ከማክሰኞ መጋቢት 4 ቀን 2010 ዓ.ም. ጀምሮ የነዳጅ ማመላለሻ ተሽከርካሪዎች ከጉዞአቸው እንዲስተጓጎሉ ጥሪ ተላልፏል ተብሎ በማኅበራዊ ሚዲያ በተናፈሰው ወሬ ጭንቀት የገባቸው አሽከርካሪዎች በመኖራቸው፣ በኮማንድ ፖስት የሚመራው የፀጥታ ኃይል ተሽከርካሪዎችን በማጀብ ወደ አዲስ አበባ ሸኝቷል፡፡
የነዳጅ ማመላለሻ ተሽከርካዎችን ለአንድ ሳምንት ለማስተጓጎል የተላለፈው ጥሪ በማኅበራዊ ሚዲያ ገጾች መነበብ ከጀመረና እንዲሁም በስሚ ስሚ ወሬው ከተናፈሰ በኋላ፣ በአገር ውስጥ በሚገኙ ከሦስት ሺሕ በላይ የነዳጅ ማመላለሻ ተሽከርካሪዎች በባለንብረቶች፣ በአሽከርካሪዎች በኅብረተሰቡ ዘንድ መነጋገሪያ ሆኖ ሰንብቷል፡፡
በጉዞ ላይ የነበሩ አሽከርካሪዎችና ባለንብረቶቹ ሥጋት ውስጥ ሲወድቁ የማዕድን፣ ነዳጅና የተፈጥሮ ጋዝ ሚኒስቴርና ኮማንድ ፖስቱ ምንም የሚከሰት ነገር እንደማይኖር በመግለጽ ሐሳብ እንዳይገባቸው ማሳሰቢያ ሰጥተዋል፡፡
በዚህ መሠረት ማክሰኞ ዕለት በጉዞ ላይ የነበሩ ተሽከርካሪዎች በያሉበት መቆም ጀምረው እንደነበር ምንጮች ገልጸው፣ ነገር ግን ከሰዓታት ቆይታ በኋላ ተሽከርካሪዎቹ በየአቅጣጫቸው ሲጓዙ ጥበቃ እየተደረገላቸው በመንቀሳቀሳቸው ማተሚያ ቤት እስከገባንበት ጊዜ ድረስ የተፈጠረ ችግር አልነበረም፡፡
በተለይ የከባድ ተሽከርካሪዎች ባለንብረቶች በድጋሚ የኢንሹራንስ ጉዳዮችን ያነሱ ሲሆን፣ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የኢንሹራንስ ኩባንያዎች በመሰል አደጋ ለሚጎዱ ንብረቶች ዓረቦን (ፕሪሚየም) እንዲሸጡ አስተባብሯል፡፡
ማክሰኞ ዕለት በመሰል አደጋ ለሚጠፉ ንብረቶች ዋስትና ስለሚፈጠርበት ጉዳይ ንግግር መጀመሩን ለማወቅ ተችሏል፡፡
የኢትዮጵያ ነዳጅ አቅራቢ ድርጅት ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ታደሰ ኃይለ ማርያም ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ በአሁኑ ወቅት በአገሪቱ በቂ የነዳጅ አቅርቦት አለ፡፡ የተፈጠረ ችግር ባይኖርም በተናፈሰው ወሬ ምክንያት አሽከርካሪዎች መደናገጥ ማሳየታቸውን፣ ነገር ግን ችግሩን ለመፍታት በቅንጅት እየተሠራ ስለሆነ ማክሰኞ ዕለት ነዳጅ የጫኑ ተሽከርካዎች ወደ አገር ገብተዋል ብለዋል፡፡ ነዳጅ የሚያመጡትም ወደ ጂቡቲ መጓዛቸው ተገልጿል፡፡
በተናፈሰው ወሬ ምክንያት ነዳጅ ላይኖር ይችላል የሚል ሥጋት በመፈጠሩም በተለይ ቤንዚን ለመቅዳት ሠልፎች ተስተውለዋል፡፡
አቶ ታደሰ እንደሚሉት የኢትዮጵያ የቤንዚን ፍላጎት በቀን 1.5 ሚሊዮን ሊትር ነው፡፡ ይህ መጠን በገበያ ውስጥ ቢኖርም፣ ከሥጋት አሽከርካሪዎች ቤንዚን ለመቅዳት በመሽቀዳደማቸው እዚህም እዚያም ሠልፎች ተስተውለዋል ብለዋል፡፡