ ወፈፌዎች ምክንያት ህልውናዋ አደጋ ውስጥ እንዲወድቅ የሚፈልጉ ካሉ፣ ጠባቸው አገሩን በጥልቅ ፍቅር ከሚወደው ሕዝብ ጋር ነው፡፡ በአገር ጉዳይ ባዕዳን ጣልቃ የሚገቡት ከሕዝብ ይልቅ ለሥልጣን ያሰፈሰፉ ወይም ሥልጣን ወይም ሞት ብለው የወሰኑ ካሉ ብቻ ነው፡፡ እንዳለመታደል ሆኖ ግን አንድ የምዕራብ አገር መሪ ወይም እንደራሴው በተንቀሳቀሰ ቁጥር ጥገኞች ሲወራጩ ማየት የተለመደ ሆኗል፡፡ የአገሩን ሚስጥር ከሚሸጠው ሞሽላቃ ጀምሮ የአገር ጉዳይ ደንታ የማይሰጠው ከንቱ ድረስ ብዙ ትዝብቶች አሉ፡፡ አሜሪካም ሆነች ሩሲያ እያሰሉ የሚመጡት ዘላቂ ጥቅማቸውን ነው፡፡ ይህንንም ጥቅም ለማስከበር እስከቻሉት ድረስ እጅ ከመጠምዘዝ አይመለሱም፡፡ ግንኙነቱን ከፖለቲካ ሥልጣን አንፃር ብቻ በመመልከት የአገርን ጉዳይ ችላ ማለት በታሪክ ያስጠይቃል፡፡ የአጥቂነትና የተከላካይነት ባህሪ ተላብሶ በባዕዳን የፖለቲካ ቁማር መስከር ለአገር አይበጅም፡፡ ሕዝብም አይፈልገውም፡፡
ኢትዮጵያ አገራችን ከምንም ነገር በላይ ሰላም ያስፈልጋታል፡፡ ሰላም እንዲሰፍን ደግሞ የሕዝቡ ዴሞክራሲያዊና ሰብዓዊ መብቶች መከበር አለባቸው፡፡ ፈረንጅ ዴሞክራሲያችሁ ታዳጊ ነው ስላለን የምንፅናና ካለን፣ ወይም በንዴት የሚያነጫንጨን ካለን ማዘን ያለብን በራሳችን ነው፡፡ ያለፉት 27 ዓመታት ብዙ የምንማርባቸውና ብዙ አመርቂ ውጤቶችን የምናስመዘግብባቸው መሆን ቢችሉ ኖሮ፣ በባዕዳን ዘንድ መዘባበቻ የሚያደርገን ችግር ውስጥ አንገባም ነበር፡፡ ሰላማዊው የፖለቲካ ትግል ሕዝብን ማዕከል ቢያደርግና በሰጥቶ መቀበል መርህ መንቀሳቀስ ቢቻል እኮ፣ ለአገራችን ዴሞክራሲያዊ ምርጫም ይባል ሐሳብን በነፃነት መግለጽ፣ መደራጀም ሆነ የፈለጉትን የፖለቲካ ፓርቲ መደገፍ ብርቅ አይሆንም ነበር፡፡ ፍትሕ ርቆ እንደተሰቀለ አይቀርም ነበር፡፡ በእኩልነት መስተናገድ አያጨቃጭቅም ነበር፡፡ መከፋትና ማመፅ የወጣቱ የትውልድ አጀንዳ አይሆንም ነበር፡፡ በዚህም ሳቢያ ክቡር የሆነው የሰው ሕይወት በከንቱ አይጠፋም ነበር፡፡ ይህ መሆን ባለመቻሉና ችግሮች የበለጠ በመባባሳቸው ሳቢያ ያጋጠመን ቀውስ ሌሎችን እንዳሳሰባቸው እንሰማለን፡፡ ያደፈጡ ታሪካዊ ጠላቶች ደግሞ እርስ በርስ ተባልተን እስክንዳከም ይጠብቁናል፡፡ አገር ያለችው እንዲህ ዓይነት አጣብቂኝ ውስጥ ነው፡፡
የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ አሁንም አንፃራዊ ሰላም ለማስገኘት ካልሆነ በስተቀር፣ ዘለቄታዊ መፍትሔ እንደማያመጣ ማንንም ያለማንገራገር ያግባባል፡፡ አሁን በፍጥነት የሚያስፈልገው የደፈረሰውን ሰላምና መረጋጋት ወደነበረበት መመለስ ነው፡፡ ለዚህ ደግሞ ትግዕሥት ያስፈልጋል፡፡ ይኼ ትዕግሥት የሚጀምረው የተተኪውን ጠቅላይ ሚኒስትር ሹመት ከማመቻቸት ጀምሮ ነው፡፡ የሥልጣን ሽግግሩ ፍፁም ሰላማዊ፣ ዴሞክራሲያዊና የኢትዮጵያ ሕዝብን የሚያግባባ ቢሆን የምትጠቀመው አገር ናት፡፡ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ አፈጻጸም ጥንቃቄ የተሞላበት፣ ሕግና ሥርዓትን ከማስከበር የዘለለ እንዳይሆን መሥራት ተገቢ ነው፡፡ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ለመገንባት የሚቻለው ለብጥብጥና ለበለጠ ችግር የሚዳርጉ ድርጊቶች ሲወገዱ ነው፡፡ አገሪቱ በገጠማት ችግር ሳቢያ ሕዝብ እየተጎዳ ነው፡፡ ንግድና ኢንቨስትመንት እየተቀዛቀዙ ነው፡፡ ወጥቶ መግባት እያስፈራ ነው፡፡ ይህንን ዓይነቱን ጨፍጋጋ ወቅት በብልኃት ማሳለፍ ያስፈልጋል፡፡ ይህ ብልኃት ሁሉንም ወገን የሚያግባባና አገርን ማዕከል ያደረገ መሆን አለበት፡፡ አንዱ አሸናፊ ሌላው ተሸናፊ ሆኖ የሚወጣበት ውጣ ውረድ አገር ከማጥፋት ውጪ የሚፈይደው የለም፡፡ ኢትዮጵያውያን በሙሉ በዚህ አሳሳቢ ወቅት በፅሞና መነጋገር አለባቸው፡፡ የሚወዷት እናት አገራቸው ከዚህ ቀውስ ወጥታ ለዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ፣ ለአስተማማኝ የኢኮኖሚ ዕድገትና ለዘለቄታዊ ሰላም እንድትበቃ የማድረግ ኃላፊነት የመላ ኢትዮጵያውያን መሆኑን ማመን አለባቸው፡፡ የአገር ፍቅር ትርጉሙ ጥንታዊያን ኢትዮጵያውያን እንዳደረጉት ለአገር ማንኛውንም ዓይነት መስዋዕትነት በመክፈል መታደግ እንጂ፣ አገርን ለቀውስ እየዳረጉ ሕዝብን የማይወጣው ችግር ውስጥ መክተት አይደለም፡፡ ለሥልጣን ብቻ ሲሉ አገር የሚያተራምሱ ከታሪካዊ ጠላቶች ተለይተው አይታዩም፡፡ የአገር ህልውና ለድርድር መቅረብ አይችልምና!