Friday, December 8, 2023
- Advertisment -
- Advertisment -

የሞያሌው ክስተት መወገዝ አለበት!

መሰንበቻውን በሞያሌ በንፁኃን ዜጎች ላይ የደረሰው ሞትና የአካል ጉዳት በፍፁም ማጋጠም የሌለበት ከመሆኑም በላይ፣ ድርጊቱ በፅኑ ሊወገዝ ይገባል፡፡ ይህ ዓይነቱ ድርጊት የዜጎችን በሕይወት የመኖርና የአካል ደኅንነት መብትን ከመግፈፍ በተጨማሪ፣ በምንም ዓይነት ሁኔታ ተቀባይነት የሌለው ነው፡፡ በዚህ አሳዛኝ ግድያ ምክንያት ሕዝብ በመንግሥት ላይ ያለውን አመኔታ ከማጣት ጀምሮ፣ የአገሩን ዕጣ ፈንታ የበለጠ በሥጋት እንዲያይ ግፊት ተፈጥሮበታል፡፡ ወትሮም በሰብዓዊ መብቶች አያያዝ ምክንያት ስሟ በዓለም አደባባይ የሚብጠለጠልባት አገር ቀውስ ተዘፍቃ፣ ‹በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ› የሚሆንባት አጋጣሚ ሲፈጠር የበለጠ ያስመርራል፡፡ በተሳሳተ መረጃ በመመራት የዘጠኝ ንፁኃንን ሕይወት በማጥፋት፣ በ12 ሰዎች ላይ የአካል ጉዳት ያደረሱ የመከላከያ ሠራዊት አባላት በቁጥጥር ሥር መዋላቸው ተሰምቷል፡፡ በተቻለ ፍጥነት ድርጊቱ ተጣርቶ ለፍርድ መቅረብ አለባቸው፡፡ ለሕዝብም ይፋ መሆን አለባቸው፡፡ በተፋጠነ የፍርድ ሒደትም ቅጣታቸውን ሊያገኙ ይገባል፡፡ ክቡር የሆነው የሰው ሕይወት በተሳሳተ መረጃ በሚል ምክንያት ደመ ከልብ ሆኖ መቅረት ስለሌለበት፣ በዕዝ መዋቅሩ ውስጥ የሚመለከታቸው ሁሉ ፍትሕ ፊት ሊቀርቡ የግድ ይላል፡፡

ዜጎች ሰብዓዊ ፍጡር በመሆናቸው የማይደፈርና የማይገሰስ በሕይወት የመኖርና የአካል ደኅንነት መብት ሲኖራቸው፣ ይህንንም የማስከበር ትልቅ ኃላፊነት ያለበት መንግሥት ነው፡፡ አገሪቱ በዓለም አቀፍ ደረጃ በተፈራረመቻቸው የሰብዓዊ መብት ሰነዶችም ሆነ፣ በሕገ መንግሥቱ ዋስትና የተሰጣቸው መሠረታዊ መብቶች ካልተከበሩ የሚጠየቀው መንግሥት ነው፡፡ በሞያሌ በደረሰው አሳዛኝ ድርጊት ኃላፊነት ያለባቸው ተጠያቂዎችን ለፍርድ ማቅረብ ያለበት መንግሥት ሲሆን፣ ሐዘንን በመግለጽ ብቻ ችላ ተበሎ የሚታለፍ ጉዳይ አይደለም፡፡ ከዚህ ቀደምም ሆነ ሰሞኑን በተፈጸሙ ግድያዎች፣ የአካል ጉዳቶችና የማፈናቀል ድርጊቶች በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ተሳታፊ የሆኑ ግለሰቦችና ተቋማት በሕግ ፊት ተጠያቂ መሆን አለባቸው፡፡ ወደ ሞያሌ አቅንቷል የተባለው የመከላከያ ሠራዊቱ ከፍተኛ አዛዦች የሚገኙበት አጣሪ ቡድን ያለማንም ጣልቃ ገብነት ሪፖርቱን በሀቅ ሊያቀርብ ይገባል፡፡ አጣሪ ቡድኑ የጥቃቱ  ሰለባ የሆኑ ቤተሰቦችን፣ ተጎጂዎችን፣ የዓይን ምስክሮችን፣ የአገር ሽማግሌዎችንና የተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎችን በግልጽ በማነጋገር የተጣራ ሪፖርት ይዞ መምጣት ይጠበቅበታል፡፡

ሌላው ትኩረት መደረግ ያለበት አንድ በሚገባ የሠለጠነ የሻለቃ ጦር ግዳጁን ለመወጣት እንቅስቃሴ ሲያደርግ በተሳሳተ መረጃ እንዴት ሊመራ ቻለ? በወቅቱ የሠራዊቱ ባልደረቦች ንፁኃን ዜጎች ላይ ያለምንም ማጣራት እንዴት ተኩስ ሊከፍቱ ቻሉ? በእጃቸው የጦር መሣሪያ ያልያዙ ሰዎች ላይ ተኩስ ከመክፈት በፊት፣ ሌሎች የሚወሰዱ መሠረታዊ የሚባሉ የጥንቃቄ ቅድመ ዕርምጃዎች እንዴት ተግባራዊ አልሆኑም? ለምሳሌ እጃቸውን ወደ ላይ አድርገው ሰላማዊ መሆናቸውን እንዲገልጹ፣ ወይም ወደ ሰማይ የማስጠንቀቂያ ተኩስ ማድረግ አይቻልም ነበር? የታጠቀ ጠላትስ ቢሆን መጀመርያ እጁን እንዲሰጥ ወይም እንዲማረክ ጥረት ይደረጋል? ወይስ ዝም ተብሎ ተኩስ ይከፈታል? በአነስተኛ መስዕዋትነት ወይም ኪሳራ ውጤት ማግኘት የሚችል ሠራዊት አባላት ሲቪሎች ላይ ዝም ብለው ሲተኩሱ ምክንያቱ ምን ይሆን? ብሎ ሕዝብ ውስጥ ለሚብላሉ ጥያቄዎች ትክክለኛ ምላሽ መገኘት አለበት፡፡ ማጣራቱና ምርመራው እንደተጠናቀቀ ተጠያቂዎች በወታደራዊ ፍርድ ቤት እንደሚዳኙ ተገልጿል፡፡ ይህ ሲሆን ደግሞ የፍርድ ሒደቱ ግልጽነት ሊኖረው ይገባል፡፡ መረጃዎችም ለሕዝብ በፍጥነት መድረስ ይኖርባቸዋል፡፡ በወታደራዊ ፍርድ ቤት ምንም እንኳ ከብሔራዊ ደኅንነት ጋር በተያያዘ በችሎቱ የሚነሱ ሚስጥራዊ ጉዳዮች መኖራቸው ግልጽ ቢሆንም፣ ግልጽነት መኖሩ ግን መተማመን ለመፍጠር ይረዳል፡፡

አገሪቱ መስቀለኛ መንገድ ላይ ቆማ ከቀውስ ውስጥ ለመውጣት ሙከራ እያደረገች ባለችበት በዚህ ወቅት፣ በየቦታው የሚያጋጥሙ የሞትና የአካል ጉዳት አደጋዎች በየጊዜው ሰቆቃ እየፈጠሩ ነው፡፡ ላለፉት ሁለት ዓመታት በላይ ሞት፣ የአካል ጉዳትና መፈናቀል የአገሪቱ መለያ ሆነዋል፡፡ አንፃራዊ ሰላምና መረጋጋት በነበረባት አገር በሰከነ መንገድ በመነጋገር ያጋጠሙ ችግሮችን መፍታት እያቃተ፣ ሊተካ የማይችለው ክቡር የሰው ሕይወት በከንቱ ይጠፋል፡፡ ተተኪውን ጠቅላይ ሚኒስትር ለመሰየም የሚያስችለውን ሒደት የኢሕአዴግ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ በስብሰባ ለመጀመር ዋዜማ ላይ ሆኖ፣ ሞያሌ ውስጥ የዘጠኝ ዜጎች ሕልፈት ሲሰማ ለቀናት ሰፍኖ የነበረው ዕፎይታ ወደ ዘሐን ተለውጧል፡፡ አሁንም በሌላ ሥፍራ ምን ያጋጥም ይሆን የሚለው ደግሞ የሕዝቡ የተለመደ ሥጋት ሆኗል፡፡ በእንዲህ ዓይነቱ ሁኔታ ውስጥ እስከ መቼ ይዘለቃል? እንደሚታወቀው የፀጥታ ኃይሎች ሥምሪት ሲወጡ ከምንም ነገር በላይ ቅድሚያ መስጠት ያለባቸው ለዜጎች ሕይወትና የአካል ደኅንነት ነው፡፡ በየደረጃው ያሉ ኃላፊዎችም ይህንን መሠረታዊ ጉዳይ ከምንም ነገር በላይ ቅድሚያ ሊሰጡ ይገባል፡፡ እርግጥ ነው አንዳንዴ ስህተት ቢያጋጥም እንኳን፣ ስህተቱ ሊያደርሰው የሚችለው ጉዳት እጅግ በጣም አነስተኛ መሆን አለበት፡፡ ከምንም ነገር በላይ ለጥንቃቄ ትኩረት መስጠት አደጋን ይቀንሳል፣ ወይም እንዳይኖር ያደርጋል፡፡

መንግሥት ሕዝብን ማረጋጋት አለበት፡፡ ሰላሙና ደኅንነቱ የተረጋገጠ እንዲሆንም በተግባር ማሳየት ይኖርበታል፡፡ ተተኪውን ጠቅላይ ሚኒስትር ለመሰየም በሚደረገው ጥረትም ከአገር በላይ ምንም ነገር እንደሌለ በመተማመን የጋራ መግባባት ላይ መድረስ ተገቢ ነው፡፡ የገዥው ፓርቲ ኢሕአዴግ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባላት ከፍተኛ አመራሮች እንደ መሆናቸው መጠን፣ ውስጣቸው ይኖራል ተብሎ የሚታሰበውን አለመግባባት በሰከነ መንገድ በመፍታት የጋራ የፖለቲካ ውሳኔ ላይ መድረስ ይጠበቅባቸዋል፡፡ የሥልጣን ሽግግሩ በተሳካ ሁኔታ ተከናውኗል የሚባለው ቢያንስ ሕዝብን ማግባባት ሲቻል ነው፡፡ በኢሕአዴግ ምክር ቤት የግንባሩ ሊቀመንበር ሲመረጥም ሆነ በፓርላማ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሲሰየም፣ በሕዝብ ዘንድ የጋራ የሆነ ስሜት ሊፈጥር ይገባል፡፡ ይህም ሒደት ቀጣዩን ምርጫም ሆነ ለዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ የሚያግዙ መሠረቶችን ለመጣል የሚረዳ በመሆኑ፣ በቅንነት ለአገር የሚጠቅም ተግባር ማከናወን ተስፋ ሰጪ ይሆናል፡፡ ከሥልጣን በላይ ሕዝብ አለ፣ አገር አለች ብሎ መወሰን የሚጠቅመው ግጭቶችን ለማስቀረትና የተቃወሰውን ሰላም ለማስመለስ ነው፡፡ ከዚህ አሳዛኝ ቀውስ ውስጥ መውጣት ይገባል፡፡

ኢትዮጵያም ሆነች ይህ ጨዋና አስተዋይ ሕዝብ አሁን ያለው አሳዛኝ ሁኔታ አይመጥናቸውም፡፡ የኢትዮጵያ ሕዝብ እርስ በርሱ ተደጋግፎና ተሳስቦ፣ ብሔርና እምነት፣ ቋንቋና ባህል፣ ወዘተ. ሳይገድቡት ያለችውን በፍቅር ተካፍሎ የሚኖር ተምሳሌታዊ ሕዝብ ነው፡፡ ተጋብቶና ተዋልዶ አርዓያነትን ማሳየት የቻለም ነው፡፡ ይህንን የመሰለ ሕዝብ ይዞ ቀውስ ውስጥ መቆየት ያስተዛዝባል፡፡ በየጊዜው ግጭት እየተቀሰቀሰ የሰው ክቡር ሕይወት ሲጠፋ፣ የአካልና የሥነ ልቦና ጉዳት ሲደርስና ታይቶ የማይታወቅ የአገር ውስጥ መፈናቀል ሲያጋጥም ወዴት እያመራን ነው? ተብሎ በስክነትና በጥልቀት መነጋገር ይገባል፡፡ ይህንን የመሰለ ታሪካዊ ሕዝብና ይህችን ታሪካዊት አገር ከገቡበት አረንቋ ውስጥ በፍጥነት ማውጣት የግድ ነው፡፡ አገር መስቀለኛ መንገድ ላይ ቆማ ሕዝቡ ግራ በተጋባበት በዚህ አሳሳቢ ጊዜ፣ በቀውስ ላይ ቀውስን መደራረብ ከማይወጡት አዘቅት ውስጥ ይከታል፡፡ አሁንም ጊዜ ስላለ ለመፍትሔ መረባረብ ይገባል፡፡ በዚህ አጋጣሚ በሞያሌ በተፈጠረው አሳዛኝ ክስተት ሕይወታቸው ለጠፋና ጉዳት ለደረሰባቸው ወገኖች ጥልቅ ሐዘናችንን እንገልጻለን፡፡ ለቤተሰቦቻቸውም መፅናናትን እንመኛለን፡፡ ክስተቱም መወገዝ አለበት እንላለን!

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች

ታዋቂው የኤሌክትሮኒክስ ብራንድ አይቴል የስትራቴጂ ለውጥ አካል የሆነውን አዲስ አርማ እና መለዮ ይፋ አደረገ።

በአለማችን ታዋቂ ከሆኑት የኤሌክትሮኒክስ ብራንዶች መካከል አንዱ የሆነው እና...

የጠቅላላ ጉባኤ ስብሰባ ጥሪ ለሸገር አነስተኛ የፋይናንስ ተቋም አ.ማ ባለአክሲዮኖች በሙሉ

ለሸገር አነስተኛ የፋይናንስ ተቋም አ.ማ ባለአክሲዮኖች በሙሉ የሸገር አነስተኛ የፋይናንስ...

[የክቡር ሚኒስትሩ ጸሐፊ፣ የሌላ ሚኒስትር ጸሐፊ ከሆነችው የቅርብ ወዳጇ ጋር በስልክ እየተጨዋወቱ ነው]

አንቺ ግን ምን ሆነሽ ነው? ጠፋሁ አይደል? ጠፋሁ ብቻ?! ምን ላድርግ ብለሽ...

በሱዳን ላይ ያጠላው የመከፋፈል ዕጣና ቀጣናዊ ተፅዕኖው

የሱዳን ጦርነት ስምንተኛ ወሩን እያገባደደ ይገኛል፡፡ ጄኔራል አብዱልፈታህ አልቡርሃን...

ኦሮሚያ ኢንሹራንስ በግሉ ኢንሹራንስ ዘርፍ ሁለተኛውን የገበያ ድርሻ ለመያዝ ያስቻለውን ውጤት ማስመዝገቡን ገለጸ

ኦሮሚያ ኢንሹራንስ ኩባንያ የባንኮች የጥሬ ገንዘብ እጥረት፣ የመለዋወጫ ዕቃዎች...
spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

ለአገልግሎት ሰጪ ተቋማት የደንብ ልብስ አለባበስ የጌጣጌጥና መዋቢያ አጠቃቀም ደንብን ማውጣት ለምን አስፈለገ?

በዳንኤል ንጉሤ በሆቴልና መሰል አገልግሎት ሰጪ ተቋማት ባለሙያዎች የደንብ ልብስ አለባበስ፣ የጌጣጌጥ አጠቃቀም የገጽታና የውበት አጠባበቅን አስመልክቶ በተዘጋጀው ረቂቅ ደንብ ላይ ውይይት ተካሂዷል፡፡ ረቂቅ ደንቡን ያዘጋጀው...

ትኩረት ለሕዝብና ለአገር ደኅንነት!

ኢትዮጵያ ውስጥም ሆነ በቅርብ ርቀት ባሉ አገሮች፣ እንዲሁም ራቅ ባሉ የአፍሪካና የዓለም አገሮች ውስጥ የሚስተዋሉ ዘርፈ ብዙ ችግሮች የተፅዕኖ አድማሳቸው እየሰፋ ነው፡፡ ኢትዮጵያ ሌላው...

የአስተሳሰብና የአስተዳደር ዘይቤ ለውጥ ያስፈልጋል!

ኢትዮጵያ ውስጥ ሕዝቡን በጋራ አስተሳስረው የሚያኖሩ በጣም በርካታ ማኅበራዊ እሴቶች አሉ፡፡ እነዚህ ለዘመናት ከትውልድ ወደ ትውልድ ሲሸጋገሩ የኖሩ እሴቶች አገር ለማቆም ትልቅ አስተዋፅኦ ነበራቸው፣...