Friday, April 19, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜና‹‹ኢትዮጵያ ላጋጠማት ችግር መፍትሔው ለሕዝቡ ሰፋ ያለ ነፃነት መስጠት እንደሆነ ፅኑ እምነታችን...

‹‹ኢትዮጵያ ላጋጠማት ችግር መፍትሔው ለሕዝቡ ሰፋ ያለ ነፃነት መስጠት እንደሆነ ፅኑ እምነታችን ነው››

ቀን:

የኢትዮጵያ ወቅታዊ ሁኔታና የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ማብራሪያ

የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሬክስ ቲለርሰን

በአወዛጋቢ ንግግራቸው የሚታወቁትና ለአፍሪካ ግልጽ ፖሊሲ የላቸውም ተብለው የሚነገርላቸው ዶናልድ ትራምፕ የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ሆነው ከተሾሙ በኋላ፣ ለመጀመርያ ጊዜ በከፍተኛ ኃላፊነት ደረጃ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሬክስ ቲለርሰን የካቲት 28 ቀን 2010 ዓ.ም. ኢትዮጵያ መጥተው ነበር፡፡ ሚኒስትሩ አዲስ አበባ የቆዩት ለ38 ሰዓታት ቢሆንም፣ በቆይታቸው ኢትዮጵያና አሜሪካ ስላላቸው የሁለትዮሽ ግንኙነት በተመለከተ ከኢትዮጵያ መንግሥት ኃላፊዎች ጋር ከመነጋገራቸውም በላይ፣ ኢትዮጵያ ስላለችበት ወቅታዊ ሁኔታ መግለጫ ሰጥተዋል፡፡ ሚኒስትሩ ወደ ኢትዮጵያ ይመጣሉ ከተባለበት ጊዜ ጀምሮ የተለያዩ አከራካሪ አስተያየቶች ሲደመጡ ነበር፡፡ የእሳቸው ወደ ኢትዮጵያ መምጣት የሽግግር መንግሥት በሚቋቋምበት ሁኔታ ላይ ለመምከር ነው ከሚለው ጀምሮ ሌሎች ሐሳቦች ሲንሸራሸሩ ተደምጧል፡፡ ሚኒስትሩ ስለኢትዮጵያ ወቅታዊ ሁኔታ ሲናገሩ፣ መንግሥታቸው ስለሁከትና ስለሰዎች ሕይወት መጥፋት የኢትዮጵያ መንግሥት ያለውን ምልከታ እንደሚረዳና እንደሚጋራው ገልጸው፣ ‹‹ኢትዮጵያ ላጋጠማት ችግር መፍትሔው ለሕዝቡ ሰፋ ያለ ነፃነት መስጠት እንደሆነ ፅኑ እምነታችን ነው፤›› ብለዋል፡፡ በኢትዮጵያ የሥልጣን ሽግግር እየተከናወነ እንደሆነ ገልጸው፣ ይህም በፈቃደኝነት የሚደረግ ሥልጣን ማስተላለፍ የመጀመርያው ነው ብለዋል፡፡ ለታዳጊው የኢትዮጵያ ዴሞክራሲም አዎንታዊ ምሳሌ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ 

- Advertisement -

Video from Enat Bank Youtube Channel.

የኢትዮጵያ ፖለቲካዊ ችግር አሁንም መቋጫ አላገኘም፡፡ በተለያዩ ዓመታት የተለያየ መልክና ገጽታ እየያዘ የመጣው የአገሪቱ ቀውስ አሁንም አፋጣኝ ፖለቲካዊ መፍትሔ እንደሚያሻው እየተነገረ ነው፡፡ ባለፈው ሳምንት ዜጎችን ለሞትና ለአካል ጉዳት የዳረገ ችግር ተፈጥሮ ነበር፡፡ በኦሮሚያ ክልል በተጠራው የሥራ ማቆም አድማ ብቻ ዜጎች ለሕልፈተ ሕይወት ተዳርገዋል፡፡ በአገሪቱ የተፈጠረው አለመረጋጋት የተለየ መልክ እየያዘ መምጣቱን፣ የመከላከያ ሚኒስትርና የኮማንድ ፖስቱ ሴክሬታሪያት ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ ሲራጅ ፈጌሳ የካቲት 28 ቀን 2010 ዓ.ም. በሰጡት መግለጫ ተናግረዋል፡፡ ‹‹በተፈጠረው ሁከት በ17 የፀጥታ አካላት ላይ ጉዳት ደርሷል፣ በአራት ተሽከርካሪዎች ላይ ቃጠሎና በአሥር የሕዝብ ማመላለሻ አውቶብሶች ደግሞ በድንጋይ መሰባበር ችግር ደርሷል፡፡ የቀሌ ጽሕፈት ቤቶች ተቃጥለዋል፡፡ የመሣሪያ ነጠቃ ድርጊትም ተከናውኗል፤›› ሲሉ በጋዜጣዊ መግለጫቸው ወቅት አስረድተዋል፡፡

መንግሥት በአገሪቱ በተለይም 2010 ዓ.ም. ከገባ ወዲህ እየተባባሰ የመጣውን ቀውስ ለማስቆም በመላ አገሪቱ ለስድስት ወራት ተግባራዊ የሚሆን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ቢያውጅም፣ በሰውና በንብረት ላይ ጉዳት ደርሷል፡፡ አዋጁ ከታወጀ በኋላ ግን አንፃራዊ መረጋጋት መታየቱን አቶ ሲራጅ አስረድተዋል፡፡ ቀውሱም ገጽታውን እየተቀየረና የቀለም አብዮት መልክ እየያዘ እንደመጣ አስረድተዋል፡፡

በአወዛጋቢ ንግግራቸው የሚታወቁትና ለአፍሪካ ግልጽ ፖሊሲ የላቸውም ተብለው የሚነገርላቸው ዶናልድ ትራምፕ የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ከሆኑ በኋላ፣ ለመጀመርያ ጊዜ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ሬክስ ቲለርሰን የካቲት 28 ቀን 2010 ዓ.ም. ከቀትር በኋላ ወደ ኢትዮጵያ መጥተው ነበር፡፡ ሚኒስትሩ ወደ ኢትዮጵያ ይሄዳሉ ተብሎ ከተሰማበት ጊዜ ጀምሮ የተለያዩ ሐሳቦች ሲንፀባረቁ ተስተውሏል፡፡ የእሳቸውን ወደ ኢትዮጵያ የመምጣት ዕቅድ ከተሰማ ጀምሮ፣ አገር አቀፍና ዓለም አቀፍ ሚዲያዎች በዘገባዎቻቸው ሰፊ ሽፋን ሰጥተውታል፡፡ በአንድ በኩል የእሳቸው ወደ ኢትዮጵያ መምጣት ለረዥም ጊዜ የአሜሪካ አጋር እንደሆነች የሚነገርላት ኢትዮጵያ ቀውስ ውስጥ መግባት አሳስቧት ነው የሚሉ፣ በሌላ በኩል ደግሞ ኢትዮጵያ ስላለችበት ወቅታዊ ሁኔታ ሳይሆን ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ለማጠናከር ነው የሚሉ አስተያየቶች ሲነገሩ ተደምጧል፡፡ ከአሜሪካ መንግሥት ደግሞ በአገሪቱ ሰላማዊ የሥልጣን ሽግግር በሚካሄድበት ላይ ለመምከር ነው የሚለው ተሰምቷል፡፡

የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ቲለርሰንና የኢትዮጵያ አቻቸው ወርቅነህ ገበየሁ (ዶ/ር) የካቲት 29 ቀን 2010 ዓ.ም. በሸራተን ሆቴል ጋዜጣዊ መግለጫ ሲሰጡ፣ ዶ/ር ወርቅነህ በመክፈቻ ንግግራቸው እንዳሉት፣ ከአሜሪካ አቻቸው ጋር በቀጣናዊና በአኅጉራዊ ሰላምና ደኅንትነት፣ እንዲሁም በሁለቱ አገሮች መካከል ስላለው የምጣኔ ሀብት ግንኙነት ውይይት አድርገዋል፡፡

የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር በበኩላቸው፣ በኢትዮጵያና በአሜሪካ መካከል ስላለው የጋራ ጥቅም ከኢትዮጵያ አቻቸው ጋር ውይይት ማድረጋቸውን ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ ጠቁመዋል፡፡ የሁለቱ አገሮች የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች የጋራ መግለጫ ከመስጠታቸው በፊት ቲለርሰን ከአፍሪካ ኅብረት ኮሚሽን ሊቀመንበር ሙሳ ፋቂ መሃማት ጋር ውይይት አድርገዋል፡፡ የውይይታቸውን ይዘት በተመለከተም በኅብረቱ አዳራሽ ለጋዜጠኞች መግለጫ ሰጥተዋል፡፡

ቲለርሰንና መሃማት መግለጫቸውን በአምስት ሰዓት ትኩል የጨረሱ ሲሆን፣ ቀጣይ ፕሮግራም ከቀኑ ስድስት ሰዓት ላይ በሸራተን ሆቴል ተገኝተው ከዶ/ር ወርቅነህ ጋር ስለሁለቱ አገሮች ግንኙነትና የኢትዮጵያ ወቅታዊ ሁኔታ መግለጫ ይሰጣሉ ተብሎ ተጠብቆ ነበር፡፡ ነገር ግን ሁለቱ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች በዝግ ያካሄዱት ስብሰባ ረዘም ያለ ጊዜ ፈጅቷል፡፡ ይህም ከታቀደለት ሰዓት በላይ በመውሰድ ሚኒስትሮቹ እስከ ስምንት ሰዓት ተኩል ድረስ በዝግ መክረዋል፡፡

ዝግ ስብሰባቸውን አጠናቀው መግለጫ ሲሰጥ የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር እንደተናገሩት፣ በአገሪቱ ሰላማዊ የሥልጣን ሽግግር በሚደረግበት ሒደት ላይ ውይይት አድርገዋል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም አገሪቱ ከገጠማት ቀውስ እስከ ደቡብ ሱዳና ሶማሊያ የሰላም ሁኔታ፣ እንዲሁም ከምሥራቅ አፍሪካ ከተለያዩ አገሮች ተፈናቅለው በኢትዮጵያ ስለሚኖሩ ስደተኞች ጉዳይ እስከ ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ ደረጃ ሰላም ማስከበር በስፋት ውይይት ማድረጋቸውን ጠቁመዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ የሥልጣን መልቀቂያ ጥያቄ በማቅረባቸው ሰላማዊ የሥልጣን ሽግግር ለማድረግ የተጀመረው ሒደት ሊጠናከር ይገባል ያሉት ቲለርሰን፣ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን በተመለከተ ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡ አሜሪካ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን በተመለከተ ያላትን አቋም ቀደም ብላ እንደገለጸች አስታውሰው፣ ‹‹ግጭት ለየትኛውም ችግር መፍትሔ ሊሆን ስለማይችል የኢትዮጵያ ሕዝብ የመፍትሔ ሒደቱ አካል ሊሆን ይገባል፤›› ብለዋል፡፡  

ለስድስት ወራት ተግባራዊ እንደሚሆን የተገለጸው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በሚኒስትሮች ምክር ቤት የካቲት 9 ቀን 2010 ዓ.ም. ሲታወጅ በፅኑ ከተቃውሙት አገሮች መካከል አንዷ አሜሪካ ነበረች፡፡ ቲለርስን በንግግራቸው አሜሪካ አቋሟን መቀየርና አለመቀየሯን በግልጽ ባይጠቁሙም፣ ‹‹በመንግሥት የተገለጸውን የሕይወት መጥፋት አሳሳቢነት እንጋራለን፣ እንገነዘባለን፡፡ ለሕዝብ የበለጠ ነፃነት መስጠት እንጂ፣ መገደብ እንዳልሆነ አጥብቀን እናምናለን፤›› ሲሉ አስረድተዋል፡፡

ቲለርሰን የፀጥታ ኃይሎች ሁከትን ሲከላከሉ ሕግና ሥርዓት በተሞላበት መንገድ እንዲሆን ከኢትዮጵያ መንግሥት አቻቸው ጋር ውይይት ማድረጋቸውን ጠቁመዋል፡፡ ‹‹የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ በተቻለ መጠን በአጭር ጊዜ መነሳት እንዳለበት እናምናለን፤›› ሲሉ አክለዋል፡፡ የኢትዮጵያ መንግሥት ለስድስት ወራት ተግባራዊ የሚሆን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ማወጁ የሚታወስ ሲሆን፣ ሚኒስትሩ የአዋጁ ቆይታ እንዲቀንስ ቢጠቁሙም፣ በምን ያህል ወይም እስከ መቼ ድረስ ተግባራዊ ሊሆን እንደሚገባ አላብራሩም፡፡

አገሪቱ በገጠማት ቀውስ ሳቢያ ንፁኃን ዜጎች ተጎጂ እንዳይሆኑ ጥንቃቄ ያስፈልጋል ሲሉ ቲለርሰን ጠቁመዋል፡፡ መንግሥት የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮችንና ጋዜጠኞችን በመፍታቱ የሚበረታታ እንደሆነ ገልጸው፣ ኢትዮጵያዊያን አሁንም ሁከት ሳይኖር መንቀሳቀስ አለባቸው ሲሉ አሳስበዋል፡፡ ‹‹ጋዜጠኞችንና የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮችን ጨምሮ በሺሕ የሚቆጠሩ ዜጎችን ከእስር በመልቀቅ የተወሰደውን ዕርምጃ እንደግፋለን፡፡ በነፃነት የመናገር፣ የመሰብሰብና ተጨማሪ ፖለቲካዊ ነፃነቶችን የመፍቀድ ዕርምጃዎች እንዲወሰዱ እናበረታታለን፤›› ብለዋል፡፡

በታኅሳስ ወር የኢሕአዴግ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ለአሥራ ሰባት ቀናት ያደረገውን ስብሰባ ሲያጠናቅቅ ባወጣው መግለጫ፣ በአገሪቱ ብሔራዊ መግባባት ለመፍጠር ሲባል ጉዳያቸው በፍርድ ቤት የተያዘና ተፈርዶባቸው በእስር ላይ የሚገኙ ዜጎችን ለመፍታት ቃል መግባቱ የሚታወስ ነው፡፡ በዚህም መሠረት እስካሁን ድረስ በአሥር ሺሕ የሚቆጠሩ ዜጎች ከእስር መለቀቃቸውን መዘገቡ ይታወሳል፡፡ የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትርም ይህን ጅምር አድንቀው፣ ወደፊት መንግሥት ከዚህ የተሻለ ዕርምጃ ይወስዳል ብለው ተስፋ እንደሚያደርጉ በመግለጫቸው ጠቁመዋል፡፡

የአሜሪካና የኢትዮጵያ ግንኙነት ከአንድ መቶ ዓመታት በላይ እንዳስቆጠረ ቲለርሰን ጠቁመዋል፡፡ ሁለቱ አገሮች በፀጥታ፣ በሰላምና በፀረ ሽብር፣ እንዲሁም በልማት አብረው እየሠሩ መሆኑንም አክለው ገልጸዋል፡፡

ዶ/ር ወርቅነህና ሬክ ቲለርሰን በጋራ ጋዜጣዊ መግለጫ ከመስጠታቸው በፊት፣ አሜሪካ በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁና ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ከሥልጣን ለመውረድ ጥያቄ ማቅረባቸውን በተመለከተ ምን ዓይነት አስተያየት ይሰጣሉ? የሚለው ዋነኛ መነጋገሪያ አጀንዳ ሆኖ ነበር፡፡ አገሪቱ ቀውስ ውስጥ ከመግባቷ ጋር በተያያዘም በአገር ውስጥም ሆነ በውጭ አገር የሚገኙ አንዳንድ ኢትዮጵያዊያን የሽግግር መንግሥት መቋቋም አለበት ሲሉ ተደምጠዋል፡፡ አቶ ሲራጅ ጋዜጣዊ መግለጫ ሲሰጡ የሽግግር መንግሥት እንዲቋቋም የሚጠይቁ ዜጎች አሉና የመንግሥት ምላሽ ምንድነው? የሚል ጥያቄ ተጠይቀው፣ ‹‹የኢሕአዴግ መንግሥት በሕዝብ የተመረጠ በመሆኑ የሽግግር መንግሥት አይቋቋምም፤›› የሚል ምላሽ ሰጥተው ነበር፡፡ አንዳንድ ወገኖች አሜሪካ በኢትዮጵያ የሽግግር መንግሥት እንዲቋቋም ፍላጎት አላት ሲሉ ተደምጠውም ነበር፡፡

በዚህ ሳቢያ የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር በዚህ ላይ ምን ይላሉ? የሚለው በጉጉት ሲጠበቅ ነበር፡፡ ይሁን እንጂ አሜሪካ የጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም በፈቃዳቸው ከሥልጣን ለመልቀቅ ጥያቄ ማቅረብ፣ ለኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን ለአፍሪካም ተምሳሌት የሚሆን ነው ማለታቸውን ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ጽሕፈት ቤት የተገኘው መረጃ ያመለክታል፡፡

የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ከጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ጋር ውይይት ማድረጋቸው ታውቋል፡፡ በውይይቸው ወቅትም ኢትዮጵያ አሁን ስላለችበት ወቅታዊ ሁኔታና ሁለቱ አገሮች ስላላቸው ግንኙነት ሰፊ ውይይት አድርገዋል፡፡

አገሪቱ በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ሥር ብትሆንም የተለያዩ አገሮች የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮችና ዲፕሎማቶች ወደ ኢትዮጵያ መጥተው ነበር፡፡ የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ወደ ኢትዮጵያ ከመምጣታቸው አንድ ቀን ቀደም ብሎ፣ የተባበሩት ዓረብ ኤምሬትስ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሼክ አብዱላህ ቢን ዘይድ አል ናህያን ለይፋ የሥራ ጉብኝት የካቲት 27 ቀን 2010 ዓ.ም. አዲስ አበባ ገብተው ነበር፡፡ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ከጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ጋር በነበራቸው ቆይታም፣ ሁለቱ አገሮች ግንኙነታቸውን በሚያጎለብቱባቸው ፖለቲካዊ ጉዳዮች ላይ ምክክር ማድረጋቸውን መረጃዎች ያመላክታል፡፡

ኢትዮጵያ ሰላምና መረጋጋትን ለማስፈንና ሽብርተኝነትን ለመዋጋት ከተባበሩት ዓረብ ኤምሬትስ ጋር በትብብር እንደምትሠራ ዶ/ር ወርቅነህ ተናግረዋል፡፡ የተባበሩት ዓረብ ኤምሬትስ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር በበኩላቸው፣ አገራቸው ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን ግንኙነት ለማጠናከር ቁርጠኛ መሆኗን ሸራተን ሆቴል በተካሄደው የሁለቱ አገሮች የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች የምክክር መድረክ ላይ ጠቁመዋል፡፡

ኢትዮጵያ ባለፈው ሳምንት ከተቀበለቻቸው እንግዶች መካከል የሩሲያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሰርጌ ላቭሮብ ይገኙበታል፡፡ ሰርጌ ላቭሮቭ የካቲት 29 ቀን 2010 ዓ.ም. ምሽት አዲስ አበባ ገብተው ነበር፡፡ በቆይታቸውም ከዶ/ር ወርቅነህና ከፕሬዚዳንት ሙላቱ ተሾመ (ዶ/ር) ጋር ተገናኝተው ስለሁለቱ አገሮች ግንኙነት ውይይት ምክክር አድርገዋል፡፡

የሁለቱ አገሮች የውጭ ጉዳይ ሚኒስተሮች በሸራተን ሆቴል ያደረጉትን ውይይት ካጠናቀቁ በኋላ ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥተዋል፡፡ በመግለጫው እንደተጠቆመው ሁለቱ አገሮች በኢነርጂ ዘርፍ በተለይም በኑክሌር ኢነርጂ፣ በሳይንስና ቴክኖሎጂ፣ እንዲሁም በትምህርት ዘርፍ ተባብሮ ለመሥራት ተስማምተዋል፡፡ ኢትዮጵያ አየር መንገድ ወደ ሞስኮ ለመብረር ሁኔታዎች እየተጠናቀቁ መሆኑንም ዶ/ር ወርቅነህ ገልጸዋል፡፡ ሩሲያ ለኢትዮጵያ 162 ሚሊዮን ዶላር የዕዳ ስረዛ እንዳደረገችና በሺሕ የሚቆጠሩ ኢትዮጵያዊያን በሩሲያ ትምህርታቸውን እየተከታተሉ እንደሆነ ተብራርቷል፡፡

የኢትዮጵያና የሩሲያ ግንኙነት 120 ዓመታትን እንዳስቆጠሩ መረጃዎች የሚያመለክቱ ሲሆን፣ ሁለቱ አገሮች በዋናነት በኢነርጂ፣ በሳይንስና በትምህርት መስኮች በትብብር እንደሚሠሩ ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የተገኘው መረጃ ያመለክታል፡፡

በኢትዮጵያ ባለፈው ሳምንት በተለይም ከሰኞ እስከ ረቡዕ ድረስ በአገሪቱ አንዳንድ አካባቢዎች አለመረጋጋቶች እንደነበሩና አለመረጋጋቱም የቀለም አብዮት መልክ እያያዘ መምጣቱን አቶ ሲራጅ ጠቁመው ነበር፡፡ አቶ ሲራጅ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ከታወጀ በኋላ በኮማንድ ፖስቱ የተሠሩ ሥራዎችን ባብራሩበት ወቅት እንደተናገሩት፣ ከአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ መታወጅ በኋላ የፀጥታ አካላትን ጨምሮ በተቋማትና ፋብሪካዎች ላይ ጥቃት ተፈጽሟል፡፡ ኮማንድ ፖስቱም በዚህ ተግባር ተሳትፈዋል ያላቸውን ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ሥር እያዋለ እንደነበር ጠቁመዋል፡፡ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ከታወጀ በኋላ አገሪቱ በአንፃራዊነት መረጋጋት እንደታየባትም ገልጸዋል፡፡

አገሪቱ በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ውስጥ ከመሆኗ ጋር ተያይዞ የዜጎች ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች እንዳይጣሱ ቁጥጥርና ክትትል የሚያደርግ መርማሪ ቦርድ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መቋቋሙን መዘገባችን የሚታወስ ሲሆን፣ መርማሪ ቦርዱ ከየካቲት 29 ቀን 2010 ዓ.ም. ጀምሮ ወደ ሥራ እንደገባ ለማወቅ ተችሏል፡፡

የኢሕአዴግ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴም ከእሑድ መጋቢት 2 ቀን 2010 ዓ.ም. ጀምሮ ስብሰባ እንደሚያካሂድና አገሪቱ ያለችበትን ወቅታዊ ሁኔታ እንደሚገመግም የጽሕፈት ቤቱ ኃላፊ አቶ ሽፈራው ሽጉጤ ገልጸዋል፡፡ የሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ስብሰባ እንደተጠናቀቀም የኢሕአዴግ ብሔራዊ ምክር ቤት ስብሰባ እንደሚካሄድ፣ በዚህ ወቅትም የተጓደሉ የፓርቲው አመራሮች እንደሚመረጡ አቶ ሽፈራው አስረድተዋል፡፡

አገሪቱ በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ሥር ብትሆንም እንግዶችን እየተቀበለችና እያስተናገደች ሰንብታለች፡፡ ባለፈው ሳምንት በኦሮሚያ ክልል ተከስቶ የነበረው የሥራ ማቆም አድማ እንደቆመና የዜጎች ሁለንተናዊ እንቅስቃሴ ወደ ቀድሞ ሁኔታው እንደተመለሰ ከመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽሕፈት ቤት የተገኘው መረጃ ያመለክታል፡፡ ነገር ግን በኦሮሚያ ክልል የኮማንድ ፖስቱን መመርያ ጥሰዋል የተባሉ የወረዳ፣ የዞንና የክልል የተለያዩ መሥሪያ ቤቶች ኃላፊዎች በቁጥጥር ሥር እየዋሉ እንደነበር ለማወቅ ተችሏል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ሰላማዊ የፖለቲካ ትግልና ፈተናው

የኦሮሞ ነፃነት ግንባር (ኦነግ) የፖለቲካ ኦፊሰር የአቶ በቴ ኡርጌሳን...

አበጀህ ማንዴላ! አበጀሽ ደቡብ አፍሪካ!

በአየለ ት. የፍልስጤም ጉዳይ የዓለም አቀፍ ፖለቲካንም ሆነ የተባበሩት መንግሥታትን...

የውጭ ባለሀብቶች ለኢትዮጵያውያን ብቻ በተፈቀዱ የንግድ ዘርፎች እንዲገቡ የመወሰኑ ፋይዳና ሥጋቶች

ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አዓመድ (ዶ/ር) የውጭ ኩባንያዎች በጅምላና ችርቻሮ...