Wednesday, October 4, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊ‹‹የነበርኩበትን የድህነት ዓለም ሕይወቴ ነው ብዬ አልተቀበልኩትም›› ካፒቴን አበራ ለማ

‹‹የነበርኩበትን የድህነት ዓለም ሕይወቴ ነው ብዬ አልተቀበልኩትም›› ካፒቴን አበራ ለማ

ቀን:

ከዓመታት በፊት በኦሮሚያ ክልል ምዕራብ ሸዋ አካባቢ መንትያ ወንድማማቾች ተወለዱ፡፡ ከእጅ ወደ አፍ በሆነ ኑሮ ሁለቱን ሕፃናት ማሳደግ የተሳናቸው ወላጆቻቸውም በማደጎ መልክ አንዱን ሕፃን ለሰው ሰጡ፡፡ አሳዳጊዎች ሕፃኑን የወሰዱት በድህነት እንዳይቸገር ለማገዝ እንጂ የልጅ ችግር ኖሮባቸው አልነበረም፡፡ አጋጣሚው ግን በሕፃኑ ሥነ ልቦና ላይ ተፅዕኖ ሳያሳድር አላለፈም፡፡ እንደሌሎቹ ሕፃናት እንክብካቤ አላገኘም፡፡ የቤተሰብ ፍቅር አልታደለም፡፡ ‹‹እንደሌሎች ሕፃናት የሚወደኝ አልነበረም፡፡ ተስሜ አላደኩም፡፡ ሕፃናቱን ቤተሰቦቻቸው ሲስሟቸውም እቀና ነበር፤›› በማለት ካፒቴን አበራ ለሚ፣ በማደጎ የቆዩበት ሁኔታ አሳድሮባቸው የነበረውን የሥነልቦና ጫና ያስታውሳሉ፡፡

በዚህ መልኩ ስምንት ዓመት እስኪሞላቸው ቆይተዋል፡፡ ሊዘልቁበት ግን አልፈቀዱም፡፡ ወደ ቤተሰቦቻቸው ለመመለሰም ፈለጉ፡፡ ከስምንት ዓመታት በኋላ ወደ ትውልድ ቀያቸው ተመለሱ፡፡ ገና ከጅምሩ ዓለም ጀርባዋን የሰጠቻቸው ካፒቴን ኑሮ ከድጡ ወደ ማጡ ሆነባቸው፡፡ ወላጆቻቸውን በሕይወት አላገኙም፡፡ አጋጣሚው ልባቸውን ቢሰብረውም ወደ ኋላ መመለስ አልሆነላቸውም፡፡ በትውልድ ቀዬአቸው የዕለት ጉርስ ፍለጋ ደፋቀና ማለት ጀመሩ፡፡ አቅማቸው የፈቀደውን ሁሉ ይሠሩ ጀመር፡፡ በብዛትም መኪና ያጥቡ ነበር፡፡ ከሕይወት የገጠሙት ትግል ከመማር አላገዳቸውም፡፡ በጥረታቸው እስከ ሰባተኛ ክፍል ተማሩ፡፡

ፓይለት የመሆን ፍላጎት ያደረባቸው ገና በልጅነታቸው ነበር፡፡  ‹‹ከአንድ ጓደኛዬ ጋር መኪና እያጠብኩኝ ነበር፡፡ ልጁ ቁልደኛ ብጤ ነበር፡፡ አንድ ቀን መኪና እያጠብን ደግሞ አውሮፕላን እናጠብ ይሆናል አለኝ፡፡ በንግግሩ እየሳኩኝ ለምን እንነዳለን አትልም አልኩት፡፡ እሱም በቃ እሺ አጥበን እንነዳለን አለኝ፡፡ ንግግሩን ሁሌም አስታውሳለሁኝ›› በማለት የትላንት ሕልማቸውን እየኖሩት ይናገራሉ፡፡

 የተለያዩ በራሪ ሥራዎች እየሠሩ ቆየተዋል፡፡ ጥረታቸውም ከፍተኛ ነበር፡፡ ነገሮችም ከዕለት ወደ ዕለት መሻሻል ማሳየት ጀመሩ፡፡ በአንድ ወቅትም መልካም አጋጣሚ እንደፈጠረላቸው ከሚናገሩት ሚሽነሪ ጋር ተገናኙ፡፡ ጥረታቸውን ያስተዋሉት ሚሽነሪም በብዙ ነገር ይረዷቸው ነበር፡፡ በሥራ ምክንያት ወደ ጎረቤት አገር ኬንያ ሲጓዙም ካፒቴንን አስከትለው ነበር፡፡ የአንደኛ ደረጃ ትምህርታቸውን እዚህ ያጠናቀቁት ካፒቴን፣ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን በኬንያ ተከታተሉ፡፡ ነገር ግን ‹‹የሚረዳኝ አግኝቻለሁ›› ብለው ከመሥራት አልተቆጠቡም ነበር፡፡ በኬንያ ኑሮን ለመደገፍ ከትምህርታቸው ጎን ታክሲ ላይ ይሠሩ ነበር፡፡ ሌሎች የተለያዩ የሥራ ዘርፎችንም ሞክረዋል፡፡ ኑሮን ለማሸነፍ ያደርጉት የነበረውን ጥረትም ‹‹የትግል ስም ይውጣልኝ›› ሲሉ ይቀላለዱ እንደነበር ያስታውሳሉ፡፡

በዚህ ጊዜ ሁሉ ያጡት የቤተሰብ ፍቅር ውስጥ ውስጡን ይቆጫቸው ነበር፡፡ ‹‹በልጅነቴ የቤተሰብ ፍቅር አለማግኘቴ ያስቆጨኝ ነበር፡፡ ራሴንም የተበደልኩና አሳዛኝ ሰው አድርጌ እገምት ነበር›› የሚሉት ካፒቴን በአንድ ወቅት ቁጭታቸውን ከውሳጣቸው የሚያወጣና የመንፈስ ጥንካሬ የለገሳቸው ንግግር ለዛሬው ማንነታቸው ትልቁን ሚና እንደተጫወተ ይናገራሉ፡፡ ‹‹መምህሬ ነው፡፡ አንድ ቀን እያስተማረን ሳለ በመካከል ማስተማሩን አቁሞ ከማን እንደምትወለዱ፣ የት እንደምትወለዱና ይዛችሁ የምትወለዱት የሰውነት ቅርፅ የእናንተ ጥፋት አይደለም፡፡ ሕይወቴ ይሄ ነው ብላችሁ የተቀበላችሁ ጊዜ ያኔ ጥፋተኛ ናችሁ፤›› የሚል ነበር፡፡ መልዕክቱ ለሕይወት ያላቸውን አመለካከትና ፍልሰፍና እንደቀየረውም ይናገራሉ፡፡ እርምጃቸውን ከበፊቱ የተሻለ ይሆን ዘንድ መበረታት ጀመሩ፡፡  ትምህርታቸውንም አጥብቀው ይከታተሉ ጀመር፡፡ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን እንዳጠናቀቁም እዚያው ኬንያ የበረራ ትምህርት ተማሩ፡፡

ከዚያ እንደጨረሱም በአውስትራሊያ የአቪኤሽን ማኔጅመንት ተማሩ፡፡ በአውስትራሊያ ቀርተው የሚሠሩበት ዕድል ቢኖራቸውም በአገር ውስጥ የማገልግል ሕልም ስለነበራቸው ወደ ኢትዮጵያ መጡ፡፡ ከዚያ በፊት በኬንያና በታንዛኒያ ኤርፖርቶች የመሥራት አጋጠሚው እንደነበራቸው ‹‹በትንንሽ አውሮፕላኖች›› ቱሪስቶችን አመላልስ ነበር፤›› በማለት ይናገራሉ፡፡ ከ15 ዓመታት በፊት ወደ ኢትዮጵያ የመጡት ካፒቴኑ በኢትዮጵያ አየር መንገድ ተቀጥረው ማገልግል ችለዋል፡፡

በብርቱ ተፈትነው እዚህ የደረሱት ካፒቴኑ ወላጆቻቸውን በልጅነታቸው ቢነጠቁም በወንድማቸው ይፅናኑ ነበር፡፡ ዳሩ ግን ሕይወቱ እንዳለፈ የሰሙት ወደ ኢትዮጵያ ከተመለሱ በኋላ ነበር፡፡ ይህም ተስፋ አላስቆረጣቸውም፡፡ ይበልጥ መሥራት ጀመሩ፡፡

የሰው አስተሳሰብ በመቀየር ድህንነትን መቅረፍ እንደሚቻል በራሳቸውም ምስክርነት ይሰጣሉ፡፡ ‹‹የነበርኩበትን የድህነት ዓለም ሕይወቴ ነው ብዬ አልተቀበልኩም፡፡ ራሴን ለማሻሻል መሞትም ካለብኝ እየጣርኩ እሞታለሁ እንጂ ዝም ብዬ አልቀመጥም፤›› ይላሉ፡፡ በዚህም ምንም እንኳ በየእንቅስቃሴያቸው ፈታኝ አጋጣሚዎች ቢገጥማቸውም ‹‹ፈተናዎቹ እዚያው አላስቀሩኝም›› በማለት የጥረታቸውን ውጤት ያወሳሉ፡፡

ካፒቴን የልጅነት ሕልማቸው በነበረው ሙያ የመሥራት ዕድሉን ቢያገኙም፣ በቃኝ ብለው አልተቀመጡም፡፡ ‹‹መሆን ብቻ በቂ አይደለም፡፡ አጋጣሚውን ተንተርሶ ለኅብረተሰቡ አንድ አዲስ ነገር ማምጣት ያስፈልጋል፤›› ይላሉ፡፡ ይህንን እውን ለማድረግም ከሙያቸው ጋር ተያያዥነት ያላቸውን የተለያዩ ድርጅቶች ማቋቋም ችለዋል፡፡ በመጀመሪያም ኢኩዌተር ቱር ኤንድ ትራቭል (Equator Tour and Travel) የተሰኘ የጉዞ ወኪል አቋቁመዋል፡፡ ኢኩዌተር በአንድ ሚሊዮን ብር ካፒታል የተቋቋመ ድርጅት ሲሆን፣ ጥቂት ለማይባሉ ሰዎች የሥራ ዕድል ፈጥሯል፡፡

እ.ኤ.አ. በ2008 ሁለተኛ ድርጅታቸው የሆነውን ኤርኢትዮጵያ የተባለ የበረራ አገልግሎት የሚሰጥ ተቋም በአሥር ሚሊዮን ብር ካፒታል አቋቋሙ፡፡ ነገር ግን ጥቂት እንደሠሩ ስያሜው ከኢትዮጵያ አየር መንገድ ስም ጋር እንደሚመሳሰል በመግለጽ  ባለሥልጣን መሥሪያ ቤቱ ስያሜውን እንዲቀይሩ ትዕዛዝ ሰጣቸው፡፡ በ2010 ናሽናል ኤርዌይስ በሚልም እንደገና አቋቋሙት፡፡ ቀጥሎም ሦስተኛ ድርጅታቸውን ናሽናል አቪኤሽን ኮሌጅ አቋቋሙ፡፡

በመጀመሪያ ባቋቋሙት ድርጅት ብዙ ትርፋማ መሆን ባይችሉም አገልግሎቱን አላቋረጡም፡፡ ‹‹ትግል ለምጃለሁ አንድ ነገር በአንድ ጊዜ ሙከራ ባይሳካም በጥረት መሳካቱ አይቀርም፡፡ ለጊዜው ግን ትኩረቴን የሳቡት ኮሌጁና የበረራ አገልግሎት የሚሰጥበት ተቋማት ናቸው›› ይላሉ፡፡

እንደ እሳቸው ገለጻ፣ ኮሌጁን ለማቋቋም ጥቂት የማይባሉ አሰልቺ ውጣ ውረዶችን አልፈዋል፡፡ ‹‹አዲስ እንደመሆኑ በቶሎ ፈቃድ ማግኘት አልቻልንም›› ሲሉ ካጋጠሟቸው ችግሮች መካከል ፈቃድ ለማግኘት የነበረው ውጣ ውረዱ ከፍተኛ ፈተና እንደነበር ይናገራሉ፡፡ ድርጅቱ መስፈርቶችን አሟልቶና ሕጋዊ ሰውነት አግኝቶ አገልግሎት መስጠት ከጀመረ በኋላ ከተማሪዎች ሥነ ልቦና ጋር በተያያዘ ችግር እንደነበር ይናገራሉ፡፡

ትምህርቱን ያጠናቀቁ ተማሪዎች የብቃት ማረጋገጫ ፈተና የሚሰጣቸው ከካናዳ ነው፡፡ ምንም እንኳ ትምህርቱን ጠንቅቀው ያወቁ ቢሆንም በፈተናው ያለፉት ‹‹ከአንድ ዲፖርትመንት አንድ ተፈታኝ እንዲሁም ከሌላኛው ሁለትና ሦስት ነበሩ›› ሲሉ የተቀሩት ማለፍ እንዳልቻሉ ያስታውሳሉ፡፡ አጋጣሚው ተስፋ አስቆራጭ ቢሆንም ‹‹ችግር ሲገጥመኝ ችግሩ ላይ ከማተኰር ይልቅ መፍትሄው ላይ ማተኮር ይቀናኛል›› ያሉት ካፒቴኑ፣ ችግሩን የሚቀርፉበትን መፍትሄ ማፈላለግ ጀመሩ፡፡

በወቅቱ በፈተናው ውጤት ባስመዘገቡትና ባላስመዘገቡት ተማሪዎች የአቅም ልዩነት አልነበረም፡፡ ይልቁኑ በከፍተኛ ውጤት እንደሚያጠናቅቁ ይጠበቁ የነበሩ ተማሪዎችም ፈተናውን ማለፍ አልቻሉም ነበር፡፡ ለዚህም የሥነ ልቦና ዝግጅት ዋናው ችግር ሲሆን፣ ቋንቋም አንዱ እንደነበር ይናገራሉ፡፡ በመሆኑም ከኢንዱስትሪው ትምህርት ውጪ የሳይኮሎጂና የኮሙዩኒኬሽን ትምህርት መስጠት ጀመሩ፡፡ በዚህም ችግሩን ሙሉ ለሙሉ መቅረፍ ችለዋል፡፡  ነሐሴ 23 ቀን 2007 ዓ.ም. በኢትዮጵያ ኤርፖርቶች ድርጅት ለሁለተኛ ጊዜ ያስመረቋቸው ተማሪዎችም ከፍተኛ ውጤት አስመዝግበው ያጠናቀቁ ሲሆን፣ ሙሉ ለሙሉም አልፈዋል፡፡ ‹‹ለዚህ መብቃት የቻልነው የአስተሳሰብ ለውጥ ለመፍጠር በሠራነው ሥራ ነው፤›› ይላሉ፡፡

የኮሌጁ እህት ኩባንያ የሆነውንና የበረራ አገልግሎት የሚሰጠውን ድርጅት ጅማሮ  ሲያብራሩም ‹‹ከዚህ ቀደም ለግሉ ዘርፍ የተከለከለ ሴክተር ነበር፡፡ አሁን ግን ተፈቅዶልን ሥራ ጀምረናል፡፡ ይሁን እንጂ እንደ ኬንያና ደቡብ አፍሪካ አላደገም›› ይላሉ፡፡ ይህም ዋጋ እያስከፈላቸው እንደሆነ ይናገራሉ፡፡ አገልግሎቱን የሚሰጡት በቻርተር ሲሆን፣ የመቀመጫ ገደብ ተጥሎበታል፡፡ ከዚህ ቀደም ከ20 መቀመጫ የበለጠ መያዝ አይችሉም ነበር፡፡ ነገር ግን አሁን ተሻሽሎ እስከ 50 መቀመጫ ድረስ እንዲጠቀሙ ተፈቅዶላቸዋል፡፡ ይሁን እንጂ 50 መቀመጫ ያላቸው አውሮፕላኖች የሚያመርት ድርጅት የለም፡፡ ይህም የሚሰጡት አገግሎቱ በፕራግራም የተመሠረተ እንዳይሆን አድርጎታል፡፡ ‹‹እንዳገኘን ነው የምንሠራው የመቀመጫ ገደብ ባይጣልብን ግን በሳምንት በተወሰኑ ቀናቶች በፕሮግራም ለመሥራት ያስችለናል፤›› ይላሉ፡፡

የተቀመጠው ገደብ እንዲነሳ ለመንግሥት ጥያቄ ያቀረቡ ሲሆን፣ በቅርቡም መፍትሄ እንደሚያገኙ ዕምነታቸው ነው፡፡ ከዚህ ባሻገር ከበርካታ ታዋቂ ሰዎች ጋር የሚገናኙበትን አጋጣሚ የፈጠረላቸው ሲሆን፣ ከቢልጌትስ፣ ከዱባዩ ንጉሥ ልጅ፣ የተለያዩ የሆሊውድ አክተሮችና ሌሎችንም እንዲያገኙ አስችሎዋቸዋል፡፡ በዚህም ደስተኛ መሆናቸውን ይናገራሉ፡፡ በተቋሞቻቸው ከሚያደርጉት እንቅስቃሴ በተጓዳኝም ለወጣቱ የአስተሳሰብ ለውጥ ላይ ያተኮሩ ሥልጠናዎችን እንደሚሰጡ ይናገራሉ፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

[ክቡር ሚኒስትሩ ወደ መኖሪያ ቤታቸው ሲገቡ ባለቤታቸው በቴሌቪዥን የሚተላለፈውን ዜና በመገረም እየተመለከቱ አገኟቸው]

ምንድነው እንዲህ ቀልብሽን የሳበው? ስለሰላም ኖቤል ሽልማት ዜና እየተመለከትኩ ነበር። እና...

የወሎ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ መመሥረትና የአማራ ክልል ጥያቄ

አማራ የኢሕአዴግ አንዱ መሥራችና አጋር ከሆነው ብሔረ አማራ ዴሞክራሲያዊ...

የሽንኩርት ዋጋ ሰማይ የነካበት ምክንያት ምንድነው?

ባለፉት ሁለትና ሦስት ሳምንታት የሸማቾችን ኪስ ካስደነገጡ መሠረታዊ ከሚባሉ...

የአዲስ አበባ ንግድ ምክር ቤት ኤግዚቢሽን ማዕከልን እንዲያስተዳድር የተሰጠው ኮንትራት ለምን ተቋረጠ?

በአዲስ አበባ ከተማ ለንግድ ትርዒት ዝግጅት ብቸኛ በመሆን የሚጠቀሰው...