Sunday, September 25, 2022
ሌሎች ዓምዶች
  - Advertisement -
  - Advertisement -

  የተመረጡ ፅሑፎች

  ለዘመኑ የሚመጥን ዘመናይ አገልግሎት

  በየትኛውም መስክ ለሕዝብ የሚቀርቡ አገልግሎቶች ቀልጣፋ እንዲሆኑ ለማድረግ ዘመናዊነት ትልቅ ቦታ ይሰጠዋል፡፡ የአገልግሎት አሰጣጥን ለማቀላጠፍም በአሁኑ ወቅት እየተተገበሩ ካሉ ዘመናዊ አሠራሮች መካከል በኤሌክትሮኒክስ የተደገፉ አገልግሎቶች ተጠቃሾች ናቸው፡፡

  የቴሌኮሙዩንኬሽን መሠረተ ልማት ላይ ተመርኩዘው አገልግሎት እየሰጡ ከሚገኙ አሠራሮች የሚጠበቀውን ያህል ባይሆንም፣ ተስፋ ሰጪ ክዋኔዎችን እያየን ነው፡፡ ሞባይል ስልኮችን በመጠቀም አገልግሎት የሚሰጡ ልዩ ልዩ ሥርዓቶች ብቅ ማለት ጀምረዋል፡፡ ወረቀት ላይ የተመሠረቱ ሥራዎችን እየለወጡ ነው፡፡ ከዚህ አንፃር የአገራችን የፋይናንስ ተቋማት በግልና በጋራ በመሆን እየተገበሯቸው የመጡት አዳዲስ አሠራሮች ተጠቃሽ ሊሆኑ ይችላሉ፡፡

  ባንኮች የኤቲኤም ማሽኖችን ቀስ በቀስ ከሞባይል ስልኮች ጋር በማስተሳሰር ገንዘብ በሞባይል ማንቀሳቀስ የሚቻልበትን ሥርዓት መዘርጋት ጀምረዋል፡፡ ይህንን አገልግሎት ለማስፋት ተጨማሪ ሥራዎች እየተሠሩ ናቸው፡፡ የሕዝብ ማመላለሻ ድርጅቶች ከዚሁ የባንኮች የኤሌክትሮኒክስ የባንክ አገልግሎት ጋር አስተሳስረው የመንገደኞች የጉዞ ትኬት እንዲቆርጡ እየተደረገ ነው፡፡ እንደ ኢትዮጵያ አየር መንገድ ያሉ ተቋማትም የጉዞ ትኬቶችን በተመሳሳይ መንገድ ማቅረብ ጀምረዋል፡፡ ሲኒማ ቤቶችም ለታዳሚዎቻቸው የኤሌክትሮኒክስ መግቢያ ትኬት እያዘጋጁ ነው፡፡ ይህ የሚያሳየን በኤሌክትሮኒክስ የባንክ አገልግሎቶች ብዙ መሥራት እንደሚቻል ነው፡፡ በአገሪቱ ውስጥ ከ25 ሚሊዮን በላይ የባንክ ደንበኞች የተለያዩ ክፍያዎችንና ግብይቶችን በዚሁ በዘመናዊው የኤሌክትሮኒክስ ዘዴ መፈጸም የሚችሉበትን ዕድል አግኝተዋል፡፡ የባንክ ተጠቃሚዎች ቁጥር እየጨመረ በሚሄድበት ጊዜም ይህ ዘመናዊ አገልግሎት ወሳኝ ሥፍራ እየያዘ ይመጣል፡፡ ከዚህ አንፃር በርካታ አገልግሎት ሰጪዎች ራሳቸውን ከዘመናዊ አገልግሎት ጋር ማስተሳሰር እንደሚኖርባቸው አያጠያይቅም፡፡

  በተለይ ለሰጡት አገልግሎት በየወቅቱ ክፍያ የሚሰበሰቡ የግልም ሆኑ የመንግሥት ተቋማት፣ ለአገልግሎታቸው የሚጠይቁትን ክፍያ ደንበኞቻቸው ያሉበት ድረስ እየሄዱ መክፈል የማይገደዱበት ጊዜ መምጣቱ በግልጽ እየታየ ነው፡፡ የኤሌክትሮኒክስ ባንክ አገልግሎት እየተስፋፋ መምጣት ገንዘብ ለማዘዋወር ወይም ለወዳጅ ዘመድ ገንዘብ በመላክ ብቻ እንደማይወሰን አመላካች ነው፡፡

  በአገር አቀፍ ደረጃ ዘመናዊ የባንክ አገልግሎቶች እንዲስፋፉ ለማድረግ እንቅስቃሴ መጀመሩ ቢታወቅም፣ ከዚህ ጥረት ጎን ለጎን ሌሎቹም ተቋማት በዚህ መስመር እንዲጓዙ ለማድረግ ብዙ መሠራት ይኖርበታል፡፡ የውኃ፣ የመብራት የትምህርት ቤትና የሌሎችም ክፍያዎች ሁሉ በዚሁ መስመር እንዲጓዙ የሚደረግበት አሠራር አዝጋሚ ነው፡፡ ግብር ለመክፈል የሚታየውን ትርምስ በዘመናዊው የባንክ አገልግሎት በኩል ማስተሳሰርና ክፍያውን በባንክ ያውም በኤሌክትሮኒክስ ዘዴ ከፋይና ተከፋይ ሳይጉላሉ መስተናገድ እንደሚችሉ ቢታወቅም፣ ይህንን ሥርዓት ለመተግበር የሚታው ዳተኝነት ቀላል አይደለም፡፡

  እንዲህ ያሉ ተቋማት ባንኮቹ ከሚያድጉት ጥረት ባሻገር እንዲህ ወዳሉት አገልግሎቶች እንዲገቡ የሚጠይቅ፣ የማስፈጸሚያ አሠራር ሊተገበር ይገባል፡፡ የጥሬ ገንዘብ እንቅስቃሴ በዚህ መንገድ ሊገታና የገንዘብ ንክኪ ከወረቀት ወደ ኤሌክትሮኒክስ መቀየር እንዳለበት ሳይታለም የተፈታ ነው፡፡ የተጀመሩ አገልግሎቶች እንዲስፋፉ፣ ዘመናዊ አገልግሎቶችም እንዲጎለብቱ ከተፈለገ ለዘመናይ አሠራሮች መትጋት ይገባል፡፡

  ዘመናዊ የባንክ የክፍያ ሥርዓት በተገቢው መንገድ ለሕዝቡ ከማዳረስ አኳያ የምንመለከታቸው ችግሮች ግን ከየትኛውም ዕርምጃ በፊት ቀድመው መፈታት ይኖርባቸዋል፡፡ ለምሳሌ ለአገሪቱ ዘመናዊ የክፍያ ሥርዓትን ለመተግበር እንደ አብነት የሚታየውና የሁሉንም ባንኮች ኤቲኤሞችን በማስተሳሰር በየትኛውም ባንክ ካርድ፣ ከየትኛውም ባንክ ገንዘብ ማንቀሳቀስ የሚያስችለው የኢትስዊች አገልግሎት ደጋግሞ  የሚያጋጥመውን ችግር መግለጽ ይቻላል፡፡

  ደንበኛው ከፈለገውና በአቅራቢያው ከሚያገኘው የባንክ ኤቲኤም ገንዘብ ማውጣት እንዲችል ታስቦ የተዘረጋው መሠረተ ልማት፣ በአግባቡ እንዳይተገበር ከሚያደርጉት ችግሮች ውስጥ፣ የአንዳንድ ባንኮች ኤቲኤም ማሽኖች የሌሎች ባንኮችን ኤቲኤም ካርዶች በቶሎ ማስተናገድ አለመቻላቸው አንዱ ነው፡፡ አልፎ አልፎም ቢሆን የሌላ ባንክ የኤቲኤም ካርድ የማይቀበሉ መኖራቸውም ሲታይ፣ እንዲህ ያሉ ሁኔታዎች ከወዲሁ መቀረፍ እንደሚገባቸው ያመላክታል፡፡ በአንድ ሙከራ አገልግሎቱን ማግኘት አለመቻልም ተደጋግሞ ይስተዋላል፡፡ የኢቲኤም ካርድ ይዘው የሚሰለፉ፣ አጠገባቸው የሌላ ባንክ ኤቲኤም እያለ የባንካቸውን ብቻ ለመጠቀም የሚገደዱ በርካቶች ናቸው፡፡  እንዲህ ዓይነቶቹ ችግሮች ሲደጋገሙ መታየታቸው ወደፊት ለሚታሰበው ዘመናዊ አገልግሎት እንቅፋት ሊሆን ስለሚችል፣ ይህንን አገልግሎት ያለእንከን ለመተግበር የሚያስችል አቅም መፍጠር እንደሚገባ ያስገነዝባል፡፡

  ሌላው ትልቁ ሥጋት የቴሌኮም አገልግሎትን የሚመለከተው ነው፡፡ የኤሌክትሮኒክስ አገልግሎቶች ያለ ቴሌኮም ግንኙነት አይታሰቡም፡፡ ኔትወርክ በጠፋ ቁጥር የሚፈጠረው ትርምስ ከኤቲኤም ገንዘብ ለማውጣት ብቻ ሳይሆን፣ ባንክ ቤት ሄዶ ገንዘብ ለማንቀሳቀስም ጭምር የማይቻልበት በመሆኑ፣ እነዚህን አገልግሎቶች ስናስብ ኢትዮ ቴሌኮም እንዲህ ያለውን መደነቃቀፍ ማስቀረት እንደሚኖርበት ሳንዘነጋ ነው፡፡ ዛሬ ላይ የኔትወርክ መታጎል እንደቀድሞ በሞባይል ስልክ ግንኙነታችንን በመረበሽ ብቻ የሚወስን ሳይሆን፣ የገንዘብ እንቅስቃሴንም የሚገታ ነው፡፡ ከዚህ ጎን ለጎን በየሠፈሩ የሚታየው የመብራት መቆራረጥም ሌላው የተበላሸ አገልግሎት መገለጫ ነው፡፡ ገንዘብ ለማውጣት ማሽኑን አዘው ምላሽ እየተጠባበቁ ባሉበት ቅጽበት መብራት በመጥፋቱ አገልግሎቱ የሚቋረጥባቸው፣ ጊዜያቸው የሚቃጠልባቸውና ንትርክ ውስጥ የሚያስገባቸው አጋጣሚ እያታየ በመሆኑ እንዲህ ያለውን አሠራር ማሻሻል ለአገልግሎቱ መቀላጠፍ ይበጃል እንላለን፡፡

  የጥሬ ገንዘብ ዝውውርን ለማስቀረትና ዘመናዊ የክፍያዎች ሥርዓቶች እንዲሰርፁ ለማድረግ ግንዛቤ ላይ የሚሠሩ ሥራዎች ወሳኝ ናቸው፡፡ ዜጎች ስለአገልግሎቱ በቂ ግንዛቤ እንዲኖራቸው መደረግ አለበት፡፡ ከዚሁ ጎን ለጎን ለአገልግሎቱ የበቃና የተማረ የሰው ኃይል ምን ያህል እየተዘጋጀ ነው የሚለውም ትኩረት ሊሰጠው ይገባል፡፡

  የፋይናንስ ተቋማት ባለሙያዎች የሚሠለጥኑበት ሁነኛ ተቋም የሌላት አገር ከመሆኗ አንፃር ዘመናዊውን አገልግሎት በበቂ ባለሙያ ለመምራት የሚያስችል ተቋም መፍጠሩም ሲታሰብበት ይገባል፡፡ በመሆኑም መጪውን ጊዜ ያገናዘበ የባንክ አገልግሎት ለመስጠት የሚያስችሉ ባለሙያዎች የሚፈልቁበት የትምህርት ተቋም መፈጠር አለበት፡፡ እንዲህ ካሉ አገልግሎቶች ጋር ተያይዞ የሚፈጠረውን የሳይበር ውንብድና ለመቆጣጠርም በዘርፉ ብቁና አዋቂ ዜጎችን የሚያፈራ ተቋም መመሥረትና ማበልጸግ ግድ ይላል፡፡

  Latest Posts

  - Advertisement -

  ወቅታዊ ፅሑፎች

  ትኩስ ዜናዎች ለማግኘት