ከሰሞኑ የዓለም አቀፍ እግር ኳስ ማኅበር (ፊፋ) ተወካዮች በአዲስ አበባ ቆይታ አድርገው፣ የአገሪቱን የስፖርት አመራሮችና ዕጩ ተወዳዳሪዎችን አነጋግረው ተመልሰዋል፡፡ ተወካዮቹ የብሔራዊ ፌዴሬሽኑን ቀጣይ አመራሮች ለመምረጥ በነበረው ሒደት ሲከናወን የቆየውንና ያለውን ሽኩቻ ተከትሎ ለማጣራት ወደ ኢትዮጵያ እንደሚመጣ ከተነገረ ሰነባብቷል፡፡
ይሁንና ለሽኩቻው መንስዔ ብቻም ሳይሆን መሠረታዊ ስህተት ሆነው ያገኟቸውን ጉዳዮችም አንስተው፣ ቅሬታቸውንም ገልጸው እንደተመለሱ ምንጮች በተለይ ለሪፖርተር አረጋግጠዋል፡፡
የብሔራዊ ፌዴሬሽኑ አመራሮች ተጠራርተው ለኃላፊነት የሚሰየሙበት አካሄድ ብቃትና አቅምን መነሻ ያደረገ ሳይሆን ‹‹ብሔር ተኮር›› መሆኑና የብሔር ተዋጽኦ ላይ የተመሠረተ መሆኑ በፊፋ መልዕክተኞች ዘንድ ትዝብት ውስጥ የገባ አሠራር ሆኖ መገኘቱም እየተነገረ ይገኛል፡፡ ከዚህም በላይ የአመራሩን የምርጫ ሒደትና አጠቃላይ ያለውን ነገር እንዲያመቻች በጉባዔው የተሰየመው አስመራጭ ኮሚቴ በራሱ የዓለም አቀፉን ሕግጋት የጣሰ ስለመሆኑ ጭምር ተወካዮቹን ማስገረሙ ተነግሯል፡፡
በዚህ አግባብ ለአስመራጭነትም ሆነ ለምርጫ የቀረበ አካል ‹‹የእኔ ካልሆነ ሌሎች የመጡበት አግባብ ትክልል አይደለም ብሎ አፉን ሞልቶ መናገር የሚችልበት አንደበት ሊኖር አይችልም፤›› የሚል መደምደሚያ ላይ ስለመድረሱ ጭምር የሚናገሩ አሉ፡፡ እንደነዚህ ወገኖች አስተያየት ከሆነ፣ መልዕክተኞቹ የዓለም አቀፉን ተሞክሮ መነሻ በማድረግ በተለይም እግር ኳስ ከብሔርና ከክልል ገብ አሠራሮች ካልተላቀቀ በቀር፣ ስፖርታዊ መርሆዎች ገለልተኝነትን ማለትም ከፖለቲካ፣ ከሃይማኖትና ከሌሎችም ተፅዕኖዎች ነፃ መሆን እንዳለበት ጭምር ያምናሉ፡፡ በተጨባጭ መሬት ያለው አሠራር የዓለም የእግር ኳስ መሠረታዊ ድንጋጌን የሚጥስ ለዚያም አንድ የተወሰነ አካልንም ብቻ ተጠያቂ በማድረግ ለችግሩ መፍትሔ ማግኘት እንደማይቻል የፊፋ ልዑካን ትዝብታቸውን መናገራቸው ታውቋል፡፡
የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንታዊና የሥራ አስፈጻሚ ምርጫ ከጥቅምት 30 ወደ የካቲት 24 ቀን 2010 ዓ.ም. ሲንከባለል መቆየቱ ይታወቃል፡፡ ለዚህ ዋናው ምክንያት ደግሞ በአንድም ሆነ በሌላ ምርጫው የሚመለከታቸው ወገኖች ከእግር ኳሱ ይልቅ የግል ፍላጎትን መነሻ በማድረግ የፊፋ የምርጫ ሥነ ምግባር ኮድ ‹‹ተጥሷል አልተጣሰም›› በሚል ለፊፋ ሲላኩ የቆዩ ደብዳቤዎች በዋናነት ይጠቀሳሉ፡፡
ጉዳዩን ሲከታተል የቆየው ፊፋ መጋቢት 3 ቀን ሁለት ተወካዮቹ አዲስ አበባ ገብተው ከምርጫው ጋር ተያይዞ ይመለከታቸዋል ያሏቸውን ወገኖች አነጋግረው በእዚያው ዕለት ምሽት ላይ መመለሳቸው ታውቋል፡፡
ለተወካዮቹ በተለይም ከአስመራጭ ኮሚቴው ስብሳቢ የቀረበላቸው አቤታቱ፣ በዓለም አቀፍ የምርጫ ሕግ መሠረት በአስመራጭነት መሰየም የሌለባቸው ሰዎች መካተታቸው፣ በተጨማሪም ለምርጫው የክልል ውክልና ማግኘት የሌለባቸው ዕጩ ተወዳዳሪዎች መኖራቸውና ለዚያም መንግሥታዊ አካሉ ይሁንታ መስጠቱ የሚሉት ይጠቀሳሉ፡፡
ከዕጩ ተወዳዳሪዎች ጀምሮ የተለያዩ አካላትን በአዲስ አበባ ሒልተን በተናጠል ያነጋገሩት የፊፋ ተወካዮች፣ ከአፍሪካም አልፎ ለዓለም እግር ኳስ እዚህ ደረጃ መድረስ ከሚጠቀሱ አገሮች ኢትዮጵያ አንዷ መሆኗ፣ ችግሮች ቢፈጠሩ እንኳን ለእግር ኳሱ ሲባል ቀላሉንና የተሻለውን መንገድና አማራጭ መከተል አስፈላጊነቱን በመግለጽ ምክረ ሐሳብ ሰጥተዋል፡፡ የምርጫው ቀንና ቦታን በሚመለከት ልዑካኑ ይዘው የተመለሱትን መረጃ መሠረት በማድረግ ፊፋ ለኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን እንደሚያሳውቅም ይጠበቃል፡፡