በሕገ መንግሥታዊ ሥርዓት የሕግ አውጭውና የሕግ ተርጓሚው ሥራ ለየቅል ነው፡፡ የመጀመሪያው ሕግ ይሠራል፣ ሁለተኛው የወጣውን ይተረጉማል፡፡ ሕግ ሠሪው ችሎት ተሰይሞ አይተረጉምም፣ ሕግ ተርጓሚውም በትርጉም ሰበብ ሕግ አይሠራም፡፡ በንድፈ ሐሳብ ደረጃ ይህ ነገር ግልጽ ቢመስልም በተግባር የሁለቱ ልዩነት ሰፊ ላይሆን ይችላል፡፡ ሕግ ተርጓሚው በተጨባጭ ለቀረቡለት ጉዳዮች ዳኝነት ሲሰጥ የሕጉን ግልጽ/ጥሬ ትርጉም በመሳት፣ በማስፋት፣ በመለጠጥ፣ በመተው ወዘተ. የተለየ መልዕክት ያለው ሕግ እንደቀረጸ የሚያሳይ ፍርድ ሊሰጥ ይችላል፡፡ በዚህ ጊዜ ሕግ የማውጣትና የመተርጎሙ ሥራ መካከል የምናሰምረው መስመር ሊጠብ ይችላል፡፡ በዚህ ጽሑፍ የምንመለከተው ጭብጥ ለዚህ ዓቢይ ማሳያ ነው፡፡ ፍርዱ ከመያዣ ምዝገባ ጋር በተያያዘ የተሰጠ ሲሆን፣ የሚያጠነጥነው በፍትሐ ብሔር ሕግ ቁጥር 3058(1) በመተርጎም ዙሪያ ነው፡፡ ይህ ድንጋጌ ‹‹የማይንቀሳቀስ ንብረት የመያዣ መብት ውጤት የሚኖረው ከተጻፈበት ቀን አንሥቶ እስከ አሥር ዓመት ድረስ ነው፤›› ይላል፡፡ የድንጋጌው ጥሬ ትርጉምና ይዘቱ ግልጽ ቢመስልም/ቢሆንም ሰበር ችሎት ግን በገዥው ፍርዶቹ ከይዘቱ የራቁ፣ ከሕግ አውጭውም መንፈስ የተፋቱ ፍርዶች ሰጥቷል፡፡ በቀጣዩ የጽሑፉ ክፍል የፍርዶቹን አመጣጥ በመግለጽ የመያዣ ባህርያት፣ አመዘጋገብ፣ የማብቂያ ጊዜ፣ ውሉን ስለማደስና ያለማደስ ውጤትን በመቃኘት የሰበር አቋምን ፍትሐዊነት እንመለከታለን፡፡
የጉዳዩ አመጣጥ
ለዚህ ጽሑፍ የተመረጡት የሰበር ፍርዶች በሰበር መዝገብ ቁጥር 44800 ጥቅምት 5 ቀን 2002 ዓ.ም. እና በሰበር መዝገብ ቁጥር 40109 ጥቅምት 1 ቀን 2003 ዓ.ም. የተሰጡ ናቸው፡፡ በመጀመርያው ጉዳይ አመልካች አቶ አብዱራዛቅ ሐሚድ ሲሆኑ ተጠሪው የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ነው፡፡ በሁለተኛው ጉዳይ ደግሞ አመልካች የኢትዮጵያ ልማት ባንክ ሲሆን፣ ተጠሪው ደግሞ አቶ ተክሌ ዋከኔ ናቸው፡፡ በሁለቱም ጉዳዮች ግለሰቦች ተከራካሪዎች ሦስተኛ ወገን መያዣ ሰጪዎች ሲሆኑ፣ የመያዣ ውሉ ከተቋቋመ አሥር ዓመት ያለፈ በመሆኑ መያዣው እንዲፈርስላቸው ጠይቀዋል፡፡ ችሎቱ የተለያዩ ምክንያቶችን በመጥቀስ የመያዣ ውል ከተቋቋመ ከአሥር ዓመታትም በኋላ የፀና ስለመሆኑ በመተንተን ለባንኮቹ ፍርዱን ሰጥቷል፡፡
በመጀመርያው መዝገብ ሐሚድና ቤተሰቡ የግብርና ውጤቶች ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር ከባንኩ ብድር ሲወስድ አቶ ሐሚድና አመልካች ሁለት ቤቶቻቸውን በመያዣ የሰጡ ሲሆን፣ ባንኩ የአቶ ሃሚድን ቤት በሐራጅ ሸጦ ዕዳውን መልሷል፡፡ አመልካች በሰጡት ቤት የተገባው የመያዣ ውል ደግሞ አሥር ዓመት ያለፈው በመሆኑ ቀሪ ነው፡፡ ባንኩ ካርታውን እንዲመልስልንና ያልተከፈለ ዕዳ ካለም እንዲከፍል ብጠይቀውም ፈቃደኛ ባለመሆኑ በፍርድ ቤት መያዣው ፈራሽ እንዲሆንልኝ ሲሉ ጠይቀዋል፡፡ የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤቱ ባፀደቀው የመጀመርያ ደረጃ ፍርድ ቤት ውሳኔ ዕዳው ያልተጠናቀቀ በመሆኑና ባንኩ በፍትሐ ብሔር ሕግ ቁጥር 3058(1) የተመለከተው የአሥር ዓመት ጊዜ ከማለፉ በፊት በመያዣ ንብረቱ ላይ እንቅስቃሴ የጀመረ በመሆኑ ክሱ ተቀባይነት የለውም ተብሏል፡፡ ሰበር ችሎቱ በግለሰቡ አመልካችነት የቀረበውን ማመልከቻ ባለገንዘቡ የመያዣ ውሉ ከተመዘገበበት ቀን ጀምሮ አሥር ዓመት በመብቱ መገልገል ጀምሯል ሊባል የሚችለው መቼ ነው? የሚል ጥያቄ በማንሳት ባንኩ የአሥር ዓመቱ ጊዜ ሳያልፍ ለመያዣ ሰጪው ማስጠንቀቂያ ከሰጠ በመብቱ መገልገል ጀምሯል በማለት የቤቱ ሽያጭ ሳይጠናቀቅ አሥር ዓመት ማለፉ ብቻውን የመያዣ ውሉን ቀሪ አያደርገውም በማለት የአመልካችን ጥያቄ ውድቅ አድርጓል፡፡
በሁለተኛው መዝገብ አቶ ሽፈራው ቡሌ ከባንኩ ብድር ሲወስዱ ተጠሪ ቤታቸውን በመያዣ መስጠታቸውን በመግለጽ የብድር ውሉም ሆነ የመያዣ ውሉ ሳይታደስ አሥራ ሦስት ዓመት ያለፈው በመሆኑ የመያዣ ውሉ በፍትሐ ብሔር ሕግ ቁጥር 3058 መሠረት ቀሪ ሆኖ ባንኩ የያዘውን የቤቱን ካርታና ፕላን እንዲመለስላቸው ዳኝነት ጠየቁ፡፡ ባንኩ በሰጠው መልስ ታህሳስ 14 ቀን 1988 ዓ.ም. የተፈረመው የመያዣ ውል ጥቅምት 9 ቀን 1988 ዓ.ም. ለክፍለ ከተማ አስተዳደር በተጻፈ ደብዳቤ ለቀጣይ አሥር ዓመት እንዲታደስ የተደረገ መሆኑን ጠቅሶ ክሱ ውድቅ እንዲደረግ ጠየቀ፡፡ ጉዳዩን በመጀመርያ ደረጃ የተመለከተው የምሥራቅ ወለጋ ዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤት ውሉ የታደሰውና የዋሱን ኃላፊነት የሰጠው ያለመያዣ ሰጪው ዕውቅናና ፈቃድ በመሆኑ የመያዣ ውሉ እንዲታደስ አይቆጠርም በማለት ሳይታደስ አሥር ዓመት ያለፈውን የመያዣ ውሉ ቀሪ አድርጎታል፡፡ አመልካች ለኦሮሚያ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ይግባኝ ያቀረበ ቢሆንም ጠቅላይ ፍርድ ቤቱ ይግባኙን ሰርዞታል፡፡ የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት አመልካች ያቀረበውን ማመልከቻ ተቀብሎ የሥር ፍርድ ቤቶችን ፍርድ ገልብጦታል፡፡ ሰበር ችሎቱ ለፍርዱ በሰጠው ምክንያት የፍትሐ ብሔር ሕግ ቁጥር 3058/2/ እና 1632/2/ ተገናዘበው ሲታዩ የመያዣ ውሉ ከተመዘገበ አሥር ዓመት ሳይሞላው በመብቱ ተጠቃሚ የሆነው ወገን እንዲታደስለት ከጠየቀ ውሉ የሚታደስ መሆኑን የገለጸ ሲሆን፣ ‹‹ከድንጋጌዎቹ አቀራረፅና ይዘት መረዳት የሚቻለው የማይንቀሳቀስ ንብረት መያዣ ውሉ አንዴ ከተመዘገበ ይህንኑ ውሉ የማደስ ተግባር ለመፈጸም የአስያዡ ፈቃድ እንደገና መረጋገጥ ያለበት ስለመሆኑ የሚያሳይ አንቀጽ አለመሆኑን ነው፤›› በሚል ያለ አስያዡ ፈቃዱ የታደሰውን መያዣ የሥር ፍርድ ቤቶች ውድቅ ማድረጋቸው አግባብነት የለውም በማለት ሽሮታል፡፡
ስለመያዣ ውል አጠቃላይ ነጥቦች
በባለገንዘብና በባለዕዳ መካከል በሚመሠረት ግዴታ ባለዕዳው ግዴታውን ያልተወጣ እንደሆነ ይህንን ግዴታ ለመወጣት ማረጋገጫ የሚሰጥ ሰው ዋስ ይባላል፡፡ በሕግ ዋስትናው የሰውና የንብረት በሚል በሁለት የሚከፈል ሲሆን፣ በንብረት ላይ የሚመሠረት ዋስትና ተንቀሳቃሽ መያዣ (Pledge) ወይም በዚህ ጽሑፍ የምንመለከተው የማይንቀሳቀስ ንብረት መያዣ (Mortgage) ሊሆን ይችላል፡፡ ለዚህ ጽሑፍ እንዲረዳ የማይንቀሳቀስ ንብረት መያዣን ‹‹መያዣ›› በሚለው የወል አጠራር እንጠቀምበታለን፡፡ እንደማንኛውም ዋስትና መያዣ ደባል ግዴታ እንደመሆኑ መጠን በልዩ ሁኔታ ካልሆነ በቀር በዋናው ግዴታ መኖርና ቅቡልነት (Validity) ላይ መሠረት ያደረገ ነው፡፡ የፍትሐ ብሔር ሕግ ቁጥር 1926/ እና 1923 መያዣ በውል ሲመሠረት ግልጽና የማያሻማ፣ የገንዘብ መጠኑን የሚገልጽ፣ (3045(2)፣ 1924) ከዋናው ግዴታ ያልከበደ፣ በጽሑፍ የተደረገና በምስክር የተረጋገጠ (3045፣ 1723) ሊሆን ይገባዋል፡፡ የፍትሐ ብሔር ሕግ ቁጥር 1928 በግልጽ እንደሚያስቀምጠው ውሉ ከተደረገ በኋላ በባለገንዘቡና በባለዕዳው መካከል የሚደረግ ሌላ ውል የዋሱን ግዴታ ሊያብስበት አይችልም፡፡ ለዕዳ መክፈያ ጊዜ አራዝሞ የመስጠትን ጉዳይ በተለይ ዋሱን ሳያስፈቅድ ባለገንዘቡ ለባለዕዳው የመክፈያ ጊዜ አራዝሞ የሰጠ እንደሆነ ዋሱ ነፃ ይሆናል፡፡
በማይንቀሳቀስ ንብረት ላይ የሚመሠረት የመያዣ መብት ከተፈጸመበት ቀን አንሥቶ ካልተመዘገበ በሕግ ፊት ውጤት እንደማይኖረው በፍትሐ ብሔር ሕግ ቁጥር 3052 ተደንግጓል፡፡ ምዝገባው የሚደረገው በማይንቀሳቀስ ርስት መዝገብ ሲሆን፣ የአመዘጋገቡ ሥርዓት የማይንቀሳቀሱ ንብረቶች አመዘጋገብ ሥርዓትን ይከተላል፡፡ የማይንቀሳቀስ ንብረት አመዘጋገብ ከፍትሐ ብሔር ሕግ ቁጥር 1553 እና ተከታዮቹ ቁጥሮች በዝርዝር በሕጉ የተደነገገ ሲሆን፣ መያዣን በተመለከተ ስለአመዘጋገቡ፣ ስለጊዜው ቆይታ፣ ስለሚመዘገቡት ነገሮችና ስለሚሰረዝበት ሁኔታ የተወሰኑ ድንጋጌዎችን አስቀምጧል፡፡
የማይንቀሳቀስ ንብረት የመያዣ መብት የቆይታ ጊዜ አሥር ዓመት ነው፡፡ የፍትሐ ብሔር ሕግ ቁጥር 3058(1) የማይንቀሳቀስ ንብረት የመያዣ መብት ውጤት የሚኖረው ከተጻፈበት ቀን አንሥቶ እስከ አሥር ዓመት ድረስ ነወ፡፡ በዚህ መሠረት የፍትሐ ብሔር ሕግ ቁጥር 1623 መያዣ ከተመዘገበ አሥር ዓመት ሆኖት እንደሆነና እንዲታደስ ካልተጠየቀ ዓቃቤ መዝገቡ በሥልጣኑ ምዝገባውን እንደሚሰርዘው ይደነግጋል፡፡ የአሥር ዓመቱ ጊዜ ከማለፉ በፊት ይህ ውል እንዲታደስ አዲስ የመዝገብ ማጻፍ ጉዳይ የተፈጸመ እንደሆነ ፀንቶ የሚቆይበት ዘመን ይራዘማል፡፡ የመያዣ ውሉ ከአሥር ዓመት በኋላ ያልታደሰ ከሆነ ግን የመያዣ ምዝገባው ስለሚሰረዝ ንብረቱን በመያዣ የሰጠ ሦስተኛ ወገን ካለበት ኃላፊነት ነፃ ይሆናል፡፡
በሰበር ፍርዱ ላይ አጭር ምልከታ
የሰበር ችሎቱ በጽሑፉ መግቢያ ላይ በገለጽናቸው ሁለት መዛግብት የሰጣቸው ፍርዶች የመያዣ ምዝገባ የሚቆይበትን ዘመን፣ ይህ ጊዜ ሲያልፍ ስለሚኖረው ውጤትና የመያዣ መብቱ ስለሚታደስበት ሁኔታ የተመለከተ ነው፡፡ እነዚህን ነጥቦች ሕጉን መሠረት አድርገን በፍርዱ የተሰጡትን ትንታኔዎች ለመቃኘት እንሞክር፡፡
ቀዳሚው ነጥብ የመያዣ ውል ምዝገባ የቆይታ ጊዜ ነው፡፡ ሕጉ የመያዣ ምዝገባ ከተጻፈበት ጊዜ አንሥቶ ለአሥር ዓመታት የፀና እንደሆነና ምዝገባው ካልታደሰ እንደሚሰረዝ ይደነግጋል፡፡ የአሥር ዓመቱ የጊዜ ቆይታ አቆጣጠር ለአገራችን ሕግ ባዕድ አይደለም፡፡ በፍትሐ ብሔር በውል ወይም ከውል ውጭ ግዴታዎች የመፈጸሚያ ረዥም ጊዜያት በሌላ መልኩም የይርጋ ደንብ አሥር ዓመት እንደሆነ የፍትሐ ብሔር ሕግ ቁጥር 1845 እና 1677 የጣምራ ንባብ ያሳያሉ፡፡ ሰበር ችሎትም ይህንኑ ጊዜ በብዙ አስገዳጅ ትርጓሜዎች አረጋግጦታል፡፡ የመያዣ ምዝገባን በተመለከተ በመጀመርያው ፍርድ አከራካሪ የሆነው የአሥር ዓመቱ ጊዜ እንዴት ይቆጠራል? የአሥር ዓመቱ የጊዜ ገደብ ዓላማስ ምንድን ነው? የሚለው ነው፡፡ ሕጉ የአሥር ዓመቱ ጊዜ ከተጻፈበት ጊዜ ጀምሮ የሚቆጠር መሆኑንና ጊዜው ሲጠናቀቅ መያዣው እንደሚሰረዝ እንጂ በመካከል ይህ ጊዜ ስለሚቋረጥበት ወይም ስለሚራዘምበት ደንብ አይገልጹም፡፡ ድንጋጌው የይርጋ ደንብም ባለመሆኑ ይርጋ የሚቋረጥባቸው የፍትሐ ብሔሩ ድንጋጌዎች ከዚህ ጋር ፈጽሞ አይገናኙም፡፡ ሰበር ችሎቱ ባንኮች በመያዣ የያዙት ንብረት ላይ ብድርን በፍርድ ቤት ለማስመለስ የአሥር ዓመት ጊዜው ከመጠናቀቁ በፊት ዕርምጃ የሚወስዱ ከሆነ (ማስጠንቀቂያ ሲሰጡ፣ ሐራጅ ሽያጭ ማስታወቂያ ካወጡ ወዘተ.) ዕዳቸውን ሳይመልሱ ጊዜው ቢያልፍ እንኳን የመያዣ መብቱ እንደማይሰረዝ ገልጿል፡፡ ይህ የሰበር አቋም የአሥር ዓመቱ ጊዜ ባለገንዘቡ መብቱን ለመጠቀም የመጀመርያ/የመንደርደርያ ጊዜ እንደሆነ አመላካች ነው፡፡
ይህ የሰበር ትንታኔ በሕጉ ከተቀመጠው ደንብ ጋር የሚጣጣም አይደለም፡፡ በሕጉ የጊዜ ገደብ ሲመቀጥ ሕግ አውጭው የራሱ ዓላማ አለው፡፡ የመያዣ መብት የቆይታ ጊዜን ሕጉ አሥር ዓመት ብሎ መወሰኑ ይህ ጊዜ ሳይጠናቀቅ ባለገንዘቡ መብቱን ተጠቅሞ እንዲጨርስ ለማድረግ ነው፡፡ በዚህ ረገድ ባለገንዘቡ የሚገባው ግዴታ ይህንኑ የጊዜ ዘመን ካላገናዘበ መያዣው አሥር ዓመት ካለፈው የሚሰረዝ መሆኑ አጠያያቂ አይደለም፡፡ የፍትሐ ብሔር ሕግ ቁጥር 3058 መያዣ ተቀባዩ መብቱን መገልገል የጀመረው መቼ ነው የሚል ጥያቄ እንድናነሳ ክፍተት አይሰጠንም፡፡ ድንጋጌው ለአቆጣጠር አያስቸግርም፡፡ መያዣው ከተጻፈበት ቀን ጀምሮ አሥር ዓመት አልፎታል ወይም አላለፈውም? የሚለውን ጥያቄ ማጣራት ብቻ የሚጠይቅ ነው፡፡ ከዚህ አንፃር ሰበር ችሎቱ መብትን ለመገልገል የተጀመረበት ጊዜ የሚለውን መሥፈርት ከሕጉ እንዳላገኘው ግልጽ ነው፡፡ ባንኩ ምንም ዓይነት ጥረት እያደረገም ቢሆንም የአሥር ዓመት ጊዜ በመሀል ካለፈ ዓቃቤ መዝገቡ መያዣውን ሊሰርዘው ይገባል፡፡ የባንኩ መከራከርያ ቅቡልነት የሚኖረው በአሥር ዓመት ጊዜ ውስጥ መብቱን ተጠቅሞ ዕዳውን ከሰበሰበ ወይም ዕዳውን ሳይሰበስብ መያዣው አሥር ዓመት ሳያልፈው ምዝገባው መታደሱን በማስረዳት ብቻ ነው፡፡
ማስጠንቀቂያ በመስጠት የአሥር ዓመቱን ጊዜ ማራዘም ከተቻለ ግን የመያዣ ውሉን ምዝገባ በጊዜ ገደብ መወሰንም አያስፈልግም፡፡ ማንም ሰው ከአሥር ዓመት በፊት ማስጠንቀቂያ በመስጠት ጊዜውን ትርጉም ማሳጣት ይችላል ማለት ነው፡፡ ማስጠንቀቂያ መስጠት እንኳን በሕግ የተቀመጠን የምዝገባ ጊዜ ለማራዘም የይርጋ ጊዜ እንኳን ለማቋረጥ ምክንያት አይሆንም፡፡ ማስጠንቀቂያ መስጠቱ በባንኮች የፎርክሎዥር ሥልጣን መሠረት የተሰጠ መሆኑም የተለየ ውጤት የለውም፡፡ በሕግ የሚቀመጥ የጊዜ ገደብ ባለመብቱ በጥንቃቄ በተቀመጠው ጊዜ መብቱን በትክክል እንዲጠቀም ባለዕዳውም (በዚህ ጊዜ መያዣ ሰጪው) ያለበትን ኃላፊነት ዝንተ ዓለም ሳይጠብቁ በተወሰነው ጊዜ ኃላፊነቱን እንዲወጣ ወይም ባለገንዘቡ በገለልተኝነት ጊዜውን ካሳለፈ የመብቱ ገደብ እንዲመለስለት ማስቻል ነው፡፡
በመጀመሪያው መዝገብ የአመልካች ጠበቃ አቶ አስቻለው አሻግሬ በኢትዮጵያ የሕግ ጆርናል በጻፉት ትችትም የሰበር ችሎቱ ከሕጉ ግልፅ ንባብ በመውጣት ፍርድ መስጠቱን ተችተዋል፡፡ እንደ እርሳቸው አመለካከት ሰበር ችሎቱ በፍርዱ በግልጽ ባያሰፍረውም ጉዳዩን ይርጋ ማቋረጥን ከሚደነግገው የፍትሐ ብሔር ሕግ ቁጥር 1851 አንፃር ተመልክቶታል፡፡ አቶ አስቻለው የፍትሐ ብሔር ሕግ ቁጥር 1851 ዋናውን ግዴታ በተመለከተ እንጂ የመያዣ ግዴታውን በተመለከተ ጠቃሚ አለመሆኑን ገልጸው፣ ለባንኮች የተሰጠው የፎርክሎዠር ሥልጣንም የፍትሐ ብሔር ሕግ ቁጥር 3058 ያልሻረ በመሆኑ ችሎቱ የደረሰበት መደምደሚያ የተሳሳተ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
ሁለተኛው ነጥብ አሥር ዓመት ሊያልፈው የተቃረበ የመያዣ ውል ምዝገባ እንዴት ይራዘማል? የሚለው ነው፡፡ የመያዣው ዕድሳት በማን አመልካችነት ይከናወናል? የአስያዡስ ፈቃድ ለዕድሳቱ አስፈላጊ ነው ወይስ አያስፈልግም? የሚለው ነጥብ መታየት ይኖርበታል፡፡ የፍትሐ ብሔር ሕግ ቁጥር 3058(2) ‹‹ይህ የተወሰነ ጊዜ ከማለፉ በፊት ይህ ውል እንዲታደስ አዲስ የመዝገብ ማጻፍ ጉዳይ የተፈጸመ እንደሆነ ፀንቶ የሚቆይባት ዘመን ይራዘማል፤›› በማለት ይደነግጋል፡፡ ድንጋጌው ማን ለማሳደስ እንደሚያመለክት ከመግለጽ ይልቅ አዲስ የመዝገብ ማጻፍ እንደሚከናወን ብቻ ይገልጻል፡፡ ስለዚህ ባለገንዘቡም ይጠይቀው ባለዕዳው አዲስ ምዝገባ የሚከናወንበት ሥርዓት ግን መፈጸም ይኖርበታል፡፡ አዲስ የምዝገባ ሥርዓትን በተመለከተ ደግሞ ሕጉ በፍትሐ ብሔር ሕግ ቁጥር 1602 እና 1605 ላይ እንዲሟሉ የሚጠይቃቸው ሰነዶችና መረጃዎች አሉ፡፡ ከእነዚህ ውስጥ ከምዝገባ ጥያቄው ጋር የተያያዙ ተጨማሪ ወይም አስረጂ ሰነዶች ብዛት፣ ዓይነት፣ የማጣቀሻ ቁጥር ይገኝበታል፡፡ ከዚህ አንፃር የመያዣ ውል ሲታደስ ለመታደስ መነሻ የሆኑት የመያዣ ውል አስፈላጊነት አያጠያይቅም፡፡ ይህ ደግሞ የባለገንዘቡንና የመያዣ ሰጪውን ስምምነት የሚጠይቅ ይሆናል፡፡ የመያዣ ውል ተዋዋይ ወገኖች ቀደም ሲል የነበረውን ግዴታቸውን ለማራዘም በዚህ መነሻነት የዕድሳቱ ጥያቄ በማንም ይቅረብ በማን የተዋዋዮቹ ስምምነት በሌለበት ሁኔታ የመያዣ ውል ዕድሳትን ማከናወን አይቻልም፡፡
የመያዣ ምዝገባውን ማንም መብት አለኝ የሚል አካል ያለበቂ አስረጂና ተገቢ ሰነድ የማያራዝመው ከሆነ የምዝገባውንና የምዝገባ ጊዜውን ቆይታ ትርጉም ያሳጣዋል፡፡ መመዝገብ የሚያስፈልገው ባለገንዘቡን ከሌሎች ገንዘብ ጠያቂዎች የቀዳሚነት መብት ለመስጠት ሲሆን፣ ባለገንዘቡ በፈለገ ሰዓት ያለመያዣ ሰጪው ስምምነት መያዣውን የሚያራዝም ከሆነ የባለመያዣ ሰጪውን ኃላፊነት ዘለዓለማዊ ያደርገዋል፡፡ ሌሎች ባለገንዘቦችም በቀዳሚነት በምዝገባው ሽፋን ከባለመያዣ ሰጪው ጋር የሚያደርጉትን ግብይት የሚያጣብበው ይሆናል፡፡ የጊዜውም ወሰን ትርጉም አይኖረውም፡፡ ባለገንዘቡ በፈለገ ጊዜ እያራዘመ የአሥር ዓመቱን ገደብ በሰፊው ይለጥጠዋል፡፡
ከውል መሠረታውያን መርሆዎችም በመነሳት የመያዣ ውል ምዝገባ መራዘም የመያዣ ሰጪውን ፈቃድ እንደሚጠይቅ መከራከር አሳማኝነት አለው፡፡ በውል ሕግ ውል ተዋዋዮቹ በገቡባቸው ግዴታዎች እነዚሁም አስገዳጅ እንዲሆኑ የተስማሙበትን በሚገልጸው የፈቃድ መስጠት ላይ የተመሠረተ ነው፡፡ በዚህ መነሻነት ማንኛውም ውል ሲመሠረትና ሲለወጥ ወይም በተወሰኑ ሁኔታዎች ሲቋረጥ የተዋዋዮቹ ስምምነት አስፈላጊ ነው፡፡ በተያዘውም ጉዳይ የመያዣው ውል የምዝገባው ጊዜ መራዘሙን በተመለከተ መያዣ ሰጪውና ተቀባዩ ያደረጉት ግልጽ ስምምነት ከሌለ ከአሥር ዓመት የበለጠ ተፈጻሚነት ሊኖረው አይችልም፡፡
የምሥራቅ ወለጋ ከፍተኛ ፍርድ ቤትም ከዋስትና ውል መሠረታዊያን አንፃር ያላዋሉ ፈቃድ የመያዣ ውል መራዘሙ/መታደሱ ተገቢ አለመሆኑን የገለጹበት ሁኔታ አሳማኝ ነው፡፡ የመያዣ ውል ከዋናው ግዴታ ያልከበደ ግዴታ መሆን እንደሚገባውና ውሉ ከተመሠረተ በኋላም በባለገንዘቡና በዋናው ባለዕዳ መካከል የሚደረግ ግዴታውን የማክበድ ስምምነት ከዋስትናው ነፃ እንደሚያደርገው ከሕጉ መረዳት ይቻላል፡፡ የሰበር ችሎቱ በፍትሐ ብሔር ሕግ ቁጥር 1928(2) የዋስትና አጠቃላይ ደንቡ ለመያዣ ውል መታደስ ተፈጻሚ ስለመሆኑ አለመሆኑ ሳይተች ማለፉም የዋስትና መሠረታውያንን እንዲጥስ አድርጎታል፡፡ እንደማንኛውም የዋስትና ውል የመያዣ ውል ያለመያዣ ሰጪው ስምምነት የሚታደስ ከሆነና የመያዣ ሰጪን ግዴታ ያከበደ ከሆነ መያዣው ፈራሽ ነው፡፡ ባለገንዘብ የዋናውን ባለዕዳ የብድር መጠን ከጨመረ፣ የወለድ አተማመኑን ከጨመረና የመክፈያ ጊዜውን ካራዘመ ፈቃዱን ያልሰጠው መያዣ ሰጪ ከኃላፊነቱ ነፃ ይሆናል፡፡ የመያዣ ውል የምዝገባ ጊዜ ሲታደስ ለዋናው ባለዕዳ የመክፈያ ጊዜ ማራዘም መሆኑ ሊዘነጋ አይገባም፡፡ የፍትሐ ብሔር ሕግ ቁጥር 1928/1/ ለዋሱ ጥቅም የተቀረፀ ስለመሆኑ ፕሮፌሰር ጥላሁን ተሾመ ‹‹የኢትዮጵያ የውል ሕግ መሠረታዊ ሐሳቦች›› በሚለው መጽሐፋቸው ይገልጻሉ፡፡ እንደርሳቸው አመለካከት ‹‹የጊዜው መራዘም የዋሱን ግዴታ ሊያከብድ የሚችል ጣጣ ስለሚያመጣ ነው፡፡ በተራዘመው ጊዜ ውስጥ የዋናው ባለዕዳ የመክፈል ችሎታ ቢቀንስ፣ ንብረቱን በተለያዩ መንገዶች ቢያሸሽ ወይም በሌላ ሰው ስም ቢያዛውር፣ ንብረቱን በአፈጻጸም የሚሸጡ ሌሎች ባለገንዘቦች ቢመጡ፣ ባለዕዳው ቢሰወር ወዘተ. የጉዳት ኃላፊነቱን የሚሸከመው የጊዜ መራዘሙን ያለዋሱ ስምምነት ለዋናው ባለዕዳ የሰጠው የሥር ባለገንዘቡ ብቻ ይሆናል፤›› በሚል በአግባቡ ገልጸውታል፡፡
በሌላ በኩል ሰበር ችሎቱ ከማይንቀሳቀስ ንብረት ምዝገባ ጋር በተያያዘም ያቀረበው ትንታኔ አሳማኝ አይደለም፡፡ ችሎቱ የፍትሐ ብሔር ሕግ ቁጥር 1632(2)ን በመጥቀስ በተመዘገበው መብት ተጠቃሚ የሆነው ወገን ይኸው የተወሰነ ጊዜ ከማለፉ በፊት እንዲታደስለት ከጠየቀ ውል እንዲታደስ መመዝገብ የሚችል መሆኑን ገልጿል፡፡ ሰበር ችሎቱ የተጠቀሰው ድንጋጌ መያዣው ከተመዘገበ አሥር ዓመት ሆኖት እንደገና እንዲታደስ አልተጠየቀ እንደሆነ የተመዘገበውን ዓቃቤ መዝገቡ በሥልጣኑ ይሰርዘዋል የሚል በመሆኑ፣ ባለገንዘቡ እንዲታደስለት ከጠየቀ መያዣው ያለቅድመ ሁኔታ ይታደሳል የሚል ትርጉም አይሰጥም፡፡ ጠያቂው ባለገንዘቡ ሊሆን እንደሚችል ከዚህ ድንጋጌ መረዳት አይቻልም፡፡ የሆነ ሆኖ ማንም ይጠይቀው ማን ሊሟሉ የሚገባቸው ሰነዶችና መረጃዎች ካልተሟሉ ግን መያዣው ሊታደስ አይገባም፡፡ መያዣው የሚታደሰው በአዲስ የምዝገባ ሥርዓት ስለመሆኑ የፍትሐ ብሔር ሕግ ቁጥር 3058 ስለሚገልጽ የተሻሻለው የመያዣ ውልና የተሻሻለው የብድር ውል ካልቀረበለት ዓቃቤ መዝገቡ ሊመዘገብ አይችልም፡፡ የመያዣ ውል ከተሻሻለ ደግሞ ሦስተኛ ወገን መያዣ ሰጪው ፈቃዱን ስለመስጠቱ አስረጂ መሆኑ አይቀርም፡፡
የሕጉ የማይንቀሳቀስ ንብረት ምዝገባ ድንጋጌዎች የመያዣ ውል መሰረዝን የተመዘገበ ጽሑፍ ማቃናትና መሰረዝ በሚቻልበት ክፍል ውስጥ ይመለከታቸዋል፡፡ ከእነዚህ ድንጋጌዎች ለመረዳት እንደሚቻለው በመያዣ ውሉ ላይ የጐደለ ወይም ያልተስተካከለ ነገር ሲኖር በፍርድ ቤት ፈቃድ ካልሆነ በቀር ዓቃቤ መዝገቡ ማቃናት እንደማይችል ነው፡፡ የመያዣ ውሉ መሰረዝም በተመሳሳይ መልኩ በፍርድ ቤት የሚከናወን ሲሆን፣ የባለጉዳዮቹ ስምምነት አስፈላጊ ስለመሆኑ በፍትሐ ብሔር ሕግ ቁጥር 1631 ተደንግጓል፡፡ የመያዣ ውል ሲሰረዝ የመብት ተጠቃሚው ፈቃድ እንደሚያስፈልግ አከራካሪ አይሆንም፡፡ ዓቃቤ መዝገቡ ያለ ፍርድ ቤት ፈቃድ የመያዣ ውል ምዝገባን በልዩ ሁኔታ የመሰረዝ ሥልጣን የተሰጠው ምዝገባው አሥር ዓመት ካለፈው ሲሆን፣ ይህም የመያዣ ሰጪው ፈቃድ እንደሚያስፈልገው ከድንጋጌዎቹ አቀራረጽ መረዳት ይቻላል፡፡ የመያዣ ምዝገባ ማቃናትና መሰረዝ በባለገንዘቡ (በመብት ተጠቃሚው) ጠያቂነት ብቻ እንደሚከናወን አመላካች ድንጋጌ ባለመኖሩ ዓቃቤ መዝገቡ አሥር ዓመት ያለፈውን የመያዣ ውልም ያለመያዣ ሰጪው ፈቃድ በባለገንዘቡ ጠያቂነት ብቻ ለማከናወን አይችልም፡፡
ማጠቃለያ
የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንት አቶ ተገኔ ጌታነህ በታተሙ የሰበር ችሎት ፍርዶች መጻሕፍት መግቢያ በተደጋጋሚ እንደሚገልጹት የሰበር ችሎቱ ፍርዶች ምንም እንከን የላቸውም የሚባሉ አይደሉም፡፡ በሕግ ጆርናሎች፣ መጽሔቶችና ጽሑፎች በተደጋጋሚ ከሚሰጡ ትችቶች በመነሳት በችሎቱ የሚሰጡ አንዳንድ ፍርዶች ችሎቱ ውሳኔዎችን ወጥና ተገማች የማድረግ ዓላማውን ማሳካት እንደሚቸግረው አመላካች ናቸው፡፡ አንዳንድ ፍርዶች ከሕጉ ጥሬ ንባብና ከመንፈሱ በተቃረኑ መጠን ተከራካሪዎች በሕጉና በችሎቱ ላይ ያላቸውን መተማመን እንዳያሳጣቸው ሥጋት አለ፡፡ ችሎቱ ሕግ ተርጓሚ እንጂ ሕግ አውጭ ባለመሆኑ በተቻለ መጠን ከሕጉ ደረቅ ትርጉም ሳይወጣ ፍርድ ካልሰጠ ተዓማኒነቱ አከራካሪ ይሆናል፡፡
በዚህ ጽሑፍ ከማይንቀሳቀስ ንብረት መያዣ ምዝገባ ጊዜና ዕድሳት ጋር በተያያዘ የተመለከተባቸው ሁለት ፍርዶች ለዚህ ማሳያ ናቸው፡፡ ሕጉ ለማንም በሚገባ ቋንቋ የማይንቀሳቀስ መያዣ ምዝገባ ከአሥር ዓመት በኋላ ካልታደሰ እንደሚሰረዝ ደንግጓል፡፡ ሕጉ በዚህ ጊዜ ባለገንዘቡ መብቱን መጠቀም ካልቻለ የመያዣ መብቱ እንደሚሰረዝበት የገለጸ በመሆኑ ምንም ዓይነት መብትን ያለመጠቀም ምክንያት መሰረዙን አያስቀረውም፡፡ ባንኮችን በተለየ የሚገዛ ድንጋጌ በሌለበት ሁኔታ ማስጠንቀቂያ መስጠት ጊዜውን ያራዝማል ማለት ሌላ የሕግ ድንጋጌ መቅረጽ ነው፡፡ ባንኮች መያዣው እንዲታደስ ያላቸውንም አማራጭ ሲጠቀሙ መያዣ ሰጪው ስምምነቱን ካልገለጸ ምዝገባው ሊሰረዝ ይገባል፡፡ የመያዣ ሰጪውን ፈቃድ የመስጠት ግዴታ ከውል ሕግ መሠረታዊያን፣ ከዋስትና ባህርያትና ከማይንቀሳቀስ ንብረት ምዝገባ ድንጋጌዎች መረዳት ይቻላል፡፡ በዚህ ረገድ ሰበር ችሎቱ በሁለቱም ጭብጦች የሰጠው ፍርድ የሕጉን መንፈስ ያልተከተለና ከሕጉ ደረቅ ንባብ ጋር የማይጣጣም ነው፡፡
በየጊዜው የሚጻፉ የሰበር ፍርድ ትችቶችን አሰባስቦ ዳኞችና ባለድርሻ አካላት ምክክር እንዲያደርጉ ካልተመቻቸ የፍትሕ ሥርዓቱን በአግባቡ ማሳደግ አይቻልም፡፡ የጠቅላይ ፍርድ ቤቱ ፕሬዚዳንት የብዙ ዓመታት ተሞክሮ ያላቸው አገሮች ልምድም የሰበር ፍርዶች በጊዜ ሒደት እየተሻሻሉ እንደሚሄድ ቢነገሩንም ተገቢው ጥረት ካልተደረገ የፍርዶቹን ጥራት ማሳደግ አይቻልም፡፡ የሕግ ምሁራን፣ ዳኞችና በተለያዩ ዘርፍ የሚገኙ የሕግ ባለሙያዎች በውይይት፣ በትችት፣ በጥናት ወዘተ. ለፍርዶቹ ጥራት አስተዋጽኦ ካላደረጉ ሌሎች አገሮች የደረሱበትን ዕድገት ማግኘት አስቸጋሪ መሆኑ አይቀርም፡፡
ከአዘጋጁ፡- ጸሐፊውን በኢሜይል አድራሻቸው [email protected] ማግኘት ይቻላል፡፡