Sunday, April 2, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ጎመጁ ኦይል የፔትሮናስ ምርቶች ለማከፋፈል ስምምነት ፈረመ

- ማስታወቂያ -

ተዛማጅ ፅሁፎች

    የኤታኖልና የሞተር ዘይት ማደባለቂያ ሊገነባ ነው

ጎመጁ ኦይል ኢትዮጵያ የተሰኘው አገር በቀል የነዳጅ ኩባንያ ፔትሮናስ የተባለ ታዋቂ ዓለም አቀፍ የነዳጅ ኩባንያ በኢትዮጵያ ብቸኛ ወኪል በመሆን፣ የፔትሮናስ ቅባትና የሞተር ዘይቶችን ለማከፋፈል የሚያስችለውን ስምምነት ተፈራረመ፡፡

      ፔትሮናስ የማሌዥያ መንግሥት ኩባንያ ነው፡፡ በነዳጅና ጋዝ ፍለጋና ልማት፣ በነዳጅ ማጣሪያ፣ በሞተር ዘይትና ቅባት ምርት፣ በመርከብ ትራንስፖርት፣ በጎማ ዛፍ ልማትና በማዳበሪያ ምርት የተሰማራ ግዙፍ ኩባንያ ነው፡፡ የማሌዥያን ኢኮኖሚ በዋነኛነት በማንቀሳቀስ የሚታወቀው ፔትሮናስ፣ ኢትዮጵያ ውስጥ በጋምቤላና በሶማሌ ክልሎች ውስጥ የነዳጅ ፍለጋ ሥራ ማካሄዱ ይታወሳል፡፡

      የፔትኖናስ የቅባትና ዘይት ክንፍ ከጣሊያን ኤፍ ኤል ሰሌኒያ ከተባለው የፊያት ቅባትና ዘይት አምራች ኩባንያ ጋር እ.ኤ.አ. 2008 በመዋሀድ፣ ፔትሮናስ ሉብሪካንትስን ጣሊያን ቱሪን ውስጥ አቋቁመዋል፡፡

      የፔትኖናስ ሉብሪካንትስና ጎመጁ ኦይል ኢትዮጵያ ሰኞ መጋቢት 3 ቀን 2010 ዓ.ም. በሸራተን አዲስ በሰጡት የጋራ መግለጫ የፔትሮናስ የሞተር ዘይትና ቅባቶችን ያስተዋወቁ ሲሆን፣ ጎመጁ ኦይል ኢትዮጵያ ውስጥ የፔትሮናስ ብቸኛ ወኪል በመሆን ምርቶቹን እንዲያስተዋውቅና እንዲያከፋፍል መስማማታቸውን አስታውቀዋል፡፡

      የፔትሮናስ ሉብሪካንትስ የአፍሪካና የመካከለኛው ምሥራቅ የሽያጭ ኃላፊ ስቲቨን ቫንለንሂድ የፔትሮናስ ቅባትና ዘይቶች ለከባድ የጭነት ማመላለሻ ተሽከርካሪዎች፣ ለሕዝብ ማመላለሻ አውቶቡሶች፣ ለቀላል ተሽከርካሪዎች፣ ለከባድ የኮንስትራክሽንና የግብርና ማሸነሪዎችና ለፋብሪካዎች የሚያገለግሉ እንደሆነ ገልጸዋል፡፡ ኤፍ ኤል ሰሌኒያ የተባለው የፊያት ኩባንያ እ.ኤ.አ. በ1936 ጀምሮ በተለይ ለፊያት ተሽከርካሪዎች የተመረጡ ዘይትና ቅባቶች ሲያመርት መቆየቱን የገለጹት ሚስተር ስቲቨን፣ ይህ ኩባንያ ከፔትሮናስ ጋር ከተዋሀደም በኋላ ለኢቬኮና ኒው ሆላንድ ተሽከርካሪዎች የተመረጡ ዘይትና ቅባቶች ማምረት መቀጠሉን ገልጸዋል፡፡

      ኢትዮጵያ ውስጥ የኢቬኮ ተሽከርካሪዎች በብዛት እንደሚገኙ የገለጹት ሚስተር ስቲቨን፣ የኢቬኮ ተሽከርካሪዎች ከፋብሪካ ሲወጡ የፔትሮናስ ምርት የሆኑ ዘይትና ቅባቶች እንዲጠቀሙ እንደሚመከር ተናግረዋል፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ የሚገኘው ኢቬኮ ኩባንያ ከአገሪቱ ሕግ ጋር በተያያዘ ምክንያት የፔትሮናስ ዘይትና ቅባቶችን ለማስመጣት ሳይችል መቆየቱን ገልጸዋል፡፡ ‹‹አሁን ግን በጎመጁ ኦይል በኩል የፔትሮናስ ዘይትና ቅባቶች ለኢትዮጵያ ገበያ ማቅረብ በመቻላችን ደስተኞች ነን፤›› ብለዋል፡፡

      ፔትሮናስ ሉብሪካንትስ አውሮፓ ውስጥ በጣሊያን፣ በቤልጅየምና በስፔን ሦስት ግዙፍ የሞተር ዘይትና ቅባት ፋብሪካዎች አሉት፡፡ ምርቶቹን በአውሮፓ፣ በመካከለኛው ምሥራቅ፣ በእስያና በአፍሪካ በስፋት እንደሚያከፋፍል ተገልጿል፡፡ በዓመት 600,000 ሜትሪክ ቶን ቅባትና ዘይት በማምረት ከ1.7 ቢሊዮን ዶላር በላይ ገቢ እንደሚያስገባ ተነግሯል፡፡

      የጎመጁ ኦይል ኢትዮጵያ ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ ይግዛው መኮንን በዓለም ቀዳሚ የሞተር ዘይትና ቅባት አምራች የሆነውን ፔትሮናስ ኩባንያ ወደ ኢትዮጵያ ማምጣት በመቻሉ፣ ለጎመጁ ኦይል ትልቅ ስኬት እንደሆነ ገልጸዋል፡፡ ‹‹የፎርሙላ ዋን የመኪና ውድድር ስፖንሰር የሆነው ፔትሮናስ የሚያመርታቸው የሞተር ዘይትና ቅባቶች ከፍተኛ የጥራት ደረጃ ያላቸው ናቸው፡፡ በአገራችን ለሚገኙ ተሽከርካሪዎችና ማሽኖች ከፍተኛ ጠቀሜታ ይኖራቸዋል፤›› ብለዋል፡፡

      አቶ ይግዛው ጎመጁ ኦይል 24 ዘመናዊ የነዳጅ ማደያዎችን ከፍቶ አገልግሎት መስጠት ከጀመረ አንድ ዓመት በላይ እንደሆነ ገልጸው፣ በአሁኑ ወቅት የማደያዎቹ ብዛት 40 ማድረሱን፣ እንዲሁም በቀጣይ በሞተር ዘይትና ቅባት፣ ቡታ ጋዝና ሬንጅ ምርቶች አቅርቦት ላይ አትኩሮ እንደሚሠራ ገልጸዋል፡፡

      አቶ ይግዛው ለሪፖርተር እንደተናገሩት፣ የመሬት ዕጦትና አነስተኛ የትርፍ ህዳግ የነዳጅ ኩባንያዎችን የሚፈታተኑ ዋነኛ ችግሮች ናቸው፡፡ ‹‹እነዚህ የቆዩና እስካሁን ያልተቀረፉ የዘርፉ ዋነኛ ተግዳሮት ናቸው፡፡ አሁንም ቢሆን መንግሥት ችግራችንን ተመልክቶ የመፍትሔ ዕርምጃዎች ይወሰዳል ብለን ተስፋ እናደርጋለን፤›› ብለዋል፡፡

      የጎመጁ ኦይል ኢትዮጵያ መሥራችና ማኔጂንግ ዳይሬክተር አቶ ቴዎድሮስ የሺዋስ፣ በአዲስ አበባ ያለውን የመሬት አቅርቦት ችግር በመመልከትና ለወጣቶች የሥራ ዕድል ለመፍጠር የሚያስችሉ ተንቀሳቃሽ የነዳጅ ማደያዎችን ወደ አገር ውስጥ ማስገባቱን አስታውሰው፣ ተንቀሳቃሽ ማደያዎቹን በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ለተደራጁ አነስተኛና ጥቃቅን ማኅበራት ለማስረከብ በመንቀሳቀስ ላይ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡

      ‹‹በዓለም ቀዳሚ ከሆነው ፔትሮናስ ኩባንያ ጋር አብረን ለመሥራት በመቻላችን ደስተኞች ነን፤›› ያሉት አቶ ቴዎድሮስ፣ በቀጣይ ጎመጁ ኦይል የኤታኖል ነዳጅ፣ የሞተር ዘይትና የቅባት ማደባለቂያ ለመገንባት በዝግጅት ላይ እንደሆነ ገልጸዋል፡፡ ‹‹የኤታኖልና ቤንዚን ማደባለቂያ፣ እንዲሁም የሞተር ዘይትና ቅባቶች ማደባለቂያ ለመገንባት በተባበሩት ዓረብ ኤምሬትስ ከሚገኙ አምራቾች ጋር የጀመርነውን ድርድር እያጠናቀቅን ነው፤›› ብለዋል፡፡

      ጎመጁ ኦይል ኢትዮጵያ በአቶ ቴዎድሮስ የሺዋስና ባለቤታቸው ወ/ሮ ገነት ገብረ እግዚአብሔር በ53 ሚሊዮን ብር ካፒታል በ2007 ዓ.ም. የተመሠረተ ሲሆን፣ በቅርቡ ካፒታሉን ወደ 100 ሚሊዮን ብር አሳድጓል፡፡ ከ300 ሚሊዮን ብር በላይ በሆነ ወጪ 16 የነዳጅ ማደያዎች የገነባው ጎመጁ በአጠቃላይ 40 ማደያዎች ሲኖሩት፣ 60 በመቶ በራሱ አቅም 40 በመቶ ደግሞ በግለሰቦች የተገነቡ ናቸው፡፡ ኩባንያው በነዳጅ ማደያ ሕንፃ ግንባታና በነዳጅ ማመላለሻ ተሽከርካሪዎች ግዢ በአጠቃላይ ከአንድ ቢሊዮን ብር በላይ ኢንቨስት በማድረግ ለ1,000 ያህል ዜጎች የሥራ ዕድል እንደፈጠረ አስታውቋል፡፡

 

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች