Sunday, April 14, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊበጣና ሐይቅ ላይ የተንሰራፋውን የእንቦጭ አረም ለማስወገድ የተገዛው ማሽን ሥራ ጀመረ

በጣና ሐይቅ ላይ የተንሰራፋውን የእንቦጭ አረም ለማስወገድ የተገዛው ማሽን ሥራ ጀመረ

ቀን:

በጣና ሐይቅ ላይ የተንሰራፋውን የእንቦጭ አረም ለማስወገድ ከአንድ ሚሊዮን ብር በላይ የወጣበትና ከቻይና ተገዝቶ የገባው ማሽን ሥራ መጀመሩ ታወቀ፡፡

አማጋ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር በተባለ አገር በቀል ድርጅት የግዥ  ወጪው ተሸፍኖ የመጣው የእንቦጭ ማስወገጃ ማሽን ሰኞ መጋቢት 3 ቀን 2010 ዓ.ም. በአማራ ክልል ከፍተኛ አመራሮች በተገኙበት በይፋ ተመርቆ ሥራ መጀመሩን፣ የአማራ ክልል የአካባቢ ደንና ዱር እንስሳት ጥበቃ ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር በላይነህ አየለ (ዶ/ር) ለሪፖርተር ተናግረዋል፡፡ ማሽኑም አረሙን በማጨድ ረገድ ውጤታማ መሆኑን ዳይሬክተሩ ጠቁመዋል፡፡

ዋና ዳይሬክተሩ የእንቦጭ አረምን ለመከላከል የክልሉ መንግሥትና ሕዝብ በርካታ እንቅስቃሴዎችን ሲያደርጉ እንደነበር አስታውሰው፣ ይህን ጥረት ለመደገፍ አማጋ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር በ52 ሺሕ ዶላር ማሽኑን ከቻይና ገዝቶ እንዳመጣና በጣና ሐይቅ ላይ ለሃያ ቀናት ሙከራ ሲያደርግ ከቆየ በኋላ በይፋ ሥራ እንዲጀምር መደረጉን ጠቁመዋል፡፡

- Advertisement -

Video from Enat Bank Youtube Channel.

የእንቦጭ አረምን በኬሚካል፣ በሰው ጉልበትና በማሽን አማካይነት መከላከል እንደሚቻል የጠቆሙት ዋና ዳይሬክተሩ፣ ‹‹እስካሁን የእንቦጭ አረምን ለመከላከል ስንሞክር የነበረው በሰው ጉልበት ነው፡፡ አሁን ግን ጣናን ለመጠበቅ በማሽን የመከላከል ሥራ ጀምረናል፤›› ብለዋል፡፡

‹‹የኢትዮጵያ ሕዝብ ድጋፍ እንዲያደርግ በተለያየ መንገድ ስንጠይቅ ቆይተናል፡፡ አቅሙ ያላቸው ግለሰቦች ድጋፍ እንዲያደርጉ ስንጠይቅ ነበር፡፡ ይህን ጥሪ ምክንያት በማድረግና የውጭ ምንዛሪ እጥረትን በመጋፈጥ አማጋ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር ምላሽ ሰጥቷል፤›› ሲሉ አብራርተዋል፡፡

ከቻይና የተገዛውን የእንቦጭ አረም ማስወገጃ ማሽን ወደ አገር ቤት ለማስገባት የፈጀውን የትራንስፖርት ወጪም የክልሉና የፌዴራል መንግሥት እንደሸፈኑ ዋና ዳይሬክተሩ ተናግረዋል፡፡ ማሽኑ የገባው  ከሃያ ቀናት በፊት እንደነበር አስታውሰው፣ እስካሁን ድረስ ሙከራ ሲያደርግ እንደነበርና ውጤታማ መሆኑ ሲረጋገጥ በይፋ ሥራ እንዲጀመር መደረጉን ገልጸዋል፡፡ ማሽኑ ውጤታማ እንዲሆንም ከሙያና ቴክኒክ ተመርቀው የወጡ ወጣቶች ሥልጠና ሲጠጥ እንደቆየ ጠቁመዋል፡፡

አሁን የተገዛው ማሽን በሐይቁ ላይ የተንሰራፋውን አረም ሙሉ በሙሉ ማስወገድ ይችላል? ተብሎ ጥያቄ የቀረበላቸው ዋና ዳይሬክተሩ በሰጡት ምላሽ፣ ‹‹ማሽኑ በአንድ ሰዓት አምስት ሺሕ ካሬ ሜትር ላይ ይሠራል፡፡ ይኼ ማሽን አሥር ሰዓት ሲሠራ አምስት ሔክታር ቦታ ማፅዳት ይቻላል ማለት ነው፤›› ብለዋል፡፡

ማሽኑ መሥራት የጀመረው ከሐይቁ ዳር መሆኑን ጠቁመው፣ ከዳር ያለውን የእንቦጭ አረም እየሰበሰበ ማስወገድ ሲጀምር መሀል ያለው እየተሳበ ወደ ዳር እንደሚጠጋ ገልጸዋል፡፡ ማሽኑም በሐይቁ ላይ የተንሰራፋውን አረም ሙሉ በሙሉ ያስወግዳል ተብሎ እንደማይታሰብና ችግሩን ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ለማስገወድ ከተፈለገ፣ ቢያንስ በአንዴ ከአሥር በላይ ማሽኖች እንደሚያስፈልጉ ጠቁመዋል፡፡ ‹‹ይኼም ሆኖ ግን የሰው ጉልበት ወሳኝ ነው፡፡ ይኼ ማሽን በትንሹ 60 ሳንቲ ሜትር ጥልቀት ይፈልጋል፡፡ ከዚህ ውጪ ያለውንና ማሽኑ የማይደርስበትን ቦታ በሰው ጉልበት ነው መሠራት ያለበት፤›› ሲሉ አስረድተዋል፡፡

በ2010 ዓ.ም. የእንቦጭ አረም ከአምስት ሺሕ ሔክታር በላይ የሚሆነውን የሐይቁን ክፍል ሸፍኖ እንደሚገኝና ከአምስት መቶ ሔክታር በላይ የሚሆነውን በሰው ጉልበት ማስወገድ መቻሉን ተናግረዋል፡፡

ማሽኑ ከመገዛቱ በፊት በጎንደርና በባህር ዳር ዩኒቨርሲቲዎች አረሙን ለማስወገድ የተለያዩ ጥረቶች ሲደረጉ እንደነበር መዘገባችን የሚታወስ ሲሆን፣ በጎንደር ዩኒቨርሲቲ ተሠርቶ ሙከራ አድርጎ የነበረው ማሽን የሚቀሩት ሥራዎች እንዳሉ ገልጸዋል፡፡ አረሙን የማስወገጃ ሌላኛው መንገድ ጢንዚዛዎችን ወደ ሐይቁ በመልቀቅ አረሙን እንዲበሉት የማድረግ ዘዴ እንደሆነ የሚታወቅ ሲሆን፣ በባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ ጢንዚዛዎችን የማራባት ሒደት አሁንም በሚፈለገው ደረጃ ላይ እንዳልደረሰ አስረድተዋል፡፡

በጣና ሐይቅ ላይ የተንሰራፋውን የእንቦጭ አረም ለማስወገድ የፌዴራል መንግሥት እገዛ አነስተኛ ነው መባሉን በተመለከተ መዘገባችን የሚታወስ ሲሆን፣ በአሁኑ ወቅት የደንና የአየር ንብረት ለውጥ ሚኒስቴር ጉዳዩን በሙሉ ባለቤትነት ይዞ እየሠራ እንደሆነ ዋና ዳይሬክተሩ ተናግረዋል፡፡ ሚኒስቴሩ አረሙን ለመከላከል በሚደረገው ጥረት ያግዝ ዘንድ አንድ አዲስ መኪና ገዝቶ ከማስረከቡ በላይ፣ ሦስት ሚሊዮን ብር ድጋፍ ማድረጉን ጠቁመዋል፡፡ ነገር ግን የውኃ አካላትን የማስተዳደር ሚና ያለው የውኃ፣ መስኖና ኤሌክትሪክ ሚኒስቴር እስካሁን ምንም ዓይነት ድጋፍ አለማድረጉን ጠቁመዋል፡፡ ይህን በተመለከተ የውኃ መስኖና ኤሌክትሪክ ሚኒስቴር የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊን አስተያየተቸውን እንዲሰጡ ቢደወልላቸውም፣ በተደጋጋሚ ስብሰባ ላይ ነኝ የሚል ምላሽ በመስጠታቸው ምላሻቸውን ማካተት አልተቻለም፡፡

በጣና ሐይቅ ላይ የተንሰራፋውን የእንቦጭ አረም ለመከላከል በሚደረገው ጥረት የግል ባለሀብቶች ድጋፍ ወሳኝ መሆኑን መምጣቱን ዋና ዳይሬክተሩ አስታውሰዋል፡፡ እስካሁንም በባህር ዳር ከተማ ከሚገኘውና ኮከብ ቀለም ፋብሪካ ከተሰኘው ድርጅት በየወሩ የሚደረግ የገንዘብ ድጋፍ እንዳለ ጠቁመዋል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም አቶ በላይነህ ክንዴ የሚባሉ ባለሀብት እስካሁን አንድ ሚሊዮን ሦስት መቶ ሺሕ ብር ድጋፍ ማድረጋቸውን ገልጸዋል፡፡ አትሌት ደራርቱ ቱሉ ሁለት መቶ ሺሕ ብር፣ የዳሸን ባንክ የዳይሬክተሮች ቦርድ ሁለት ሚሊዮን ብር ድጋፍ ማድረጋቸውን ጠቁመው፣ ከአገር ውጭ ደግሞ ‹‹ግሎባል ኮኦሌሽን ፎር ሌክ ጣና›› የተሰኘው ተቋም በተለያዩ አገሮች የሚገኙ ኢትዮጵያዊያንን  በማስተባበር የእንቦጭ ማስወገጃ ማሽን መግዛቱንና በአሁኑ ወቅት ወደ አገር ቤት እየገባ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

 

 

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የም እና መስህቦቿ

በቱባ ሀገሬ የም በማዕከላዊ ኢትዮጵያ የሚገኝ ሲሆን ከአዲስ አበባ በ239...

ከሴራ ፖለቲካ በስተጀርባ ጥቅማቸውን የሚያስጠብቁ ኃይሎች

በመኮንን ሻውል ወልደ ጊዮርጊስ የአፄ ቴዎድሮስ መንግሥት የወደቀው ከመቅደላ በፊት...

ስለዘር ፖለቲካ

በሀብታሙ ኃይለ ጊዮርጊስ  ‹‹በቅሎዎች ዝርያችን ከአህያ ነው እያሉ ይመፃደቃሉ›› የጀርመኖች...

አማርኛ ተናጋሪዋ ሮቦት

በአዲስ አበባ ከተማ በሚገኘው የሳይንስ ሙዚየም፣ ሚያዝያ 2 ቀን...