Sunday, April 2, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

የአዳማው ኩሪፍቱ ሪዞርት ቃጠሎ ደረሰበት

- ማስታወቂያ -

ተዛማጅ ፅሁፎች

በቦስተን ፓርትነርስ ሥር ከሚተዳደሩ ሪዞርቶች፣ ሆቴሎችና ሬስቶራንቶች መካከል አንዱ የሆነው የአዳማው ኩሪፍቱ ሪዞርት ሰኞ፣ መጋቢት 3 ቀን 2010 ዓ.ም. በደረሰበት የእሳት አደጋ ሳቢያ ውድ የመኝታ ክፍሎችን ጨምሮ 24 ልዩ ክፍሎች መውደማቸው ታወቀ፡፡

የኩሪፍቱ ሪዞርትና ስፓ ባለቤት አቶ ታዲዮስ ጌታቸው ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ የእሳት አደጋው መጋቢት 3 ቀን 2010 ዓ.ም. ከረፋዱ 4፡30 ገደማ ተቀስቅሶ ፕሬዚዴንሺያል ስዊትስ የሚባሉትን ጨምሮ በ24ቱም ክፍሎች ውስጥ የነበሩ መገልገያዎች ሙሉ ለሙሉ አውድሟል፡፡ የአደጋው መንስዔ በሆቴሉ ክፍሎች አቅራቢያ የነበረ የኤሌክትሪክ ኃይል ተሸካሚ መስመር በፈጠረው ግንኙነት (ኮንታክት) የእሳት አደጋ በመቀስቀሱ ሲሆን፣ ይኸው የኤሌክትሪክ መስመር እንዲቀየር በተደጋጋሚ አቤቱታ ሲቀርብበት እንደቆየ አቶ ታዴዎስ ገልጸዋል፡፡

ቦስተን ፓርትነርስ የአዳማውን ኩሪፍቱ ሪዞርት ለ15 ዓመታት ከተከራየ በኋላ አሁን በእሳት አደጋ የተቃጠሉትንና ባህላዊ አገነባብ የሳር ክዳን የለበሱትን ልዩ ክፍሎች በሪዞርት ደረጃ አገልግሎት ሲሰጡ ነበር፡፡

የእሳት አደጋው እንደተከሰተ የአካባቢው ነዋሪዎች፣ የፌዴራልና የኦሮሚያ ፖሊስ አባላት እንዲሁም ከሞጆ ደረቅ ወደብና ከኢትዮጵያ አየር ኃይል የተውጣጣ የእሳት አደጋ ሠራተኞች ቡድን በመምጣት እሳቱን በማጥፋት እገዛ መረባረባቸው ታውቋል፡፡ በአዳማ ከተማ የሚገኘው የትራክተር ፋብሪካና የከተማው የእሳት አደጋ ሠራተኞችም እሳቱን ለማጥፋት በማገዛቸው ጭምር፣ እሳቱ ወደ ሌሎች የሆቴሉ ይዞታዎችና ክፍሎች እንዳይዛመት መግታት አስችለዋል፡፡ በተለይ የአካባቢው ነዋሪዎች፣ የክልሉና የፌዴራል ፖሊሶች እንዲሁም የመከላከያ ሠራዊት አባላት ርብርብ እንዳስገረማቸው የገለጹት አቶ ታዲዮስ፣ የስድስት ዓመት ታዳጊ ጭምር በጣሳ ውኃ እየቀዱ ቃጠሎውን ለማጥፋት ያደረጉት ርብርብ ስሜት ይነካ ነበር ብለዋል፡፡

የደረሰውን ውድመትና ያስከተለውን የጉዳት መጠን ለማወቅ እየተጠና በመሆኑ በአሁኑ ወቅት ግምቱን ማወቅ ያስቸግራል ያሉት አቶ ታዲዮስ፣ የተቃጠሉትን ክፍሎች ወደነበሩበት ደረጃ ለመመለስ የመልሶ ግንባታ ሥራ መጀመሩንና በአጭር ጊዜ ውስጥም ወደ ቀድሞ ሥራቸው እንዲገቡ ይደረጋል በማለት ገልጸዋል፡፡

 በአዳማ የሚገኘው ኩሪፍቱ ሪዞርት ወደ ሥራ የገባው ከሦስት ዓመት በፊት ሲሆን፣ በአደጋው የተቃጠሉትን ክፍሎች ጨምሮ 96 የመኝታ ክፍሎች እንደነበሩት ለማወቅ ተችሏል፡፡

ኩሪፍቱ ሪዞርቶችና ሆቴሎች በይዞታው ሥር በሚገኙ ሆቴሎች ላይ ከዚህ ቀደም አደጋ አጋጥሞት አያውቅም፡፡ በአዳማ የደረሰው አደጋም ቢሆን ከሆቴሉ አቅምና ቁጥጥር ውጭ በሆነ ምክንያት የተፈጠረ ሲሆን፣ አደጋ ያደረሰው የኤሌክትሪክ መስመርም ቢሆን የደረሰውን አደጋ ከማድረሱ በፊት በተፈጠረ ሥጋት ሳቢያ ለኤሌክትሪክ ኃይል አገልግሎት መሥሪያ ቤት በተደጋጋሚ እንዲያስተካክል ማመልከታቸውን አቶ ታዲዮስ አስታውሰዋል፡፡ በወቅቱ ሊስተካከል ባለመቻሉ ግን አደጋውን አስከትሏል፡፡ ከአደጋው በኋላ ግን መሥሪያ ቤቱ መስመሩን ማስተካከሉ ታውቋል፡፡

ኩሪፍቱ ሪዞርት ከ15 ዓመታት በፊት ሥራ የጀመረው በቢሾፍቱ ከተማ ኩሪፍቱ ሐይቅ ዳርቻ በገነባው ሪዞርት አማካይነት ነበር፡፡ በአሁኑ ወቅት በቦስተን ፓርትነርስ ሥር የሚተዳደሩና በመገንባት ላይ የሚገኙ 13 ሆቴሎችና ሬስቶራንቶች ያሉት ሲሆን፣ በባህር ዳር፣ በቡራዩ በገለአርታና በዝዋይ የሚገኙት ሪዞርቶች ይጠቀሳሉ፡፡

በጂቡቲ ደሴትም የሪዞርት ሆቴል እየገነባ እንደሚገኝም ይታወቃል፡፡ በጂቡቲ የሚገኘው የጂቡቲ ኩሪፍቱ ፕሮጀክት በመጀመርያው ምዕራፍ ከ150 ሚሊዮን ብር በላይ ፈጅቷል፡፡ ‹‹ኢትዮጵያ ቪሌጅ›› የሚል መጠሪያ የተሰጠው ይህ ፕሮጀክት በአሁኑ ወቅት ግንባታው እየተጠናቀቀ ይገኛል ተብሏል፡፡ የኢትዮጵያ ባህላዊ ምርቶችን የሚስተዋውቁ መደብሮችን አካቶ እየተገነባ የሚገኘው ኢትዮጵያ ቪሌጅ ሪዞርት ሆቴል፣ በዚህ ዓመት ወደ ሥራ ይገባል ተብሎ ይጠበቃል፡፡ ኩሪፍቱ ሪዞርትና ስፓ ለሁለት ሺሕ ቋሚና ጊዜያዊ ሠራተኞች የሥራ ዕድል ያስገኘ ሲሆን፣ ኢትዮጵያ ቪሌጅ ወደ ሥራ ሲገባም አንድ ሺሕ ሠራተኞችን የመቅጠር አቅም እንዳለው ተጠቅሷል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች