Wednesday, February 8, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

የአሜሪካ የብድር ዕዳ ማስጠንቀቂያና ችላ ያለችው ድጋፍ 

- ማስታወቂያ -

ተዛማጅ ፅሁፎች

በኢትዮጵያ ጉብኝት ያደረጉት የአሜሪካው ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሬክስ ቲለርሰን ከቻይና የሚገኘው ብድር የሚያስከትለውን የብድር ዕዳ መነሻ በማድረግ ማስጠንቀቂያ አዘል ምክር ለአፍሪካ አገሮች አስተላልፈው ወደ ኬንያ አቅንተዋል፡፡

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ንግግር፣ የአፍሪካ አገሮች ለብድር ሲሉ ‹‹ሉዓላዊነታቸውን›› የሚጋፋ ስምምነት ውስጥ ከመግባት እንዲቆጠቡ የሚያሳስብ ነው፡፡ አፍሪካውያኑ ከሚቀርብላቸው ዝቅተኛ የወለድ ማስከፈያ ያለው ብድር በስተጀርባ ስላለው ጉዳይ በጥሞና እንዲመረምሩ፣ አጥብቀው እንዲደራደሩ፣ ስለሚፈርሙት የብድር ስምምነትም በሚገባ እንዲያጤኑ ምክር የለገሱት ቲለርሰን፣ ዝቅተኛ ብድሮች የኋላ ኋላ መዘዝ እንዳያመጡባችሁ የሚል ድምፀት ያለው መልክዕት አስተላልፈዋል፡፡

ከውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ቲለርሰን ጉብኝት ቀደም ብለው ለአፍሪካ ጋዜጠኞች የቲለርሰንን ጉብኝትና የሚወያዩባቸውን ጉዳዮች በማስመልከት ማብራሪያ የሰጡት፣ የአፍሪካ ጉዳይ ተጠባባቂ ረዳት ሚኒስትሩ አምባሳደር ዶናልድ ያማማቶ ናቸው፡፡ አምባሳደር ያማማቶ በርካታ የአፍሪካ አገሮች ከቻይና በዝቅተኛ ወለድ በሚያገኙት ብድር ሳቢያ አብዛኛው የኢኮኖሚያቸው ድርሻ በብድር የተያዘ ስለመሆኑ ተናግረው ነበር፡፡ አንዳንድ አገሮች የኢኮኖሚያቸውን 50 በመቶ ድርሻ፣ አንዳንዶች እስከ 100 በመቶ፣ ከዚህ ሲከፋም እስከ 200 በመቶ በሚደርስ ብድር ዕዳ ውስጥ ኢኮኖሚያቸውን መክተታቸው አሥጊ እንደሆነ አሳስበው ነበር፡፡

ከአሜሪካ ማስጠንቀቂያ ቀደም ብሎ የዓለም ባንክ በተደጋጋሚ ሲያስተጋባው የቆየው ይኼው የብድር ዕዳ መጠን፣ እንደ ኢትዮጵያ ያሉ ዝቅተኛ የዕዳ መጠን ይታይባቸው የነበሩ አገሮችንም የሚመለከት እንደነበር አይዘነጋም፡፡ ባንኩ ከዚህ ቀደም ባወጣቸው ሪፖርቶች መሠረት ኢትዮጵያ ከዝቅተኛ የብድር ዕዳ ተሸካሚነት ሥጋት ወደ መካከለኛ ደረጃ መሸጋገሯን ያመላከቱ መረጃዎችን አውጥቶ እንደነበር ሲታወስ፣ የአገሪቱ አጠቃላይ የዕዳ መጠን ከጠቅላላ ኢኮኖሚዋ እስከ 65 በመቶ መድረሱን አመላክቶ ነበር፡፡ ምንም እንኳ የዕዳው መጠን ከኢኮኖሚው መጠን ይህን ያህል ድርሻ መያዙ አገሪቱ ዕዳ መክፈል አትችልም ወይም የመክፈል አቅም የላትም ወደሚለው ድምዳሜ የማይወስድ ስለመሆኑ ባለሙያዎች የሚስማሙበት ቢሆንም፣ የዕዳው እየበዛ መምጣት ግን ቀስ በቀስ የአገሪቱን የልማት ሥራዎች በመቀነስ ወደ ዕዳ መክፈሉ እንድታዘነብል ሊያስገድዳት እንደሚችል ግን ሳይገልጹ አላለፉም፡፡

ከዚህ ጎን ለጎን በሁለት ሳምንት በፊት ይፋ የተደረገው የኢትዮ የውጭ ብድርና ዕርዳታ መጠን እንደማሳያ ሊቀርብ ይችላል፡፡ የገንዘብና ኢኮኖሚ ትብብር ሚኒስቴር ይፋ ባደረገው መሠረት፣ አገሪቱ የውጭ ብድርና ዕርዳታ የምታገኘው በሁለት ምንጮች ነው፡፡ አንደኛው የበይነ መንግሥታዊ ተቋማት ወይም መልቲላተራል ከሚባሉ አካላት የሚገኘው ሲሆንበዚህ ውስጥ የዓለም አቀፍ የፋይናንስ ተቋማት፣ የአውሮፓ ኅብረትና የተባበሩት መንግሥታት ተቋማት ይካተታሉ፡፡ ሁለተኛው ምንጭ የመንግሥታት ትብብር፣ ሁለትዮሽ ወይም ባይላተራል በሚባለው በኩል የሚገኘው ሲሆን፣ በዚህ በኩል የቻይና አስተዋጽኦ ጎልቶ ይታያል፡፡ ይሁንና ይህ የብድርና የዕርዳታ ምንጭ ሁሉንም የልማት አጋር መንግሥታት እንደሚያካትት የሚኒስቴሩ መረጃ ይጠቁማል፡፡

በመሆኑም ከመልቲላተራል ምንጮች 210 ዓ.ም. ስድስት ወራት ውስጥ በብድር የተገኘው 20.971 ቢሊዮን ብር እንደሆነ ይፋ አድርጓል፡፡ በዕርዳታ የተገኘው ገንዘብ 34.577 ቢሊዮን ብር በመሆኑ በድምሩ 55.548 ቢሊዮን ብር በስድስት ወራት ውስጥ የተገኘ አዲስ የገንዘብ መጠን እንደሆነ ሚኒስቴሩ አስታውቋል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም በስድስቱ ወራት ውስጥ ከመንግሥታት ትብብር ወይም ከባይላተራል ምንጮች፣ 16.970 ቢሊዮን ብር በብድር እንዲሁም 16.828 ቢሊዮን ብር በዕርዳታ መገኘቱ ታውቋል፡፡ በመሆኑም በጠቅላላው 33.798 ቢሊዮን ብር አዲስ ብድርና ዕርዳታ መገኘቱ ተመልክቷል፡፡

በስድስት ወራት ውስጥ ከሁለቱም የፋይናንስ ምንጮች የተገኘው ገንዘብ ሲታይም፣ 37.941 ቢሊዮን ብር በብድር እንዲሁም 51.405 ቢሊዮን ብር በዕርዳታ የተገኘ በመሆኑ በጠቅላላው ድምር 89.346 ቢሊዮን ብር አዲስ ብድርና ዕርዳታ መንግሥት ማግኘቱን ሚኒስቴሩ አስታውቋል፡፡

ከተገኘው ወይም ቃል ከተገባው ገንዘብ ውስጥ የተለቀቀው ወይም ወደ መንግሥት የፈሰሰው ገንዘብ መጠንን በተመለከተም፣ ሚኒስቴሩ መረጃዎችን ይፋ አድርጓል፡፡ በመሆኑም ለፕሮጀክቶችና ፕሮግራሞች ማስፈጸሚያ ከመልቲላተራል ምንጮች በብድር የተለቀቀው ገንዘብ 9.414 ቢሊዮን ብር ሲሆን፣ በዕርዳታ የተለቀቀው ደግሞ 11.553 ቢሊዮን ብር በመሆኑ፣ በድምሩ  20.967 ቢሊዮን ብር የውጭ ሀብት ፍሰት ማግኘቱን ጠቅሷል፡፡

ከመንግሥታት ወይም ከባይላተራል ምንጮች በኩል የተለቀቀውን ገንዘብ በተመለከተውም ከ29 ቢሊዮን ብር በላይ መገኘቱን ሚኒስቴሩ ጠቅሷል፡፡ ይኸውም ከብድር 19.980 ቢሊዮን ብርከዕርዳታ ደግሞ 9.496 ቢሊዮን ብር በመገኘቱ በጠቅላላው 29.476 ቢሊዮን ብር ያህል የውጭ ሀብት ፍሰት መመዝገቡ ታውቋል፡፡ በአጠቃላይ 2010 ዓ.ም. ስድስት ወራት ውስጥ ከሁለቱም ማለትም ከባይላተራልና ከመልቲላተራል ምንጮች በብድር 29.394 ቢሊዮን ብር፣ በዕርዳታ 21.049 ቢሊዮን ብር፣ በድምሩ ከ50 ቢሊዮን ብር በላይ የሀብት ፍሰት መመዝገቡን የገንዘብና ኢኮኖሚ ትብብር ሚኒስቴር አስታውቋል፡፡

በሚኒስቴሩ ትንታኔ መሠረት ከሁለቱም ምንጮች የተመዘገበው የ50.443 ቢሊዮን ብር ፍሰትካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት የብድርና ዕርዳታ ፍሰት (28.5703 ቢሊዮን ብር) ጋር ሲነፃፀር፣ 21.873 ቢሊዮን ብር ወይም 43.36 ከመቶ ጭማሪ የታየበት ነው፡፡ እንደ ሬክስ ቲለርሰንና ዶናልድ ያማማቶ ማስጠንቀቂያ ከሆነ እንዲህ ያለው እያደገ የመጣ የብድር ዕዳ አብዛኞቹን አፍሪካ አገሮች ዳግም ወደ ከፍተኛ የብድር ተሸካሚ ደሃ አገሮች አዙሪት ውስጥ እንዳይከታቸው ያሠጋል፡፡

አሜሪካ ምንም እንኳ ዕዳ እንዳይበዛባችሁ የሚለውን ማሳሰቢያ ብትሰጥም በዚያው አግባብ፣ ከቻይና በሚገኘው ገንዘብ አፍሪካውያኑ የገነቧቸውን በርካታ የመሠረተ ልማት አውታሮች ምን ያህል ጉልህ ሚና እንደሚጫወቱ ጠንቅቀው እንደሚገነዘቡ በጨረፍታም ቢሆን ሲጠቃቅሱ ተደምጠዋል፡፡ የቻይና ገንዘብ እንዲቀር ሳይሆን፣ ዕዳው ከምትሸከሙት በላይ እንዳይሆን አስቡበት ያሉት ቲለርሰን፣ አገራቸው ለአፍሪካ ስለምትሰጠው ድጋፍ ግን ብዙም አልጠቀሱም፡፡

አሜሪካ ከ57 ቢሊዮን ዶላር ያላነሰ ድጋፍ እንደምትሰጥ መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡ ይህም አብዛኛው ለጤና ክብካቤ ሥራዎች የሚውል ሲሆን፣ ለትምህርት፣ ለግብርናና ለሌሎችም ዘርፎች የሚውል ብድርና ዕርዳታ ነው፡፡ ይሁንና ለመሠረተ ልማት አውታሮች ግንባታ የምትሰጠው ብድርም ሆነ ዕርዳታ እንደሌለ ግን አምባሳደር ያማማቶ ከሰጡት ማብራሪያ ለመረዳት ተችሏል፡፡ ይብሱንም አሜሪካ ለአፍሪካ ከምትሰጣቸው ዕርዳታዎች ውስጥ ‹‹ትርጉም የማይሰጡ፤›› ያለቻቸውን ፕሮግራሞች እንደምትዘጋ፣ በዚህም የምትሰጠው የገንዘብ ድጋፍም ሊቀንስ የሚችልበት አጋጣሚ ሰፊ መሆኑን ከያማማቶ ማብራሪያ ለመገንዘብ ተችሏል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች