Wednesday, September 27, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

የደቡብና የኦሮሚያ ክልል ቡና አቅራቢዎች ከ1.5 ቢሊዮን ብር በላይ የባንክ ዕዳ እንዲሰረዝላቸው ጠየቁ

ተዛማጅ ፅሁፎች

  • ዕዳው የማይሰረዝ ከሆነ ግን የ15 ዓመታት ጊዜ ያስፈልገናል ብለዋል

በደቡብ ክልልና በኦሮሚያ የጉጂ ዞን የሚገኙ ቡና አጣቢዎች፣ አበጣሪዎችና አቅራቢዎች፣ ለዓመታት የተከማቸባቸውን ከ1.5 ቢሊዮን ብር በላይ የሚገመት የባንክ ዕዳ መንግሥት እንዲሰርዝላቸው ጠየቁ፡፡ የብድር ዕዳውን በወቅቱ መክፈል ያልቻሉት መንግሥት በተለያየ ጊዜ ባካሄዳቸው የፖሊሲ ለውጦች ሳቢያ በደረሰባቸው ኪሳራ እንደሆነ አስታውቀዋል፡፡

ከዚህ ቀደም በመንግሥት ልዩ መመርያ የባንክ ዕዳ መክፈያ ጊዜ እንዲራዘምላቸው የተፈቀደላቸው የደቡብና የኦሮሚያ (ጉጂ ዞን) ቡና አቅራቢዎች፣ የእስካሁኑ የመንግሥት ዕርምጃ በቂ ሆኖ እንዳልተገኘ  በማኅበሮቻቸው በኩል በጥምረት ባቀረቡበት ጥያቄ፣ የተከማቸባቸውን ዕዳ ለመክፈል የማይችሉበት ደረጃ ላይ እንደሚገኙ ለመንግሥት በጻፉት ደብዳቤ ጠቅሰዋል፡፡

በተለይም የጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤትን ጨምሮ፣ ለኢትዮጵያ ንግድ ባንክና ለተለያዩ የመንግሥት ተቋማት በተላከው ደብዳቤ፣ ከዚህ ቀደም የብድር መክፈያ እንዲራዘምላቸው፣ በግል ባንኮች ይፈለግባቸው የነበረው ከ1.5 ቢሊዮን ብር በላይ የብድር ዕዳ ወደ ንግድ ባንክ እንዲዛወር በማድረግ መንግሥት እንዳገዛቸው አስታውሰዋል፡፡ በቡና አቅራቢዎቹ ሐሳብ መሠረት መንግሥት ተፈጻሚ ያደረገው ውሳኔ እንደነበር አስታውሰው፣ ዕርምጃው ግን የቡና አቅራቢዎቹን አንገብጋቢ የህልውና ችግር በጊዜያዊነት ከማቃለል የዘለለ ፋይዳ እንዳላመጣ ተጠቅሷል፡፡ ሆኖም በተራዘመው የብድር መክፈያ ጊዜ ውስጥ ያለባቸውን ዕዳ መክፈል እንደማይችሉና አሁንም ኪሳራ ላይ መሆናቸውን በመግለጽ ድጋሚ አቤት እንዲሉ እንዳስገደዳቸው በሁለቱ ቡና አቅራቢዎች ማኅበራት ኃላፊዎች ፊርማና ማኅተም ተደግፎ ለመንግሥት አካላት የተላከው ደብዳቤ ይጠቅሳል፡፡

የደቡብ ክልልና የኦሮሚያ ክልል የቡና አጣቢዎች፣ አበጣሪዎችና አቅራቢዎች የዘርፍ ማኅበር በጻፈው ደብዳቤ ‹‹የቡና አምራች አርሶ አደርና በቡና ንግድ ሥራ ላይ የተሰራማው አቅራቢና ቡና ላኪ፣ የኢሕአዴግ መንግሥት በተከተለው የተሳሳተ የቡና ፖሊሲ ምክንያት ጉዳት ላይ ወድቀዋል፤›› በማለት ቅሬታውን በመግለጽ ይጀምራል፡፡ ከእነዚህ መካከልም ነባሩን የቡና ተጠሪ ተቋም ማለትም የቀድሞውን ቡናና ሻይ ባለሥልጣን በማፍረስ፣ ቡናን ከሌሎች ሰብሎች ጋር በመደመር በግብርና ሚኒስቴር ሥር እንዲሆን ማድረጉ አርሶ አደሩ ‹‹በኤክስቴንሽን እንዳይደገፍ፣ ቡና በምርጥ ዘር እንዳይታገዝ፣ የበሽታ መከላከል ምርምር እንዳይኖር. . .›› ማድረጉን ማኅበሩ ተችቷል፡፡

 በዚህ አኳኋን መከሰት የጀመረው ችግር ሥር እየሰደደ በመምጣት አሁን የሚገኝበት አዘቅት ውስጥ መግባቱን ዋቢ የሚያደርገውም በቅርቡ የወጣውን የቡና ግብይት ሥርዓት ማሻሻያ አዋጅን ነው፡፡ አዋጁ ከተተገበረ በኋላ በወራት ልዩነት ውስጥ ለመንግሥት የተሰነዘረው የቡና አቅራቢዎቹ ጥያቄ፣ ለአቤቱታ ያበቃቸውን በርካታ ምክንያቶች ጠቅሷል፡፡

 በቅርቡ መተግበር የጀመረው የቡና ሪፎርም አዋጅ በቡና አቅራቢዎች ግፊት ጭምር እንደመጣ በመጥቀስ፣ አዋጁ ጠቀሜታዎች እንዳሉትም በዝርዝር አስቀምጧል፡፡ ከዚህ ቀደም የነበረው ችግር ላይ ነጋዴዎቹና መንግሥት ተማምነው የግብይት ሥርዓቱ እንዲቀየር በተወሰነው መሠረት ሰኔ 30 ቀን 2009 ዓ.ም. የወጣው አዋጅ ለችግሩ መፍትሔ መስጠቱን እንደሚቀበሉት ነጋዴዎቹ አስታውሰዋል፡፡

‹‹ይሁን እንጂ በ2009 ዓ.ም. ጥቅምት ወር ላይ የገንዘብ ችግራችን ተቀርፎ ግብይት የገባነው ስንኮንነው በነበረው የገበያ ሥርዓት ውስጥ እያለን በመሆኑ፣ የተበደርነውን ገንዘብ እንደቀደሙት ዓመታት ሁሉ ለሥራው ምንም ተጨማሪ እሴት በማይጨምሩና በየደረጃው ለተፈጠሩ ደላሎች ማከፋፈላችን ግድ ነበር፤›› በማለት ገልጸዋል፡፡ አያይዘውም፣ መንግሥት የችግሩን መጠን በመረዳቱ የቡና ግብይትን ለማስተካከል ሕግ ቢያወጣም ደንብና የአፈጻጸም መመርያውን ሳያወጣ በመዘግየቱ ግን በ2009 ዓ.ም. ለሥራ ማስኬጃ የተሰጣቸውን ገንዘብ ለመመለስ አዳጋች እንደሆነባቸው ይጠቅሳሉ፡፡ ከግል ባንኮች የተገዛው (የተዛወረው) ብድር ለአራት ዓመታት እንዲራዘም ተደርጎ የአንድ ዓመት የዕፎይታ ቢሰጥበትም፣ ብድሩ ሳይከፈል ጊዜው በመድረሱና ዕዳውን ለመክፈል የሚያስችል አቅም ባለመገኘቱ ድጋሚ ለመንግሥት አቤቱታ ለማቅረብ እንዳስገደዳቸው በደብዳቤያቸው አስታውቀዋል፡፡

ከዚሁ በሥራ ማስኬጃነት ከተሰጣቸው ገንዘብ ላይ ተከማችቶ ለቆየው ብድር ወለድ በመክፈላቸው ለሥራ የተሰጣቸው ገንዘብ ሙሉ በሙሉ ወደ ሥራ አለመግባቱን፣ በዚህም ሳቢያ ያለባቸውን ብድር በተቀመጠው ጊዜ ውስጥ ለመመለስ እንዳልቻሉ ነጋዴዎቹ ይገልጻሉ፡፡

የቡና ግብይትን ያሻሽላል የተባለው አዋጅ ቢወጣም አሁንም የቀድሞ አሠራሮች እንዳሉ በመሆናቸው፣ እንደታሰበው ተጠቃሚ የሚሆኑበትን ሥራ ለመሥራት እንዳላስቻላቸው ቡና አቅራቢዎች አስታውቀው፣ የአዋጁ ማስፈጸሚያዎች በአፋጣኝ አለመውጣታቸው ለገጠማቸው ችግር ተጠቃሾች ከሚደረጉት ምክንያቶች ውስጥ እንደሆኑ አስፍረዋል፡፡

ከዚህ ቀደም በመንግሥትም በተለይም በንግድ ባንክ ታሳቢ ተደርጎ የነበረው መፍትሔ፣ የሥራ ማስኬጃ ገንዘብ ለቡና አቅራቢው ቢሰጠው፣ ሠርቶ በማትረፍ ዕዳውን ቀስ በቀስ ይከፍላል ከሚል መነሻ ነበር፡፡ ቡና አቅራቢዎቹ ግን ኪሳራ ያደረሰብን ተሻሻለ የተባለው የገበያ ሥርዓት ነው በማለት ወደ ተጨማሪ ኪሳራ የገቡትም ሥርዓቱን የሚመራው ሕግና ማስፈጸሚያዎች አለመጣጣም ያመጣው ዱብ ዕዳ ነው ይላሉ፡፡ ‹‹ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ጋር በገባነው ውል መሠረት፣ የብድር ዕዳ ግዴታችንን ለመወጣት ከፍተኛ ችግር ውስጥ እንገኛለን፤›› በማለትም በተፈጠረው የተሳሳተ የግብይት ሥርዓት ምክንያት ቡና አቅራቢዎቹ ሁሉ ንብረታቸውን እየሸጡ እንደሚገኙ፣ በኢትዮጵያ ምርት ገበያ ውስጥ ወንበር ያላቸው ‹‹ደላሎች››ም የቡና አቅራቢዎቹን ንብረት በመግዛት እንደሚገኙ በመግለጽ ድርጊቱን ኮንነዋል፡፡ በዚህ ምክንያት ቀደም ሲል ተቀረፈ የተባለው ችግር ይልቁንም ማኅበራዊ ቀውስ እያስከተለ መቀጠሉ እንደማይቀር የሚገልጹት ነጋዴዎቹ፣ ለሚያቀርቧቸው የመፍትሔ ሐሳቦች በአስቸኳይ መፍትሔ እንዲሰጥ ጠይቀዋል፡፡

ቡና አቅራቢዎቹ ካቀረቧቸው ጥያቄዎች ውስጥ አንደኛው ካሳ እንደሚገባቸው የሚጠይቅ ነው፡፡ ‹‹ጥፋትና ጉዳት ሲደርስ፣ ጉዳት ያደረሰው ግለሰብ ወይም ድርጅት ወይም የመንግሥት ፖሊሲ ከሆነ ለጉዳቱ ተመጣጣኝ ካሳ መክፈልን ባህላችንና የአገሪቱ ሕግ ያስገድዳል፤›› በማለት ኪሳራ የደረሰባቸው በግብይት ሥርዓትና በፖሊሲ ችግር መሆኑን መንግሥት አምኖ ለጉዳታቸው ተመጣጣኝ ካሳ መክፈል አለበት ብለዋል፡፡ ከዚህም ባሻገር ለአራት ዓመታት የመክፈያ ጊዜው ተራዝሞ የነበረው ብድር፣ አሁን ባለው ሁኔታ በወቅቱ ሊከፈል ስለማይችል ‹‹ቢቻል ዕዳው ቢሰረዝልን፣ መሰረዝ ካልቻለም የብድሩ መክፈያ ጊዜ በ15 ዓመታት እንዲራዘም፣ የተራዘመው ብድር ግን ከወለድ ነፃ እንዲደረግል፤›› የሚል ጉልህ ጥያቄ አቅርበዋል፡፡

በቡናና ሻይ ልማትና ግብይት ባለሥልጣንና በደቡብ ክልል ቡና አጣቢዎች፣ አበጣሪዎችና አቅራቢዎች ዘርፍ ማኅበር እንዲሁም በቡና ላኪዎች መካከል በተደረገው ድርድር መሠረት ነጋዴዎቹ ቡናቸውን በኪሳራ በመሸጣቸውና የሥራ ማስኬጃውን ብድር ሙሉ ሙሉ በወቅቱ መክፈል ስለማይቻሉ የአቅራቢው ችግር መጠን እየተናጠ ለአራት ዓመት የመክፈያ ጊዜ ተሰጥቶን እንዲራዘምልንም ብለዋል፡፡

 የግብይት ሥርዓቱን ማሻሻያ አዋጅ የሚተገበርበት ደንብ በአስቸኳይ ለሚኒስትሮች ምክር ቤት ቀርቦ ሥራ ላይ እንዲውል ጠይቀዋል፡፡ በአዲስ መልክ የተቋቋመው የቡናና ሻይ ግብይትና ልማት ባለሥልጣን ለጉዳዩ ትኩረት ሰጥቶት፣ የኢትዮጵያ ቡና በሚላክባቸውም ሆነ በአዳዲስ መዳረሻ አገሮች ውስጥ ለማስተዋወቅ አስፈላጊው ሥራ መሠራት ይኖርበታል ብለዋል፡፡ ከዚህም ሌላ የቡና አቅራቢው የቡና ግብይት ሥራ ማስኬጃ ብድር ወለዱ ተቀንሶለት፣ ለቡና ላኪዎች በሚሰጠው የወለድ ምጣኔ ልክ ወለድ እንዲከፍል ይደረግ ሲሉም መንግሥትን ጠይቀዋል፡፡ ለዚህ ጥያቄያቸው ዋቢ ያደረጉትም ለአበባ ምርት ግብዓት አቅራቢዎች የሚሰጠው ብድር ከአበባ ኤክስፖርተሮች እኩል በሆነ የወለድ ምጣኔ እንደሚከፈልበት በመጥቀስ ነው፡፡ የቡና አቅራቢውም፣ ለላኪዎች አቅርቦ ወደ ውጭ የሚላክ በመሆኑ፣ በቡናና በአበባ ላኪዎች በኩል የሚተገበረው የወለድ መክፈያ ምጣኔ፣ ለአቅራቢዎችም እኩል እንዲደረግ በማለት አቤቱታቸውን አሰምተዋል፡፡ ይህንን መንግሥት ሊያደርግልን ይገባል በማለት ከዘረዘሯቸው ጥያቄዎች ውስጥ አካተው አቅርበዋል፡፡

መንግሥት ያለባቸውን ችግር በመገንዘብ ከዚህ ቀደም በግል ባንኮች የነበረባቸውን ብድር ወደ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ እንዲዛወር በሚደረገበት ወቅት በዕድሉ ያልተጠቀሙና ዕዳቸው ወደ ንግድ ባንክ ያልዞረላቸው አባሎቻቸውም ዕድሉ እንዲሰጣቸው ጠይቀዋል፡፡ የቡና ሪፎርም ከመተግበሩ በፊት ወደ አርሶ አደሩ በመውረድ የአባልነት መታወቂያ በማደል በአቅራቢውና በአርሶ አደሩ መካከል በኦሮሚያና በደቡብ ክልል ከፍተኛ ችግር በመፍጠር ላይ የሚገኙ አቅራቢዎችና ላኪዎች ያከፋፈሉትን መታወቂያ በአስቸኳይ በመሰብሰብ፣ በሪፎርሙ መሠረት እንዲመሩ መንግሥት እንዲያስገድዳቸውም የሁለቱ ክልሎች ቡና አቅራቢዎች አሳስበዋል፡፡

ቀደም ብሎ የነበረውን የተሳሳተ ፖሊሲ መንግሥት እንዲስተካከልና ቆም ብሎ እንዲያስብበት በመጠየቅ በ1992 ዓ.ም. የተቋቋመው የሲዳማ ቡና አቅራቢዎች ማኅበር ችግሩን ብቻም ሳይሆን የመፍትሔ ሐሳቦችንም በማቅረብ መንግሥትን ለማሳሰብ ሲሞክር ቢቆይም፣ ለጥያቄዎቹ መፍትሔ ሳያገኝ እስከ 2008 ዓ.ም. ድረስ መቆየቱን አስታውሷል፡፡

ለችግሩ መባባስ ሌላው ምክንያት የሆነው በ2000 ዓ.ም. የተቋቋመው የኢትዮጵያ ምርት ገበያ ነው ተብሏል፡፡ ምርት ገበያው በፈጠረው የገበያ ሥርዓት መሠረት፣ ቡና ነጋዴው የቡና ንግዱን በባለቤትነት እንዳይመራ ከመጀመርያ ደረጃ ገበያ ጀምሮ እስከ መጨረሻው የሽያጭ ሒደት ድረስ በደላላ በኩል እንዲገበያይ ዕድል መፍጠሩ ነው ችግሩ የሚል አመለካከት እንዳላቸውም በደብዳቤያቸው አንፀባርቀዋል፡፡ የቡና አቅራቢው የባለቤትነት መብት ሕገ መንግሥቱን የሚፃረር፣ ሀብት የማፍራት መብትና በሀብቱ የመጠቀምና የማዘዝ መብቱን የሚነጥቅ አሠራር እንዳለበት የገለጹት የተጠቀሱት ቡና አቅራቢዎቹ፣ በዚህ ምክንያት የቡና ግብይት ሰንሰለት በመብዛቱ ወጪውም ከፍተኛ ሊሆን እንደቻለ ይገልጻሉ፡፡ ወጪን የመሸከም ግዴታ በአቅራቢው ላይ ብቻ መጣሉም አዳጋች ነበር ይላሉ፡፡ ወደ መፈልፈያ መጥቶ ከተዘጋጀ በኋላ ወደ ኢትዮጵያ ምርት ገበያ ሲቀርብ ለቡና ናሙና ለሚወስድ ወዛደር፣ ለቅምሻ፣ ለመጋዘን ኪራይ፣ ለኢትዮጵያ ምርት ገበያ የኮሚሽ ክፍያን ጨምሮ፣ የቡና ግብይት ወንበር ባላቸው በኩል ካልሆነ መሸጥ አትችሉም መባላቸውም ከችግሮቹ መካከል የሚመደብ እንደሆነ በደብዳቤያቸው አካተዋል፡፡ በተለይ በምርት ገበያው ወንበር ላላቸው አሻሻጮች የሚከፈለው ኮሚሽን በአንድ መኪና ጭነት ወይም በ10,000 ኪሎ ግራም ከ35,000 እስከ 40,000 ብር የሚደርስ ወጪ እንደሚታከልበት በምሳሌነት ጠቅሰዋል፡፡ ይህ ወጪ የሚሸፈነው በቡና አቅራቢው ሲሆን፣ ይህንን ወጪ ሸፍኖ ቡናውን ለገበያ ለማቅረብም የቤተሰቡን ንብረት ሳይቀር በዋስትና አስይዞ ከተበደረው የባንክ ገንዘብ ላይ ወጪ በማድረግ እንደሆነ ተጠቅሷል፡፡ እንዲህ ያሉ የምርት ገበያው አሠራሮች ቡና አቅራቢዎቹ ላይ ባስከተለው ኪሳራ ሳቢያ በ2004 ዓ.ም. መከፈል የነበረበትን የባንክ ዕዳ መክፈል ወደማያስችላቸው ደረጃ እንዳደረሰው አስታውሰዋል፡፡ ለዚህም የቀድሞውን የምርት ገበያውን አሠራር ኮንነዋል፡፡

ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ እንዲህ ያሉትን ችግሮች በማቅረብ ብድሮቹ እንዳይበላሹ የማራዘሚያ ጥያቄ እንዲሰጣቸው ተደርጎ የሁለት ዓመት የብድር ማራዘሚያ ጊዜ እንደፈቀደላቸው ማድረጉ አይዘነጋም፡፡ ይህ ዕርምጃ ግን ችግሩን ከመፍታት ይልቅ እያባባሰው እንደሄደ አቤቱታ ቀርቦ ነበር፡፡ ለሁለተኛ ጊዜ ብድር ሳይከፈል ማራዘም የብሔራዊ ባንክ ሕግ ስለማይፈቅድ፣ አበዳሪ ባንኮች በ2007 ዓ.ም. የቡና አቅራቢዎቹ ለዋስትና ያስያዙትን ንብረት መሸጥ ጀምረው ነበር፡፡ ይህንን ተከትሎም መንግሥት ዕርምጃ ወስዷል፡፡ ከዕርምጃው በፊት ግን በደቡብና በኦሮሚያ ክልል 36 የቡና መፈልፈያ ኢንዱስትሪዎችና 100 በዋስትና የተያዙ ድርጅቶች በባንኮቹ ተሽጠው ነበር፡፡ በወቅቱ የባንክ ዕዳቸውን ያልከፈሉ አቅራቢዎች፣ በሐዋሳ ከተማ ብቻ ከ1,000 በላይ ቤቶች፣ 200 የቡና ማጠቢያዎችና ድርጅቶች እንደሚሸጡና ከ10,000 በላይ ዜጎች እንደሚፈናቀሉ መረጃ በማቅረባቸው መንግሥት ጣልቃ በመግባት ብድሩ ከግል ባንኮች ይልቅ የብድር ዕዳ ማስከፈያ ምጣኔው ወደሚቀንሰው ንግድ ባንክ ዕዳቸው እንዲዛወር መደረጉ ይታወሳል፡፡

በመሆኑም የሁለቱ ክልሎች ማኅበራት የዕዳ ይሰረዝልን አልያም የ15 ዓመታት ማራዘሚያ ይሰጠን የሚለውን አቤቱታቸውን ለጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት፣ ለንግድ ባንክ፣ ለደቡብ ክልል መንግሥት፣ ለቡናና ሻይ፣ ልማትና ግብይት ባለሥልጣንና ለሌሎችም መንግሥታዊ መሥሪያ ቤቶች በደብዳቤ ማስታወቃቸው ታውቋል፡፡ ደብዳቤው የደረሳቸው መሥሪያ ቤቶች ምን ምላሽ እንደሰጡ ለማጣራት ተሞክሮ፣ የጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት ጉዳዩን እንዲያጣራ ለቡናና ሻይ ባለሥልጣን ትዕዛዝ ማስተላለፉን ለማወቅ ተችሏል፡፡

ባለሥልጣኑ ለሪፖርተር ጨምሮ እንዳስታወቀው፣ ቡና አቅራቢዎቹ የተካተቱበትና ሌሎችም የሚመለከታቸው የመንግሥት አካላት የሚተፉበት ጥናት እንዲደረግ ተወስኖ እንቅስቃሴ ተጀምሯል፡፡ ሁሉን አቀፍ ጥናት ከተካሄደ በኋላ በሚገኘው ግብረ መልስ መነሻነት መፍትሔ እንደሚሰጥበትም አብራርቷል፡፡  

የደቡብና የኦሮሚያ ክልል ቡና አጣቢዎች፣ አበጣሪዎችና አቅራቢዎች የዘርፍ ማኅበር በሥሩ ከ1,500 በላይ አባላት እንዳሉት መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች