- በጣም ተጨንቄያለሁ ክቡር ሚኒስትር?
- ምንድነው የሚያስጨንቅህ?
- እንቅልፍ ወስዶኝ አያውቅም፡፡
- ታዲያ የእንቅልፍ ኪኒን ለምን አትወስድም?
- ኪኒኑስ ከየት ይመጣል?
- ከፋርማሲ ነዋ፡፡
- ዶላር የለማ፡፡
- ማን ዶላር ዋጥ አለህ?
- ኪኒኑ እኮ በዶላር ነው የሚገዛው፡፡
- አየህ ለዚህ ነው ኢኮኖሚያችን ማኑፋክቸሪንግ ላይ ማተኮር አለበት የምንለው፡፡
- ከማኑፋክቸሪንግ በፊት መቅደም ያለበት ነገር አለ፡፡
- ምንድነው የሚቀድመው?
- ሰላም ነዋ፡፡
- ስለዚህ ሰላም ለማስፈን አንድ ፕሮጀክት መንደፍ አለብን፡፡
- ምን ዓይነት ፕሮጀክት?
- በመጀመርያ የሰላም ምልክት እንፈልግ፡፡
- የሰላም ምልክት ምንድነው?
- ነጭ እርግብ፡፡
- ምን?
- በቃ አሁኑኑ ነጭ እርግብ ማርባት እንጀምር፡፡
- እንዴ ለምን?
- ሕዝቡ ውስጥ የሰላምን ሐሳብ ለማስረፅ ነዋ፡፡
- እንዴት ነው በነጭ እርግብ ሕዝቡ ውስጥ ሰላም የሚሰርፀው?
- ከዚያም ባለፈ ሌላ የምናደርገው ነገር አለ፡፡
- ምን?
- ፋሲካ እየደረሰ መሆኑን ታውቃለህ አይደል?
- ገና አንድ ወር ይቀረዋል፡፡
- ስለዚህ ለሠራተኛው ለበዓል ዶሮዎች ገዝተን እንሰጣለን፡፡
- የምን ዶሮ?
- ነጫጭ ዶሮዎች፡፡
- እየቀለዱ ነው ክቡር ሚኒስትር?
- እሱ ብቻ አይደለም፡፡
- ደግሞ ሌላ ምን አለ?
- ለወንዶች ሠራተኞቻችን ነጫጭ ከረባት እንሰጣለን፡፡
- እ. . .
- ለሴቶቹ ደግሞ ነጫጭ ሻርፕ፡፡
- ወይ ክቡር ሚኒስትር?
- ከቻልን ደግሞ ሠራተኞቹ ተደራጅተው ቅርጫ ይግቡ፡፡
- የምን ቅርጫ?
- ነጭ በሬ የምናድርበትን ቅርጫ ነዋ፡፡
- ምንም ሊገባኝ አልቻለም ክቡር ሚኒስትር?
- ሕንፃችንም ነጭ ቀለም ይቀባ፡፡
- ለምን?
- ሰላምን ባገኘናት አጣጋሚ ልንዘምራት ይገባል፡፡
- ይህን ፕሮጀክት ከሰላም ጋር ምን አገናኘው ታዲያ?
- አንተ አይገባህም እንዴ?
- ሰላምና ነጭ ነገሮችን ምን አገናኛቸው?
- ሰላምና ነጭ ቀለም ሊነጣጠሉ አይችሉም፡፡
- ክቡር ሚኒስትር ሰላም የሚመጣው እኮ የሕዝቡ ጥያቄ ሲመለስ ነው፡፡
- ይኼ የሕዝቡ ጥያቄ አለመሆኑን በምን አወቅክ?
- ክቡር ሚኒስትር የሕዝቡ ጥያቄ የቀለም አልመሰለኝም፡፡
- አንተ አልገባህም፡፡
- ብቻ ይኼ ፕሮጀክት እርስዎንም በኋላ እንዳያስጠይቅዎት፡፡
- በምን?
- በቀለም አብዮት!
[የክቡር ሚኒስትሩ ሾፌር ከቢሯቸው ወደ ቀጠሮ ቦታቸው እየወሰዳቸው ነው]
- ምን ሆነህ ነው የምታዛጋው አንተ?
- ይቅርታ ክቡር ሚኒስትር፡፡
- ይኼን አረቄ አሁንም አልተውክም አይደል?
- የምን አረቄ?
- ያው ምሽቱን አረቄህን ስትለጋ ታመሽና አሁን ታዛጋለህ፡፡
- የምትበላው የላት የምትከናነበው አማራት አሉ፡፡
- እሱን እንኳን ተወው፡፡
- እርስዎ ግን በጣም ነው የሚያስቀኑኝ፡፡
- እንዴት?
- በቃ ኢትዮጵያ ውስጥ ሳይሆን ፓሪስ የሚኖሩ ነው የሚመስሉት፡፡
- አልገባኝም?
- ሁሉ ነገር የተመቸዎት ነዎት፡፡
- እዚች ወርቅ አገር ላይ ተቀምጬ እንዴት አይመቸኝ?
- እኔ ግን እየተማረርኩ ነው፡፡
- ምንድነው የሚያማርርህ?
- ኑሮ ነዋ ክቡር ሚኒስትር?
- ስማ ዝም ብለህ አታሟርት፡፡
- ክቡር ሚኒስትር ምግብ እኮ የምበላው በቀን አንዴ ነው፡፡
- ይቺን ይወዳል ሰውዬው፡፡
- ምነው ክቡር ሚኒስትር?
- ተቃውሞ ላይ ነህ እንዴ?
- የምን ተቃውሞ?
- ማለቴ በቀን አንዴ የምትበላው ለምንድነው?
- ኑሮ ተቃውማኝ ነዋ፡፡
- ድሮም አንተ ተቃዋሚ እንደሆንክ ገብቶኛል፡፡
- ምን እያሉ ነው ክቡር ሚኒስትር?
- የታላቁ መሪን ራዕይ ለማበላሸት ነው የምትሠራው ማለት ነው?
- እንዴት ማለት?
- እሳቸው ሕዝቡ በቀን ሦስቴ እንዲበላ ነበር የሚያልሙት፡፡
- እሱ ታዲያ የእሳቸው ራዕይ ሊባል አይችልም፡፡
- ምን?
- እሱ ህልም ነው፡፡
- እንደ አንተ ዓይነት ተቃዋሚዎች ናቸው እኮ አገር የሚያሰድቡት፡፡
- ምን እያሉ ነው ክቡር ሚኒስትር?
- እንደዚህ ዓይነት ለም አገር ላይ እየኖርክ በቀን አንዴ ነው የምበላው ስትል አታፍርም?
- ምን ላድርግ ክቡር ሚኒስትር?
- የአገሪቷ ኢኮኖሚ እኮ በሁለት አኃዝ እያደገ ነው፡፡
- አይሳሳቱ ክቡር ሚኒስትር፡፡
- ዓለም የመሰረከው ነው ስልህ?
- አሁን በሁለት አኃዝ እያደገ ያለው ኢኮኖሚው አይደለም፡፡
- ታዲያ ምኑ ነው እያደገ ያለው?
- ግሽበቱ!
[ክቡር ሚኒስትሩ ከደላላ ወዳጃቸው ጋር እያወሩ ነው]
- በጣም አሳስቦኛል ክቡር ሚኒስትር?
- ምኑ ነው ያሳሰበህ?
- የወዳጃችን ጉዳይ ነዋ፡፡
- የትኛው ወዳጃችን?
- እርስዎም ረሱት ክቡር ሚኒትር?
- እኔ በርካታ ወዳጅ ስላለኝ ስለየቱ ነው የምታወራው?
- ዋናው ወዳጃችን ነዋ፡፡
- ለምን ጊዜዬን ታቃጥልብኛለህ?
- የትልቁ ሆቴል ባለቤት ናቸዋ፡፡
- ውይ በሞትኩት ምን ሆኑ?
- በቃ ቄሱም ዝም መጽሐፉም ዝም ሆነ እኮ ነገራቸው፡፡
- እንዴት?
- ደብዛቸው ጠፋ እኮ፡፡
- በነገራችን ላይ እኔም ናፍቀውኛል፡፡
- የሆነ ነገር ለምን አንሞክርም?
- ምድነው የምንሞክረው?
- እሳቸውን ማስፈታት ነዋ፡፡
- እንዴት አድርገን?
- ይኸው እናንተ በአሥር ሺዎች የሚቆጠሩ እስረኞችን እየለቀቃችሁ አይደል እንዴ?
- ታዲያ እኛ እሳቸውን መቼ አሰርናቸው?
- አይ ያው ከእናንተ ልምድ እንዲወስዱ ለምን አትመክሯቸውም?
- ቢሆንማ ደስ ይለኛል፡፡
- በጣም የሚያሳዝነው ደግሞ ሚዲያው ራሱ ስለእሳቸው አለመዘገቡ ነው፡፡
- ያው ተረቱ እንደዚያው ነው፡፡
- የትኛው?
- በወደቀ ዛፍ ምሳር ይበዛበታል የሚለው ነዋ፡፡
- ለነገሩ እውነትዎትን ነው፡፡
- እንዴት?
- ይኸው በዚህ ዓመት ከሊስቱ ወጡ እኮ፡፡
- ከየትኛው ሊስት?
- ከቢሊየነሮች ሊስት ነዋ፡፡
- ለምን?
- እኔ አላወቅኩም፡፡
- ሊወረስ ይሆን እንዴ?
- ምኑ?
- ሀብታቸው፡፡
- ኧረ የሰይጣን ጆሮ ይደፈን፡፡
- ምነው?
- ማን ሊያሳክመን? ማን ሊያዝናናን?
- ስለእሱ እንኳን አታስብ፡፡
- እንዴት?
- እኛ እኮ በመተካካት እናምናለን፡፡
- አልገባኝም ክቡር ሚኒስትር?
- እሳቸው ከሊስት ውስጥ ቢወጡም እኔ ልተካቸው ተግቼ እየሠራሁ ነው፡፡
- ማንን?
- ባለሀብቱን!