Monday, September 25, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ኪንና ባህልአዲስ ገጽታ

አዲስ ገጽታ

ቀን:

አቶ ኡመር ሁሴን ተወልደው ያደጉት በራያና አዘቦ ማይጨው ከተማ ነው፡፡ አጐታቸው በትውልድ ቀዬአቸው የታወቁ ሸማኔ ነበሩ፡፡ አቶ ኡመር አዘውትረው ከአጐታቸው ጋር ይገናኙ ነበርና ሙያውን ተማሩ፡፡ በሽመና መተዳደር የጀመሩት በ21 ዓመታቸው ሲሆን፣ አሁን የ56 ዓመት ጐልማሳ ናቸው፡፡ አቅማቸው ቢደክምም በሕይወታቸው ከሽመና ሥራ ተለይተው እንደማያውቁ ይናገራሉ፡፡ በሚኖሩበት አካባቢ ባህላዊ አልባሳት በጣም ተፈላጊ ስለሆኑ ከዓመት ዓመት የሞቀ ገበያ እንዳላቸው ይገልጻሉ፡፡

የሰባት ልጆች አባት የሆኑት አቶ ኡመር፣ ቀድሞ ልጆቻቸው በትምህርት ብቻ እንዲገፉ ያበረታቷቸው ነበር፡፡ በመሆኑም ልጆቻቸው በተለያየ የሙያ ዘርፍ ይገኛሉ፡፡ የመጨረሻ ልጃቸው የአሥራ አንደኛ ክፍል ተማሪ ሲሆን፣ ከሌሎቹ ልጆቻቸው በተለየ ሙያውን ሊያስተምሩት እየተጣጣሩ ነው፡፡ ‹‹ሙያውን ካላስረከብኩ ከእኔ ጋር ያልፋል፤ ልጄ ሽመና ሲማር ግን ለትውልድ እንደሚተላለፍ አስባለሁ፤›› ይላሉ፡፡

የሚሸምኑት በባህላዊ መንገድ ሲሆን፣ ልጃቸውም ይህንኑ እንዲከተል ይሻሉ፡፡ እንደ እሳቸው ባህላዊውን መንገድ ቢመርጡም ሙያው መዘመኑ የወጣቱን ትኩረት እየሳበ ነው፡፡ ከጊዜ ወደ ጊዜ ሽመና በዘመናዊ መሣሪያ መታገዙና አልባሳትም ከተለመደው መንገድ ውጪ መቅረባቸው መልካም ነው፡፡

አቶ ኡመርን ያገኘናቸው በኦሮሞ ባህል ማዕከል በተካሄደ ‹‹አዲስ ገጽታ›› የተሰኘ ዝግጅት ላይ ነው፡፡ ከነሐሴ 26 ቀን 2007 ዓ.ም. ጀምሮ ለአምስት ቀናት የተካሔደው ዝግጅቱ እንደሳቸው በሽመናና በሌሎችም ከባህላዊ አልባሳት ጋር የተያያዙ ሥራዎች ላይ የተሰማሩ የተሳተፉበት ነው፡፡ አቶ ዑመር በራያ የሚዘወተሩትን ጋቢ፣ ነጠላ፣ ቀሚስ፣ እንዲሁም ከላምና ከበሬ ቆዳ የተሠሩ ጫማዎች አቅርበዋል፡፡ ‹‹ለአዲስ ዓመት፣ ለአሸንዳ ወይም ሌሎች በዓላት የሚለበሱ ልብሶችን ለዕይታም፣ ለሽያጭም ለአዲስ አበባው ሰው አቅርቤአለሁ፤›› ይላሉ፡፡

በአካባቢያቸው ለሽመና ትልቅ ክብር ይሰጣል፡፡ በመሆኑም የሚያስፈልጓቸውን ጥሬ ዕቃዎች በቀላሉ እንደሚያገኙና ምርቶቻቸውንም በፍጥነት እንደሚሸጡ ያስረዳሉ፡፡ በዚያው ዝግጅት ላይ ያገኘናቸው አቶ ኃይሉ ቶለሬ ከአቶ ኡመር የተለየ ሐሳብ ሰንዝረዋል፡፡ የሚሠሩት ሽሮ ሜዳ በሚገኝ የሸማኔዎች ማኅበር ታቅፈው ነው፡፡

እሳቸው እንደሚሉት፣ ለሽመና የሚያስፈልጉ እንደ ጥለትና ማግ ያሉ ጥሬ ዕቃዎች እየተወደዱ መምጣታቸው ሥራቸውን ከባድ አድርጐታል፡፡ ከዚህ ባሻገር ሸማኔዎች ከሙያው ተገቢውን ጥቅም እንደማያገኙም ይገልጻሉ፡፡ የሽመና ውጤቶችን ከሸማኔዎች ገዝተው ለገበያ ከሚያቀርቡ ነጋዴዎች መካከል አብዛኞቹ ያላግባብ ዋጋ በመጨመር እንደሚጠቀሙ ይናገራሉ፡፡ ይህም የባህል ልብስ ዋጋ ከጊዜ ወደ ጊዜ የማይቀመስ እንዲሆን አድርጓል፡፡ የጥበብ መወደድ የገዥዎችን ቁጥር ውስን አድርጐታል፡፡

አቶ ኃይሉ ሽመና የተማሩት ከአባታቸው ነው፡፡ አባታቸው ከሚሠሩበት ወቅት በተሻለ ዛሬ ላይ ለሙያው ክብር ቢሰጠውም ብዙ እንደሚቀረው ይገልጻሉ፡፡ ሸማኔዎች ተገቢውን የገንዘብ ጥቅም ካላገኙ ሙያውን የሚቀላቀሉ ወጣቶች አይኖሩም ይላሉ፡፡ አባታቸው ዕድሜአቸው ገፍቶ ሽመናን ሲያቆሙ ቤተሰባቸውን ለማስተዳደር ተቸግረዋል፡፡ እሳቸውም ተመሳሳይ ዕጣ እንዳይገጥማቸው በመስጋት ከሽመና ጐን ለጐን የጥበቃ ሥራ ይሠራሉ፡፡ ‹‹ሙያውን አከብረዋለሁ፤ አዋጭ ግን አይደለም፤›› ይላሉ፡፡

አቶ ኃይሉ የኢትዮጵያ የባህል አልባሳት በዓለም አቀፍ መድረክ ሲቀርቡ እንዲሁም አገር ውስጥ ባማረ ዲዛይን ተሠርተው በልዩ ልዩ ክንውኖች ሲለበሱ ማየት ቢያስደስታቸውም፣ በአልባሳቱ ዝግጅት የመነሻውን ድርሻ የሚይዙትን ሸማኔዎች ታሳቢ ያደረገ ቢዝነስ መሆን እንዳለበት ይገልጻሉ፡፡

ባህላዊ አልባሳት ለበዓላት ወይም ለተለያዩ መሰናዶዎች ከመዋላቸው በላይ ያላቸው ዓለም አቀፍ ዕውቅና እየናረ መጥቷል፡፡ በዘርፉ ያሉ ባለሙያዎች በቢዝነሱ ያላቸው ድርሻ ምን ያህል የሰፋ ነው የሚል ጥያቄ የሚያነሱም አሉ፡፡ እንደ አቶ ኡመርና አቶ ኃይሉ በተመሳሳይ ሙያ ያሉና በተለያየ ቦታ የሚኖሩ ባለሙያዎች የሚገናኙበት መድረክ ጠባብ ነው፡፡

ሸማኔዎች ብቻ ሳይሆኑ ጥሬ ዕቃ አቅራቢዎች፣ ዲዛይነሮችና ሌሎችም ባለሙያዎች ሥራዎቻቸውን በአንድነት የሚያቀርቡበት አጋጣሚ አናሳ እንደሆነ የዘርፉ ባለሙያዎች ይናገራሉ፡፡ ‹‹አዲስ ገጽታ›› በተባለው ዝግጅትም በዘርፉ ከመጀመሪያው እስከ መጨረሻው ባሉ ሙያተኞች መካከል ያለውን ትስስር ለማጥበቅ እንደታለመ አዘጋጆቹ ይናገራሉ፡፡

በዘርፉ የሚስተዋሉ ችግሮችን ለመቅረፍ የባለድርሻ አካላት አብሮነት እንደሚያስፈልግ የምትናገረው የአዘጋጆቹ ፋሽን ዲዛይነርስ አሶስዬሽን (ኤፍዲዴ) ሥራ አስኪያጅ ዲዛይነር ወ/ሮ እጅጋየሁ ኃይለጊዮርጊስ ነች፡፡ የፈትል፣ ሽመና፣ ጥልፍ፣ ስፌትና ዲዛይን ባለሙያዎች መካከል ትስስር ለመፍጠር ዝግጅቱን አሰናድተዋል፡፡

ዝግጅቱ ሽመናን በዘመናዊ መንገድ ለማከናወን የሚያስችሉ መሣሪያዎችን የሚያመርቱ ድርጅቶችንም አሳትፏል፡፡ ከእነዚህ አንዱ ኤቲደብሊው ኢንጅነሪንግ ሲሆን፣ የመፍተያ፣ የማዳወሪያ፣ የሽመናና ሌሎችም መሣሪያዎች ያመርታል፡፡

ከድርጅቱ ሠራተኞች አንዱ አቤል ዳንኤል እንደሚናገረው፣ ሽመና በባህላዊ መንገድ ሲሠራ የሚጠይቀውን ጊዜና የሰው ኃይል ለመቆጠብ የሚያግዙ መሣሪያዎች ያመርታሉ፡፡ በባህላዊ መንገድ ለሚሠሩ ሸማኔዎች ስለመሣሪያዎቹ አጠቃቀም ሥልጠና ይሰጣሉ፡፡ አልባሳት የተፈለገውን ቅርጽ እንዲይዙ ሽመና ትልቁን ድርሻ እንደሚወስድ የሚገልጸው ዳንኤል፣ መሣሪያዎቹን ሸማኔዎች በሚፈልጉት ይዘት እንዲያመርቱ በየጊዜው እንደሚያሻሽሏቸው ያስረዳል፡፡

በዘመን አመጣሽ መሣሪያዎች ከሚገለገሉ አንዷ ጥጥ ፈታይ ወ/ሮ መሠረት ቦጋለ ናት፡፡ የአራት ልጆች እናት የሆነችው መሠረት፣ የምትፈትለው በምታገኘው ክፍት ጊዜ ነው፡፡ ጥጥ እየፈተለች ለሸማኔዎች ታስረክባለች፡፡ በእጅ ከመፍተል በማሽን መጠቀም ቢያፈጥናትም፣ ጥጥ በእጅ ሲፈተል የተሻለ ውበት እንደሚኖረው ትናገራለች፡፡

ከሦስት አሠርታት በላይ በሽመና ሥራ የተዳደሩት የጋሞ ጐፋ ዞን ተወላጁ አቶ ክፍሌ ውታ ደግሞ ዘመናዊ መሣሪያ የባህላዊውን ያህል አያረካቸውም፡፡ ድንጉዛ፣ ቡልኮ እና ጋቢ በዝግጅቱ ያቀረቧቸው ምርቶች ናቸው፡፡ በእንጨት ትካል ላይ አዳውረው በእጃቸው የሚሠሩት ጥበብ ጊዜ ቢወስድም እንደሚያምርላቸው ይናገራሉ፡፡

ዲዛይነር መዓዛ ደምሴ ወደሙያው ከገባች አሥር ዓመታት አስቆጥራለች፡፡ ደብረ ዘይት ከተማ ውስጥ የባህል አልባሳት መሸጫ ሱቅ አላት፡፡ ባህላዊ አልባሳት በዘመናዊ መንገድ መዘጋጀታቸው የለባሽን ቀልብ እየሳበ እነደሆነ ታምናለች፡፡ ባህላዊ አልባሳት በማንኛውም ቦታ እንዲለበሱ የሚዘጋጁበት መንገድ ምቹ መሆን እንዳለበት ትገልጻለች፡፡ በባህላዊም በዘመናዊም መንገድ የሚሠሩ ባለሙያዎች የየራሳቸውን ገበያ እንደሚያገኙ ታምናለች፡፡ ‹‹ባህላዊውን የአልባሳት አቀራረብ ብወደውም ተመችቶኝ የምሠራው ዘመናዊውን ነው፤›› የምትለው መዓዛ፣ ሰዎች በዲዛይነር የተሠሩ ልብሶችን መጠቀም ማዘውተር መጀመራቸው ገበያውን እንዳሰፋውም ታስረዳለች፡፡

የመዓዛን ሐሳብ የምትጋራው ዲዛይነር ወ/ሮ እጅጋየሁ፣ በባህላዊ አልባሳት ዝግጅት የሚሳተፉ ባለድርሻ አካላት መሰባሰባቸው ለፋሽን ዕድገት አስተዋጽኦ ያበረክታል ትላለች፡፡ ከክልል ከተሞች የተውጣጡ ባለሙያዎች መካተታቸው ለዘርፉ የሚሰጠውን ትኩረት ከፍ እንደሚያደርገው ታምናለች፡፡ በመካከላቸው የገበያና የሙያ ትስስር ሲፈጠር የተሻለ እንደሚያመርቱም ትገልጻለች፡፡

በዝግጅቱ ወደ 150 የሚደርሱ ባለሙያዎች ተሳትፈዋል፡፡ ፋሽን ላይ ያተኮረ የፓናል ውይይት፣ የዲዛይነሮች የስኬች ውድድርና የፋሽን ትዕይንትም የዝግጅቱ አካል ናቸው፡፡ ዲዛይነሯ እንደምትለው፣ በዘርፉ ያሉ ሙያተኞችንና አገሪቱንም ተጠቃሚ ለማድረግ ዝግጅቱ አንድ ዕርምጃ ነው፡፡

ከፈታይ እስከ ዲዛይነር መገናኘታቸው ለሚገጥሟቸው ችግሮች የጋራ መፍትሔ እንዲያፈላልጉ እንደሚረዳ፣ በባህላዊና በዘመናዊ መንገድ የሚሠሩ ባለሙያዎች ለዘርፉ የሚያበረክቱት አስተዋጽኦ እኩል እንዲታይ መሰል መሰናዶዎች መለመድ እንዳለባቸው፣ መሰባሰባቸው የባህል አልባሳት ምቹ፣ ዘወትር የሚለበሱ፣ ፍትሐዊ ዋጋ የሚጠየቅባቸውና በቀላሉ የሚገኙ ለማድረግ እንደሚያነሳሳ ትገልጻለች፡፡

ዝግጅቱን ከኤፍዲኤ ጋር ያዘጋጁት ሜኖይት ኢኮኖሚክ ዴቨሎፕመንት አሶስዬሽን (ሜዳ) እና የባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር ናቸው፡፡ በባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር የባህል ኢንዱስትሪ ከፍተኛ ባለሙያ አቶ ታደሰ አዳነ የባህል ልብስ አምራቾች በአገር ውስጥ እንዲሁም በውጭ የሚኖራቸውን ገበያ ለማስፋት እርስ በእርስ የሚደጋገፉበት ተመሳሳይ መድረክ ቢበራከት ለዘርፉ ዕድገት አጋዥ ይሆናል ብለዋል፡፡

 

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የቤት ባለንብረቶች የሚከፍሉትን ዓመታዊ የንብረት ታክስ የሚተምን ረቂቅ አዋጅ ተዘጋጀ

በአዋጁ መሥፈርት መሠረት የክልልና የከተማ አስተዳደሮች የንብረት ታክስ መጠን...

እንደ ንብረት ታክስ ያሉ ወጪን የሚያስከትሉ አዋጆች ከማኅበረሰብ ጋር ምክክርን ይሻሉ!

የመንግሥትን ገቢ በማሳደግ ረገድ አስተዋጽኦ እንዳላቸው የሚታመኑት የተጨማሪ እሴት...

ለዓለምም ለኢትዮጵያም ሰላም እንታገል

በበቀለ ሹሜ ያለፉት ሁለት የዓለም ጦርነቶች በአያሌው የኃያል ነን ባይ...