Wednesday, June 19, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

ማኅበራዊ​​​​​​​ሥጋት የደቀነው አዲሱ ወረርሽኝ

​​​​​​​ሥጋት የደቀነው አዲሱ ወረርሽኝ

ቀን:

ውስብስብ የአንጎል ቀዶ ሕክምና በተሳካ ሁኔታ በሚካሄድበት እንዳሁኑ ዘመን አይደለም፡፡ ማንኛውንም ዓይነት በሽታን ወይም የሕመም ስሜትን ማስታገስና መፈወስ በሚቻልበት ወቅት ሳይሆን ሥልጣኔ ገና ዳዴ በሚልበት በጥንታዊ ዓለም ነበር፡፡ ጠንከር ባለ በሽታ የተያዘ መጨረሻው ሞት በነበረበት፣ ከሰው ወደ ሰው የሚተላለፉ በሽታዎች በቀላሉ በወረርሽኝ መልክ በሚከሰቱበት በዚያ ዘመን ነበር የጅስቲኒያን (The Plague of Justinian)  ወረርሽኝ በታሪክ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸውን ሰዎች በአንዴ ጥርግ ያደረገው፡፡

ወረርሽኙ በ541 እንደተከሰተ ነበር በተለያዩ የዓለም ክፍሎች ተዳርሶ ከ25 እስከ 50 ሚሊዮን ሰዎችን በአንዴ የፈጀው፡፡ ይህም እስከዛሬ ከተከሰቱና በርካቶችን እንደ ቅጠል ካረገፉ ከባድ ወረርሽኞች በአስከፊነቱ የመጀመርያ ደረጃ እንዲይዝ ያደረገው ነበር፡፡

በ16ኛው ምዕት ዓመት አጋማሽ የተከሰተው ብላክ ፕሌግ (Black Plague) ነበር፡፡ መነሻውን በእስያ አህጉር ያደረገው ይህ ወረርሽኝ ወደ ተለያዩ የዓለም ክፍሎች የተዛመተው በአይጦች አማካይነት ነበር፡፡ ወረርሽኙ በተከሰተ ከስድስት እስከ አሥር ቀናት ውስጥ ባሉት ጊዜያት 80 በመቶ የሚሆኑ በበሽታቸው የተጠቁ ሰዎች አለቁ፡፡

- Advertisement -

በርካቶችን በመቅጠፍ የሚታወቀው አሁንም ያልተገታው እ.ኤ.አ. በ1960 የተከሰተው የኤችአይቪ ወረርሽኝ ነው፡፡ ለዚህ ወረርሽኝ እስካሁን ድረስ ፈውስን ማግኘት ከባድ ሆኖ ቆይቷል፡፡ እስካሁን 70 ሚሊዮን ሰዎችን ያጠቃ ሲሆን፣ 39 ሚሊዮን የሚሆኑትን ደግሞ ለሞት ዳርጓል፡፡

ከቀደምት ዘመናት እ.ኤ.አ. ከ1918 እስከ 1920 ድረስ የቆየው ስፓኒሽ ፍሉም (የኅዳር በሽታ) በሚሊዮኖች ሰዎችን ሲገድል፣ በሃያኛው ምዕት ሁለተኛ አጋማሽ በነበረው ኤዥያን ፍሉ ደግሞ ብዙዎችን ቀጥፏል፡፡ እነዚህ በወረርሽኞች በሰዎች ሕይወት ላይ ከባድ ጥፋት ያደረሱና በታሪክ የማይዘነጉ ክፉ አጋጣሚዎች ናቸው፡፡

በቅርቡ ተከስተው የነበሩ እንደ ኢቦላ፣ ዚካ ቫይረስና ኮሌራ የመሳሰሉት ምላሽ የተገኘላቸው በጤናው ዘርፍ የተሠሩና በመሠራት ላይ የሚገኙ የምርምር ሥራዎችና ዝግጅቶች በመኖራቸው ነው፡፡ እነዚህ ወረርሽኞችን መቆጣጠር እስኪቻል ድረስ ግን የበርካቶችን ሕይወት አመሰቃቅሏል፣ ለሞት ዳርጓል፣ ቤተሰብ እንዲበተን ምክንያት ሆኗል፡፡

‹‹መሰል የጤና ቀውሶች ከመከሰታቸው አስቀድሞ አስፈላጊው ዝግጅት በበቂ ሁኔታ ቢደረግ የተመዘገበው የአደጋ በዚህ መጠን አስከፊ ባልሆነ ነበር›› የሚሉት አቶ ኃይለ ሚካኤል ጌታቸው በአርማወር ሀንሠን የምርምር ተቋም የምርምር ሥልጠና አስተባባሪ ናቸው፡፡

አርማወር ሀንሠን በሕክምናው ዘርፍ የሚገኙ መሠረታዊ የምርምር ሥራዎች የሚሠራ ተቋም ነው፡፡ በባክቴሪያና በቫይረስ የሚመጡ እንዲሁ ቆላማ በሆኑ አካባቢዎች በስፋት የሚከሰቱ የተዘነጉ በሽታዎች ላይ ምርምር ሲያደርግ ከ40 ዓመታት በላይ አስቆጥሯል፡፡ ተቋሙ ከኖርዌይ፣ ከስዊድን ሴፍ ዘቺልድረንና ከኢትዮጵያ መንግሥት ጋር በተደረገው ሦስትዮሽ ስምምነት የተመሠረተ ነው፡፡

‹‹ባለፉት የተለያዩ ዓመታት በዓለም ደረጃ የተከሰቱ እንደ ኢቦላ፣ ሳልስ፣ ፍሉ የመሳሰሉት ወረርሽኞች ነበሩ፡፡ እነዚህ ወረርሽኞች በተለያዩ ምክንያቶች በአየር ለውጥ አልያም በሌላ በድጋሚ ሊከሰቱ የሚችሉበት ዕድል ሰፊ ነው፤›› የሚሉት አቶ ኃይለ ሚካኤል እንዲህ ላሉ አጋጣሚዎች ተገቢውን ምላሽ መስጠት የሚያስችል ዝግጅት መኖሩን ማረጋገጥ የኮአሊሽን ፎር ኤፒደሚክ ፕሪፔርድነስ ኢኖቬሽን (ሴፒ) ተግባር መሆኑን ይናገራሉ፡፡

በምዕራብ አፍሪካ ተከስቶ በነበረው የኢቦላ ወረርሽኝ ዓለም አቀፍ ማኅበረሰቡ ያደረገው ርብርብ ወረርሽኙን ለመቆጣጠር ያስቻለ ነበር፡፡ ይሁንና መቆጣጠር እስኪቻል ድረስ ጥቂት የማይባሉ ሕይወታቸውን ገብረዋል፡፡ እንዲህ ያሉ ጉዳቶች ከመድረሳቸው በፊት ወረርሽኞችን መቆጣጠር ሴፒ የተቋቋመበት ዋና ዓላማ መሆኑን አቶ ኃይለ ሚካኤል ይናገራሉ፡፡ ከወራት በፊት የኖርዌይ ልዑል አልጋ ወራሽ ኢትዮጵያን ለመጎብኘት ወደ እዚህ በመጡበት ወቅት የኢትዮጵያ መንግሥት የዚህ አጋርነት አባል በመሆን ስምምነት ተፈራርሟል፡፡

ሴፒ የመጀመርያውን ኮንፈረንስ በኢትዮጵያ ያደረገው ባለፈው ሳምንት አጋማሽ በአለርት ግቢ ነበር፡፡ የኮንፈረንሱ ዓላማም ቀጣይ የትኩረት አቅጣጫ ሆነው አስፈላጊው የምርምርና የዝግጅት ሥራ የሚያስፈልጋቸውን የበሽታ ዓይነቶች መለየት ነበር፡፡ በወረርሽኝ ደረጃ በመከሰት ከባድ ጉዳት ሊያደርሱ ይችላሉ ተብለው የተለዩት በሽታዎች ሚድል ኢስት ሪስፓራቶሪ ሲንድረምና ላስ ፊቨር ናቸው፡፡

መነሻው መካከለኛው ምሥራቅ የሆነው ሚድል ኢስት ሪስፓራቶሪ ሲንድረም በስፋት ተከስቶ በወረርሽኙ ሰዎች ሕይወታቸውን አጥተዋል፡፡ ከእንስሳት ወደ ሰው እንዲሁም ከሰው ወደ ሰው የሚተላለፈው በሽታው ትኩሳት፣ ሳልና የትንፋሽ ማጠር ምልክቶችን ያሳያል፡፡ 80 በመቶ የሚሆነው የበሽታው ሥርጭት እስካሁን በሳዑዲ ዓረቢያ የተመዘገበ ነው፡፡ በወረርሽኙ ከተያዙ መካከል 35 በመቶዎቹ መሞታቸውን የዓለም ጤና ድርጅት ሪፖርት ያሳያል፡፡

እ.ኤ.አ. ከ2012 ጀምሮ በ27 አገሮች ተከስቷል፡፡ አልጄሪያ፣ ባህሬን፣ አውስትራሊያ፣ ጀርመን፣ ጣልያን በሽታው ከታየባቸው አገሮች መካከል ናቸው፡፡ በኢትዮጵያም በአርብቶ አደሩ ማኅበረሰብ አካባቢ በተለይም በግመሎች ላይ ተከስቷል፡፡ ወረርሽኙ ሊያደርስ የሚችለውን ጉዳት አስቀድሞ መከላከል ላይ ያተኮረ ክትባት የማዘጋጀትና የማምረት ሥራ እንዲሠራ ሴፒ እንቅስቃሴ እያደረገ እንደሚገኝ ሴፒ በጋዜጣዊ መግለጫው አስታውቋል፡፡

ከዚህ ዓመት አጋማሽ ጀምሮ በተለያዩ የምዕራብ አፍሪካ አገሮች በተለይም በናይጄሪያ ለ90 ሰዎች ሞት ምክንያት የሆነው ላሣ ፊቨርን በተመለከተም ሴፒ ተመሳሳይ ሥራ እየሠራ ይገኛል፡፡ ከተባይ ወደ ሰው፣ ከሰው ወደ ሰው የሚተላለፈው ይህ በሽታ የአካባቢና የግል ንጽሕና በመጠበቅ፣ ተባዮችን ቤት ከመግባት በማገድ መከላከል ይቻላል፡፡

የሴፒ ዋና ሥራ አስፈጻሚው ዶ/ር ሪቻርድ ሀችት ‹‹ኢትዮጵያ ላለፉት 20 ዓመታት በመጀመርያ ደረጃ ጤና አጠባበቅ ላይ በሠራችው ሥራ ስኬታማ ውጤት አስመዝግባለች፡፡ ይህ ለሌሎችም አገሮች ምሳሌ መሆን ይችላል፡፡ ሊከሰቱ በሚችሉ ወረርሽኞች ዙሪያ አብረን በመሥራታችንም ደስተኛ ነን፤›› ብለዋል፡፡ እንደ ሚድል ኢስት ሪስፓራቶሪ ሲንድረም ያሉ ወረርሽኞች በወረርሽኝ ደረጃ ቢከሰቱ ግን አገሪቱ ለሁለት አሠርታት የለፋችበትን የጤናውን ዘርፍ አደጋ ላይ እንደሚጥል፣ አስቀድሞ ዝግጅት ማድረጉ ግን ወሳኝ መሆኑ ተሰምሮበታል፡፡ ሴፒ እ.ኤ.አ. በ2017 በህንድ፣ በኖርዌይ መንግሥት፣ በቢልኤንድ ሚሊንዳ ጌትስ ፋውንዴሽንና በዌልካም ኤንድ ወርልድ ኢኮኖሚክ ፎረም ትብብር የተቋቋመ ነው፡፡ በአሁኑ ወቅት በጀርመን፣ በጃፓን፣ በአውስትራሊያ፣ በቤልጂየምና በካናዳ መንግሥታት ድጋፍ ይደረግለታል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የንብረት ማስመለስ ረቂቅ አዋጅና የሚስተጋቡ ሥጋቶች

ከሰሞኑ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የቀረበው የንብረት ማስመለስ ረቂቅ...

የመጨረሻ የተባለው የንግድ ምክር ቤቱ ምርጫና የሚኒስቴሩ ውሳኔ

በአገር አቀፍ ደረጃ ደረጃ የንግድ ኅብረተሰቡን በመወከል የሚጠቀሰው የኢትዮጵያ...

ሚስጥሩ!

ጉዞ ከካዛንቺስ ወደ ስድስት ኪሎ፡፡ የጥንቶቹ አራዶች መናኸሪያ ወዘናዋ...