በተለያዩ ዓለም አገሮች ለትውልድ የሚተርፉ አገራዊ ፋይዳቸው የጎላ ግንባታዎች ይከናወናሉ፡፡ ግንባታዎቹ በመሠረተ ልማት አውታርነት ለዜጎች ከሚሰጡት ቁሳዊ አገልግሎት ባሻገር ትልቅ ግምት የሚሰጣቸው ታሪካዊ ቅርስ እስከመሆን ይደርሳሉ፡፡ ታዲያ ግንባታቸው ተጠናቆ ወደ ሥራ እንዲገቡ ለማስቻል የሚኖረው ትግል የገንዘብ አቅምን ከመፈታተን ይጀምራል፡፡ በተለይም እንደ ኢትዮጵያ ላሉ ታዳጊ አገሮች ነገሮች በይበልጥ መባድ እንደሚሆኑ ጥያቄ የለውም፡፡ ትግሉ የሚጀምረውም መሰል አገራዊና ግዙፍ ግንባታዎች ለአንድ አገር ዕድገት የሚኖራቸውን ሚና ለዜጎች ከማስተማር ይጀምራል፡፡ ማኅበረሰባዊ ንቃትና ግንዛቤን ለመፍጠር፣ መቀራረብን በማምጣት ረገድ ደግሞ ጥበብ የተለየ ሚና ትጫወታለች፡፡
የመሠረት ድንጋይ መጋቢት 24 ቀን 2003 ዓ.ም. ተጥሎ ግንባታው ከተጀመረ ሰባተኛ ዓመቱን የያዘው የታላቁ ኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብም መሰል አገራዊ ፋይዳ ያለው በጥበብ የታጀበ ንቅናቄ ያስፈለገው ግዙፍ ፕሮጀክት ነው፡፡ ሙሉ ለሙሉ በኢትዮጵያውያን ባለሙያዎች እየተገነባ የሚገኘው ግድቡ በአሁኑ ወቅት በከፊል ተጠናቋል፡፡ ግድቡን ዕውን ለማድረግም ከ10.8 ቢሊዮን ብር በላይ ከማኅበረሰቡ የተሰበሰበ ሲሆን፣ ማኅበረሰቡ የእኔነት ስሜት እንዲሰማው፣ የቻለውን ሁሉ እንዲያደርግ የተለያዩ ሥራዎች የተሠሩት ማኅበረሰቡን ማቀራረብ በሚችሉ ኪነ ጥበባዊ ክንውኖች ነው፡፡
የዚህ ኪነጥበባዊ አካል የሆነው የቁንጅና ውድድሩም መጋቢት 1 ቀን 2010 ዓ.ም. በግዮን ሆቴል ተካሂዷል፡፡ የህዳሴ ግድቡ አምባሳደር የምትሆነዋን ቆንጆ የተመረጠችው ከሁሉም ክልሎችና ከተማ አስተዳደሮች የተወጣጡ ቆነጃጅት መካከል ነበር፡፡ ቆነጃጅቱ በባህላዊ አልባሳት አሸብርቀው ነበር የቀረቡት፡፡
በየክልሉ የአምባሳደርነት ማዕረግ የተሰጣቸው ከአንድ እስከ ሦስት የወጡት ቆነጃጅት 27 ነበሩ፡፡ በተሰጣቸው ቁጥር መሠረት ወደ መድረኩ እየወጡ የመጡበትን ክልልና በየአካባቢያቸው የሚገኙ ባህላዊና ትውፊታዊ መገለጫዎች ለታዳሚው እያስረዱ በቄንጠኛ አረማመድ ሰበር ሰካ እያሉ ይመለሳሉ፡፡ ዳግም ስማቸው እስኪጠራ ከመጋረጃ ጀርባ ሆነው ይጠባበቃሉ፡፡
በየዘርፉ የተሰማሩ ባለሙያዎች እንዲሁም ዲዛይነሮች የዳኝነቱን ቦታ ይዘዋል፡፡ ቀደም ብሎ ተወዳዳሪዎች ላይ ከሚታየው የተክለ ሰውነታቸው ማማር ባሻገር ሊያውቋቸው የሚገቡ መሰረታዊ የቁንጅና ሕጎችና ውስጣዊ ዝግጅት እንዲኖራቸው የአራት ቀናት ያህል ሥልጠና እንዲወስዱ ተደርጓል፡፡ በተጨማሪም ከውድድሩ ባሻገር የግድቡ አምባሳደር ሆነው ሲመረጡ ወደ ማኅበረሰቡ ወርደው ከሕዝቡ ጋር ተቀራርበው እንዴት መሥራት እንዳለባቸውም ጭምር አስፈላጊውን መሠረታዊ ግንዛቤ ተሰጥቷቸዋል፡፡
በኔክስት ዲዛይን፣ በዮርዲ ዲዛይን፣ በፀደይና በፍቅር ዲዛይን ደምቀው ከቀረቡት 14 ተወዳዳሪዎች ሰባቱን መለየት ለዳኞቹ አስቸጋሪ ነበር፡፡ በመጨረሻም ሰባት ቆነጃጅት ውስጥ በአምባሳደርነታቸው የሚጠብቃቸውን ግዴታ እንዴት ትወጡታላችሁ? ለሚለው ከዳኞች ለቀረበው ጥያቄ በሰጡት ምላሽ ሩት አያሌው ከሰሜን ወሎ፣ ሉሲ ገደቦ ከአዲስ አበባና ሰዓዳ አልሀጂ ከቤንሻንጉል ጉሙዝ ከአንድ እስከ ሦስት በመውጣት የግድቡ አምባሳደር ሆነው ተመርጠዋል፡፡ እንደየደረጃቸው ከ15ሺ እስከ 35ሺ ብር ቦንድ ተሸላሚ ሆነዋል፡፡
በቀጣይም የሦስቱ አምባሳደሮች ድርሻ የሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነቶችን ከማጠናከር አንፃር በአገር ውስጥና ከአገር ውጭ በመዟዟር ስለግድቡ አጠቃላይ ሁኔታና ፋይዳ ማሳወቅ እንዲሁም አስፈላጊውን መረጃ መስጠት ነው፡፡
በኢትዮጵያዊ አለባበስ የተሸቀረቀሩት ተወዳዳሪዎች ውስጥ 14ቱ በቀረበላቸው ጥያቄ መሠረት ተለይተው ሲቀሩ ቀሪዎቹ ደግሞ ወደ መጡበት ክልል ተመልሰው በአምባሳደርነታቸው ሚና ሊቀጥሉ እንደሚገባቸው አደራ ተሰጥቷቸዋል፡፡
የግድቡን ሴት አምባሳደር ለመምረጥ በየክልሎቹና በሁለቱ የከተማ አስተዳደሮች ተዘዋውሮ ቆነጃጅትን የመምረጡ ሒደት ስድስት ወራት ፈጅቷል፡፡ በሁሉም አካባቢዎች ቁንጅና ውድድር በማካሄድና ከ1 እስከ 3 የወጡትን ለሁለተኛው ዙር ውድድር የማዘጋጀት ሥራ ሲሠራ የከረመውም ‹‹የታላቁ ህዳሴ ግድባችን የአገራችን ኅብረ ዜማ የህዳሴያችን ማማ›› በሚል መሪ ቃል ነበር፡፡
ከአንደኛ ደረጃ እስከ ዩኒቨርሲቲ ደረጃ ትምህርታቸውን እየተከታተሉ የሚገኙ ቆነጃጅት የተሳተፉበት የቁንጅና ውድድሩ የህዳሴውን ሦስት እንስት አምባሳደሮች ለመለየት ከየክልሉ 33 ተወዳዳሪዎችን ቢለዩም በዚህኛው ውድድር የተሳተፉት ግን 27ቱ ብቻ ነበሩ፡፡
ክልላቸውን ወክለው ከመጡት 27 ተወዳዳሪዎች ውስጥ የአፋርና የደቡብ ክልል ስልጤ ዞን ባህላቸውን ብቻ በመድረኩ ላይ በማሳየት ከውድድሩ ራሳቸውን አግልለዋል፡፡ በተቀራኒው ከህዳሴ ግድብ ሥፍራ የመጡት የቤንሻንጉል ጉሙዝ እንስቶች የበርታ፣ ማኦና ሺናሻ ብሔሮችን ባህል ለታዳሚው አስተዋውቀዋል፡፡
ከ6,450 ሜጋ ዋት በላይ እንደሚያመነጭ የተነገረለት የህዳሴ ግድቡን ለማጠናቀቅና በኅብረተሰቡ ዘንድ ግንዛቤ ለመፍጠር የሙዚቃ ድግስ ከማዘጋጀት ጀምሮ እግር ኳስ ጨዋታዎችም አንዱ የግንዛቤ ማስጨበጫ አካል ነበር፡፡ የመጀመሪያው ዙር የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ውድድር መጠናቀቅ በኋላ የኢትዮጵያ ቡና፣ ሲዳማ ቡና፣ ኤሌክትሪክና ደደቢት ያሳተፈ የዋንጫ ጨዋታ ተከናውኖ እሑድ መጋቢት 2 ቀን 2010 ዓ.ም. ኢትዮጵያ ቡና ሲዳማ ቡናን 2 ለ 1 በመርታት የህዳሴው ግድብ ዋንጫ አንስቷል፡፡