ነሐሴ አጋማሽ ላይ በአሸንዳ በዓል የደመቀችው መቐለ ከተማ ሦስት ጉልቻ የጎለቱ፣ ጎጆ የወጡ ሙሽሮችንም አስተናግዳለች፡፡ ሠርጉ ነሐሴ 17 ቀን 2007 ዓ.ም. የሆነለት አንዱ ሠርግ መልሱ በነሐሴ 19 ቀን ላይ ሲውል፣ በባህላዊ ልብስ የደመቁትን ሙሽሮች አመሻሽ ላይ ሊወስድ፣ በመቐለ ጎዳና ከቀትር በኋላ ሲሽከረከር የነበረው በተሸለሙ ፈረሶች ሲጎተት የነበረውን ያጀቡት ሠረገላ በፈረሶች ሲገተቱ የነበሩት የቮልስ ዋገን ጉራጆች ናቸው፡፡ (ፎቶ በሔኖክ ያሬድ)
*****
ሰው መሆን ሌላ ነው
ቀን – ደምን
ደም – ቀለምን
ቀለም – ደግሞ – ስምን
ሲጠራ – ሲመራ
ሰው መሆን ገረመኝ
እማ – ያገባኝን
ቀን ሽቶኝ – ለመጣሁ
ቀን ትቶች – ልሔደው
ተልኬ በመጣሁ
ነፋስ እገዛ ብዬ
ቀን – ደምን
ደም – ቀለምን
ቀለም ደግሞ ስምን
ሲገዛ – አ – የሁ፡፡
ቁራ ልሁን – እርግብ
የቱ ይሻለኛል …?
ገበያው ጎተተኝ – ያልመጣሁበቱ
አደራው ከበደኝ – የታመንኩበቱ፡፡
እርግብ – ልሁን – ቁራ
የቱ ይሻለኛል…?
ሰው መሆን – ሲያስጠላ
ሰው መሆን – ሲያስፈራ
ዕርግብ ልሁን ቁራ …?
አገኘሁ አዳነ ድልነሳሁ ‹‹ጨለማን ሰበራ›› 1997
*************
ሕልም በየፈርጁ
ፈላስፋው ጋሊኖስ እንዲህ አለ፡- ሕልሞች እርስ በርሳቸው ከተቀላቀሉቱ ካራቱ ባሕርያት (ከነፋስ ከእሳት ከውኃ ከመሬት) ይወለዳሉ፡፡
ደም በሕዋሱ ውስጥ ሲጸና (ሲዘዋወር) ሰውዬው በሕልሙ ያማረ ያማረ ቀያይ ነገርንና ደስ የሚያሰኘውን ዓይነት ያያል ደም ሲጎርፍ ሲፈስ እሳት ሲሞቅ አገሩ ዳሩ ገደሉ በእሳት ሲቃጠል መብረቆች ሲያንፀባርቁ መብራቶች ሲብለጨለጩ ይህንና ይህን የመሳሰሉትን የደም ኅብር ዓይነቶች ሲያይ ያድራል፡፡ (ደም እሳታዊ ጠባይና ኅብር ነው)፡፡
ሳፍራ በሕዋሳቶቹ ውስጥ በብርታት ሲንቀሳቀስ ሰውዬው ክንፍ አውጥቶ እንደ ወፍ ሲበር፣ ሲሮጥ ሲዞር፣ ሲመለስ መሬት ሲዞርበት ይህንና ይህን የመሳሰለውን የነፋስ ዓይነት በማየት ሲባክን ያድራል፡፡ (ሳፍራ ነፋሳዊ ጠባይ ነው)፡፡
በልቀም ሲጸና ወንዞችንና ባሕሮችን በረዶንና ዝናምን ሲያይ ያድራል፤ ከውኃ ውስጥ ገብቶ ሲዋኝ ሲራጭ ውኃን ሲጠጣ፣ ነጫጭ ነገሮችንና እነዚህን የመሳሰሉትን የውኃ ዓይነቶች ሲያይ ያድራል (በልቀም ማያዊ ጠባይ ነው)፡፡
ሰው በነዚህ በ፬ ጠባዮች መንቀሳቀስና መነዋወጽ ምክንያት በሕልሙ ሲፈራ ሲደነግጥ፣ ሲንቀጠቀጥ ያድራል፡፡ የፍርሃት ዓይነቶች ሦስት ናቸው፡፡ እነሱም ፍርሃት፣ ድንጋፄ፣ ረዓድ ይባላሉ፡፡ (ፍርሃት የልብ፣ ድንጋፄ የናላ፣ ረዓድ የጉልበት ናቸው)፡፡
የውኃ ባሕርይ (በልቀም) ሲጸና ውኃ ስትዋኝ እባሕር ውስጥ ስትጠልቅ ጎርፍ ወሰደኝ እስከ ማለት አድርሶ ያቃዣል፡፡
የነፋስ ባሕርይ (ሳፍራ) ሲጸና አሞሮች በሰማይ ሲበሩ አንተ ስትሮጥ ሰዎቹም ሲሮጡ አይሮፕላኖች በሰማይ ሲያንዣብቡ ይታዩሃል፡፡
የመሬት ባሕርይ (ሳውዳ) ሲጸና ጉድጓድ ሲውጥህ መቃብር ሲቆፈር ተራራው ሲናድ አገሩ ሁሉ ሲታረስ ይህን የመሳሰለውን ቅዠት ያሳይሃል፡፡
ሊቀ መዘምራን ሞገስ ዕቁበ ጊዮርጊስ
‹‹አንጋፋ ፈላስፋ›› (1953)
*********
40 ኪሎ ግራም ፀጉር የተሸለተለት በግ
በአውስትራሊያ በግዙፍነቱ የሚታወቅ ነው፡፡ ኑሮውም በጫካ ሲሆን በተለይ በአውስትራሊያ በካንቤራ ነዋሪዎች ይታወቃል፡፡ ከፀጉሩ መብዛት የተነሳ ዓይኖቹ የተሸፈኑ ነበሩ፡፡ ያሳለፍነው ማክሰኞ ግን ክሪስ ለተባለው በግ አዲስ ምዕራፍ ይዞ ብቅ ብሏል፡፡ የፀጉሩ መብዛት ለጤናው እክል መሆኑ ያሳሰባቸው በገለጹት መሠረት የክሪስ ፀጉር ተሸልቷል፡፡ ፀጉሩ 40.5 ኪሎ ግራም የመዘነ ሲሆን፣ ከዚህ ቀደም ኒውዚላንዱ ሽሬክ በግ 27 ኪሎ ግራም ፀጉር በመመዘን አስመዝግቦ የነበረውን ሪከርድ ሰብሯል፡፡ በመስከረም 2007 ላይ ሸዋን ከተባለ በግ ላይ የተሸለተው ፀጉር 23 ኪሎ ግራም መመዘኑን ኤቢሲ ዘግቧል፡፡ ክሪስ ከዚህ ቀደም በፀጉራምነታቸው ከሚታወቁ በጎች ሁሉ በልጦ ተገኝቷል፡፡ ፀጉሩን ከተሸለተ በኋላ አየሩን እስኪላመደው ድረስ ብርድ ልብስ የለበሰ ሲሆን፣ ከጫካ ሕይወቱ አውጥቶ በበረት ውስጥ የሚያኖረው ገበሬ ያገኛል ተብሎ እንደሚገመትም ዴይሊሜል ዘግቧል፡፡
*************
የአዳም ረታ ትሩፋቶች
ተጓዥ ዝንቦች
ተቀምጬ ስገነዘብና ስመለከት ሌላ ምን ነገሮች አይ ነበር? ብዙ፡፡ ብዙ፡፡ ለምሳሌ ዝንቦች፡፡
እዚያ ንፋስ መውጫ ብዛት ካላቸው እንስሳት (ነፍሳት) የመጀመሪያዎቹ ዝንቦች ናቸው፡፡ እኔ ምንገድ ዳር አደባባይ መሀል ተቀምጬ በመዋሌ የማያማኝ ግን አልነበረም፡፡ ማንንም ሰው ግን አልጎዳሁም፡፡ ትንሽ ቁራጭ መሬት ላይ… ትንሽ የከሳች፣ የተበደለች ቂጤን አስቀምጬ የልጅነት ዓይኖቼን ባንከባለልኩ፡፡ …
በጋ፣ በጋ ከተማችን እሳት መሀል እንደተጣለች ሁሉ ትግላለች፡፡ አየሩ ይርገበገባል፡፡ ጠራራም ቢሆን ኮቴን አውልቄ ራሴ ላይ አድርጌ ከጉብታዋ አልሔድም፡፡ ያን ጊዜ ከተማዋ ውስጥ ከሰው ይልቅ በዝቶ የማየው ዝንብ ነበር፡፡ ለጫወታ ፍጡር የለበትም ብዬ በጠረጠርኩት አቅጣጫ ድንጋይ አንስቼ ስወረውር ድንጋዩ ከወደቀበት ቦታ ዝንብ ዥው ብሎ ይነሳል፡፡ በተለይ የሳምንት ገበያ ቅዳሜ ሆኖ… እሁድ ዕለት ቀትር ላይ ከተማው ዝንብ ብቻ ነው፡፡ በዚያ በምታነድ ፀሐይ ጋቢውን የተከናነበ ሰው… ሳያቋርጥ ባሕር ውስጥ እንደተጣለ ግን ዋና እንደማያውቅ እጆቹን እያወናጨፈ ይሄዳል (ስለምን በዚያ የሚያስጮህ ግለት ቦርጫም ጋቢ ለብሶ ወዲያ ወዲህ ይላል?)፡፡
ቃሪያ እንደቆረጠሙ ሁሉ ሳያቋርጡ ፊታቸውን በእጆቻቸው የሚያራግቡ አሉ፡፡ ጉልበቶቹ የቆሰሉ ልጅ ጥቋቁር የዝንብ ኮኮቦች እንደ ጌጥ ተሸክሞ በቀስታ ይቀዝፋል (ምን አንቀራፈፈው? የተሸከማቸው ዝንቦች ከበዱትን?)፡፡ ሌላ ንፍጡን ያልሰበሰበ ብላቴና ገፁ ላይ የዝንብ እግረኛ፤ ገፁ ዙሪያ አየር ውስጥ ሌላው ተረኛ፡፡ በገበያው ውስጥ በቀስታ መሬት እያየሁ ስሄድ…ዕርጥበት አገኛለሁ…… ይሔ እርጥበት ምራቅ ነው፡፡ ብዙ ጊዜ እዚህ እርጥበት መሐል… ወይ ከእርጥበቱ ትንሽ ሳንቲ ሜትር ፈቀቅ ብሎ ባቡዋራ የተለወሰች እግሮቿ ተሳስረው… ክንፎቿ ረጥበው መብረር አቅቷት የምትንገዳገድ ዝንብ አትጠፋም… አንዳንዴ ከወደቁበት አንስቼ ሳያቸው… የሚጋጥሙኝ አካለ ስንኩላን ሆነው ነው፡፡ አልፎ አልፎ ያሳዝኑኛል… አንድ መብረር ታላቅ ስጦታቸውን ተነፍገው… በሰው የሳቅ ቃጭል ታጅበው ጀርባቸው በባልጩት ድንጋይ ተሰብሮ (የሚተፋ (ተፊ) ቦታ አይመርጥምና) በምራቅ አሲድ ሲቃጠሉ ሳይ ………፡፡
አንድ ዕለት እዚያችው ጉብታዬ ላይ ተቀምጬ ስመለከት… ዝንቦች ከጠዋቱ ወረራቸውን መጀመራቸው ገባኝ፡፡ ጥያቄዎች መጠየቅ ጀመርኩ፡፡ እነዚህ ዝንቦች ከየት መጡ? እዚህ ምን ይሠራሉ? ሌሎች ከተሞችስ ላይ እንደዚህ ዐይነት የዝንብ ወረራ ይካሄዳልን? አስፈላጊ ግን ቸል የተባሉ ጥያቄዎች ነበሩ፡፡
‹‹ግራጫ ቃጭሎች››