- ለቡና ግብይት መቀነስ የፖለቲካ ትኩሳቱ አስተዋፅኦ አድርጓል ተብሏል
የኢትዮጵያ ምርት ገበያ በየካቲት 2010 ዓ.ም. ያገበያየው የምርት መጠን ከቀዳሚዎቹ ሁለት ወራቶች ያነሰ አፈጻጸም የታየበት እንደሆነና የግብይት መጠኑም እንደቀነሰ መረጃዎች አሳይተዋል፡፡
የምርት ገበያውን የየካቲት ወር የግብይት አፈጻጸም የሚያሳየው መረጃ፣ በወሩ ያገበያየው የምርት መጠን 65,631 ቶን እንደሆነ ያሳያል፡፡ በጥር ወር የነበረው ግን 81,830 ቶን እንደነበር ይታወሳል፡፡ ምርት ገበያው በታኅሳስ ወር ያስመዘገበው 105,208 ቶን የግብይት መጠን ከመሆኑ አንፃር፣ የየካቲት ወር አጠቃላይ ግብይት መጠን አኳያ ሲታይ ከቀዳሚዎቹ ሁለት ወራት አፈጻጸም ያነሰ ሆኖ ተገኝቷል፡፡
ከተገበያየው የገንዘብ መጠን አንፃርም የየካቲት ወር አፈጻጸም አነስተኛ ሆኗል፡፡ የምርት ገበያው ወርኃዊ መረጃዎች እንደሚያሳዩት፣ በታኅሳስ ወር የነበረው አጠቃላይ የግብይት መጠን 4.4 ቢሊዮን ብር ነበር፡፡ በጥር ወር መጠነኛ ቅናሽ በማሳየት የግብይቱ የገንዘብ መጠን ወደ 4.2 ቢሊዮን ብር ዝቅ ብሎ ነበር፡፡ ከዚህ አንፃር የየካቲት ወር አጠቃላይ የግብይት መጠን 3.3 ቢሊዮን ብር የተመዘገበበት በመሆኑ ከሁለቱ ወራት ግብይት ያነሰ አፈጻጸም የታየበት ወር ሆኗል፡፡
ባለፉት ተከታታይ ሁለት ወራት ውስጥ ከፍተኛ የግብይት ክንውን የነበራቸው ቡናና ሰሊጥ፣ በየካቲት ወር ቀንሰዋል፡፡ በተለይም የሰሊጥ ግብይት 1.1 ቢሊዮን ብር ብቻ ሆኗል፡፡ በታኅሳስ ወር የነበረው የሰሊጥ ግብይት የ2.2 ቢሊዮን ብር ልውውጥ የተካሄደበት ሲሆን፣ በጥር ወር ወደ 1.5 ቢሊዮን ብር ዝቅ ያለ ግብይት ማስመዝገቡ ይታወሳል፡፡ ከዚህም ያነሰ ግብይት በየካቲት ወር የተመዘገበበት የቡና ምርት ከቀደሙት ወራትም ያነሰ ሆኗል፡፡
በጥር ወር 35,472 ቶን ቡና ለገበያ ቀርቦ በ2.6 ቢሊዮን ብር የተገበያየ ሲሆን፣ በየካቲት ወር ለግብይት የቀረበው ቡና መጠን ግን ወደ 29,415 ቶን ዝቅ ያለ ነበር፡፡ የተገበያየበት ዋጋም በሁለት ቢሊዮን ብር የተወሰነ ነበር፡፡
በተከታታይ ወራት ዕድገት ሲያሳይ የነበረው የግብይት መጠን በየካቲት ወር የቀነሰበትን ምክንያት ባይብራራም፣ ከፍተኛ ጭማሪ ሲታይበት የነበረው የሰሊጥ ምርት ግን በየካቲት ወር በከፍተኛ ደረጃ ቀንሶ ተገኝቷል፡፡
እንደ ምርት ገበያው መረጃ፣ በታኅሳስ በምርት ገበያው ተገብይቶ የነበረው የሰሊጥ ምርት 66,764 ቶን እንደነበር ያመለክታል፡፡ በጥር 39,260 ቶን ሰሊጥ ያገበያየው ምርት ገበያው፣ በየካቲት ግን ለገበያ የቀረበው ሰሊጥ መጠን ወደ 28,929 ቶን ወርዷል፡፡
በየካቲት ወር በተካሄደው ግብይት ምርት ገበያው 3.3 ቢሊዮን ብር ዋጋ ያለውን፣ 65,631 ቶን ምርት ሲያገበያይ፣ ከዚህ ውስጥ 29,415 ቶን ቡና በሁለት ቢሊዮን ብር፣ 28,229 ቶን ሰሊጥ በ1.1 ቢሊዮን ብር፣ 5,660 ቶን ነጭ ቦሎቄ በ88 ሚሊዮን ብር፣ 1,627 ቶን አረንጓዴ ማሾ በ30 ሚሊዮን ብር አገበያይቷል፡፡
የካቲት ወር የግብይት አፈጻጸሙን የተመለከተው የምርት ገበያው ተጨማሪ መረጃ በወሩ ከፍተኛው የግብይት ድርሻ የቡና ሲሆን የግብይቱን 45 በመቶ በመጠንና 63 በመቶ በዋጋ ይዟል፡፡ በቡና ግብይት ውስጥ ለውጭ ገበያ የሚቀርብ ቡና የግብይቱን 59 በመቶ በመጠንና 53 በመቶ በዋጋ ግንባር ቀደም ሲሆን፣ ስፔሻሊቲና የአገር ውስጥ ቡና ተከታዩን ደረጃ ይዘዋል፡፡ 15,789 ቶን ያልታጠበ ለውጭ ገበያ የሚቀርብ ቡና በ983 ሚሊዮን ብር የተገበያየ ሲሆን፣ ከዚህ ውስጥ ያልታጠበ ጅማ ቡና 37 በመቶ የግብይት መጠን በመያዝ ቀዳሚ እንደሆነ ተጠቅሷል፡፡
በየካቲት ወር 1,671 ቶን የታጠበ ለውጭ ገበያ የሚቀርብ ቡና በ128 ሚሊዮን ብር የተገበያየ መሆኑንም አመልክቷል፡፡ የታጠበ የሲዳማ ቡና የግብይቱን 70 በመቶ ድርሻ በመያዝ እንደሚመራ ያመለከተው ይኸው መረጃ 4,093 ቶን ለአገር ውስጥ ፍጆታ የሚውል ቡና በ231 ሚሊዮን ብር ተገበያይቷል፡፡ በዚህ ዘርፍ ያልታጠበ የአገር ውስጥ ቡና 54 በመቶ የግብይት መጠን በማስመዝገብ ቀዳሚ ሆኗል ተብሏል፡፡ በተጨማሪም በወሩ ውስጥ 7,863 ቶን ስፔሻሊቲ ቡና በ731 ሚሊዮን ብር የተገበያየ ሲሆን፣ ከዚህ ውስጥ 1,044 ቶን ያልታጠበ ስፔሻሊቲ ቡና በ123 ሚሊዮን ብር፣ 6,818 ቶን የታጠበ ስፔሻሊቲ ቡና በ608 ሚሊዮን ብር እንደተገበያየም ምርት ገበያው አስታውቋል፡፡
የወሩ የሰሊጥ ግብይት መጠን 44 በመቶ፣ በዋጋ 33 በመቶ በማስመዝገብ፣ ከቡና በመከተል በሁለተኛ ደረጃ የተቀመጠ ሲሆን፣ ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ጊዜ ጋር ሲነጻጸርም ዋጋው በ45 በመቶ እንዲሁም በግብይት መጠኑ በሁለት በመቶ ማደጉ ተመልክቷል፡፡ በየካቲት ወር በምርት ገበያው ከተገበያየው ሰሊጥ ውስጥ ነጭ ሁመራ ወይም ጎንደር ሰሊጥ 71 በመቶ የግብይት መጠንና 72 በመቶ የግብይት ዋጋውን በመያዝ ይመራል፡፡ ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ጊዜ ጋር ሲነጻጸርም የግብይት መጠኑ በ12 በመቶ የግብይት ዋጋው ደግሞ በ57 በመቶ ጨምሯል፡፡
በወሩ ከፍተኛ ለውጥ የታየበት የምርት ዓይነት በየካቲት ወር የተገበያየው የማሾ ምርት ነው፡፡ ካለፈው ወር ጋር ሲነጻጸር የግብይት መጠኑ በ80 በመቶ እንዲሁም ዋጋው በ107 በመቶ ጭማሪ አሳይቷል ተብሏል፡፡ አማካይ የሽያጭ ዋጋውም ከጥር ወር ጋር ሲነጻጸር የ13 በመቶ ዕድገት አስመዝግቧል፡፡ በቦሎቄ ግብይት 5,470 ቶን ነጭ ድቡልቡል ቦሎቄ በ86 ሚሊዮን ብር ተገበያይቶ በመጠንና በዋጋ በተመሳሳይ 97 በመቶ ከፍተኛ ድርሻ ይዟል፡፡ ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ጊዜም ጋር ሲነጻጸር የግብይት መጠኑ በ63 በመቶ የግብይት ዋጋው በ73 በመቶ እንደሆነም ተገልጿል፡፡
የቡና ግብይት በየካቲት ወር ላስመዘገበው አነስተኛ የግብይት አፈጻጸም ፖለቲካዊ ቀውሱ አስተዋፅኦ ማድረጉን ሪፖርተር ከምርት ገበያው ባገኘው መረጃ አረጋግጧል፡፡ ይኸውም ምርት ወደ ግብይት ማዕከላት በወቅቱ ሊጓጓዝ ባለመቻሉ ሲሆን፣ ሌላኛው ምክንያት ደግሞ ላኪዎች በእጃቸው የሚገኘውን ክምችት ለገበያ ከማቅረብ በመቆጠባቸው ጭምር እንደሆነ ምርት ገበያው ገልጿል፡፡